Sunday, 16 October 2016 00:00

“ይዟት፣ ይዟት በረረ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ባሏን ታፋጥጠዋለች።
“ጎረቤታችን ካለችው ሴትዮ ጋር እንደተኛህ ያለወቅሁ መሰለህ!” ትለዋለች፡፡ “ይሄን ትክዳለህ?” ባል ሆዬ ቆሌው ይገፈፋል፡፡ ግን እዚህ አገር ጥፋትና ስህተት (‘እንዲሁም ቅሽምና’ የሚለው ይግባበት) ማመን ብሎ ነገር የለም አይደል…መልሶ ያፈጥባታል።
“ዝም ብለሽ አትዘባረቂ! እኔ ከእሷ ጋር ልተኛ አልተኛ በምን አወቅሽና ነው!” ይላታል፡፡ ‘መረጃ ሳይሆን ማስረጃ አምጪ’ አይነት ነገር፡፡ ሚስቲቱ ጥሩ ነው…
“በምን አወቅሽ! በምን እንዳወቅሁ ልንገርህ… ትናንትና ባሏ የአንተን ሙታንቲ አድርጎት ነበራ!” ብለ አረፈችው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እናማ አያውቁም ተብሎ ለሚደረጉት ነገሮች ሁሉ…አለ አይደል…“ሙታንቲያችሁ’ ታይቶ ነበራ!” የሚባል ነገር መኖሩ ይጣፍልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ መአት ሰርጎች ይደገሱ የለ…ሀሳብ አለን፡፡ አንዳንድ የሰርግ ላይ ግጥሞች ወይ ይስተካከሉልን፣ አለበለዛ ከሰርግ ‘መዝገበ ቃላት’ ላይ ይፋቁልን፡ ልክ ነዋ… አሁን ለምሳሌ “ይዟት፣ ይዟት በረረ...” የሚለው ዘፈን “ደስ ይበላችሁ…” ከማለት ይልቅ “ይዟት ሲሄድ ዝም ብላችሁ ታያላችሁ እንዴ!” አይነት ሊመስል ይችላላ! ኮሚክ እኮ ነው…ሽማግሌ ተልኮ “እሺ ልጃችንን ውሰዳት ሰጥተንሀል” ከተባለ በኋላ… የምን “ይዟት በረረ…” ብሎ አቤቱታ ነው!
ባይሆን ይሄ ‘ሊዘፈንልን’ የሚገባ ሌሎች አለን... ከወ/ሪትነት ወደ ወ/ሮነት የተሸጋገረችውን እማወራ በመስኮት ዘለን ሳንገባ፣ ጓሮ ለጓሮ ሳንሾካሾክ… በቴክስት ሜሴጅ ብቻ ይዘን የምንበር! ቂ…ቂ...ቂ… ደግሞላችሁ…ለመሥሪያ ቤት የፊልድ ጉዞ ወይም ለ‘ወርክሾፕ’ በተሄደበት ‘የሰው ቆንጆ’ ይዘን ባልተያዘልን ሆቴል ክፍል ‘ኩሼ’ ብለን “ብርድ ልብሱን ልደርብልሽ…” ምናምን ለምንባባል ነው “ይዟት በረረ…” ማለት!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ብሪቷን እንደ ዶላርም፣ እንደ ዩሮም እያደረግን ወደ ‘ፈረንጅ’ በተመቸው መንገድ ለምናሻግር ነው “ይዟት በረረ…” ማለት፡፡ (እኛ… “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ…” እያልን ስንተርት…ገንዘብ ራሱ በራሱ ‘የሰማይ መንገድ ለመደ እንዴ!  ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ… “ይዟት በረረ…” ማለት ቻይኖቹ አንድ ጊዜ “እነዚህ ሰዎች ሌላ አገር አላቸው እንዴ!” አሉ እንደተባለው ‘ሌላ አገር’ ላላቸው ነው፡፡ ልጄ…እዚህ ምስኪን የአገሬ ሰው “የዛሬስ እንደሚሆን አለፈ፣ ነገንስ እንዴት አውሎ ያሳድረን ይሆን!” እያለ ከእንቅልፍ ተኳርፎ እያለ፣ ‘ቆፍረን ወዳመቻቸነው’ ሌላ የቀበሮ ጉድጓድ ሽው ለምንለው፣ (መቼም ‘ባዶአችንን’ አንሄድ) ነው፡፡
ስሙኝማ…ነገርን ነገር ያነሳው የለ…እዚህ አገር ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ፣ ‘ተራው’ ህዝብ በየቤቱና በየእምነት ተቋማቱ ዕንባውን ሽቅብ ሲረጭ…በበርካታ ተቋማት ውስጥ ኃላፊዎቹ ‘የበላቸው ጅብ’ አልጮህ ሲል አይገርማችሁም! አሀ…ወይ ‘በተሰወሩ’ ቁጥር ቁልፉን እየሰጡን ይሂዱዋ!
