Sunday, 16 October 2016 00:00

ባለ አንድ ዓይናዎች!!

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(8 votes)

ትውፊታውያን የሀገራችን ሰዓሊዎች የማያመዛዝንን ሰው ሲስሉ አንድ ዓይና አድርገው ይስሉት ነበር፡፡ ሰፋ አድርጎ የማያይ፤ እውነትን በከፊል ብቻ የሚቀበላት፤ ከሚያውቀው ውጭ ሌላ ነገር ያለ የማይመስለው ነው ማለታቸው ነው። ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› የሚል አባባልም አለ፡፡ ዕውቀትህን፣ አመለካከትህንና አካሄድህን ባሻሻልክ ቁጥር ያላየኸውን ታያለህ፣ ያልሰማኸውን ትሰማለህ፤ ያልተገለጠልህ ይገለጥልሃል፤ የረቀቀው ይጨበጥልሃል፤ እውነት ነው ያልከው ውሸት፣ ውሸት ነው ያልከውም እውነት ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ ሲሉ ነው፡፡
ቀደምት ሊቃውንት ሁለት ዓይን የተሰጠን በአንዱ የራሳችንን፣ በሌላው የሌላውን ለማየት ነው፤ ሁለት ጆሮ የተሰጠን በአንዱ የራሳችንን፣ በሌላው የሌላውን ለመስማት ነው፡፡ ሁለት እጅ የተሰጠን በአንዱ ለመስጠት፣ በሌላው ለመቀበል ነው፡፡ ሁለት እግር የተሰጠን በአንዱ ወደ ራሳችን፣ በሌላው ወደ ሌላው ለመሄድ ነው ይሉ ነበር፡፡  
ሞንጎልያውያንም ከዚህ ጋር የሚሄድ ብሂል አላቸው፡፡
በአንዲት የሞንጎልያ ትንሽ መንደር ውስጥ በምትገኝ ኩሬ አንዲት ዓይን ብቻ ያለቺው ዕንቁራሪት ይኖር ነበር፡፡ ለእርሱ ዓለም ማለት ያቺ ኩሬ፣ ንጉሥም ማለት እርሱ ነው፡፡ ከእርሱ ኩሬ የተሻለ ቦታ፣ከእርሱም የበለጠ ዕድለኛ የለም፡፡ የሚመኘው ነገር ቢኖር እርሱ ያገኘውን ይህንን ታላቅ ነገር የሚካፈለው ጓደኛ እንዲያገኝ ብቻ ነበር፡፡
አንድ ቀን በአካባቢው ከባድ ዝናም ጣለ፡፡ ምድሪቱንም የሚገለባብጣት መሰለ፡፡ ዕንቁራሪቱ በዚያች ለእርሱ ምርጥ በሆነችው ኩሬ ውስጥ በመሆኑ ምንም ነገር አይመጣብኝም ብሎ አመነ። ዝናቡ ግን አካባቢውን ደበላልቆ ከኩሬው ማዶ የሚገኘውንና ዕንቁራሪቱ መኖሩን የማያውቀውን ኡቩስኑር የተባለውን ጨዋማ ባሕር እንዲሞላ አደረገው፡፡ ባሕሩ ሲሞላ በውስጡ የነበሩትን እንስሳት ተፋቸው፡፡ አንዱ የባሕር ዔሊም በጎርፉ ተወስዶ የማያውቀው ቦታ ወደቀ፡፡
ዔሊው የኡቩስኑር ባሕርን ሊያየው አልቻለም። የት ቦታ እንዳለም አላወቀም፡፡ ወደ የት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበትም ግራ ገባው፡፡ ነገር ግን በቆሙበት ቦታ ከመሞት እየሄዱ መሞት ይሻላል ብሎ መጓዝ ጀመረ፡፡ ቢሄድ፣ ቢሄድ፣ ቢሄድ መንገዱ ሊያልቅለት፣ ባሕሩንም ሊያገኘው አልቻለም። እንዲያውም እየደከመውና እየራበው መጣ፡፡ ሙቀቱንም መቋቋም አልቻለም፡፡ ወደ ኡቩስኑር ባሕር ሳልደርስ ልሞት እችላለሁ ብሎ ሠጋ፡፡
