Sunday, 16 October 2016 00:00

ያገር ሰላም

Written by  ድርሰት - ቺኑዋ አቼቤ ትርጉም - ፈለቀ አበበ
Rate this item
(2 votes)

ናይጄሪያዊው ደራሲ ቺኑዋ አቼቤ የትውልድ ሀገሩን አፍ መፍቻ ኢቦ ቋንቋ ያህል በሚያውቀው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመፃፍ የአፍሪካን ባህል
ለአለም ያስተዋወቀና፤ በተለይም Things Fall Apart በተሰኘ ድርሰቱ ላቅ ያለ ዝናን የተቀዳጀ ደራሲ ነው፡፡ ይኸ Civil Peace የተሰኘው
አጭር ልቦለዱ፤ በናይጄሪያ ብዙ ሕዝብ ያለው የኢቦ ጎሳ ‹‹ ነጻ የቢያፍራ ሪፐብሊክ ›› ብሎ ራሱን ለመገንጠል ባስነሳውና ከ1967-70 እ.ኤ.አ
ደም ያፋሰሰውን፤ አስከፊው ውጤቱ የቢያፍራ ሕዝቦችን በክፉ ጠኔ የደቆሰውንና ሚሊዮኖች በረሀብ የረገፉበትን የእርስ በርስ ጦርነቱን
ማብቂያ መቼት አድርጎ የጻፈው ነው፡፡

ጆናታን ኢዌቡ፤ ራሱን እጅግ በጣም እድለኛ ሰው አድርጎ ነበር የቆጠረው፡፡ ሰላም በተገኘ ማግስት የመጀመሪያዎቹ ጭጋጋማ ቀናት፤ ተጠፋፍተው የቆዩ ወዳጆች ሲገናኙ እርስ በርስ ከሚለዋወጧቸው ሰሞነኛ የሰላምታ አይነቶች ሁሉ፤ ‹‹እንኳን አተረፈህ!›› መባል ለእርሱ ፍጹም ልዩ ትርጉምና ጥልቅ ሀሴት ነበረው፤ ልቡ ጥግ ድረስ ዘልቆ የሚሰማ፡፡ ከጦርነቱ የተረፈው በምንም መመዘኛ ከማይገምታቸው አምስት በረከቶች ጋር ነዋ፡፡ የራሱን ነፍስ ጨምሮ፡ ከሚስቱ ማሪያና ከአራቱ ልጆቻቸው ሦስቱ ጋር። እንደ ምርቃትም ደግሞ አሮጌው ብስክሌቱም ተርፋለታለች፡፡ የብስክሌቷ መትረፍ ጉዳይም ቢሆን ለእርሱ ተአምር ነበረ፤ ምንም እንኳ ከአምስት ሰዎች ህይወት ጋር እሚነፃፀር ባይሆንም፡፡
ብስክሌቷም የራሷ የሆነ ታሪክ ነበራት፡፡ ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት አንድ ቀን ‹‹የአስቸኳይ ወታደራዊ ተልእኮ ጥሪ!›› ደረሳት፡፡ ብስክሌቱን ከራሱ መነጠል እንደ መርግ ቢከብደውም፤ ‹በአለቆቹ የዋህነት ተስፋ አድርጎ›፤ አሳልፎ ለመስጠት ፈቀደ፡፡ የለበሰው አሮጌ መናኛ ልብስ፡ አውራ ጣቶቹ ሾልከው የተጫማቸው አንዱ ሰማያዊ ሌላኛው ቡኒ አይነት ቀለም ያላቸው ጫማዎቹ፡ ወይም ደግሞ በእስኪርቢቶ በፍጥነት ጫር ጫር ተደርገው ትከሻው ላይ የተለጠፉለት ባለ ሁለት ኮከብ የማእረግ ምልክቶች፤ እኒህ ሁሉ አሳስበውት አልነበረም፡፡ ብዙ መልካም የሆኑና