Saturday, 22 October 2016 10:51

የማህጸን ካንሰርን ...ማከምና ማዳን ይቻላል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

የሴት ልጅ እንቁላል ልክ የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ መያዣ ተብሎ እንደሚጠራው ነው። የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ መያዣ ውጭ ወጥቶ የሚታይ ሲሆን የሴት ልጅ ግን በሆድ እቃ ውስጥ ከማህጸን ጋር ተያይዞ በግራና በቀኝ በኩል የሚገኝ ነው። የእንቁላሉ ዋና ጥቅም ሴትን ሴት የሚያሰኛት እንዲሁም ሆርሞኖችን የሚያመነጩ ናቸው። ስለዚህም ያ አካል በትክክል እየሰራ ከሆነ አንዲትን ሴት በትክክል ይገልጻታል። ከጥቅሞቹም መካከል በወንድ ላይ ጎልቶ የማይታየው ጡት በሴት ላይ ግን መኖሩ፣ የሰውነት ቅርጸን በሚመለከትም ለምሳሌ ስብ የተለያዩ አካላት ላይ በተለይም በመቀመጫ አካባቢ ከወንድ ይልቅ ሴት ላይ መኖሩ ከእንቁላሉ ስራ ጋር አብረው የሚመጡ ናቸው። አንድ ሴት በየወሩ የወር አበባ እንዲኖራት ለማድረግ እና ማህጸኑዋ በትክክል በየወሩ እንዲሰራ ለማድረግ ተፈጥሮአዊው እንቁላል ያግዛል። አንድ ሰው ይፈጠራል፣ ያድጋል ከዚያም ለአቅመ አዳም ይደርሳል፣ ልጅ ይወልዳል፣ ያሳድጋል...ወዘተ የሚለው በትክክል እንዲጉዋዝ በተፈጥሮ የተሰጠ ጸጋ ወሳኝነት አለው።
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ
ጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ ከአሁን ቀደም ከሰጡት ማብራሪያ ጥቂቱን ነበር ከላይ ያስነበብናችሁ። አንዲትን ሴት ሴት ሊያሰኛት የሚችለውን የማህጸን ክፍል ለማሳየት ያህል ነበር። በዚህ እትም ያነጋገርናአው ዶ/ር መብራቱ ጀምበር በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሐኪም ናቸው። ከእሳቸው ጋር ባደረግነው ውይይትም በማህጸን ካንሰር ዙሪያ ያገኘናቸውን አንዳንድ ነጥቦችን ለንባብ ብለናል።
ጥያቄ፡- የማህጸን ካንሰር ሲባል እንዴት ይገለጻል?
መልስ፡- ማህጸን የተለያዩ ክፍሎች አሉት። በመጀመሪያው የሚገኙት የማህጸን ከንፈሮች ናቸው። ከዚያም ወደውስጥ የሚያስገባው ክፍል ማለትም ብልት የሚባለው አለ። ከዚያም የማህጸን በር የሚገኝ ሲሆን ወደውስጥ እየገባን ስንሄድ የማህጸን ግድግዳው ይገኛል። ቀጥሎም የዘር ማስተላለፊያ ቱቦዎች የሚገኙ ሲሆን ጎን ለጎንም የዘር ፍሬዎቹ አሉ። ይሄ አፈጣጠር በአጠቃላይ ማህጸንን የሚያካትት ነው። ስለዚህም የማህጸን ካንሰር ሲባል በተጠቀሱት ክፍሎች ሊከሰት ይችላል። አስቀድሞ የሚከሰተው ግን በማህጸን በሩ ወይንም አፍንጫ በሚባለው ላይ ነው። ሌሎቹ ላይ ግን የሚከሰተው አነስተኛ በሆነ መንገድ ነው።
ጥያቄ፡- በማህጸን በር ላይ የተከሰተው ካንሰር በምን ፍጥነት ወደ ሌሎቹ የማህጸን ክፍሎች ይራባል?