ወደ ባሕሩ በቀላሉ ሊደርስ እንደማይችል የተረዳው ዔሊ፤ ነፍሱን ሊያድንለት የሚችል አንዳች ውኃ እየፈለገ ሳለ የዕንቁራሪቱን ኩሬ ተመለከተ። በዔሊ ፍጥነት ተንከላውሶ እዚያ ኩሬ ውስጥ ተወርውሮ ዘፍ አለ፡፡ ዔሊው ኩሬው ውስጥ ዘፍ ሲል፣ የኩሬው ውኃ ከጥፋት ውኃ ባልተናነሰ ተናወጠ፡፡ ዕንቁራሪቱም ሰምቶት የማያውቀውን በመስማቱና አይቶት የማያውቀውን በማየቱ በድንጋጤ ልቡ ቀጥ አለች፡፡ ከሰዓታት በኋላ ሲረጋጋ አንዳች የሚያህል ፍጡር በኩሬው ውስጥ ሲንከላወስ ተመለከተ፡፡
‹ለመሆኑ ማነህ? ከየትስ መጣህ? እዚህስ ምን ታደርጋለህ?› የጥያቄ መዓት አወረደበት፡፡ ዔሊው ጥሙን የሚያስታግሥለትን ውኃ ከተጋተ በኋላ፣‹እኔ ዔሊ ነኝ፡፡ የመጣሁትም ከኡቩስኑር ባሕር ነው። እዚያ በተከሠተ ጎርፍ ከባሕሩ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ ወደ ባሕሩ እመለሳለሁ ብዬ ስጓዝ በውኃ ጥም ልሞት ደረስኩ፡፡ ፈጣሪ ይመስገን፤ እዚህ ኩሬ ውስጥ ጣለኝ› አለው፡፡
‹ታድያ አሁን ምን እያሰብክ ነው?› አለው ዕንቁራሪቱ፡፡ ‹እኔ ወደ ባሕሩ መመለስ ነበር የምፈልገው፡፡ ነገር ግን መንገዱን አላውቀውም። በመካከልም በውኃ ጥም እንዳልሞት ፈራሁ። እናም ካላስቸገርኩህ በጋው እስኪያልፍ እዚህ አንተ ጋ ብከርም ምን ይመስልሃል?› አለው፡፡ ለብዙ ዘመናት ብቻውን የኖረው ዕንቁራሪት፣ ጓደኛ ስላገኘ ደስ ብሎት ፈነጠዘ፡፡ ይህን እርሱ በኩሬው ውስጥ ያገኘውን ልዩ ደስታና ርካታ የሚያካፍለው ጓደኛ አገኘ፡፡
ዔሊው የበጋውን ወቅት የሚያሳልፍበት ቦታ በማግኘቱ እፎይ ያለ ቢመስለውም ዕንቁራሪቱ ግን በጥያቄዎች ያጣድፈው ነበር፡፡ ከኩሬው ውጭ ያለውን ዓለም የማያውቀው፣ በዓለም የመጨረሻው፣ ትልቁና ምቹው ቦታ ኩሬው የሚመስለው ዕንቁራሪት የጥያቄ ናዳ አወረደበት፡፡ ‹ለመሆኑ ያንተ ባሕር እንደዚህ ኩሬ ውብና ምቹ ነው› አለው፡፡ ዔሊውም ዕንቁራሪቱን ላለማስከፋት ብሎ ‹ያንተ ኩሬ ውብና ምቹ ነው› አለው፡፡ ዕንቁራሪቱም በዚህ ተደሰተና ‹ለመሆኑ ያንተ ባሕር ከእኔ ኩሬ ይበልጣል› አለው። ዔሊውም ‹የኡቩስኑርን ባሕር ከዚህ ትንሽ ኩሬ ጋር ማነጻጻር የማይታሰብ ነው፡፡ ወርድና ቁመቱን ማንም ሊለካው አይችልም፤ እጅግ ሰፊ፣ ጥልቅና ምቹ ነው፡፡ አያሌ የባሕር እንስሳት ይገኙበታል› አለና መለሰለት፡፡
ዕንቁራሪቱ ደነገጠ፡፡ እዚህ ኩሬ ውስጥ የገባው እጅግ ውሸታም ዔሊ ነው ብሎ አመነ፡፡ ከዚህ ኩሬ የበለጠ ነገር በዓለም ላይ ሊገኝ አይችልም። ዕንቁራሪቱ በአንድ ዓይኑ ሲያያት የእርሱ ኩሬ ለእርሱ እጅግ ሰፊ፣ ማንም ሊደርስባት የማይቻላት ናት፡፡ ለመሆኑ በዓለም ላይ ከዚህ የሚበልጥ ምን ምቹ ቦታ ይገኛል? ብሎ አሰበና፣‹የኡቩስኑር ባሕር የሚባል ነገር የለም፤ ቢኖርም ከዚህ ኩሬ ፈጽሞ ሊበልጥ አይችልም፡፡ አንተ ውሸታም ነህ፡፡ ሆን ብለህ እኔን ለማስደነቅና ከዚህ እንድወጣ ለማድረግ ነው እንጂ ከዚህ የሚበልጥ ባሕር ፈጽሞ የለም፡፡ በዓለም ላይ ያለው ብቸኛው፣ ታላቁና ምቹው ውኃ ይሄ ኩሬ ነው› አለው፡፡
