Saturday, 10 March 2012 10:51

እንደ ስብሐት

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(0 votes)

ከአዘጋጁ:- ውድ አንባብያን፤ በዚህ አምድ በአንጋፋው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር የአፃፃፍ ዘዬ የተኳሉ ጥበባዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እንዲሁም ፍልስፍናዊ መጣጥፎችና ወጐች ይስተናገዳሉ፡፡ እግረመንገዳችንንም ዕውቁን የብዕር ሰው ስብአት ለአብን እየዘከርን፡፡ ለአምዱ የሚመጥኑ ጽሑፎችን ብትልኩልን ሚዛን ላይ እያወጣን እንደየሁኔታውና አግባቡ እናስተናግዳለን፡፡

ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰንና ተአምረ ሁለትነታቸው

እንዲህ በእንዲህ ለመፃፍ የተነሳንበትን ድፍረት ከየት እንዳመጣነው ከተጠየቅን መልሳችን “እንጃ” ነው፡፡ ለአጥብቆ ጠያቂ ደግሞ ከአማልክቱ የቀለለ ሰበብ አናገኝም፡፡ አንዳንዴ እኮ ነዝናዛ አይታጣም፡፡ ፈርዶብን ችኮ መንቻኮ ቢገጥመንስ? ጥሎ መሄድ ቁርጠኛ ውሳኔአችን ነው፡፡ አንጠራጠርም! ሳይንሳዊ ሀቅ ነው! ወደፊት!

የዛሬ ጉዳያችን የጊዜ መኪና እንዲኖረን ግድ ብሏል፡፡ ያንን የጊዜ መኪናችንን ቆስቁሰን ወደ ኋላ በመንዳት ጥቂት መቶ አመታት እንጓዛለን፡፡ (ጊዜ ታክሲ አይደለ…ለሚል አሽሟጣጭ ጆሮ ሳናስተርፍ) አሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ስንደርስ መኪናችንን ማቆም፣ በሩን መክፈት፣ መውረድ እንዳለብን እንዳንረሳና ጉድ እንዳንሆን ብቻ! የሰው ጭቅጭቅና ሽሙጥ ሃሳባችንን ሰርቆብን፡፡

አስተናጋጃችን Dr. Samuel Johnson ናቸው፡፡ እንግሊዝ አገራቸውን ብርግድ አድርገው ከፍተው በሐበሻ ወግ “ቤት ለእንግዳ” ይሉናል “ኧረ ደግ አይደለም፣ ገብታችሁ አረፍ ብላችሁ ምናምን አፋችሁ ላይ አድርጋችሁ” ሊሉንም ይችላሉ፡፡ የእኛን ያህል ትህትና አጥተው በእንግዳ ወግ ውሃ አሙቀው እግራችንን ባያጥቡን አንቀየማቸውም፡፡

ዶክተር ጆንሰንን አንቱ ብለናል፡፡ አንቱታችን የአክብሮት ብቻ አይደለም፡፡ ምን ቦጣን፤ በአንድምታ የአበው ወግ ይሄን ምክንያት በውስጡ ይዟል፡፡ እንግሊዛውያን ልብ ውስጥ ዶክተር ጆንሰን አንድ ብቻ አይደሉም፡፡ (እንዲያማ ከሆነ ምኑን ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን ሆኑት?) ሁለት ናቸው፡፡ “SAMUEL JOHNSON a critical Essays” የተሰኘ መጽሐፍ ያለው ዶናልድ ጄ ግሪን እንግሊዛውያኑን ወክሎ እንዲህ ብሏል፡፡

“There will always be two Samuel Johnsons” ቢቸግረው እኮ ነው፡፡ ዶክተሩ አስገራሚ ፍጥርጥር ነበራቸው፡፡ አክብረው የክብር ቦታ ሲፈቅዱላቸው ዝቅ ያለ ሥፍራ ይገኛሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ግራ አጋቢ፡፡ በገዛ እጃቸው እኩል ይሰንጠቁ? ሁለቱ ሳሙኤል ጆንሰኖች እነዚህ ናቸው፡ አንዱ “Dear old Doctor Johnson” ይሰኛሉ፡፡ (ሰሀ የሌለባቸው አዛውንቱ ዶክተር ጆንሰን እንደማለት ነው፡፡) ሁለተኛው “Ridiculous old Doctor Johnson” ናቸው፡ “አስቂኝ ሸሜ ጉጉ እንደማለት” አስቂኙ ሽሜ ጉጉ እንዴት እንደሚያስብ እዩት፡ ይሄንን የሚነግረን የህይወት ታሪኩን የፃፈው James Boswell ነው፡፡ አንድ ጊዜ አብረው ተቀምጠው በማውራት ወይም ባለማውራት ላይ ሳሉ ድንገት ዶክተሩ “Sir” አለው፡፡ “When you get Silver in change for a guinea, look carefully at it, you may find some curious piece of coin.” (ድፍን ብር ከፍለህ መልስ ስትቀበል ልብ ብለህ ተመልከት፡፡ ምናልባት ያልታሰበ ትርፍ ሳንቲም ነጭ ሽልንግ ላይ ተለጥፎ ልታገኝ ስለምትችል እንደማለት ነው)