የላቀ የጀግንነት ገድል ያላቸው ወታደሮችንም ሲያዩዋቸው እንዲሁ ናቸውና፡፡ ከእርሱ በከፋ ሁኔታ የተጎሳቆሉም አሉ፡፡ ችግሩ አቋም አልባ ልፍስፍስ የተፈጥሮ ባህሪ ያለው ሰው መሆኑ ነበር፡፡ ስለዚህም ጆናታን የሚፈልገውን ለማድረግ በቅድሚያ ትእዛዝ አክባሪ ሆኖ መታየትን መረጠ፡፡ እናም የዘንባባ ዘንቢሉን በርብሮ ባገኘው ሁለት ፓውንድ ማገዶ ገዝቶ፤ ምግብ ሰርታ ለምትቸረችረው ለሚስቱ ማሪያ ሲሰጣት፤ እሷ ደግሞ ለካምፑ የወታደር አዛዦች፤ ጭማሪ አሳና የበቆሎ ቂጣ ሰጠቻቸውና፤ በዚህ መልኩ ብስክሌቱን መልሶ እጁ ለማስገባት ቻለ፡፡ በዚያው ምሽትም ብስክሌቱን በጥድፊያ እየጋለበ፡ የእሱን ትንሽ ልጅ ጨምሮ ሙታኑ ወዳረፉበትና የዙሪያው ቁጥቋጦ ከአይን ወደሚጋርደው የካምፑ መካነ መቃብር ሄዶ፤ብስክሌቱን ማንም በማይደርስበት ቁጥቋጦ መሀል ቀበራት፡፡ ከአንድ አመት በኋላ ጦርነቱ ሲያበቃ፤ ብስክሌቷን ቆፍሮ ሲያወጣት፤ ዝገቶቿን ለማስለቀቅ ትንሽ ዘይት መቀባባት ብቻ ነበር ያስፈለጋት፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔር ምን ይሳነዋል!›› አለ በእርካታ፡፡
ወዲያውም የታክሲ አገልግሎት እንድትሰጥ በማድረግ፤ የካምፑን አዛዦችና ቤተሰቦቻቸውን፤ ከካምፑ እስከ ዋናው አውራ ጎዳና ድረስ በተዘረጋው፤ የአራት ማይል ርቀት ባለው ሬንጅ የፈሰሰበት አስፓልት ላይ በማጓጓዝ፤ በቂ ገንዘብ አጠራቀመ። የአንድ ጉዞ ዋጋ ተመኑ ስድስት ፓውንድ ሲሆን፤ መክፈል የሚችሉ ሁሉ በዚያ መንገድ ላይ በብስክሌት ተፈናጥጠው በመጓዛቸው ብቻም ይደሰቱ ነበር፡፡ በሁለተኛው ሳምንት መጨረሻ ላይም የአንድ መቶ አስራ አምስት ፓውንድ ገቢ ለማግኘት የቻለ እድለኛ ሰው ለመሆን በቃ፡፡
ከዚህ በኋላም ወደ ኢኖጎ ከተማ ተጓዘና ሌላ ተአምር ፊቱ ድቅን ብሎ ጠበቀው፡፡ በፍፁም የማይታመን ነበር፡፡ አይኖቹን አሽቶ እንደገና ቀና ብሎ ሲያይ፤ አሁንም ፊት ለፊቱ ተገትሯል፡፡ ይህም እንዲሁ ለአምስቱ የቤተሰብ አባላት የተቸረ ሌላ በረከት ስለመሆኑ መናገር አያሻም፡፡ አዲሱ ተአምር በኦጉዪ አቅራቢያ የሚገኝ አነስተኛ መኖሪያ ቤት ነው፡፡ እውነት ነው፤ ለእግዚአብሔር ምን ይሳነዋል! ከጦርነቱ በፊት አንድ ዲታ ኮንትራክተር ከድንጋይ ያነፃቸው ሁለት ግዙፍ መኖሪያ ቪላዎች በስፍራው ላይ ቆመዋል፡፡ የጆናታን ኢዌቡ የጭቃና ቆርቆሮ መኖሪያ ቤትም ሳትሳቀቅ መሀላቸው ቆማለች። እርግጥ ነው የቤቷ በሮችና መስኮቶች የሉም፤ ከጣራዋ አምስት ቆርቆሮዎች ጭምር። ይኼ ግን ምን ችግር አለው?  