Sunday, 23 October 2016 00:00

“በእርቀ ሰላም በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የተደረገው ጥረት ከሽፏል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

     የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መተግበሩን ተከትሎ፣ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ የተደረገው ጥረትና መንግስት ተገዶ ወደ እርቀ ሰላም እንዲገባ በማድረግ፣ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የተደረገው ጥረት መክሸፉን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌታቸው አምባዬ አስታወቁ፡፡
አዋጁ ያስፈለገበትን ምክንያትና እስካሁን ያለውን አፈፃፀም ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ከትናንት በስቲያ በስፋት ያብራሩት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በአገሪቱ ላይ መረጋጋት እየተፈጠረ፣ የሰዎች ደህንነትና ቁሳዊ ሀብቶች ከውድመት እየተጠበቁ ነው ብለዋል፡፡
በተቃውሞ ወቅት በጦር መሳሪያ የታጀቡ ትንንሽ ቡድኖች ራሳቸውን በማደራጀት፣ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ፊት ለፊት ፍልሚያ የጀመሩበት ሁኔታ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፤ ሀገሪቱ የበለጠ አደጋ ላይ እንዳትወድቅ በማሰብ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁ ሀገሪቱ የተጋረጠባትን ስጋት እየቀለበሰ ነው ብለዋል፡፡
በኢሬቻ በአል ላይ የተፈጠረውን ግጭትና የህይወት መጥፋት ተከትሎ ከበአሉ የተበተነው ኃይል፣ በአዲስ አበባ  ዙሪያ ባሉ ከተሞች ሰፍሮ እንደነበር የገለፁት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ የተለያዩ ቡድኖችን በማደራጀት ሃዋሳን፣ አዳማንና አዲስ አበባን ወደ መሳሰሉ ትላልቅ ከተሞች እንዲገቡ ጥረት ሲደረግ ነበር ብለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የአዲስ አበባ ህዝብ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቆ እንደነበር        ጠ/አቃቤ ህጉ ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ የትራንስፖርት ሁኔታም ተፋልሶ ነበር የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ ወደ ህዳሴ ግድብ የሚወስደው መንገድ ለአንድ ሁለት ቀን በመዘጋቱ ለተወሰኑ ቀናት ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶች እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከሱዳን የሚገባ ነዳጅ መተማ ላይ ይታገት እንደነበርም ጠቁመው፤ ከአዋጁ በኋላ እነዚህ ሁሉ ወደነበሩበት ተመልሰዋል ብለዋል፡፡
የአዋጁ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ ‹‹የፀረ ሠላም ሃይሎች ውጥን ከሽፏል›› ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በተለይ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል በመናድ፣ መንግስትን ለመቀየር ሲደረግ የነበረው ጥረት አልተሣካም ብለዋል፡፡ ‹‹በሃይል መንግስትን መገልበጥ የማይቻልበት ሁኔታ ካለ፣ መንግስት ተገዶ ወደ እርቀ ሠላም የሚገባበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን ብለው የቀየሱት ስልት ህልም ሆኖ ቀርቷል ሲሉ አስረድተዋል አቶ ጌታቸው፡፡ ‹‹በዚህች ሃገር ቁልፍ የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው በህዝቦች ቀጥተኛ ምርጫ እንጂ በእርቀ ሠላም፣ በአቋራጭ ወደ ስልጣን የሚመጣበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል መልዕክት ያስተላለፈ ትልቅ ህጋዊ እርምጃ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡
‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም ገና ተጀመረ እንጂ የመጨረሻ እልባት ላይ የደረሰ ባለመሆኑ ያስቀመጠውን አላማ እስኪያሣካ ድረስ ህብረተሰቡ ከህግ አስከባሪ አካላትና ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል›› ብለዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከትናንት በስቲያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን የአዋጁን አፈፃፀም የሚያስከትል መርማሪ ቡድንም አቋቁሟል፡፡  

Read 9415 times