Print this page
Sunday, 23 October 2016 00:00

‘ከዕለታት አንድ ቀን…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ተከታዩ ‘ዳያሪ’ ከዕለታት አንድ ቀን የአፍራሽ ግብረ ሀይል ‘ቦዳድሶ ከተወው’ መንደር ስር ሊገኝ ይችላል፡፡
“እኔ ለጉድ የፈጠረኝ ሰው ልሁን፣ የሰው ልጅ እንዳለ ለጉድ የተፈጠረ ይሁን ግራ ገብቶኛል፡፡ (እኔ የምለው…  ‘ቀኝ ገብቶኛል’ ከማለት ይልቅ ‘ግራ ገብቶኛል’ የሚባለው እነ ማኦን ለማሳጣት ተበሎ ነው እንዴ! (ቂ…ቂ…ቂ…)
“ይኸውላችሁ…ሰዉ ምን እንደነካው ግራ ገብቶኛል! ተካፍሎ መብላት ምናምን የሚባለው ነገር ‘ጎጂ ባህል’ ሆነ እንዴ! ግራ ገባና! ደግሞስ…አለ አይደል…ላያበላ፣ ላያጠጣ ለምን ግብዣ ይጠራል!  በሌለ ጮማ፣ በተወደደ ምንቸት አብሽ … የሚጮህበት ነገር ያላጣ ሆዳችንን ለምን ያንጫጩብናል! ቅዳሜ ዕለት የሆንኩት ነገር ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማለቁን ሳያውቅ አርባ ዓመት ነው ምናምን ዋሻ ውስጥ ኖረ በተባለው ጃፓናዊ እንድቀና ሊያደርገኝ ምንም አይቀረው፡፡
“እሱ ሰው የማይጠይቀው በእሱ ቤት መኩራቱ ነው ወይ እየተባልክ ስምህ እየጠፋ ነው…’ የሚባል ነገር ሹክ ቢሉኝ እርሜን አንድ ዘመድ ቤት ሄድኩ። ‘ከዕለታት አንድ ቀን…’ እንደሚባለው፡፡ እኔ ደግሞ ዘመድ የሚባል ነገር ሲነሳ የሚታየኝ ‘ገመድ’ ከሆነ ከራርሟል፡፡ የሆነ ያልሆነውን እያነሳ ወስውሶ፣ ወስውሶ ‘ከዚህስ ኑሮ የአስር ሳንቲም ገመድ ምን አለኝ’ የሚያስብል ‘ዘመድ ተብዬ’ ሞልቷላ!
“እያጠፏት ያለችውን ስሜን በቀይ ሸክላ ለውስው ጭርሱን እንዳይሰውሯት ብዬ ነው ዘመድ ቤት የሄድኩት፡፡ ቀጠሮዬ ምሳ ሰዓት ስለሆነ ስለዝግጅቴ ባልናገርም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የሄድኩባቸው ዘመዶቼ ‘አኪር የቆመላቸው’ የሚባሉት አይነት ናቸው፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ… ወደ ሳሎኑ ልቤ ልትፈተለክ በቋፍ ነው የተረፈችው። ቆይ…  እንዴት ነው ሰዉ ቤቱን እንዲህ የሆነ የኳታር ሱልጣን ሳሎን የሚያስመስለው! ግድግዳና ቴሌቪዥኑ እኩል ሊሆን ተቃርቦ ቴሌቪዥኑን የለየሁት ማናት የሚሏት ሴትዮ ምግብ አሠራር ስታስተምር ስላየሁ ነው፡፡ (ያቺን ዕለት የተሰማኝን ብታውቁ ‘አቤት ማጋነን!’ አትሉኝም ነበር!)
“ሶፋውማ ሌላ ራሱን የቻለ ታሪክ ነው፡፡ እንዴት ተጠንቅቄ እንድተቀመጥኩ ‘በስማርት ፎን’ የሚቀርጽ ቢኖር ኖሮ…አለ አይደል… ሶፋ ላይ ሳይሆን የሆነ ‘ተጠንቀቁ’ ተብሎ የተለጠፈበት መስታወት ላይ የምቀመጥ ይመስል ነበር፡፡፡ ልጄ፣ ደሀ ሁልጊዜም እንደተጠነቀቀ ነው፡፡ ነገር በእሱ ይገናላ! እውነቱን ለመናገር ሹሮ ሜዳ እሁድ ጠዋት የተገዛች ሱሪዬ፣ ቆዳው ሶፋ ላይ የሆነ አሻራ ነገር ትተዋለች ብዬ ሳልፈራ አልቀረሁም፡፡
“እንደ እውነቱ ዘመዶቼ የተባሉትን ፊታቸውን ሳያቸው፣ ገና እንደገባሁ ተንደርድሬ ሶፋው ላይ ዘፍ ማለቴን የወደዱት አልመሰለኝም፡፡ ቢጠይቁኝ ኖሮ ያንደረደረኝ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ድንጋጤ መሆኑን እነግራቸው ነበር፡፡ ይመስለኛል… ትንሽ ሴኮንዶች ቆም ብዬ ብቆይ ኖሮ… ‘ማነሽ፣ እስቲ ከኩችና አንድ በርጩማ አምጪለት› ይሉ ነበር፡፡ ደግነቱ ጫማዬን ደጅ ማውለቄ! በር ላይ ለእንግዳ የተቀመጠው ዓይነት ነጠላ ጫማ ዝም ብዬ የትም አላስቀምጥም። ቢኖረኝ ኖሮ፣ የሆነ ባንክ ውስጥ የውድ ዕቃ ማስቀመጫ ሳጥን እከራይለት ነበር፡፡ ነጠላ ጫማም እንዲህ ያምራል!