የሆነው ይሁን፤ አሁን ሌሎቹ እንደርሱ ያሉና ገና ከጫካ ያልወጡቱ መኖሪያ ቤት ፍለጋ ከተማዋን ሳይወርሯት በፊት፤ ማልዶ ተነስቶ ከየጎረቤቱ ደጃፍ ንቅል አሮጌ ጣራና የወዳደቁ ማገሮችንና ጣውላዎችን ለመለቃቀም ወደ ኢኖጎ ከተማ ሄደ፡፡ የወላለቁትን የቤት ፍራሽ እንጨቶች፡ ቁርጥራጭ ጣውላና ብረታ ብረቶች ወደ በርና መስኮትነት ለመለወጥም፤ በአምስት የናይጄሪያ ሽልንግ ወይም በሀምሳ ቢያፍራን ክፍያ የሚሰራለትን፤ ዱልዱም መዶሻ፡ ጥርሶቹ የረገፉ መጋዝና የተወለጋገዱ አሮጌ ምስማሮችን  በስራ ከረጢቱ ያነገተ ምስኪን አናጢ አገኘ፡፡ ሂሳቡን ከፍሎ ሲያበቃ፤ በደስታ ከተጥለቀለቁት ቤተሰቡ ጋር ወደ መኖሪያ ቤቱ ገባ፡፡ የአምስት ነፍሶችን አንገቶች የተሸከሙ ትከሻዎች፡፡
ልጆቹ፤ ከወታደሮቹ መካነ መቃብር ስፍራ ማንጎ እየለቀሙ በአነስተኛ ዋጋ ለወታደሮቹ ሚስቶች ሲሸጡ፤ ሚስቱ ደግሞ፤ አዲስ ህይወት ለመጀመር ለሚንደፋደፉት የመንደሩ ነዋሪዎች ቁርስ የሚሆን ድቡልቡል ብስኩት እየጠበሰች መሸጥ ጀመረች። እርሱም ብስክሌቱን በመንደሩ ዙሪያ እየጋለበ፤ ቤተሰቡ በሚቆጥበው ገንዘብ ትኩስ የዘንባባ ፍሬዎችን ሰብስቦ፤ሰሞኑን እንደገና በተከፈተው የመንገድ ላይ የህዝብ ቧንቧ ውኃ በቤቱ ውስጥ ጠምቆ እያዘጋጀና ያለ ስስት እየቸረፈሰ እየሰፈረ፤ ለወታደሮችና ለሌሎችም በቂ ገንዘብ ላላቸው እድለኞች የሚያቀርብበት የመጠጥ መሸጫ ቤት ከፈተ፡፡
በድንጋይ ከሰል አውጪነት ይሰራበት ወደነበረው መስሪያ ቤቱ በየቀኑ ይሄድ ነበር፤ ከዚያም በየሁለት ቀኑ፤ በመጨረሻም ምን እየተካሄደ ለማወቅ ያህል ብቻ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቅ ይል ጀመር፡፡ አውጥቶ አውርዶ የደረሰበት ሀቅ ቢኖር፤ መኖሪያ ቤት ማግኘታቸው ከምንም ነገር በላይ፤ ከሚያስበውም ሁሉ በላይ ትልቅ በረከት መሆኑን ነው፡፡ እንደ እርሱ የድንጋይ ከሰል አውጪ የነበሩቱ የቀድሞ የስራ ባልደረቦቹ፤ አሁንም ድረስ ማደሪያቸውን በመስሪያ ቤቱ ጊቢ ውስጥ አድርገው፤ በትልቅ ትሪ በጋራ የሚበሉትን ምግብ ጥደው ሲያንፈቀፍቁ ነው የሚውሉት፡፡ ማንም ምንም ያለው አልነበረምና እያደር በየሳምንቱ መሄዱንም እርግፍ አርጎ ትቶ በወይን መጠጥ ቤቱ ስራ ተጠመደ፡፡
