Sunday, 16 October 2016 00:00

አሜሪካና ካናዳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሳስቧቸዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(14 votes)

“ነፃና ትችት ያዘሉ ድምፆችን ማፈንና ማሰር በራስ ላይ ውድቀትን መጋበዝ ነው”

   በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና አመፅ     ተከትሎ መንግስት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በእጅጉ እንዳሳሰባትና አዋጁ በዚህ ሁኔታ ተፈፃሚ የሚሆን ከሆነ ለተቀሰቀሰው የፖለቲካ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት እንደማያስችል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታወቁ፡፡
ቃል አቀባዩ ጆን ኪርቢ ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ መንግስት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች የማይጥስ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዜጎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰርና የኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት ጨምሮ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን መገደብ፣ ህዝባዊ ስብሰባን መከልከል፣ የሰዓት እላፊ ገደብን መጣል  እንዲሁም የመናገር መብትን መገደብ የመሳሰሉ ተፅዕኖዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ የቃል አቀባዩ መግለጫ ያመለክታል፡፡
የተቃውሞ ሰልፈኞቹና የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ተገቢ የሆኑ ብሶቶች ማዳመጥና ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው ያለው መግለጫው፤ መንግስት የዜጎቹን መብት እንዲያከብር፣ ህገ-መንግስቱ ያረጋገጠውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመደራጀት መብት እንዲያረጋግጥ እንዲሁም መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ በተግባር ላይ በማዋላቸው የታሰሩ ዜጎችን እንዲፈታ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብሏል፡፡
ነፃና ትችት ያዘሉ ድምፆችን ማፈንና ማሰር በራስ ላይ ውድቀትን የሚጋብዝ ነው ያለው መግለጫው፤ ልዩነቶችን ይበልጥ የሚያሰፉና በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሄ ለማግኘት የማያስችል እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
እስከአሁን የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወት መቀጠፉንና ከፍተኛ የሆነ ንብረት ውድመት መድረሱን የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ ሁሉም ወገኖች በአገሪቱ በቀጣይ የአመፅ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መንግስታቸው በመሬት መብት፣ የምርጫ ህግን በማሻሻልና የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ስለሚያገኘው ጥቅም እውቅና መስጠትን ለመሳሰሉ የህዝብ አቤቱታዎች እልባት እንደሚሰጥ ቃል መግባታቸውን፣ መንግስታቸው በመልካም ሁኔታ እንደሚቀበለው ቃል አቀባዩ ገልፀው፤ መንግስት እነዚህ ቃል የተገባባቸውን ጉዳዮች በአስቸኳይ በቁርጠኝነት በተግባር ላይ እንዲያውል ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ህገመንግስት የተቀመጡት መሰረታዊ ነፃነቶችና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በቀጣይ ሁሉን አካታች ማሻሻያዎች እንዲደረጉ አሜሪካ የምታበረታታ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊፈፀም ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለበት የካናዳ መንግስት አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ለአዋጁ ተግባራዊነት ሲንቀሳቀሱ ሁሉንም የሰብዓዊ መብቶች ማክበር ይገባቸዋል ያሉት የካናዳ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ስቴፉን ዲኮን፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ወደ ሰላማዊ ውይይት ሊመጡ ይገባል ብለዋል፡፡

Read 4950 times