እናማ…የሰርግ ዘፈኖች ካነሳን አይቀር… “ባልንጀሬ ስሪ ጉልቻ፣ እንግዲህ ቀረ የእናት እንጎቻ…” የሚለው ይለወጥልንማ! ልክ ነዋ…ሹሮ ወጥና ምንቸት አብሽ ሳይቀሩ ‘ታሽገው’ በሚመጡበት ዘመን፣ ጉልቻ ራሱ ምን እንደሆነ ምናምነኛ ክፍል መጽሐፍ ላይ ብቻ ባለ ስዕል ሊታወቅበት ዳር በደረሰበት ዘመን… ‘ስሪ ጉልቻ’ “ጣጂ ጉልቻ” ብሎ ነገር አይሠራም፡፡
ደግሞስ ጉልቻው የት ላይ ሊሠራ! ራሳችን እንኳን ፈታ ብለን የምንቀመጥበት ስፍራ እየጠበበን፣ ‘ጉልቻ ስሪ’ ብሎ ነገር አይሠራም። (ደግሞስ “እነ ጆሴ ሞሪንሆና እነ ኤሊፍ እያሉ ጊዜው የት ተገኝቶ ነው ጉልቻ የሚጎለተው!” ብሎ መጠየቅም ይቻላል።)
ደግሞላችሁ… “ይቺ ናት ወይ ሚዜሽ አየንልሽ…” የሚለው… አለ አይደል… ትንኮሳ ሊመስል ይችላል። በዚህ ከእያንዳንዷ ቃል እንደ ዶሮ አሥራ ምናምን ብልት በሚወጣባት ዘመን፤ ‘ጠብ ያለሽ በዳቦ’ ሊመስል ይችላል። ልክ ነዋ…ዘንድሮ እኮ ለየራሳችን ያለን ማርስን አልፎ የሚሄድ አመለካከት ተመራማሪ ጠፋ እንጂ አዲስ ፍልስፍና ምናምን ሊወጣለት የሚችል ነው፡፡ ሚዜዎቹ… “ባጀብንሽ መሰደብ አለብን እንዴ!” ምናምን የሚል ‘ወከባ’ ሊፈጥሩ ይችላሉዋ! አሀ…ሶፊ ከሳንፍራንሲስኮ፣ ጆኒ ከዲሲ፣ ሚኪ ከለንደን የላኳቸው ልብሶች ሁሉ ተለብሰው ሽክ ተብሎ የሰው ክብር መንካት አለ እንዴ!
ይልቅ በየቦታው…‘ያለአቅማቸው የተሰየሙ’…አለ አይደል… “ይሄ ነው ወይ…አለቃህ” አየንልህ” የሚባልላቸው መአት ናቸው፡፡
ደግሞላችሁ…“አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ…” የሚለው ዘፈን ይስተካከልልን፡፡ እናማ…ከእያንዳንዷ ቃል እንደ ዶሮ አሥራ ምናምን ብልት በሚወጣባት ዘመን… “ስንቱ ሸበላ እጥፍ ዘርጋ የሚልላትን ልጃችንን አሞራ ሲያይሽ ዋለ…” ማለት “እሷ ጭልፊት የሚያነሳት እንትን ነች ለማለት ነው?” ሊባል ይችላል፡፡
ለነገሩማ…ዘንድሮ ልጄ አሞራ በሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድርም ‘እያየን’ ነገር የሚገባን ‘ከተሞጨለፍን’ በኋላ ሆኗል፡፡ የምር… በሰማይ ብቻ ሳይሆን ‘በምድርም ሲያይ የሚውል አሞራ’ በዝቷላ! እናማ… ወደ ምድር ስናይ የሰማዩ፣ ወደ ሰማይ ስናይ የምድሩ ‘አሞሮች’ እያንዣበቡብን ተቸግረናል፡፡
“የዛሬ ዓመት የማሙሽ እናት…” የሚለውም ይታሰብበት፡፡ በአንድ በኩል “እየበዛችሁ ስለሆነ ቶሎ አትውለዱ፣ ብዙ አትውለዱ…” ምናምን ነገር እየተባልን (‘ተብለን እየታዘዝን’ ማለትም ይቻላል) ገና በዓመቱ መውለድ ከተጀመረ… “እነሱ በልተው አልጠገቡ በላይ በላይ ይጨምራሉ!” ልንባል ነው።
ደግሞላችሁ…የዚች አገራችን መከራ አላልቅ ብሎ… አይደለም የዛሬ ዓመት የዛሬ ወር እንኳን ምን እንደሚሆን ማን አውቆ! አይደለም የዛሬ ወር የዛሬ ሳምንትስ ምን እንደሚሆን ማን አውቆ!  ዕጣ ፈንታችን ይህን ያህል መያዣ መጨበጫ የጠፋው ሆኗላችኋል፡፡ እስቲ መጀመሪያ ትዳሩ ዓመት ይዝለቅ፡፡
