Saturday, 15 October 2016 13:15

“ቫይረሶቹ፣ ባክሪቴያዎቹ፣ ፈንገሶቹ... ወዘተ... የሚድኑ ናቸው”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

   በዚህ ሕትመት የምናስነብባችሁ ከአንድ ባለታሪክ የተላከልንን ገጠመኝ መነሻ በማድረግ ይሆናል።ባለታሪኩዋ ሕይወት ተስፉ ከቃሊቲ አቃቂ ናት።
 “...እኔ በሕይወት ዘመኔ ትዳር መስርቼ አላውቅም። ነገር ግን ከትዳር ባልተናነሰ መልኩ የነበረኝ ጉዋደኛ በጣም የማምነው እና የምወደው ነበር። ከእርሱ ጋር በትንሹ ወደ አስራ አምስት አመት ቆይተናል። በዚህ ሁሉ ጊዜ እሱም እንጋባ ብሎኝ አያውቅም። አኔም ደግሞ እሱ ካልጠየቀኝ ምንብዬ እጠይቃለሁ ስል ትዳር ለመመስረት ጥያቄ አላቀረብኩም። በዚህ መሐል ግን ሁለት ልጆችን አፍርተናል። ልጆቹ የዘጠኝና የአምስት አመት ሴትና ወንድ ልጆች ናቸው። ታዲያ... የመጀመሪያዋ ልጅ ስትረገዝ እባክህን ቢያንስ ቀለበት እንኩዋን እናድርግ ብዬ ብጠይቀው ምን ጎደለሽ እና ይህን ትጠይቂኛለሽ?... ቀለበት ምናምን ለታይታ ካልሆነ ምን ያደርጋል? ብሎ ሲቆጣኝ ዝምታ ነበር መልሴ።...
“ሰውየው ሀብታም ነጋዴ ሲሆን እኔ እስከማ ውቀው ድረስ ሚስቱ እኔ ብቻ ነኝ። በስራ ምክንያት ወደውጭ ሀገርም ድረስ ይሄዳል። እኔም ቤ ሙሉ ስለሆነ ምንም ካልጎደለኝ ምን ቸገረኝ ብዬ ዝም አልኩኝ። የሁዋላ ሁዋላ ግን አንድ ነገር ተከሰተ። እኔ ማህጸኔን እየታመምኩ ተቸገርኩ። ወደ ሕክምናው ስሄድ በግብረስጋ ግንኘነት ሳቢያ የሚተላለፍ ሕመም መሆኑ ተነገረኝ። ሕክምናውም ሁለታችንንም እንደሚመለከት እና ባለቤም መታከም እንዳለበት ነበር ከሐኪሙ ያወቅሁት። ይህንኑ ባስረዳው በጣም ተቆጣኝ። ሂጂና ለአንቺ የሚሰጡሽን ሕክምና ተከታተይ እንጂ ስለእኔ ምንአገባሽ? አለኝ። እኔም ተመልሼ ለሐኪሙ ስነግረው እጅግ አዝኖ... በይ በቃ... ወደእኛ መምጣት ካልፈለገ... ይህንን ለእራስሽ... ይህንን ደግሞ ለእርሱ ስጭ ብሎ መድሀኒት አዘዘልኝ ። እኔም ወስጄ ስሰጠው ተቀብሎኝ መኪና ኪስ ውስጥ ወረወረው። ለካንስ መድሀኒቱን አልወሰደም። ስለሆነም እኔ ሕመሙ ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ እንደገና ተመለሰብኝ።...