“ታዲያ ተቀመጥኩና ስለ ጤንነቴ ጠያየቁኝ። ‘እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ’ እያልኩ መለስኩ። ይቺ በሰበብ አስባብ እየተነሳች ትንፋሼን ስለምታሳጥረው ትክ፣ ትክ አልነገርኳቸውም። ጨጓራዬ በሆነ ባልሆነው እየከሰለ የሰው ልጅ ጨጓራ መሆኑን ለመለየት ማርስን የሚመለከቱበት ቴሌስኮፕ ሊያስፈልገው እንደተቃረበ አልነገርኳቸውም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ልክ እነሱ ሳሎን ስገባ የጀመረኝን ከፍተኛ የ‘ኮምፕሌክስ በሽታ’ አልነገርኳቸውም፡፡ ቀላል ‘ኮምፕሌክስ’ ገጠመኝ እንዴ! ምንጣፋቸውን ‘ሸጠህ ተጠቀምበት’ ቢሉኝ ኖሮ ሦስት ክፍል የኪራይ ቤቴን በአዳዲስ ዕቃ ከአፍ እስከ ገደፉ እሞላው ነበር! ለምንጣፉ የወጣው ገንዘብ የጎጆ ኢንዱስትሪ ባይከፍት ነው! ታዲያማ… ‘ኮምፕሌክስ’ ቢጠፍረኝ ምን ይገርማል!
“‘እስቲ አፍህ ምናምን አድርግ’ ተባልኩ፡፡ ለምን ይዋሻል… ያቺ ደቂቃ በናፍቆት የምጠብቃት ነበረች። በየዓረብ ቻናሉ እያሳዩ እንቁልልጭ የሚሉንን የምግብ አይነት ስሰፍርበት ይታየኝ የጀመረው ጧት ከማታ የተረፈች ዳቦዬን ተጋምሶ በተቀመጠ ለስላሳ እያራስኩ ስበላ ነው፡፡ ‘የማያውቁት አገር አይናፍቅም’ ብሎ ተረት ለምግብ አይሠራም። ቂ…ቂ…ቂ… ሸክላ ትሁን፣ ፕላስቲክ ትሁን፣ ኒኬል ትሁን … የማትለይ ሳህን ነገር  አምጥተው ፊቴ ዱብ ሲያደርጓት ልቤም አብራ ዱብ አትልላችሁም! እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ… ‘ከዕቃ ቤት አንድ አሮጌ ሳህን ፈልጋችሁ አምጡለት’ የተባለ ነው የሚመስለው፡፡ ሳህኗን ‘ከስር መዞ’ ለማውጣት ስንት አሮጌ ድስትና መጥበሻ እንዳነሱ ማሰብ ቢኖርብኝም እንደዛ አላሰብኩም፡፡
“እነሱ በቅርብ እንደበሉና እኔ እንድመገብ ነገሩኝ። ወግ አይቅር ብዬ ‘ብቻዬንማ አልበላም’ ምናምን ብዬ ተግደረደርኩ፡፡ በሆዳቸው ‘ምን ይዘባነናል፣ ደግሞ እሱን ብላ፣ አትብላ ልንል ነው እንዴ!’ እንደሚሉኝ ጠርጥሬያለሁ፡፡ ምግቡ ሲቀርብልኝ ግን ለምን መብላት እንዳልፈለጉ ገባኝ፡፡ ምግቡ አጠገብ መቀመጣቸውም እነሱ ሆነው ነው፡፡
“ይቅር ይበለኝ እንጂ… እንጀራው ጄሶም ባይሆን የሆነ ነገር የገባበት ይመስል ሳኝከው የእግሬ አውራ ጣት ድረስ ይሰማኝ ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ልሳቅ እንጂ! ወጡን ሊገልጹ የሚሉ ቃላት ገና አማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ እየፈለግሁ ስለሆነ እንዳገኘሁ ‘ዳያሪዬ’ ላይ እጽፈዋለሁ፡፡ ‘የሚጠጣ አምጡለት’ ሲባል… ጠዋት ያደረች ዳቦዬን ስበላ ያሰብኳቸው ‘ብላክ ሌብል’ ‘ሬሚ ማርቲን’ (ቀምሻቸው እኮ አላውቅም! ጉጉቱስ የመጣው ለዛ አይደል!) አንድ ሊትር ከግማሽ ለስላሳ ቀረበልኝ፡፡ እንጀራውን ወጥ የተባለው ነገር ላይ ከማጥቀስ እየፈተፈትኩ ብበላው ይሻለኝ ነበር፡፡
