Sunday, 16 October 2016 00:00

“በዚች ዕድሜያችን ስንቱን ዋጥነው!”

Written by  በተፈራ ተክሉ
Rate this item
(6 votes)

     ረዳት ይጠራል፡፡ ልጅቷ (“የዘመነችቷ” አላችሁ? የደበበ ሠይፉን ግጥም በሰበቡ ለማስታወስ:: በሰበቡ ስል ደግሞ የአስቴር አወቀ ዘፈን ትዝ አለኝ፡- “ሰበቡ ኧረ ና ሰበቡ አንት ሰበበኛ…”) አንገቷን ሰገግ አድርጋ ቃኝታ ልትመለስ ስትል ረዳት። “ከኋላ አለ” አላት፡፡ “ከኋላ ወንበር አልቀመጥም!” አለች፡፡ የሆነ መጥፎ ስድብ ይወረውራል ብዬ አቆብቁቤ ስጠብቅ ረዳት ዝም አለ፡፡ እድሜ ይስጠው፡፡ ከጎኔ የተቀመጠ ሌላ ተሳፋሪ ግን በማያገባው ጥልቅ ብሎ፡ “ከኋላ ጅብ አለ?” አለ በምጸት (ለማሳቅ፣ ወሬ ለመጀመር፣ ነገረኛ ስለሆነ ወይም ስለቸኮለ ታክሲው ሞልቶ ቶሎ መሄድ ፈልጎም ይሆናል)፡፡ እኔ ግን ላለመሳቅ ወይም አስተያየት ከመስጠት ለመቆጠብ ጥረት አደረግኩ፡፡ “መብቷ እኮ ነው!” ብዬ ብቆጣው ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን፣ ተናዶ የልጅቷን መብት እንደጣሰው፣ “የእርጎ ዝንብ!” ብሎ የመቆጣት መብቴንም ፊቴንም ቢጥሰው…፡፡ “ሆ፤ በገዛ እጄ” አለ ክበበው ገዳ፡፡
“The right to offend ወይም የማናደድ መብት የለኝም ወይ?” ስል ግን አብሰለሰልኩ (ማብሰልሰል ይሻላል)፡፡ መናደድና ማናደድ መጥፎ ነው ምናምን አይሰራም፡፡ የሚያናድድ ነገር ሲበዛስ? (‘አናዳጅ እንጅ ነዳጅ የለም’ አለ በዕውቀቱ ሥዩም)፡፡ ሆደ ሰፊነት፣ ቸለልተኝነት፣ ፍርሃት፣ እና ሌሎች ነገሮች ሊያግዱን ካልቻሉ መናደድና ማናደድ በሕግ የተጠበቁ መብቶች መሆን ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በተክለ ሰውነት ደቃቃ የሚባለው (ለምሳሌ እኔ) ያለምንም መሳቀቅ ግዙፉን ሰው፣ መናጢው ደሃ (በድጋሜ ለምሳሌ እኔ) በሀብት የፈረጠሙ ግለሰቦችን፣ ተራ የሚባሉ ግለሰቦች (ለሦስተኛ ጊዜ ለምሳሌ እኔ) ሚኒስትሮችን የማናደድ መብት ሊኖራቸው ይገባል (‘ይህ የሚሆነው ፍጹም በሆነ አለም ውስጥ ነው!’ ማብሰልሰሌን ቀጠልኩ፡፡ ‘አይ፡ ፍጹም በሆነ አለም ውስጥ የሚናደድም የሚያናድድም አይኖርም። ያለ መታከት ማብሰልሰል፣ ብቸኛው አማራጭ እስኪመስለኝ ድረስ፡፡)
ይህ ካልሆነ ግን እነዚያ በታሪክ ክፍለ-ጊዜ እንማራቸው የነበሩት በሀብት፣ በሥልጣን ወይም በጉልበት የመተማመኛ ዘመኖች ‘የፊውዳል ሥርዓት’፣ ‘የቦርዥዋዚ ሥርዓት’ ‘የአምባገነን ሥርዓት’ ታሪክ ሆነዋል ስንል እኛኑ ታሪክ አድርገውናል ማለት ነው፡፡ በንግግር ያለማመን አባዜን መግታት የሁላችንም ሀላፊነት ነው፡፡ በንግግር በማያምኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ፊት መሽቆጥቆጥ፣ ራሳችንን ሳንሱር የማድረግና የማስመሰል ባህል መበረታታት የለበትም፡፡ ለትውልድ ማሰብ አለብን። አካፋን አካፋ የማለት ድፍረት የሌለው ትውልድም በቀላሉ ከመሸንገልና ከመሸንገል (እባክዎ አንዷን ጠበቅ አድርገው ያንብቡ) ወደ ኋላ አይልም፡፡ ሀሳቦች በነጻነት መንሸራሸር ሲችሉ የተሻሉ የሚባሉ አማራጮች ይበረክታሉ፡፡ እንደ ጋሪ ፈረስ ባንድ አቅጣጫ ብቻ ተመልከቱ፣ እኔን ብቻ ስሙኝ ወይም ለኔ ብቻ አጨብጭቡ ማለት ለዚህ አሁን ላለንበት ዘመን አይመጥንም፡፡ እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ መደረጋቸው አይደለም መታሰባቸው በራሱ ያበሳጫል፡፡ የመበሳጨት መብቴ ደግሞ ቢያንስ ታፍኜ፣ ተብሰልስዬና ተብላልቼ እንደ ኑክሌር እንዳልፈነዳ ይረዳኛል፡፡