“ከማህጸኔ ፈሳሽ ይታያል። እንደገናም ሐኪሙ ጋ ተመልሼ ስሄድ ... ባለቤትሽ መድሀኒቱን መጠቀሙን አረጋግጭና ተመለሽ አለኝ። እኔም ተመልሼ ብጠይቀው...አንቺ ከየትም ለቃቅመሽ ባመጣሽው ህመም እኔ አልሰቃይም...እንዲያውም ከዚህ በሁዋላ አላውቅሽም...እየሄድሽ መድሀኒትሽን ለራስሽ ተጠቀሚ ብሎ አመነጫጨቀኝ። በጣም አዝኜ ሕክምናውን እንደገና ቀጥዬ አሁን በሰላም እኖራለሁ።ነገር ግን ሁኔታውን ሳጣራ ልክ እንደእኔ አይነት ማለትም በትዳር ከእርሱ ጋር ያልተጣመሩ... ነገር ግን ከትዳር በላይ አብረው የሚኖሩ ሶስት ሴቶች አሉ። ማንኛችንም ጋ አለ ወይንም የለም የማይባል ሰው ነው። ምክንያቱም በንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት አንድ ወር ወይንም ከዚያ በላይ በኢትዮጵያም ሆነ ዱባይ በመሳሰሉት ሀገራት ስለሚሄድ በዚያ ሰበብ ከፈለጋት ሴት ጋር የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። ነገር ግን ሕመሙ ሲመጣ ከአንዱዋ ወደሌላዋ እያዛመተ... ደግሞም አልታከምም እያለ ይኖራል። ይህንን ያረጋገጥኩት ከጉዋደኛው ነው። ችግሩ ሲፈጠር ለጉዋደኛው አማክሬው ነበርና የሰጠው መልስ...እኔ ከእሱዋ ጋር አራት ቤተሰብ አስተዳድራለሁ። ታዲያ አኔ ብታከም እነርሱ ካልታ ከሙ ምን ያደርጋል? የሚል መልስ ነበር የሰጠው። ታዲያ ይህ ትዳር ይባላል? በእርግጥ ፊርማ የለኝም እንጂ በቤተሰብ አብረውኝ በሚኖሩ የአካባቢ ህብረተሰብ ሁሉ ባል እንዳለኝ ነበር የሚታወቀው። ነገር ግን በአስቸጋሪ ጊዜ ያገኘሁት መልስ እጅግ አሳዛኝ ነው የሆነው።”
 ሕይወት ተስፉ ከቃሊቲ አቃቂ
 //////////////
ከላይ ያነበባችሁት ገጠመኝ በሌሎች አይከሰትም ማለት አይቻልም። በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ኤችአይቪን ጨምሮ ከሰው ወደሰው የመዛመት አንዱ ምክንያት ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ነው። የባለታሪኩዋን ገጠመኝ እንዳነበብነው ከሆነ ምናልባትም የእሱዋን ጉዋደኛ አምነው ከተቀመጡት ሴቶችም ይሁን ከዚያ ውጪም ከሌላ ወንድ ጋር የግብረስጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሴቶች ካሉ ችግሩ በሰውየው አማካኝነት ከአንዱዋ ወደአንዱዋ በቀላሉ የመዛመት እድል ያገኛል። ስለዚህ መጠንቀቅ ፣መታቀብ እና መጠቀም የተሰኙት መመሪያዎች በተቻለ መጠን ተግባራዊ ቢደረጉ ሰዎች ከእንደዚህ አይነት ችግር እንደሚድኑ ጥርጥር የለውም። ከፍሬ ነገሩ በመነሳት በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ምንነትና ባህርይ እናስነብባችሁ።
በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎች ሲባል፡-
የማህጸን በር ካንሰር፣
የማህጸን በር ካንሰርን የሚያመጡት ቫይረሶች በመሆናቸው ከወንድ ወደሴት በሚተላለፉበት ወቅት ለበሽታው መከሰት እንደ አንድ ምክንያት ይቆጠራል። አንዲት ሴት የማህጸን በር ካንሰር እንዳይከሰትባት ለመከላከል ሲባል የሚሰጠው ክትባት የግብረስጋ ግንኙነት መፈጸም ከመጀመሩዋ በፊት ቢሆን የሚመረጥ መሆኑን የህክምናው ዘርፍ ባለሙያዎች ያስረዳለሉ።
በአስገድዶ መደፈር ወይንም በሰምምነት በሚደረግ ግንኙነት ምክንያት የሴቷ ብልት የውስጥ ክፍል መቀደድ፣ በማስገደድም ይሁን በስምምነት በሚፈጸም ግንኙነት ሳቢያ የሚከሰት የሽንት መቋጠር ችግር፣
በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ ከሚፈጠር አግባብ ያልሆነ የኃይል መጠቀም ወይንም የሰውነት አለመመጣጠን ሳቢያ የሚፈጸም ከሆነ በሴቷ ብልት አካባቢ የሚገኙትን አካላት ጭምር የሚያጠቃ ይሆናል።
ማህጸን አካባቢ የሚፈጠር የቅማል ዘር፡-