አዎን፤ ለእግዚአብሄር ምን ይሳነዋል! ደግሞ ሌላ ያልተጠበቀ እድል ከተፍ አለ፡፡ ከአምስት ቀናት በሚለበልብ ጠራራ ፀሐይ በግብ ግብ የተሞላ ወረፋ ጥበቃ በኋላ፤ በቀውጢው ወቅት ላበረከተው አገልግሎት ወንፈል፤ የሃያ ፓውንድ ክፍያ ተቆጥሮ እጁ ላይ ተቀመጠለት፡፡ ገና የክፍያው መጀመር ሲሰማ ነበር ለእሱና ብዙ መሰሎቹ የአውዳመት ብስራት አይነት ፈንጠዝያ የፈጠረባቸው፡፡ ክፍያውንም (በስራ ቋንቋ ከጠሩት ጥቂት ሰዎች በቀር) ‹‹ድጎማ ጉርሻ›› ብለውታል፡፡
ጆናታን ገንዘቡ እጁ ላይ እንዳረፈ ያደረገው ነገር፤ ጥቅልል፡ ጭምድድ፡ እጥፍጥፍ አድርጎ በመዳፉ መሀል ጨብጦ እጁን ሱሪ ኪሱ ውስጥ መቅበር ነው፡፡ በጣም መጠንቀቅ ይገባው ነበር፡፡ምክንያቱም ከሁለት ቀናት በፊት ጠዋት ክፍያውን ተቀብሎ እንደወጣ ገንዘቡ ጠፍቶበት፤ በዚያ  የሰልፍ ውቅያኖስ መሀከል እንደ እብድ አድርጎት ራሱን ስቶ እንደተዘረረው ሰውዬ መሆን አይፈልግማ፡፡ ያ ሁሉ ወፈ ሰማይ ወረፋ ጠባቂ  ለሰውየው ከማዘን ይልቅ በጥንቃቄ ጉድለቱ እሱኑ ነበር የኮነነው። በተለይ  ደጋግሞ ልብሶቹን እያዳረሰ በሚፈትሽ ጊዜ ኪሶቹን ሲያገለባብጥ፤ በአንደኛው ኪሱ መሀል የሌባ ጭንቅላት ማሳለፍ የሚችል ሰፊ ቀዳዳ ሲያዩማ አበቃ፡፡ በእርግጥ ሰውየው፤ ብሩን ያስቀመጠው ባልተቀደደው ሌላኛው ኪሱ ውስጥ እንደነበር ገልብጦ እያወጣና እያሳየ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ስለዚህ ማንም ቢሆን መጠንቀቅ ነበረበት፡፡
ጆናታን ወዲያው ደሞ ገንዘቡን ወደ ግራ መዳፉ አዛውሮ፣ ግራ ሱሪ ኪሱ ውስጥ ከተተና ቀኝ እጁን ነፃ አደረገ፡፡ ሰላምታ ቢቀርብለት አፀፋ መስጠት እንዲችል፡፡ በዚህ መልኩም፤ እያንዳንዱን ቀረብ ያለውን ሰው በመገንገን እያስተዋለ፣ራሱን በጥብቅ ቁጥጥር ስር አውሎ ቤቱ ደረሰ፡፡
ለወትሮው ብርቱ እንቅልፋም ነበረ፤ በዚያ ምሽት ግን የጎረቤቶቹ ድምጽ ቀስ እያለ እየጠፋ ሲሄድና መንደሩ ሁሉ በጸጥታ እስኪዋጥ ድረስ አደመጠ። ከመኖሪያ ቤታቸው ጥቂት ራቅ ብሎ ካለው ስፍራ፤ የሌሊት ተረኛው ዘብ በየአንድ ሰአቱ ብረት እየቀጠቀጠ የሚያሰማውን ድምጽ፤ የሌሊቱን ሰባት ሰአት ደወል ካሰማ በኋላ፤ ሁሉም ነገር ጸጥ እረጭ አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ከቀልቡ እስከተፋታባት ቅጽበት፤ ለመጨረሻ ጊዜ በጆናታን አእምሮ የተመላለሰው ሀሳብ ይኸው መሆን አለበት፡፡ ገና ጭልጥ ያለ እንቅልፍም አልጣለውም ነበር፤ በድንገት በርግጎ ሲነሳ፡፡