በነገራችን ላይ ይህንን መብት በእጅጉ እየተጠቀሙበት ካሉ (በየአካባቢያችን የሚገኙ ብረት ከሚገፉ፣ ሽጉጥ ቢጤ ወገባቸው ላይ ሻጥ ካደረጉ፣ ሲጠጡ ጠብ ከሚሸታቸው፣ በትዕቢት ከተወጠሩና ኪሳቸው በብር ከተወጠረ ማን አለብኝ ባዮች ይሰውረን) ግለሰቦች መካከል በአሜሪካ የፕሬዚደንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካኖችን (አንዳንዶች እኒህ ሰው ፋቅ ፋቅ ቢያደርጓቸው ዴሞክራት ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ፤ ከዚህ በፊት ከነበራቸው የፖለቲካ አቋም በመነሳት) ወክለው የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። “ሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ሰዎች አስገድዶ ደፋሪዎችና ዕፅ አዘዋዋሪዎች ናቸው፣ ሙስሊም ማህበረሰቡ አሜሪካን እንዳይረግጥ አደርጋለሁ እንዲሁም የአሸባሪዎችን ቤተሰቦች እገድላለሁ፣ ጥቁሮች ፍቅር ከመሥራት ችሎታ ውጭ ሌላ ችሎታ የላቸውም፣ እኔ ያልተማረኩት ነው የሚመቹኝ (በቪየትናም ጦርነት ተማርከው አምስት ዓመታትን በእስር ቤት የተሰቃዩትን ጆን ማኬይን በነገር ለመውጋት)” በሚሉ ተቀጣጣይ እና ከፋፋይ ንግግሮቻቸው የስንቱን ቆሽት አሳረሩት (ቆሽት ግን ምንድን ነው?)፡፡ ክብሪት ነገር ናቸው። ያዋጣቸው ይሆን? ወይስ ደግሞ ሕዝቡ፤ “ከልኩ አልፈዋል” ብሎ በሕዳሩ ምርጫ ድምጹን በመንፈግ በሰለጠነ መልኩ “ዋጣት!” ይላቸው ይሆን? ብዙ የመናገር መብት አቀንቃኞች የእኒህን ሰው ሀሳቦች የሚቃወሙ ቢሆንም ራሳቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ግን ያከብራሉ፡፡ ቮልቴር እንዳለው፡- “I disapprove of what you say, but I will defend to the death your right to say it.” (በግርድፉ ሲተረጎም፡ “የተናገርከውን ነገር እነቅፈዋለሁ፤ ነገር ግን ይህንን የማለት መብትህን ሕይወቴን እስከ መሰዋት እከላከላለሁ፡፡”)
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ ሀገር ጉዞ ላይ የነበረ አንድ ግለሰብ ለምሳ ወረደና ወደ አንድ ሆቴል ጎራ አለ፡፡ ምሳ መጥቶለት እየጎራረሰ እያለ አነቀውና፤ “ኧረ ውሃ!” አለ ጮክ ብሎ፡፡ የሆቴሉ ባለቤት የሚመስልና ፈርጠም ያለ ግለሰብ (ግዴላችሁም ‘ሰውየው’ እንበለው): “ውሃ የለም” አለው፡፡ ደምበኛው፡- “ውሃ ከሌለ አልከፍልም!” ሲል ተነጫነጨ፡፡ “እየጠፈጠፍኩ እቀበልሃለሁ!” ሰውየው አጉረጠረጠ፡፡ ደምበኛ፡- “አናቴ ተከፍሎ ደም በደም ከምሆን ሒሳብ ብከፍል ይሻላል” በሚል ዋጥ አደረጋት፡፡ ከ
ሁለት ያጣ ጎመን ደምበኛ። ልጆች ሆነን ስንገረፍ ‘እሪ!’ የማለትና ያለመገረፍ መብታችንን በመግፈፍ ወላጆች “ዋጣት!” “ዋጣት!” እያሉ በፍቅር ይቀጠቅጡን ነበር ዝም እስክንል ወይም 911 (ጎረቤቶች ማለቴ ነው) መጥተው እስኪያስጥሉን። በዚች እድሜያችን ስንቱን ዋጥነው።

Read 3820 times