Sunday, 23 October 2016 00:00

ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር አልተገነባችም

Written by  በኃይለመለኮት አ e-mail:hailethegreat@yahoo.com
Rate this item
(4 votes)

ታሪክ  በግርድፍ ትርጉሙ፣ ያለፉ ሁነቶች ድምር ማለት ነው፡፡  የታሪክ ትምህርት አስተምህሮ  Historiography በፅሁፍ የተሰነዱ የሰው ልጅና የማህበረሰብ - በማህበራዊ ህይወትና ከተፈጥሮ ጋር በሚያደርጉትና ባደረጉት መስተጋብር የተፈጠረ፣ ያለፉ ጊዜ ሁነቶችን ስርዓት ባለውና ሳይንሳዊ  በሆነ መንገድ ለህብረተሰቡ ማቅረብ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ ያለፈ ታሪክ በተለያዩ ምክንያቶች አሁን ላለው ትውልድ ምሉዕ ሆነው ስለማይቀርቡ፣ ይህንን ክፍተት በተለያዩ የታሪክ ትምህርት ጥናት ዘዴዎች ለመሙላት፤ የታሪክ ምሁራን በማስረጃ የተደገፉ የታሪክ ድርሳናትን እጅግ አድካሚ ከሆነ ሳይንሳዊ ጥናት በኋላ ለህብረተሰቡ ያቀርባሉ፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ ታሪክ እጅግ በጣም ቀላልና በአንድ ጀምበር የሚፃፍ ሳይሆን አድካሚ ከሆኑ ጥናቶችና ምርምሮች በኋላ የሚፃፍ ሳይንሳዊ የእውነታ መድበል ነው፡፡ ሆኖም ታሪክን ጠንቅቆ ካለመረዳትና ከፖለቲካዊ ስሜት የተነሳ፣ ብዙ ሰዎች ታሪክን እንደፈለገቻው ሲተረጉሙት፣ ለእነርሱ እንደሚስማማ አድርገው ሲዘውሩት አንዳንዴም ሲያጣጥሉት ይታያሉ፡፡
ታሪክ የዘመናት ስሌት ውጤት ነው፡፡ ሆኖም ስሌትን በስሜት ለመተካት በሚፈልጉ ተቋማትና ቡድኖች እንዲሁም ግለሰቦች፤ ታሪክ የግድ እኔ ከምፈልገው አቅጣጫ ካልሆነ በሚል  አረዳድ፣ በታሪክ ላይ ብዥታዎች ሲፈጠሩ አስተውልናል፡፡ በምኒልክ ዘመን ፓርላማ ለምን አልኖረም? ለምን ዩኒቨርሲቲ አልተገነባም? ለምን ማርክሲዝም የህብረተሰቡ መመሪያ አልሆነም? ለምን ጎራዴና ሰይፍ ይጠቀማሉ? ለምን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አልተደረገም ? የሚሉና የሚሞግቱ ሰዎችን መመልከት፣ በአንድ ወቅት አታካች ሆኖ ነበር፡፡ በታላቁ የዓድዋ ድል እንኳን ለመስማማት የውጭ ታሪክ ፀሀፍትን እማኝ መጥራት ድረስ የተሄደበት መንገድ፣ ታሪክን በተመለከተ የምንሰጠው ብይን በአብዛኛው በስሜታችን ከምንከተለው የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ወይም ከውስጣችን በሚመነጭ ጥላቻ ላይ የተንተራሰ መሆኑ፣ መጭው ትውልድ ለታሪክ የሚኖረው እይታ ላይ ብዥታ እንዲኖረው አድርጓል፡፡
በአጠቃላይ የታሪክ ትንታኔ ትርጉም እንደ ጥናቱ አይነት በተሰበሰበው ማስረጃ ምሉእነት የሚወሰን ነው፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች እንደ ዳኞች ናቸው፡፡ ግላዊ ከሆነ ስሜት ርቀው በቀረቡ ማስረጃዎች ላይ ተንተርሰው ሙያዊ ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡
አንድ አገር በውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖ የዕድገት ሂደት ሊፋጠን ወይም ሊቀጭጭ መቻሉ እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ እውነታ ውጭ አይደለችም፡፡ በአክሱም ስርወ መንግስት ከነበረችበት የእድገት ደረጃ፣ በውጫዊው ተፅዕኖ ለተወሰነ ጊዜ የእድገት ሂደቷ ቢገታም፣ በዛግዌ ስርወ መንግስት፣ የዳግም ማንሰራራት ምልክቶች ታይተዋል፡፡ ድህረ ዛግዌ በሰሎሞናዊው ስርወ መንግስት፣ በድንበር አካባቢ ባቆጠቆጡ ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ አታካች ጦርነቶች፣ ወደ መሃል አገር የተዛወረው ስርወ-መንግስት፣ ከደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያ ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጦርነቶችን በመቋቋምና በመመከት፣ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ከሺዎች