ዔሊውም፤  ‹ወዳጄ ሞኝ አትሁን፡፡ የማታውቀውን ነገር ሁሉ የለም አትበል፡፡ አንተ በአንድ ዓይንህ ስለምታያት ይቺ ኩሬ ትልቅ ትመስልሃለች እንጂ እንኳን ከዚህ ኩሬ ከኡቩስኑር ባሕር የሚበልጡም አሉ፡፡ እኔ የያዝኩት ብቻ የመጨረሻው ነው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ዕውቀቴ የመጨረሻው ነው ብሎ እንደሚያስብ ፍጡር የሚጎዳ የለም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዕንቁራሪቱ ክፉኛ ተቆጣ፤ ‹ሞኝ አልከኝ። አንተ ከሌላ ዓለም የመጣህ ፍጡር ነህ፡፡ ከዚህ ኩሬ የሚበልጥና የተሻለ ነገር አለ ብሎ የሚለኝ ለእኔ የመጨረሻው ውሸታም ነው፡፡ ይህን ኩሬ እስካሁን እኔ ዋኝቼ አልጨረስኩትም› እያለ አመናጨቀው፡፡
ዔሊው ይህንን ንግግር ለማመን አልቻለም፡፡ የዕንቁራሪቱን ደኅነኛ ዓይን እያየ፤ ‹አንተ ይህቺን ኩሬ የዓለም መጨረሻ አድርገህ ማየትህ አይገርመኝም። ያለህ አንድ ዓይን ብቻ ስለሆነ፡፡ የሚገርመው በሁለት ዓይኑ የሚያየውን ሁሉ መቃወምህ ነው። ሁላችንም በአንተ አንድ ዓይን ልናይ አንችልም። ላንተ ያልታየህ ሁሉ የለም፤ አንተ ያልደረስክበት ሁሉ አልተፈጠረም፤ አንተ ያልኖርክበት ሁሉ ምቹ አይደለም ብለህ ታስባለህ፡፡ ዓለምን በልክህ ቀደህ ሰፍተሃታል፡፡ሁላችንም ደግሞ ባንተ ልክ እንድናሰፋት ታስባለህ፡፡ ይህ የመጨረሻው ሞኝነት ነው፡፡ እኔ ብቻ እና የኔ ብቻ ትክክል ነው ብሎ ማሰብ ነው ከዚህ ኩሬ እንዳትወጣ ያደረገህ፡፡ ሁሉንም ነገር በኩሬው ልክ ታስበዋለህ፡፡ በእውነትም አንተ የመጨረሻው ሞኝ ነህ፡፡
ብልህ ብትሆን ኖሮ ስለ ሌላውና ሌላውንም ለመስማት ትፈልግ ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ካንተ የሚያንስም፣ ካንተ የሚስተካከልም፣ ካንተ የሚበልጥም መኖሩን አምነህ ትቀበል ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ስለ ሌላው ዐውቀህ ኅሊናህን ታሰፋው ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ካንተ የተለየ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ታዳምጥ ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ለመናገር ብቻ ሳይሆን ለመስማት ዕድል ትሰጥ ነበር፡፡ በል ይመችህ፤ እዚሁ ኩሬህ ውስጥ ኑር። እውነትም ከዚህ የተሻለ ላንተ አይገኝም፡፡ እዚህ ኩሬ ውስጥ የምትኖረው ኩሬው ከሁሉም የሚበልጥ ስለሆነ ሳይሆን ላንተ ስለሚመጥንህ ነው፡፡ ቀሪ ሕይወቴን ከሞኝ ጋር ከምኖር ብልሆች ወዳሉበት እየሄድኩ ብሞት ይሻለኛል› ብሎ ከኩሬው ወጥቶ ሄደ፡፡
ዕንቁራሪቱም በአንድ ዓይኑ ሲያይ፣ የኩሬውን ግድግዳ ተመለከተው፡፡ ‹ይህ የዓለም ዳርቻ አይደለምን?! ለመሆኑ ይህ ዔሊ ከዓለም ዳርቻ ውጭ የት ሊሄድ ነው› አለ ይባላል፡፡
ኪችነር፣ ካናዳ

Read 3355 times