ይሄን ስንሰማ ሰአሊ ለነ ቅድስት! እንላለን፤ ማማተብ እንመርቃለን ስለማይበቃ፡፡ በመንገብገብ የታጠረ ሽማግሌ፣ በስስት ደዌ ሲሰቃይ እናስባለን፡፡ ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን ግን እዚህ ናቸው ሲባሉ እዚያ መገኘትን ተክነውበታል፡ በሌላኛው ገጽታቸው ደግሞ ሰሀ የሌለበት አዛውንት ናቸው፡፡ ይሄን የተከበረ አዛውንት የሚተውነው ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን፤ አስቂኙን ሽሜ ጉጉ እንደ ካፖርት አውልቆ ይመጣል፡፡ ብዙውን ጊዜ ያሳለፈው ቅጥ ባጣ ድህነት ውስጥ ነው፡፡ (ለካ ጨው የሌለው ድህነት ነው የሚባለው) እና ከለንደን ጐዳናዎች በአንዱ ሲጓዝ፣ በዚያ በረዷማ ምሽት መንገድ ዳር የወደቁ ያጋጥሙታል፡፡ አልፎ የሚሄድበት ጨካኝ ልብ የለችም፡፡ ያለውን (የሌለው እስኪሆን ድረስ) ያድላቸዋል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ይሄም አልበቃ የሚልበት ጊዜ አለ፡፡ የባሰበትን ጐዳና ተዳዳሪ አዝሎ ወደ ቤቱ በመውሰድ የድህነት ጽንፍ እስከፈቀደው ድረስ ልግስና ያደርግለታል፡፡ አንዳንዴ መኖሪያው የብዙ ቤት የለሾች መጠለያ ይሆናል፡፡

ተአምረኛው ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን ተአምረ ሁለትነታቸው ይቀጥላል፡፡ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ያንን ቀብቃባ ሽሜ ጉጉ ሆነው እየተወኑ ነው፡፡ Boswell ታሪካቸውን የሚጽፈው ወደው የሰጡትን ብቻ እየተቀበለ አይደለም፤ እየሰለላቸውም ጭምር ነው፡፡ አንድ ጊዜ ሽልንግ አበደራቸው (ይቅርታ ለዚያ ለቀብቃባው ዶክተር አበደረው) ባለው ቀን አልመለሰም፡፡ Boswell ጠየቀ፡፡ የዶክተሩ ፊት ቅጭም ብሎ ቀልድ ሁሉ ጠፋበት (የእኛን ፎካሪዎች ሳይመስል አልቀረም፡፡ ኧረ እንደውም ቁጭ እነሱን) እንደመቅበጥበጥ ሞካክሮ:-

“Boswell” አለው “Boswell ካለህ የማይመለስ ስድስት ሳንቲም አበድረኝ” ዕዳውን በሌላ ብድር ጥያቄ ሲያዳፍን መሆኑ ነው፡፡ ነቄ ነን አለ እሳት የላሰው ትውልድ!!

Boswell እንደ ራስ ጠባቂ መላእክት ወይም እንደ ቆሌዎቹ ሆኖ ነው የዶክተር ሳሙኤል ጆንሰንን የህይወት ታሪክ የፃፈው፡፡ ከመኖሪያ ቤቱ ውጭ በየሄደበት ሁሉ እየተከታተለ፡፡ በየተገኘበት እየተገኘ፣ ሲጐበኝ እየጐበኘ፣ ሲንሸራሸር እየተንሸራሸረ፡፡ ፀባዩን አሳምሮ፣ የዶክተሩን ፀባይ ችሎ፡፡ “The life of Samuel Jonson, LL.D.” ን ስናነብ የሚዘልቀን የ Boswell ልፋት ነው፡፡ በሁለት ጥራዝ ከአንድ ሺ ሁለት መቶ ገጽ በላይ በዚህ ላይ ለመጠቅጠቅ ሲባል የdialogue አፃፃፍ ደንብ አልተከተለም፡፡ የተናጋሪውን ስም እያስቀደመ ብዙ ንግግር በአንድ አንቀጽ ውስጥ ይደረድራል፡፡ በወጉ ቢፃፍ ሁለት ሺህ አይጠቅመውም፡፡ ታዲያ ለአይን ይክበድ እንጂ አንዴ ሲገቡበት ደስ እያለ ነው የሚነበበው፡፡ Boswell እንዲህ ለፍቶ አልከሰረም፡፡ እንደውም ከተገቢው በላይ አትርፏል፡፡ ይሄንን ያረጋገጥኩት በቅርቡ ነው፡፡ አንድ የLiterature መዝገበ ቃላት ላይ Doctor Johnson የሚል ሳፈላልግ See Boswell (ቦስዌልን ተመልከት) አለኝ፡፡ መጀመሪያ ተምታታብኝ፡፡ ተፃፊው እያለ ፀሐፊው? አልኩ፡፡ በኋላ ግን እንግሊዞች ትክክል እንደሆኑ ገባኝ፡፡ ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን ያለ ቦስዌል ምንድነው? ዶክተሩ እንደሆን ከመፃፍ ማውራት የሚቀለው ነበር፡፡ ቦስዌላችን መንፈስም፣ ጥላም ሆኖ ካፍ - ካፉ ባይለቅም አውርቶ ይቀር አልነበር? በሌላ በኩል:-