ዓመታት በፊት የተቋቋመውን መንግስታዊ ስርዓት ወደ ሰሜን ከሚደረጉ ጦርነቶችን ሲቋቋም ቆይቶ፣ በመጨረሻም ይህ ለተከታታይ መቶ ዓመታት ሲደረግ የነበረ ጦርነት፣ በአህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ ድል አድራጊነት፣ በመሃል ኢትዮጵያ የነበረውን ማዕከላዊ መንግስት ወደ ሰሜን ምዕራብ ጎንደር እንዲያፈገፍግ አድርጎታል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የዘመኑ ልዕለ ኃያላን ኦቶማን ቱርክና የፖርቱጋል መንግስት የውክልና ጦርነት ያደረጉበት ዘመን፣ አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ፖለቲካዊ ገፅታ የተፀነሰበት መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ሆኖም ይህንን ዘመን መነሻ አድርጎ ኢትዮጵያ እስከ 1983 ድረስ ለ400  ዓመታት ቁልቁል ስትሄድ ነበር ወደ ሚለው ጥቅል ድምዳሜ መድረስም አግባብነት ያለውም አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከ1983 በኋላ የዛሬ አራት መቶ ዓመት ወደ ነበርንበት የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመልሰን አልሄድንምና፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በተለይም ድህረ ኢጣሊያ ወረራ፣ ከ1933 ማግስት በነበሩ ጥቂት አስርተ ዓመታት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማቆም የተደረጉ ጥረቶችን በማሳያነት በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ አንዱ ስርዓተ መንግስት ለአንዱ መሰረት እየጣለ፣ አገር ህዝብና መንግስት እየተገነባ የተሄደበትን መንገድ በወፍ በረር ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ ለዚህ ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን  አቶ በረከት ስምኦን  በሸራተን አዲስ ያቀረቡት ጥናት እንዲሁም  በENN ቴሌቪዥን በነበራቸው የቃለ መጠይቅ ፕሮግራም ላይም ይህንን የሶስት መቶ ዓመትና የአራት መቶ አመታት  የቁልቁለት ጉዞ በማስመልከት የሰጡት ትንተና፣ ከምን አቅጣጫ እንደሆነ ግልፅ ስላልሆነልኝ፣ በስብሰባው ላይ የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው፤ በታሪክ ተማሪነታቸውም ይህ የ400 ዓመት የቁልቁለት ታሪክ መነሻና መድረሻው ምን እንደሆነ አቶ በረከትን አለመሞገታቸው፣ ታሪክን እንዴት ነው የሚመለከቱት አስብሎል ቁልቁል መውረድ ምንድነው? ከፍታ መውጣትና መስፈንጠርስ?  ለመውረድ የነበርንበት ከፍታ የቱ ጋር እንደነበረ ማስመር ተገቢ ነው፡፡ የዛሬ 400 ዓመት የነበረችውን ኢትዮጵያ፣ ዘመነ መሳፍንት ምን ያህል ቁልቁል ይዟት ወርዶ እንደነበረ አልተተነተነም፡ ከዚህ ቁልቁለት ለመውጣት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ አራተኛ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ያደረጉት ጥረት አልተወሳም፡፡ እንደኔ አረዳድ እውነታው  ለዛሬዋ ኢትዮጵያ እውን መሆን፣ አሁን ላላት የመሬት ስፋት፤ የኢኮኖሚ አቅም፣ ወታደራዊ ቁመና፣ ፖለቲካዊ ልዕልና የቀደምት አባቶቻችን ተጋድሎ ወሳኝ እንደነበር ነው፡፡ እነርሱ የገነቡትን ለመናድ መሞከር  በህልውና ላይ መፍረድ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ ቀን እንዳልተገነባች ሁሉ በአንድ ቀን እንዳትፈርስ ያለፉ መንግሰታት ላበረከቱት  ስራዎችና ጥረቶች እውቅና መስጠት፣ ከመንግስት የስራ ኃላፊዎችም ሆነ ከታሪክ ምሁራን ብዙ ይጠበቃል፡፡ ለመነሻ ከቅርብ ዘመኑ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት በጎ መልካም ጥረቶች በተለይም ከድህረ የኢጣሊያ ፋሺዝም ወረራ በኋላ ያሉትን ወቅቶች  እንመልከት፡፡ ይህ ፅሁፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩን ባከበረበት ወቅት በአፍሪካ ህብረት ካቀረብኩት “በድህረ ፋሺስት ዓመታት እንደ ሀገር ለመቋቋም የተከናወኑ ሁለንተናዊ ተግባራት” የተሰኘ ፅሁፍ የተቀነጨበ ነው፡፡