መልስ፡- ካንሰር በባህርይው ቶሎ ተከስቶ ቶሎ የሚያጠቃ የበሽታ አይነት አይደለም። አንድ የማህጸን በር ካንሰር ምልክት ከታየ በሁዋላ ረጅም ጊዜ እንዲያውም እስከሀያ አመት ድረስ ሊቆይ ይችላል የሚባልበት ሁኔታ አለ። ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ሲከሰት የችግሩ ተጠቂዎች ካንሰሩ እንዳለባቸው አያውቁም። ችግሩ እንዳለባቸው የሚያውቁት ደረጃው ከፍ ብሎ ማዳን ከማይቻልበት ሁኔታ ሲደረስ ነው። ለዚህም ሲባል ነው የቅድመ ካንሰር ምርመራ የሚባለው ምርመራ የሚመከረው። ምክንያቱም ቅድመ ካንሰር ምርመራው ከተደረገ ምልክቱ እንኩዋን ሲታይ ከትንሽ እስከትልቁ የህክምና ዘዴው ስለአለ ወደሌላ ደረጃ ሳይደርስ ችግሩን ማስወገድና ተጠቂዎቹም ጤናማ ሕይወትን መምራት ይችላሉ።
ስለዚህ በማህጸን ብቻም ሳይሆን በየትኛውም የሰውነት ክፍሎች ላይ ካንሰር እንደጀመረ መኖሩ ስለማይታወቅ በየተወሰነ እድሜ መደረግ የሚገባቸውን ምርመራዎች ማድረግ ተገቢ ነው። በተለይም ወደ ማህጸን ካንሰር ስንመለስ የቅድመ ካንሰር ምርመራውን የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ ከተጀመረ ጀምሮ በየትኛውም እድሜ ማድረጉ በጣም ይጠቅማል።
ጥያቄ፡- የማህጸን ፈሳሽ ለካንሰር መኖር ምልክት ይሆናልን?
መልስ፡- የማህጸን ፈሳሽ ለካንሰር መኖር አንዱ ምልክት ሊሆን ይችላል። ያ ማለት ደግሞ በሽታው ገና ሲጀምር ጀምሮ ሳይሆን ከተስፋፋ በሁዋላ የሚታይ ነው። ነገር ግን ማህጸን ላይ ፈሳሽ አለ ማለት ሁልጊዜም የካንሰር ምልክት ነው ማለት አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ፈሳሽ በተለያዩ ኢንፌክሽኖች ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌም በፈንገስ እንዲሁም በባክሪያ ሊከሰት ይችላል። አለዚያም የማህጸን ፈሳሽ በተፈጥሮም ሊኖር የሚችል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ያንን እርጥበት ሁልጊዜ እንደሕመም መነሻ አድርጎ መፍራትና መጨነቅ ሳይሆን የእርጥበቱን ምንነት በምርመራ ማወቅ ተገቢ ነው። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም አይነት የጤና ጉዳይ ማወቅ የሚቻልባቸው ጽሁፎች፣ የኢንተርኔት መረጃዎች የመሳሰሉት ሁሉ ስለሚገኙ ሐኪም ጋ ከመሄድ በፊትም ማረጋገጥ ይቻላል። ከዚያም ካለፈ ሐኪምን ማማከር ይበጃል።
ጥያቄ፡- የማህጸን ካንሰር በምን ምክንያት ይከሰታል?
መልስ፡- የማህጸን ካንሰር መነሻ ምክንያት እስከአሁን ድረስ አልታወቀም። ነገር ግን ለካንሰሩ አመቻች ናቸው የሚባሉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። እነዚህን ምክንያቶች ከመጥቀስ ውጭ የካንሰር መነሻው ይሄ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። በአሁኑ ሰአት እንደ ዋና መንስኤ ተደርገው ከሚወሰዱት ውስጥ ፓፒሎማ ቫይረስ የሚባለው ነው። ከፓፒሎማ ቫይረስ ዝርያዎችም ለካንሰር አጋላጭ ናቸው ተብለው የሚታወቁት 16/ እና 18/ የሚባሉት ናቸው ። ሌሎችም አሉ። ለምሳሌም በብልት አካባቢ እንደቡጉር መስሎ የሚበቅል እና የሚኖር በሕክምና ቋንቋው ዋርት የሚባለው ሲነኩት የማያም ምናልባትም ሊያሳክክ የሚችል ጠረኑም ጥሩ ያልሆነና እርጥበት ሊኖረው የሚችል ለካንሰሩ መከሰት ምቹ ሁኔታን ከሚፈጥሩ መካከል ተብለው ይታወቃሉ። ፓፒሎማ ቫይረስ መተላለፊያ መንገዶቹ በአንደኛ ደረጃ ግብረስጋ ግንኙነት ነው ቢባልም ነገር ግን የተለያዩ የመተላለፊ መንገዶችም አሉት። በአገላለጽ ግን በግብረስጋ ግንኙነት ከሚ ተላለፉ በሽታዎች መካከል ይጠቀሳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመከረው ነገር የግብረስጋ ግንኙነት ከሚተዋወቁት ቀድመው ከተመረመሩት እና ለራሴ ይሆነኛል ብለው ከሚተ ማመኑት ሰው ጋር ቢሆን ይመረጣል። አለበለዚያ ግን ኮንዶምን አዘውትሮ መጠቀም ይጠቅማል።
ጥያቄ፡- ልጅ መውለድ አለመውለድ ከማህጸን ካንሰር ጋር ይገናኛል?
