Sunday, 16 October 2016 00:00

ሰው ፊት ቃል ከገባህ በኋላ “ፉርሽ - ባትሉኝ” ማለት አይቻልም!

Written by 
Rate this item
(11 votes)

  በአንድ የአጫጭር ተረቶች ስብስብ ውስጥ የሚከተለው ተረት ይገኝበታል፡፡
በአንድ ድርጅት ውስጥ ከዕለታት በአንድ ቀን አስገራሚ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ሰራተኞቹ እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ ስራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተው ለምሳ ይወጣሉ፡፡
ምሳ በልተው የተመለሱት ሁሉም አንድ ላይ አልነበረም፡፡ ከምሳ በኋላ ቡናና ሻይ የሚጠጡት ዘገዩ። ምሳቸውን አቀላጥፈው የተመለሱት ደግሞ ቀድመው ደረሱ፡፡ ሆኖም የውጪው በር ላይ የተለጠፈው ማስታወቂያ, የሁሉንም ቀልብ በመሳቡ, ሰራተኞቹ በሩ ጋ ቆመው ማስታወቂያውን ያነባሉ፡፡ እንዲህ የሚል ነው ማስታወቂያው፡-
“በእዚህ ድርጅት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ስራችሁን ስታከናውኑ ዕድገታችሁን እንዳታገኙ እንቅፋት ሆኖባችሁ የነበረው ሰው፤ በትላንትናው ዕለት ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በድርጅቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ በመገኘት, አስከሬኑን በክብር መሰናበት የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን”
                          ድርጅቱ
አንብበው እንደጨረሱ፡-
“ማን ይሆን እባካችሁ?” አለ አንደኛው በሀዘን፡፡
“አሳዛኝ ነው፡፡ ሆኖም ማን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉቻለሁ” አለ ሌላኛው፡፡
አብዛኛው ሰው በየውስጡ፤
“ማነው ዕድገቴን ሲያሰናክል የነበረው?” እያለ በየሆዱ ነገር ማብሰልሰል ይዟል፡፡
የታሰበው ሰዓት ደረሰ፡፡ ሁሉም በየተራ እየመጡ, በሬሳ ሳጥን ውስጥ ያለውን ሰው ማየት ጀመሩ፡፡ ሁሉም ያዩትን ባለማመንና በድንጋጤ አፋቸውን እየያዙ በቆሙበት ደርቀው ቀሩ፡፡ በሳጥኑ ውስጥ ያዩት ሰው መንፈሳቸውን ሰቅዞ ይዞታል፡፡
የሬሳ ሳጥኑ ውስጥ አንድ ሰፊ መስተዋት ኖሯል ለካ፡፡ ወደ ሳጥኑ የተመለከተ ሰው ሁሉ መልሶ የራሱን ፊት ነበር የሚያየው፡፡ ከራሱ ምስል በታችም የሚከተለው ፅሁፍ በጉልህ ይነበባል፡-
“ዕድገትህን ሊያሰናክል የሚችል አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ እሱም አንተው ራስህ ነህ!”
“አንተ ብቻ ነህ ህይወትህን ከሥሩ መለወጥ የምትችለው፡፡
“አንተ ብቻ ነህ በደስታህ፣ በስኬትህ፣ በአስተሳሰብህና በአመለካከትህ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደር የምትችለው”
“አንተ ብቻ ነህ ራስህን ማገዝ፣ ከውድቀት ማንሳት የምትችለው፡፡
“የበላይ ጓደኛህ፣ አለቃህ፣ ወላጆችህ፣ አገርህ፣ ጓደኛህ ሲለወጥ መጠነኛ ተፅዕኖ ባንተ ላይ ሊያሳድር ይችል ይሆናል፡፡ ህይወትህ ሙሉ በሙሉ የምትለወጠው ግን አንተ ራስህ ስትለወጥ ብቻ ነው!