‹‹ማነው የሚያንኳኳው?›› የቤቱ ወለል ላይ ከጎኑ የተኛችው ሚስቱ አንሾካሾከች፡፡
‹‹እንጃ›› ትንፋሹን ውጦ መልሶ አንሾካሾከላት፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ የተሰማው አስገምጋሚ መንኳኳት፤ ረጋ ሰራሽዋን የመኖሪያ ቤት ገንጥሎ መጣል የሚችል አይነት በጣም ሀይለኛ ነበር፡፡
‹‹ማነው?›› ብሎ ጠየቀ ከደረቀ ጉሮሮው በወጣ የሚንቀጠቀጥ ድምጹ፡፡
‹‹ሌባውና አሽከሮቹ›› ረጋ ያለ ምላሽ ተሰማ፡፡ ‹‹በሩን ትከፍትልን?›› ንግግሩን ከእስካሁኖቹ ሁሉ የባሰ ከባድ ማንኳኳት ተከተለው፡፡
ቀድማ ጩኸቷን ያቀለጠችው ማሪያ ነበረች፤ እርሱ ለጠቀ፤ ከዚያም ሁሉም ልጆቻቸው፡፡
‹‹ፖሊስ! ኡ...! የጎረቤት ያለህ! ኡ...! ፖሊስ! ኡ...! አለቀልን! ገደሉን! ጎረቤቶች ተኝታችኋል?! ተነሱ! ድረሱልን! ፖሊስ! ኡ...!››
በዚህ ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ ቆዩና ድንገት ዝም አሉ፡፡ ምናልባት ሌቦቹን አስፈራርተው አባርረዋቸው ይሆናል፡፡ ፍጹም የሆነ ጸጥታም ነገሰ፡፡ ግን ለአጭር ፋታ ብቻ ነበር የቆየው፡፡
‹‹እሺ በቃ ጨረሳችሁ?›› ከውጪ ያለው ድምጽ ጠየቀ፡፡ ‹‹ትንሽ ልንረዳችሁ እንድንችል ብታደርጉን። ሄይ ዘንካቶቹ!››
‹‹ፖሊስ! ኡ...! ዘራፊዎች! ኡ...! የጎረቤት ያለህ! ኡ...! ሊጨርሱን ነው! ኡ...! ፖሊስ! ኡ...!››
ከሌቦቹ አለቃ ጋር ያሉ ቢያንስ የአምስት ሰዎች ያህል ድምጽ ይሰማል፡፡
አሁን ጆናታንና መላ ቤተሰቡ በፍርሀት ርደዋል። ማሪያና ልጆቹ ሩሀቸውን እንዳጡ ሁሉ በማይሰማ ድምጽ ይንሰቀሰቃሉ፡፡ ጆናታን ያለማቋረጥ ያቃስታል፡፡
የነገሰውን ጸጥታ ያደፈረሰ አስፈሪ ንግግር ቀጠለ። ግብረ አበሮቹ፤ የመጡበትን ጉዳይ ይፈጽሙ ዘንድ አለቃቸውን ሲጠይቁ ሰማ፤ጆናታን፡፡
‹‹ጓደኛ! ልንቀሰቅሳቸው ሞከርንኮ፤ እነሱ ግን እልም ያለ እንቅልፍ ላይ ናቸው መሰለኝ፡፡ እና አሁን ምን  እናድርግ ነው የምትለኝ? ወታደሮች እስኪመጡ ትጠብቃለህ ወይስ እኛ ሄደን አንድንጠራልህ ትፈልጋለህ? ደሞ ወታደር ሳይሻል አይቀርም፤ አይመስልህም? ፖሊስን ይቦንሰዋላ! አይደለም’ንዴ?!››
‹‹ነው እንጂ!›› አሉ ግብረ አበሮቹ፡፡ ጆናታን አሁን ደግሞ ከቅድሙም የሚበዙ ድምጾችን የሰማ መሰለውና ክፉኛ ያቃስት ጀመር፡፡ እግሮቹ ተብረከረኩበት፡፡ ጉሮሮው እንደ ብርጭቆ ወረቀት ሻከረ፡፡