በማህጸን አካባቢ የሚፈጠር የቅማል አይነት ከወንድ ወደ ሴት ወይንም ከሴት ወደ ወንድ ሲተላለፍ በሚፈጠረው የመራባት ሁኔታ ቅጫም ሊኖረው ሲችል ከዚያም ወደብብት እና ወደ አይን ፀጉር ጭምር ሊተላለፍ ይችላል።ስሜቱም በብልት ወይንም በብት ጸጉር ላይ የማሳከክእና የማቃጠል ሊሆን ስለሚችል ሴትየዋ ወይንም ሰውየው እንደዚህ ያሉ ስሜቶች ከታዩባቸው ቶሎ መፍትሔ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉት ...Sexually transmissible infectious ... ተብለው የሚለዩት ናቸው። እነርሱም በአማርኛው ፡-
ጨብጥ፣ ቂጥኝ፣ ውርዴ፣ አባኮዳ፣ ባምቡሌ፣ የሴቶችን ፈሳሽ የሚያመጣ
ፕሮቶዝዋ፣ ካንዲዳ የሚባል የፈንገስ አይነት እና ሌሎችም በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያትየሚተላለፉ ተብለው የሚፈረጁ ሕመሞች አሉ።
በብዛት በማህጸን አካባቢ የማህጸኑ፣የቱቦው እና የእጢው መቆሸሽ (pelvic inflammatory disease) በሚባል የሚጠራውን ሕመም የሚያመጡት ጎኖሪያ ጨብጥ፣ ክላይሚድያ ፣ማይኮ ፕላዝማ እና ዩሪያፕላዝማ የሚባሉ የህዋስ አይነቶች ናቸው። ስለዚህ ከግብረስጋ ግንኙት ጋር የሚያያዝ ችግር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ከተላላፊ በሽታዎቹ ጋር ያሉት ጠንቆች ፡-
ከማህጸን በላይ እርግዝና፣ ማህጸን ወይንም ብልት አካባቢ የሚኖር ሕመም፣ መካንነት ወይንም ልጅ አለመውለድ፣ በውስጥ አካል ጉበት፣ የሆድ እቃ አካባቢ መሰራጨት፣ የአእምሮ፣ የቆዳ፣ የልብ ኢንፌክሽን የማምጣት ...ወዘተ የመሳሰሉትን ሕመሞች ሊያስከትል ይችላል።
ከተጠቀሱት ሕመሞች በተጨማሪም በአለም አቀፍ ደረጃ በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት በመተላለፍ በሽታ ከሚባሉት ውስጥ ኤችአይቪ ቫይረስም አንዱ ነው።
ከግብረስጋ ግንኙነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የሰውነት ጠንቆች አሉ። እነርሱም ከላይ እንደተገለጸው ግንኙነት የሚደረግበት የሴቷ ብልት መቀደድ፣ ፊስቱላ የመሳሰሉት ነገሮች ባህሪያቸው መተላለፍ ሳይሆን በግንኙነት ምክንያት የሚከሰቱ ጠንቆች ሊባሉ የሚችሉ ናቸው።
የማህጸን በር ካሰርንም በቀጥታ ተላላፊ በሚል ከባድ ድምዳሜ መስጠት ባይቻልም ቀደም ሲል ካንሰሩ የነበረባት ሴትጋር በወሲብ የተገናኘ ሰው ወደሌላ ሴት ሲሄድ ቫይረሱን ሊያስተላልፍ ይችላል የሚሉ አስተያየቶች አሉ።
መፍትሔ ይሆናል በሚል አንዳንድ ሴቶች በግላቸው የሚወስዱዋቸው እርምጃዎች አሉ። ውሀ በማፍላት በጨው የመታጠብ ወይንም የመዘፍዘፍ እርምጃን ይወስዳሉ። ይህ በሰዎች ዘንድ ጥሩ ስሜትን ሊፈጥር ይችላል። ጨው ተፈጥሮአዊ ነገር ስለሆነ ምናልባት የማቃጠል ስሜት ይኖረው እንደሆነ እንጂ ጉዳቱ ብዙም አይታይም። ነገር ግን አንዳንድ ኬሚካሎችን እንደመታጠቢያ መውሰድ በቁስል ወይንም በተቆጣ ሰውነት ላይ ሌላ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል አይመከርም። ጨው ግን ብዙም ጥቅሙ ባይታወቅም ጉዳት ግን የለውም። ማድረግ የሚሻለው ግን፡-
ችግሩ ከመከሰቱ በፊት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ
ችግሩ ከተከሰተ በግልጽ ከፍቅረኛ ወይንም ከትዳር ጉዋደኛ ጋር መመካከር
ችግሩ ከተከሰተ በአስቸኳይ ወደጤና ተቋም በመሄድ ማማከር ይገባል።
ሰዎች አስቀድመው አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰዱ ቫይረሶቹ፣ ባክሪያዎቹ፣ ፈንገሶቹ እና የፕሮቶዞዋው እና ቅማሉን ጨምሮ የሚታከሙና ሊድኑ የሚችሉ ናቸው።
 መረጃ...
 ከተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ሰሎሞን ቁንቢ/ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና መምህር

Read 4969 times