መልስ፡- ቀደም ሲል ብዙ ልጅ መውለድ ለማህጸን በር ካንሰር ያጋልጣል ይባል ነበር። ነገር ግን አሁን እየተባለ ያለው ብዙ መውለዱ የግብረስጋ ግንኙነቱም የበዛ ስለሚሆን በቫይረሱ የመያዝ እድሉን ይጨምራል ለማለት ነው እንጂ መውለድ በራሱ ለካንሰር አጋላጭ አይደለም እየተባለ ነው።
በተለይም ከተለያየች ሴት ጋር የግብረስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ወንዶች እንዲሁም ከተለያየ ወንድ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ሴቶች ቫይረሱን የማዛመት ኃይላቸው የሰፋ ስለሚሆን ከዚያ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችል እንደሆን እንጂ ልጅ መውለድ በራሱ ከማህጸን ካንሰር አጋላጭነት እየወጣ ነው። አለመውለድን ስንመለከት ደግሞ በማህጸን ላይ ለሚከሰት ፋይብሮይድ ለተባለ እጢ ይዳርጋል እንጂ በራሱ ለማህጸን ካንሰር ምቹ ሁኔታን ፈጣሪ አይደለም። ልጅ አለመውለድ ማህጸን መስራት በሚገባው ወቅት ስራውን ባለመስራቱ ተፈጥሮአዊ አቅሙን መቀነስ እንዲሁም ቅርጹ እየተበላሽ እንዲሄድ ስለሚያደርግ የጤና እንከን ሊገጥመው ይችላል። በተለይም ፋብሮይድ ለተባለው እጢ ይጋለጣል። በእርግጥ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ቫይረሱን ለማዛመት ምቹ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የምታልፍ ሴት ልጅ ወለደችም አልወለደችም ለማህጸን ካንሰር መጋለጥዋ አይቀርም።
ጥያቄ፡- ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ለማህጸን ካንሰር ያጋልጣልን?
መልስ፡- የወሊድ መከላከያ በተለይም የሚዋጠው ለረጅም ጊዜ የሚወሰድ ከሆነ ለማህጸን ካንሰር የማጋለጥ ሁኔታ ሊኖረው ይችላል የሚል ግምት አለ። ነገር ግን ለካንሰር አመቻች ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል ካልሆነ በቀር በተጨባጭ ለካንሰር ምክንያት ይሆናል ብለን መናገር አይቻልም።
ጥያቄ፡- የማህጸን ካንሰር ከመከሰቱ በፊት ምን ጥንቃቄ ሊደረግ ይችላል?
መልስ፡- ለቅድመ ጥንቃቄ ከሚረዱ መካከል በፓፒሎማ ቫይረስ ላለመያዝ ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት አለማድረግ፣ በቤተሰብ ውስጥ የካንሰር ሕመም ከነበረ አስቀድሞ ማረጋገጥ፣ የሰውነትን ክብደት መቆጣጠር፣ ስብና ጣፋጭ ነገሮችን አለማዘውተር፣ በሐኪም ያልታዘዘ መድሀኒት አለመውሰድ፣ አንዲት ሴት ከ24-34/አመት ባለው የእድሜ ክልል በአግባቡና በግዜው መውለድ የሚገባትን ልጅ ወልዶ መጨረስ፣ በአጠቃላይም አመጋገብን መቆጣጠር፣ እስፖርት መስራት፣ ልቅ ከሆነ የግብረስጋ ግንኙነት መቆጠብ እና ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ጤንነትን መጠበቅ ተገቢ ይሆናል። የማህጸን ካንሰርን በጊዜ ከተደረሰበት ማከምና ማዳን ይቻላል።

Read 11006 times