‹‹ጓደኛ! ለምንድነው የማታወራው? የጠየቅኩህን መልስልኝ’ንጂ! ወታደሮች ሄደን እንጥራልህ ወይእ?!››
‹‹በፍጹም!››
‹‹ይመችህ! ስለዚህ አሁን ጭውቴያችን ስለ ቢዝነስ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እኛ ቀሽም ቀማኞች አይደለንም፡፡ ማጇከም፡ ማዋከብ፡ መቀወጥ ምናምን ይደብረናል፡፡ የቀውጢው ዘመን አክትሟላ! ጦርነት፤ ከሚፈነዳዱት ግሳንግሶቹ ጋር ላሽ ብሎ መርሹዋል! ከእንግዲህ የእርስ በርስ ጦርነት የለም፡፡ ይሄ ጊዜ ያገር ሰላም የተረጋገጠበት ጊዜ ነው። አይደለም እንዴ?!››
‹‹ነው እንጂ!›› አስደንጋጭ የግብረ አበሮቹ የደቦ ምላሽ ድምጽ፡፡
‹‹ከእኔ የምትፈልጉት ምንድነው? እኔ መናጢ ድሀ ነኝ፡፡ አለኝ እምለውን ሀብት ሁሉ የጦርነቱ እሳት በልቶታል፡፡ ለምን ወደኔ መጣችሁ? ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች ታውቋቸው የለ! እኛ ለራሳችን...››
‹‹አረ እኛም እንደሱ የሚል ነገር አልወጣንም! ብዙ ገንዘብ የሌለህ ሰው መሆንህንማ አላጣነውም። ግን ደሞ እኛም ካንተ የባስን ያጣን የነጣን ድሆች ነን፡፡ ቤሳ ቤስቲን የሌለን፡፡ ስለዚህ አሁን ኢናውን መስኮት በርግደውና አንድ መቶ ፓውንድ ብቻ አቀብለኸን ላጥ ብለን እንሸበለልልሀለን፡፡ ካልሆነ ግን ወደ ውስጥ ገብተን የሚጢጢውን ልጅ የጊታር ጨዋታ እናንጣጣልሀለን፤ ልክ እንደዚህ...››
የአውቶማቲክ ጠብመንጃ ተኩስ በሰማዩ ላይ ተንጣጣ፡፡ ማሪያና ልጆቹ እንደቀድሞው ድምጻቸውን አሰምተው ማልቀስ ጀመሩ፡፡
‹‹እንዴ! ቺካንሳዋ እንደገና ሙሾዋን አስነካችው! መነፋረቁ አይበጅም፡፡ ነገርናችሁ’ኮ እኛ ደደብ ሌቦች አይደለንም! ያገኘናትን ትንሽም ፍራንካ ብትሆን ተቀባብለን ላጥ እምንል ጨዋዎች ነን እንጂ። ሌላ ብዙ ስራ ይጠብቀናል፡፡ ጓደኛ! በስራ ብዛት ተወጥረን የለን’ዴ?!››
‹‹በጣም እንጂ!››
‹‹ወዳጆቼ›› ጆናታን ጎርነን ባለ ድምጽ መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹ያላችሁትን ሁሉ ልቅም አድርጌ ሰምቻለሁ፤ እናም አመሰግናለሁ፡፡ ግን እኔ አንድ መቶ ፓውንድ ቢኖረኝ ኖሮ...››
‹‹አትገግማ ሼባው! አጉል ሰፋጣ ጀምረኸን ትእግስታችን ተሟጥጦ እኛም መሳፈጥ እንድንጀምር አትወስውሰን፡፡ ጓ! ብለን ወደ ውስጥ ድርግም ካልን ደሞ አንተም ዷ! ብለህ ከነገብባው ጨረቃ ላይ ትቀራለህ፡፡ ስለዚህ የሚሻለው...››