የድህረ ፋሺስት ኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋም ተግባር         
ከ1933 የኢጣሊያ ፋሺስት ወራሪዎች ከኢትዮጵያ መባረር በኋላ ከድል የተጠበቀው ታላቅ ስራ አገሪቱን እንደገና መልሶ ማቋቋም ነው፡፡ በፋሽስቶች የተገነባ ከሚባለው የፈረሰው፣ የተቃጠለው ስፋት ያለው ነበር፡፡ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት የመጀመሪያ ስራ የነበረው በጦርነት ውስጥ ህዝብ መንፈስ ማረጋጋት ነው፡፡
የመንግስት መዋቅር መዘርጋት
በድህረ ኢጣሊያ ህዝቡን ከማረጋጋትና የምህረት አዋጅ ከተደረገ በኋላ የተወሰደው አፋጣኝ ስራ  የመንግስትን መዋቅር መዘርጋት ነው፡፡ በዚህም መሰረት የተለያየዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዲዋቀሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት  ደጃዝማች(ራስ ቢትወደድ) መኮንን እንዳልካቸው---የአገር ግዛት ሚኒስትር ፤ብላቴን(ደጃዝማች) ሎሬንሶ ታዕዛዝ - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፤አቶ መኮንን ደስታ - የትምህርትና ስነ ጥበብ ሚኒስትር፤ ብላታ አየለ ገብሬ --- የፍርድ ሚኒስትር፣ ነጋድራስ ገብረእግዚአብሔር--- የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ---የፅህፈት ሚኒስትር አቶ በላቸው ያደቴ---የፖስታ የቴሌግራፍና የቴሌፎን ሚኒስትር፣ ራስ አበበ አረጋይ--- የጦር ሚኒስትር አቶ መኮንን ሀብተወልድ---የእርሻ ሚኒስትር፣  በ1934 ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከተዋቀሩ በኋላ በመጀመሪያ የተከናወነው ስራ፣ የአውራጃ አስተዳደር መዋቅርን መዘርጋት ነበር፡፡ ምንም አይነት የተማረ የሰው ኃይልም ይሁን የፋይናንስ አቋም ላልነበረው አዲስ መንግስት አስቸጋሪ ቢሆንም በመጀመሪያው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከጠቅላይ ግዛት እስከ አውራጃ መዋቅር ተዘረጋ፡፡ ይህ እንግዲህ አገሪቱን ከፋሽስት ወታደራዊ አገዛዝ ወደ ሲቪል አስተዳደር በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ መስዋዕትነትን የጠየቀ እንደ ሀገር መልሶ የመቋቋም ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህንን መዋቅር በመዘርጋት ረገድ እንግሊዞች ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል፡፡ በዚህም ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
ትምህርት
ይህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ አገሪቱን መልሶ በማቋቋም ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊኖራቸው የሚገባ ምሁራን፣ ቴክኒሽያኖች፣ የስራ መሪዎች፣ መሐንዲሶች፣ የንግድና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች አልነበሯትም፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ፊደል የተባሉትም ምሁራን፣ የወራሪው የፋሺስት ኃይል ኢላማ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ተገድለዋል፤ ተግዘዋል ፡፡
ስለሆነም አገሪቱን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት፣ በድህረ ኢጣሊያ እንደ ሀገር ለመቋቋም ከተደረጉ ጥረቶች ውስጥ ትምህርትን በመላ አገሪቱ ማስፋፋትና የድህረ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መልሶ የሚያቋቁም የተማረ ትውልድን መፍጠር ቁልፍ ተግባር ነበር፡፡
የዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ፤ በቤተክህነትና በአንዳንድ የሀይማኖት ተቋማት ባህላዊ የሆነውን ትምህርት ከተማሩ የሀይማኖት ምሁራን ውጭ በዘመናዊ መልኩ ከተደራጀ የትምህርት ተቋም የወጡ በአገሪቱ የመልሶ ማቋቋም ተግባር ውስጥ ጉልህ ለውጥ ሊያመጣ የሚችሉ የተማሩ የሰው ኃይል አልነበራትም፡፡ ተማሩ የተባሉትም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡
በበጎ ፈቃድ በነፃ ትምህርት የሚሰጡ ሚኒስትሮች፤ ዳይሬክተሮች
“አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ሚያዝያ 17 ቀን 1934 እትም፣ ከመደበኛ ስራቸው ውጪ በበጎ ፈቃድ በነፃ ትምህርት የሚሰጡ ሚኒስትሮች ዳይሬክተሮችን ስም ዝርዝርና ስፍራውን ለህዝቡ አሳውቋል፡፡ ትምህርት የሚሰጥበት ስፍራ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ሰዓቱም ከምሽቱ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ነው - መምህራኖቹም፡-
ክቡር ልጅ መኮንን ደስታ፤ የትምህርትና ስነ ጥበብ ሚኒስትር
ክቡር ብላቴን ጌታ ሎሬንሶ ታዕዛዝ ፤የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ዶ/ር ዓለመወርቅ፤ የከብት ሐኪም
ልጅ ይልማ ዴሬሳ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር
አቶ ጌታሁን ተሰማ፤ የጽህፈት ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር
አቶ መሸሻ ኃይሌ፤ የስራ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር
አቶ ገብረ መስቀል፤ የስልክ የቴሌፎንና የፖስታ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር
የሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶችም፡- እንግሊዝ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ሂሳብ፣ አልሄሚያ (ኬሚስትሪ)፣ ፊዚክስ፣ ስነ ፍጥረት፣ ባዮሎጂ ፍትህና ርትዕ፣ በኤውሮፓ ዓይነት የፍልስፍና ታሪክ፣ ስልክ፣ የራዲዮ እውቀት፣ የኤሌክትሪክ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በበጎ ፈቃዱ በነፃ ትምህርት የሚያስተምር የሚያገለግል ባለስልጣን አለ? የተማረ የሰው ኃይል ለመፍጠር በተደረገው ጥረት መንግስት ለተማሪዎች ነፃ ምግብ፣ ነፃ ትምህርት፣ ነፃ የአዳሪ ትምህርት ቤት አቀረበ፡፡ ትምህርት በሁሉም ማሕበራዊ ህይወት ውስጥ ቅድሚያ እንዲሰጠው መሰረት ተጣለ፡፡
ሰውና ገንዘብ ጠፋ
የኢጣሊያ ፋሽስት ወታደሮች የጦር ሰፈሮች አድርገዋቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶች እንደገና ተከፈቱ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ይህን  ሁሉ ጥረት አድርጎ፣  ትምህርትን እንደሚፈለገው መጠን ለማስኬድ ችግር ተፈጠረ፡፡ ትምህርቱን ማስኬድ የሚችል የሰው ኃይልና ገንዘብ አልነበረም፡፡ ሰውና ገንዘብ ጠፋ፡፡ ገንዘብ እንኳን ቢገኝ አስተማሪን ማግኘት ችግር ነበር፡፡
በየዓመቱ ለትምህርት የሚመደበው በጀት እያደገ ቢሄድም በቂ መምህራን ግን አልነበሩም፡፡ በመሆኑም ዋንኛ ትኩረት የነበረው ተምረው አስተማሪ የሚሆኑትን ማፍራት ላይ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን፣ ህዝቡን በነፃነት ለማስተማር ማናቸውም የትምህርት ወጪ የመንግስት ዕዳ ሆኖ ሲሰራበት መቆየቱን ነው፡፡ በዚህ ረገድ የውጭ መምህራንን በመቅጠር ከእንግሊዝ፣ ከህንድ፣ ከግብፅ፣ ከአሜሪካና ከካናዳ ብዛት ያላቸው መምህራን ተቀጥረው መጥተዋል፡፡
የትምህርት ቀረጥ መጣል