ከነዛ ጎታችና አጋች ዕምነቶችህና አስተሳሰቦችህ ስትላቀቅና ለህይወትህ ኃላፊነት ያለብህ አንተና አንተ ብቻ መሆንህን ስታውቅ በእርግጥ ህይወትህ ትለወጣlች!››
                                                   *   *   *
ለውጥ ለማምጣት የራስ መለወጥ ግድ ነው፡፡ ሌላውን እንለውጣለን ተብሎ ሲታሰብ  ‹‹እኔ ተለውጫለሁ?›› `ከጥንት አስተሳሰቤስ ተላቅቄያለሁን?›› ብሎ ራስን መጠየቅ፣ ራስን መፈተሽ ዋና ነገር ነው። ሊቁ ኮንፊሽየስ፤ ካንተ ያነሱትን ሰዎች ይበልጡኛል ስትል ትሰማለህ፡፡፡ ግን ደግሞ ያንተ ደቀመዝሙሮች ናቸው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ተብሎ ሲጠየቅ፤ የደቀመዛሙርቱን ስም እየጠቀሰ፤
‹‹እገሌ፤ ቀጥተኛ ነው እንጂ እንደ ሁኔታው መለዋወጥን አይችልም (Flexibility እንዲሉ) እገሌ፣ ነገሮችን ማብራራት ይችላል እንጂ አዎ ወይም አይደለም ብሎ እቅጩን መናገርና ቀላል መልስ መስጠት አይችልም! እገሌ ደግሞ ደፋር ነው፤ ግን ጥንቁቅ አይደለም፡፡ ድፍረት አለጥንቃቄ ዋጋ የለውም፡፡ በመጨረሻም ሌላው ተማሪዬ ግርማ ሞገስ አለው፡፡ ይህ እንዴት እንደሚሳካ ያውቃል፡፡ ግን እንዴት ትሁት መሆን እንዳለበት አያውቅም፡፡ እኔ እነሱ ያልቻሏቸውን በማወቄ፣ ደቀ- መዛሙርቴ እንዲሆኑ ሆነዋል›› ሲል መለሰ ይባላል፡፡
ከላይ የጠቀስነው ስብስብ ‹‹ወዴት እያመራን ነው?›› በሚል ርዕስ የተቀነበበ ሲሆን፤ ዋና ዋና ነጥቦቹ አገራችንን ያሳዩናል፡፡ እነሆ፡-
‹‹ረጃጅም ህንፃዎች፣ ትናንሽ ትእግስቶች፣ ሰፋፊ መንገዶች፣ ጠባብ አመለካከቶች፣ የምናወጣው ብዙ፣ የሚኖረን ጥቂት፤ ብዙ እንገዛለን፤ ጥቂት እንደሰታለን፡፡
… ብዙ ዲግሪ፣ ትንሽ ማመዛዘን /ግንዛቤ… ብዙ አዋቂዎች፣ ብዙ ችግሮች፣ ብዙ መድሀኒት፣ ትንሽ ጤንነት… ጥቂት እናነባለን፣ ብዙ ቴሌቪዥን እንመለከታለን፣ አልፎ አልፎ እንፀልያለን፡፡
.. ብዙ እናወራለን፣ ትንሽ እናፈቅራለን፣ አብዝተን እንጠላለን!... ለህይወት ዕድሜ ጨምረንላታል፣ ለዕድሜ ግን ህይወት አልጨመርንላትም፡፡ ስልጣንን ለማገልገል ሳይሆን ሆድ ለመሙላት ተጠቀምንበት፡፡ ሆድ ተንዘርጥጦ አዕምሮ ግን ኮሰመነ፡፡
መከባበር በመናናቅ፣ መተዛዘን በመጠፋፋት፤ህሊና በሆድ ተተኩ፡፡ ጨረቃ ላይ ደርሰን ተመለስን፣ ግድግዳ የሚለየውን አዲስ ጎረቤታችንን መተዋወቅ ግን አቀበት ሆነብን፡፡ ከምድራችን የሚገኘውን ትንሽ ቦታ ግን አልተቆጣጠርንም፡፡… አቶምን ሰነጠቅን፣ መሰረተ-ቢስ ጥላቻዎችንንና ቅራኔዎቻችንን ግን አልፈታንም።