ደግሞስ Boswell ያለ Doctor Johnson ምን ውስጥ ይገባል? ጥቂት የጉዞ ማስታወሻ ፃፈ፣ እና ምን ይጠበስ? ይባል ነበር፡፡ እሱም ወደ አዘቅታማው መረሳት መውረዱ አይቀርለትም ነበር፡፡ ደግነቱ ሁለቱም እየተደጋገፉ እዚህ ደረሱ እንጂ (ወይስ እኛ ነን የደረስንባቸው?)

ውድ አንባብያን! ስንዘላብድ ጊዜና ወረቀት እንዳንፈጅ ልታስታውሱን ይገባል፡፡ አክብሮት ሳይጓደልብን ታዲያ! ስንቀጥል:- ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን ያንን ሁሉ ሥራ ያከናወነው በበሽታ ናዳ ውስጥ ተቀብሮ ነው፡፡ ከሞላ ጐደል የማያይና የማይሰማ ነበር፡፡ በዚህ ላይ የአእምሮ ችግርም ነበረበት፡፡ በቆዳ በሽታ ሳቢያ ፊቱ ተጉረብርቦ የቀረ፣ በመጨረሻ በደም ብዛት እጁና እግሩ የማይንቀሳቀስ ፓራላይዝ ሆነ፡፡ ግራ በሚያጋቡ የአካል እንቅስቃሴዎች ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ በዚህ ላይ የሞት ፍርሃቱ አይጣል ነው፡፡ ስለሞት ባይወራ ደስታው መሆኑን Boswell ደጋግሞ ይመሰክራል፡፡ ከተወራ ደግሞ የዶክተሩ ፍርሃት እና ንግግር እያየለ ይሄዳል፡፡ “The better a man is, the more afraid is he of death.” (የተሻለው ሰው ከማንም የበለጠ ሞቱን የሚፈራው ነው) ይላል፡፡ ተሟጋች ካጋጠመው እስኪያምኑለት ድረስ የሞት ፍርሃት የሁሉም ነው ይላል፡፡

“That it is impossible not to be afraid of death, and that those who at the time of dying are not afraid, are not thinking of death, but of applause, or something else, which keeps death out of their sight; so that all men are equally afraid of death when they see it; only some have a power of turning their sight away from it better than others”

(ሞትን አለመፍራት የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ በመሞት ላይ ሳሉ የማይፈሩ እነሱ ሞትን የማያስቡና አሜን ብለው የተቀበሉት ናቸው፡፡ ወይም በሌላ ዘዴ ሞትን ከእይታቸው ለማግለል የቻሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰዎች ሞትን ባዩ ጊዜ እኩል በፍርሃት መራዳቸው አይቀሬ ነው፡፡

አንዳንዶች ብቻ ከሌሎች በተሻለ አትኩሮታቸውን ከሞት ላይ የማንሳት ኃይል ያላቸው ናቸው፡፡) እውነት፣ በግብዝነት ካልተነዳን በስተቀር ሞትን አለመፍራት ምን ይሉት ፈሊጥ ነው? በይበልጥ ደግሞ የቁርጡ ቀን ሲመጣና ዳግም የመወለድ ዋስትና ሲጠፋ! እንዴት አንፈራ፣ እንዴት አንንቀጠቀጥ! ሞትን ያህል “ወግድ” የማይሉት ሌባ ፊታችን ቆሞ ኡ…ኡ ማለት ሲያንሰን፡፡

እሪሪሪሪሪ!! (እንደ ዘላለም ባይሆንም ከእሷ መለስ ያለች እሪታ ጋበዝኳችሁ)

ውድ ቢሮክራትአውያን:-

ጽሑፉ እንዳላለቀ ብታውቁም ቅሉ ሳምንት ስመለስ ቀጠሮ አልያዝክምና አናነብም እንዳትሉኝ ይሁን፡፡ በቸር ያገናኝ!!

 

 

Read 2320 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 10:54