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… “የዛሬ ዓመት…” ምናምን ነገር ከተነሳ ሀሳብ አለን…መቼም ‘እንዲህ አደርጋለሁ’ ብሎ መተንፈስ ዘንድሮ ወንዝ ባያሻግርም… (ሌላው ቀድሞ ጠልፎ ይሠረዋላ!) ‘ለዛሬ ዓመት’ አዳዲስ የኢንቬስትመንት ሀሳቦች አሉኝ፡፡ አንደኛው ምን መሰላችሁ… አዲስ አበባ ውስጥ ‘የቀላል ታንኳ አገልግሎት’ መስጠት ነው፡፡ ልክ ነዋ…መኪኖቹ ኩሬዎቹን ሲሸሹ፣ እኛ መኪኖቹን ስንሸሽ፣ ‘ስልጣኔ’ እኛን ሲሸሽ…ችግር ሆነብና! መጠጥ ከ18 ዓመት በታች እንደሚከለከለው..አለ አይደል….ታንኳ ላይ መሳፈርም ከ50 ኪሎ በላይ አይቻልም፡፡ መሬቱ የበለጠ ቢሰምጥስ! ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞ ከሞባይላችን ጋር የሚገጠም…የሆነ ቅጥፈት ስንናገር፣ ‘ስንረግጥ’ … “ኧረ ሰው ምን ይለኛል በል!”  ምናምን የሚል በአይነቱ ልዩ የሆነ ሶፍትዌር ማምረቻ ፋብሪካ አቋቁማለሁ፡፡ ሰው ታዲያ ያልቃል እንዴ፡፡ አሀ…‘ውሸት’ እኮ ዝም ብሎ ግለሰባዊ መሆኑ ቀርቶ ‘ተቋማዊ’ እየሆነ ነዋ፡፡
እናማ…“ኸረ ሚዜው ድሀ ነው ሽቶው ውሀ ነው” የሚለውም መሬት ለመርገጥ የሚጠየፍ ‘ቀሺም’ ሚዜ በበዛበት፣  ‘ክብረ ነክ’ ሊመስል ይችላላ! “የእሷን ዘመዶች ማነው ሀብት ደልዳይ ያደረጋቸው?” ሊባል ይችላላ! (ሚዜው ‘ፖለቲከኞች፣’ ሽቶው ‘ፖለቲካቸው’ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ይቻላል። አለ አይደል…የፖለቲከኞች ‘ድህነት’…አለ አይደል… “እሱን እንኳን ተወው!” ቢያስብልም፣ የፖለቲካቸው ‘ሽቶነት’ ግን በእርግጥም… “ምስኪን፣ ሽቶና ውሀን መለየት እንኳን አይችልም!” ሊያስብል ይችላል።) የሰውነት ክፍል ላይ ከስምንት ሀገራት የተላኩ ሽቶዎች ተቸልሰው… “ሽቶው ውሀ ነው…” ብሎ ግጥም፣ ‘ጠብ ያለሽ በዳቦ’ ሊመስል ይችላል፡፡ ግጥሙ የወጣ ጊዜ እኮ የነበረው ሽቶ ኮሎኝ ብቻ ነበር! ቂ…ቂ…ቂ…
“ማነው እነሱን የአገር አሳቢ ያደረጋቸው!” እንደሚባለው የቅሽምና ብሽሽቅ ማለት ነው። በስንት መከራ ሽክ ብሎ የመጣው ሚዜ “ድሀ” ሲባል… አለ አይደል… “እስቲ አሮጌ ተራ የማኦን ቀይ መጽሐፍ ፈልግልኝ፣” ሊል ይችላል፡፡
“ባልንጀሬ አይበልሽ ከፋ ሁሉም ይዳራል በየወረፋ…” የሚለው ግጥምም… “ማን ወረፋ ደልዳይ አደረጋችሁ!” ሊያሰኝ ይችላል፡፡ ደግሞ ‘ሰማንያ ቀዳጅ’ በበዛበት ጊዜ ወይም ግጥሙ ይሻሻልና…አለ አይደል… “በየወረፋ ታገቢያለሽ…” ብቻ ሳይሆን “በየወረፋ ትፋቻለሽ…” የሚለውም ይግባልን፡፡
የምር ግን… “ይዟት፣ ይዟት በረረ...” የሚሏት ነገር ‘ለስንት ነገር’ እንደምትሆን!!!
ደህና ሰንበቱልኝማ!


Read 6225 times