ተሰናብቼ ስወጣ… ‘ስለተጋበዙ ብቻ ግብዣ ይኖራል ማለት አይደለም’ የሚል ጥቅስ መፍጠሬን ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡
“በማግስቱ እሁድ ሠርግ ነበረኝ፡፡ ‘ከዕለታት አንድ ቀን…’ እንደሚባለው፡፡ ሰርጉ ላይ ‘የሀብታም’ ዘመዶቼን እልህ ካልተወጣሁማ’ ምናምን ብዬ የፎካከርኩ ይመስለኛል፡፡ ብቸኛዋን የክት ሙሉ ልብስ ግጥም አድርጌ ሄድኩ፡፡ እልህ ልወጣ የሄደኩት ሰውዬ እልህ ጨመርኩላችሁ፡፡ ሰባት፣ ስምንት መቶ ምናምን ሰው ጠርቶ … መቶ ሰው እንኳን የማይሸኝ ምግብ! ለምን ይዋሻል…አንድ ጉርሻ እንኳን ለመጉረስ ያደረግሁት ጥረት ሁሉ እንደከሸፈብኝ ይኸው ለታሪክ ‘ዳያሪዬ’ ላይ ጻፍኩት፡፡
ባዶ ሆዴን ይዤ ሄጄ ጭርሱን በሰርግ አዳራሽ ነፋስ ሞልቼው ተመለስኩ፡፡ ወይም የሰርጉ ካርድ ላይ… ‘ምግብ ለሁሉም ማዳረስ ባንችልም ሰርጉ አዳራሽ ውስጥ የሁሉንም ሆድ ሞልቶ ሊተርፍ የሚችል ነፋስ  እንዳለ ስናሳውቅ ደስ እያለን ነው’ ምናምን የሚል የግርጌ ማስታወሻ ምናምን ይግባልና! እየጓጓን የምንሄድ ድሆች ለምን እየተሳቀቅን እንመለሳለን! በየስብሰባው በ‘ሻሞ’ አይነት የሚታደለው ውሀ እንኳን እንጣ! ሰዉ እንዲህ ቆንቋና የሚያደርገው ምንድነው! እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ ሰርጉ አዳራሽ ውስጥ ሆዴ ከመጮሁ የተነሳ አጠገቤ የነበሩት ሰዎች አሮጌ የቮልስዋገን ሞተር የተጫንኩ ሳይመስላቸው አልቀረም፡፡
“ይኸው የቅዳሜና የእሁድ ጉድ ሳይለቀኝ ሰኞ መጣና አረፈው፡፡
‘ከዕለታት አንድ ቀን…’ እንደሚባለው፡፡ ቢሮዬ የሄድኩት የሥራ መንፈሴ ከፍተኛ ስለሆነ ሳይሆን ‘ደግሞ እንዳይለክፉኝ’ ሰበብ ላለመስጠት ባለኝ ከፍተኛ ፍርሀት ነው፡፡ ገና ግቢውን ስገባ የሳምንቱን መጨረሻ አድፍጦ ሲጠብቀኝ የቆየ ይመስል ሉሲፈር እንዳለ ነው የሰፈረብኝ፡፡
“ቢሮዬ ውስጥ ያሉት ሌሎች ሦስት ሰዎች ቀኔን እንኳን ብርሀን ሊያደርጉት ከጋበዙኝ ዘመዶቼና ሙሽሮች ጋር ሴራ የጎነጎኑብኝ ነው የመሰለኝ። እኔ ስገባ ፊታቸውን የሚያጨልሙት ይሄን ያህል ‘ፊቴ ምግብ የማይበላ’ ነኝ እንዴ! ‘ሀንድሰም’ ባልሆንም ለልጅ ማስፈራሪያነት ገና እንዳልደረስን ይታወቅልና! አንደኛው ጠጅ በርሜል ውስጥ ‘ሻወር ሲወስድ የሰነበተ’  (ቂ…ቂ…ቂ…)  ይመስላል፡፡ እኔማ  በስሙኒ አንድ ብርሌ ጠጅ መሸጥ ካበቃ በኋላ ትቼዋለሁ፡፡ በዚህ ላይ ጠጅ ከተጠጣ በኋላ ‘ራሱን ችሎ’ አይቀመጥም፡፡ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች ለማሟላት ያለውን መከራ የደረሰበት ያውቀዋል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