ከ1933-1939 የትምህርት ሚኒስቴር ስርዓት ባለው መልኩ ተቋቋመ፤ ቅርንጫፎችን፣ ወኪሎችን … በየአውራጃው አሰማራ የትምህርት ቦርድ ተቋቁሞ አባሎች ተመረጡ፡፡ በ1939 ዓ.ም የትምህርት ቀረጥ ወጣ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ዕቃ ላይ የትምህርት ቀረጥ ተጣለ፡፡ ትምህርት በመንግስት ትምህርት ቤቶች ከ1ኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ነፃ ነበር። በ1962 ዓ.ም 2114 የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 683500 ተማሪዎች፣ 14450 መምህራን ነበሩ፡፡ የተግባረ ዕድ፣ የባህርዳር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲቲዩት፣ የንግድ ትምህርት ቤቶች፣ የአምቦና ጅማ የእርሻ ትምህርት ቤቶች  ተከፈቱ፡፡ በሐረር፣ በአዲስ አበባና በደብረብርሐን የመምህራን ማሰልጠኛ ተከፍቶ ብዛት ያላቸውን መምህራን ማሰልጠን ተጀመረ፡፡ በ1923 ለሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጠው  እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተቋቋመ፡፤  በ1947 ሴቶች በሁሉም ትምህርት  ቤቶች በነፃ የመማር መብት ተጎናፀፉ፡፡ ሴቶች በትምህርት ቤቶች የመመዝገብ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው በንጉሠ ነገስቱ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ በ1955 የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ፡፡
በገንዘብ  ረገድ የተደረጉ የመልሶ መቋቋም ጥረቶች
በመልሶ መቋቋም ረገድ በድኅረ የፋሺስት ወረራ፣ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ መንግስት ከወሰዳቸው  ዓበይት የሆኑ ተግባሮች ውስጥ ግብር አንድ ዓይነት ሆኖ እንዲሰራበት መወሰኑ ነው፡፡ማንኛውም መሬት - ጠፍና ለም መሬት እየተባለ ተመደበ፡፡ የአገር ውስጥ የገቢ ቀረጥና (የኤክሳይስ) የቴምብር ገቢ የተባሉት የገቢ ምንጮች፣ ሥርዓትና ድንጋጌ የወጣለቸው በዚህ ወቅት ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ቅርንጫፍ የሆነ የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት በ1936 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ ኢትዮጵያ እንደገና ስትቋቋም፣ ዋና የገቢ ምንጭ የነበረው የጉምሩክ ቀረጥ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከ1935—1936 ዓ.ም የነበረው የጉምሩክ ቀረጥ ገቢ 200.000 ብር ነበር፡፡ ከ1938—1939 ዓ.ም ይህ ገቢ ወደ  800.000 ብር አድጓል፡፡
በዚህ ወቅት አስቸጋሪ የነበረው የግብር ማስከፈያ ኬላዎች መዘበራረቅ ነበር፡፡ ይህንን  ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት፣ ከጠረፍ እስከ ከተማ ሰፊ መዋቅሮች ተዘረጉ፡፡ ሆኖም በዚህ ወቅት የነበረው የገቢው ምንጭ በጣም የጠበበ ነበር፡፡ የፋሺስት ወራሪ ኃይል ከኢትዮጵያ እንደወጣ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አራት ዓይነት ገንዘቦች ይሰራባቸው ነበር - የኢጣሊያ ሊሬ፣ የህንድ ሩፒ፣ የምስራቅ አፍሪካ የእንግሊዝ ሽልንግ ማሪያ ትሬዛ በስራ ላይ ነበሩ፡፡ በመሆኑም በድኅረ ፋሽስት የመልሶ ማቋቋም ተግባር ውስጥ የኢጣሊያ ሊሬ እንዲጠፋ ተደረገ፡፡ የህንድ ሩፒ ብዙም የተለመደ ባለመሆኑና በህዝብም ዘንድ የነበረው ተቀባይነት አናሳ በመሆኑ፣ እርሱም እንደ ሊሬው ከገበያ እንዲወገድ ተደርጓል። የማሪያ ቴሬዛና የምስራቅ አፍሪካ የእንግሊዝ ሽልንግ በህግ ተከብረው አራት ዓመታት ያህል የመገበያያ ገንዘብ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በርክሌይ የተባለ ባንክ ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ባንክን በማቋቋም ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

Read 4242 times