Sunday, 23 October 2016 00:00

የኢንተርኔት መቋረጥ ዲቪ የሚሞሉትንም አስቸግሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ኢትዮ ቴሌኮም “ከደንበኞቼ ቅሬታ አልደረሰኝም” ብሏል

   በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ የኢንተርኔት ካፌ ከፍቶ መስራት ከጀመረ 7 ዓመታት ያስቆጠረው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ወጣት፤ በየዓመቱ በዚህ ወቅት የአሜሪካን ዲቪ ሎተሪ በማስሞላት ዳጎስ ያለ ገቢ ያገኝ እንደነበር ይናገራል፡፡ ዘንድሮ ግን በከተማዋ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ፣ የተለመደውን አገልግሎት ለደንበኞቼ መስጠት እንዳልቻለ ይገልፃል፡፡ በአማራጭነት የዋይ ፋይ አገልግሎት መስጫ ቢኖረውም በአግባቡ የሚሰራ ባለመሆኑ፣ እንኳን ዲቪ ለማስሞላት ይቅርና  የኢንተርኔት አገልግሎት በቅጡ ለመስጠት አዳግቶኛል ብሏል፡፡
የኢንተርኔት አገልግሎት በመስጠት ብቻ በቀን በአማካይ ከ300-500 ብር ገቢ ያገኝ እንደነበር የሚናገረው የኢንተርኔት ካፌ ባለቤት፤ የኢንተርኔት መቋረጥ የሥራ ዘርፉን እንዳስቀየረው ይናገራል። “የኮምፒውተር ፅሁፍ፣ መጠረዝና፣ የፎቶ ኮፒ ስራዎችን ብቻ ለመስራት ተገድጄአለሁ” ብሏል። በየአመቱ ጥሩ ገቢ ያስገኝለት የነበረው ዲቪ የማስሞላት ስራም በኢንተርኔት መቋረጥ ሳቢያ መስተጓጎሉን ገልጿል፡፡  
የዲቪ አመልካቾች በኢንተርኔት መቋረጥ የገጠማቸውን ችግር በተመለከተ ለአሜሪካ ኤምባሲ ላቀረብነው ጥያቄ፤ ችግሩ ከዲቪ ማመልከቻ ድረ ገፁ ሳይሆን ከኢንተርኔት መንቀራፈፍና መቆራረጥ ጋር የተያያዘ ነው ብሏል፡፡
“አመልካቾች የ2018 የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ ማመልከቻን በኢንተርኔት ሞልተው ለመላክ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል እንገነዘባለን፡፡ ይሄ አስቸጋሪ ሁኔታ በመከሰቱም በእጅጉ እናዝናለን፡፡  ችግሩ ያለው ከእኛ ድረ-ገፅ አይደለም፤ ከኢንተርኔት መቆራረጥና መንቀራፈፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አመልካቾች የተሻለ የኢንተርኔት ግንኙነት ለማግኘት በቀን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ሙከራቸውን በትዕግስት እንዲገፉበት እንመክራለን፡፡ ከኢንተርኔት ካፌዎች ወይም ከሌሎች የኢንተርኔት ማዕከሎች አገልግሎቱን ለማግኘት ቢሞክሩም አይከፋም፡፡ ለዲቪ አመልካቾች መልካም ዕድል እየተመኘን፣ ማንኛውም አመልካች ከጥቅምት 28 ቀን 2009 ዓ.ም በፊት ማመልከቻውን ሞልቶ መላክ እንዳለበት ለማስታወስ እንወዳለን” ብሏል ኤምባሲው፡፡
የኢንተርኔት መቋረጥን በተመለከተ ለኢትዮ ቴሌኮም ላቀረብንለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ “እስካሁን ከደንበኞቼ የቀረበልኝ ቅሬታ የለም” ብሏል፡፡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከሰሞኑ፤ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ሲዘግቡ መሰንበታቸው ይታወሳል፡፡

Read 6988 times