“ቢሮው ውስጥ ያለችው ብቸኛዋ ሴት ዓይኗ ስር በልዟል፡፡ ያው እንደተለመደው የቤቷ በር ‘ገጭቷት’ ነው፡፡ “ምን ሆንሽ?” ብዬ መጠየቅ ከተውኩ ሰነበትኩ፡፡ መልሱን አውቀዋለኋ --  ‘በር ገጭቷት’ ነው የሚሆነው፡፡ ‘አንቺ ሴትዮ ካላጣሽው ዕቃ ዘላለምሽን በበር የምትተኪኝ እኔ እንጨት ነኝ ማለት ነው!’ የሚል ባል መጥፋቱ ሲገርመኝ ይኖራል። ቆይ…አንዳንድ እንትናዬዎች፣ የእናንተ ቤት በር በቡጢ መልክ የሚጠቀልለው ‘እጅ’ አለው እንዴ! ሰበብ ለውጡ እንጂ! የቢሯችንን ሴት የበለዘ ዓይን ባየሁ ቁጥር ‘እኔ ሳገባ በር የሚገጨው እኔን ይሁን ሚስቴን ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ቂ…ቂ...ቂ… አቅም ሳይኖረኝስ!
ሦስተኛው፤
የቢሮው ሰው አይደለም፡፡ የቢሯችን የመሥሪያ ቤቱ ‘ወሬ አምራች’ ሞተር ነው፡፡ በቃ የሆነ አል አህራም ምናምን በሉት፡፡
“ሥራ አስኪያጁን ሊያነሱት ነው አሉ…”
“ንብረት ክፍሏ ማታ ማታ ጠጠር ታስወረውራለች አሉ…”
“የፋይናንስ መምሪያ ሀላፊውና የንብረት ክፍሏ ጸሀፊ እሁድ ማታ ኮተቤ አካባቢ ከአንድ ሆቴል ሲወጡ ታይተዋል አሉ…”
እኔም የሆነ ‘ወሬ’ ሲነግረኝ… ‘እውነትህን ነው?’ ‘አትለኝም!’ ምናምን ማለት ትቻለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ጉድ ልሆን ነበራ… አንድ የማልወደው የትራንስፖርት ክፍል ሀላፊ ነበር፡፡ ለእኔ ሲሆን መኪና መቼም ቢሆን አይገኝም፡፡ የዓይኔ ቀለም ይሁን፣ የፊቴ ቀለም ይሁን ወይም ጭራሽ ቀለም የሚባል ሰላፈጠረብኝ ይሁን…ብቻ አልመቸውም፡፡
አንድ ጊዜ አል አሀራማችን… ‘የትራንስፖርት ክፍል ሃላፊው ከአዲስ አበባ ውጪ ተመደበ አሉ’ ሲል እኔም… አስቤው ይሁን ሳላስበው አሁን ትዝ አይለኝም… ድምጼን ቀንሼ ‘ኸረ ሱዳን ጠረፍ ድረስ ያስፈንጥሩት’ አልኩ፡፡ ማታ ሥራ አልቆ ስንወጣ ከኋላዬ መጣና… ‘እስከ ሱዳን ጠረፍ ድረስ የምስፈነጠረው ምን አድርጌሀ ነው’ አለኝ፡፡  ከዛ በኋላ አለ አህራማችን ዜና ሲያቀርብ ማዳመጥ እንጂ ‘የአድማጭ አስተያየት’ መስጠት ትቻለሁ፡፡
“ከሥራ ወጥቼና በተከታዮቹ ቀናት የሆነውን ከዕለታት አንድ ቀን፣ ከቻልኩ በዚቹ ‘ዳየሪ፣’ ካልቻልኩ ሌላ ገዝቼ፣ ‘ከዕለታት አንድ ቀን…’ እያልኩ መጻፌ አይቀርም፡፡ እኔ ለጉድ የፈጠረኝ ሰው ልሁን፣ የሰው ልጅ እንዳለ ለጉድ የተፈጠረ ይሁን ግራ የገባኝ ነኛ!”
እናማ…ይህ ‘ዳየሪ’… ተቆፈሮም ይሁን ራሱ ፈንቅሎ ወጥቶ… ሲገኝ የእጅ ጽሁፉን ለመተየብ በጎ ፈቃደኝነቴ ይመዝገብልኝማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 6112 times