‹‹የፈጠረኝን አምላኬን እላችኋለው! ገብታችሁ በቤቴ ውስጥ አንድ መቶ ፓውንድ ካገኛችሁ ውሰዱትና ግደሉኝ! እኔንም፡ ሚስቴንም፡ ልጆቼንም ጨምራችሁ፡፡ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡ በህይወቴ ያለኝ ገንዘብ ቢኖር ‹ድጎማ ጉርሻ› ብለው ዛሬ የከፈሉኝ ሃያ ፓውንድ ብቻ ነው፡፡
‹‹ፒስ! በቃ እንመርሻለን፡፡ መስኮቱን በርግደውና ሃያ ፓውንዱን ከቹ ከቻሳ ፤ ምን እናደርጋለን፤ ይሁና እንግዲህ ፡፡››
የሌባው ግብረ አበሮች ባለመስማማት ሲያጉረምርሙ ድምጻቸው ጎልቶ ይሰማ ጀመር። ‹‹ ‹‹ ሼባው ሲፎግረን ነው! ፋራ አረገን እንዴ?!... ቀዳዳ በለው! አንሰማውም!... ሌላም ገንዘብ አለው! ሲሸመጥጠን ነው’ንጂ!...ወደ ውስጥ ገብተን በደንብ እንፈትሸው!...ሃያ ፓውንድ ምን ልናረጋት ነው?!››
‹‹ዝጉ!›› የሌቦቹ አለቃ ቀጭን ትእዛዝ እንደ መብረቅ ሲፈነዳ፤ የአጃቢዎቹ ጉርምርምታ በጸጥታ ተዋጠ፡፡ ‹‹እየሰማኸን ነው ሼባው? ገንዘቡን ቶሎ ከች አርገው!››
‹‹እሺ መጣሁ›› አለ ጆናታን፤ በጨለማው ውስጥ፤ ከመኝታ ምንጣፉ ራስጌ ያኖራትን የትንሽዬዋን የገንዘብ ሳጥኑን ቁልፍ እየዳበሰ፡፡
ገና ጎህ እንደቀደደ፤ ጎረቤቶቹና ሌሎችም ያካባቢው ነዋሪዎች ለማጽናናት ሲሰባሰቡ፤ ጆናታን አምስት የወይን ደምበጃኖቹን በብስክሌቱ እቃ መጫኛ ላይ እያነባበረ ለጉዞ በመዘጋጀት ላይ ነው። ሚስቱ በምድጃው የእሳት ወላፈን በላብ ተጠምቃ፤ በጣደችው ሰፊ የሸክላ ዋዲያት ሙሉ ዘይቷን እያንቸከቸከች፤ ድቡልቡሎቹን ሊጦች እያገላበጠች ትጠብሳለች፡፡ ትልቁ ልጃቸው ደግሞ ትናንት ወይን የተሸጠባቸው የቢራ ጠርሙሶች ቂጥ ስር የቀረውን ጭላጭ አለቅልቆ እየደፋ ጠርሙሶቹን በማጠብ ላይ ነበር፡፡
‹‹እኔ ከምንም አልቆጠርኩትም›› አላቸው ለአጽናኞቹ፤ የጫነውን እቃ ከሚያስርበት ገመድ ላይ አይኑን ሳይነቅል፡፡ ‹‹ቀድሞ ነገር ‹ድጎማ ጉርሻ› ምንድነውና? ያለፈውን ሳምንት የኖርኩት በሱ ነበር እንዴ? ወይስ ‹ድጎማ ጉርሻ› ጦርነቱ ከሰለቀጣቸው ስንትና ስንት ነገሮች ይበልጣል? ስለዬህም አቋም ያዝኩና እንዲህ አልኩ፤ ‹ድጎማ ጉርሻ› ይሉት ነገር ዶግ አመድ ይሁን! ‹ጦሱን ጥምቡሳሱን ይዞ› ይሂድልኝ፤ ሌሎቹ ስንትና ስንቱ ወደሄዱበት፡፡ ለእግዚአብሔር ምን ይሳነዋል።››
ምንጭ - GLENCOE
Civil Peace        
 by - Chinua  Achebe.

Read 2385 times