ብዙ እናነባለን፣ ትንሽ እንለወጣለን፤ ብዙ እናቅዳለን፣ ጥቂት እናሳካለን፡፡ መቸኮልን እንጂ መጠበቅን አልተማርንም፡፡ የተሻለ ገቢ እንጂ ያደገ ሥነ ምግባር የለንም፡፡
ብዙ መረጃ የሚይዝና ብዙ ሥራ ባጭር ጊዜ የሚያከናወን ኮምፒዩተር ፈጠርን እንጂ በመካከላችን ግን ብዙ ተግባቦት አልፈጠርንም፤ በብዛት ብዙ ሄደናል፤ በጥራት ግን ወደ ኋላ ተጎትተናል፡፡
ጊዜው እንዲህ ሆነ፡- ሰው በሁለት ገቢ የሚተዳደርበት፣ ትዳር ግን የሚበተንበት፣ የተሰነጣጠቁ ቤቴሰቦች የሚኖሩባቸው ግን የተዋቡ መኖሪያዎች፡፡
ወቅቱ ፈጣን ጉዞ የሚደረግበት፣ ለአንድ ሌሊት ትዳር የሚወጣበትና ግብረ-ገብነት ተሽቀንጥሮ የተጣለበት ዘመን…. ወዴት እያመራን ነው?!››
ከላይ የተጠቀሱትን በከፊል እንኳ ብናሟላ ‹‹ላሜ ወለደች ነው፡፡ በተደጋጋሚ ብለን ብለን ያልተሰሙ ዛሬ ቦታ ያገኙ ጉዳዮች ያስደስቱናል፡፡ የህዝብን ጥያቄ አንደሰማም ነበር- አዎ፡፡ መቶ ፐርሰንት አሸነፍን ማለት ራስን ማታለል ነበር- አዎን፡፡ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም-አስተዳደር እንከኖች ወዘተ የእኛው የቤት ጣጣ ነበሩ-አዎ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደራርበው ዛሬ ለደረስንበት ሁኔታ ከዳረጉን፤ እንደመፍትሔ፡- ጥፋተኞችን ለይቶ እርምጃ መውሰድ በጎ ነገር ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለግርግሮች መረጋጋት መፍትሄ መሻት አማራጭ የሌለው ነው - ትክክል፡፡ በአዋጁ አፈፃፀም ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ አግባብ የለሽ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ከወዲሁ ተጨንቆ ተጠቦ ለመግታት መዘጋጀት በጎ ነገር ነው! የሲቪክ ማህበረሰብን መኖር ማበረታታትና ማጠናከር - ዱሮ ተብሏል - ዛሬም ግድ ሆኗል!
የአገር ሽማግሌዎች በየቱም መልክ ተሰባስበው ሀሳባቸውን እንዲሰነዝሩ ከልብ ፍቃደኛ መሆን የባህላዊ ዲሞክራሲ ብሎም የዘመነው ዲሞክራሲ መሰረት ነው! ሙስናን መቃወም የዚሁ አካል ነው! ተቃዋሚዎች ቦታ እንዲያገኙ የምርጫውን ህግ እስከመለወጥ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ እሰየው ነው፡፡ “በህዝብ ፊት ቃል ከገባህ ትልቅ ነገር አደረግህ! ካልፈፀምከው ግን ትልቅ ስህተት ላይ ወደቅህ ወዮልህ!” የሚለውን አባባል መቼም አለመርሳት ነው! “ሰው - ፊት ቃል ከገባህ በኋላ “ፉርሽ - ባትሉኝ”፣ ማለት አይቻልም” የሚለው አባባል መሰረቱ ይሄው ነው!!

Read 4077 times