Sunday, 16 October 2016 00:00

‹‹በጌዴኦ የደረሰው ችግር የብሔር ግጭት አይደለም››

Written by 
Rate this item
(6 votes)

(ወ/ሮ ሂክማ ኬይረዲን፤ የደቡብ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ)

   የችግሩ ምክንያት በዲላ የንግዱ ማኅበረሰብና የጌዴኦ ዞን ሕብረት ሥራ ዩኒየን መካከል የቦታ ይገባኛል ክርክር ነበር፡፡ ባለፉት ጊዜያት ፍ/ቤቱ አክራክሮ ውሳኔም አስተሳልፎ ወደ አፈፃፀም ሂደት ሊገባ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ቦታው ለዩኒየኑ ይገባል በሚል የተወሰኑ አካላት ማኅበረሰቡን አነሳስተው በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ጉዳት ደርሷል። የፍ/ቤቱን ውሳኔ መነሻ አድርጎ ነው ግጭቱ የተከሰተው፡፡ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረትም ወድሟል፡፡ 23 ሰዎች ሞተዋል፤ ቤት ንብረት የተቃጠለባቸውና የወደመባቸው አሉ፤ ጉዳቱ ሰፊ ነው፡፡
በዚሁ ሂደት መካከል ችግሩ ሲከሰት ደንግጦ ከቤቱ የወጣ፤ ቤትንብረቱ ሲቃጠል ከቤቱ የወጣ  ሰው አለ፡፡ አንዳንድ ሰዎች የብሔር ግጭት ነው ይላሉ፡፡ ግን አይደለም፡፡ ጉዳቱ የደረሰው ከአካባቢው ብሔረሰብ ውጭ ብቻ አይደለም፡፡ ከአካባቢው ተወላጅ ሕይወቱ ያለፈ አለ፡፡ ስለዚህ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ብለን ነው መውሰድ የሚቻለው፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ውስጥም የአካባቢው ተወላጆች አሉ፡፡ ንብረታቸው የወደመው የሁሉም ነው፡፡ ስለዚህ ግጭቱ የተወሰነ ብሔረሰብ ላይ በፍፁም ያነጣጠረ አይደለም፡፡
ለተጠቂዎቹ ቀድሞ የደረሰላቸውና ሕይወታቸውን የታደገው የአካባቢው ማኅበረሰብ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የሃይመናት ተቋማት ውስጥ ተጠልለው ነው ያመለጡት፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በአርሶ አደሩ ጓሮ ነው የተጠለሉት፡፡ ቤቱን በማጋራት ከቤቱ በላይ ሲሆንበት የአካባቢውን ማኅበረሰብ አስተባብሮ ድንኳን በመደኮን፤ ውሃ፣ ምግብ፤ በማቅረብ ቀድሞ የደረሰላቸው የአካባቢ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለ ሰው ከ20-25ሺህ ይደርሳል፡፡ መንግሥት ችግሩ ከዞኑ አቅም በላይ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የፀጥታው ኃይል ገብቶ ሰላም የመፍጠርና የማረጋጋት ሥራ ሰርቷል፡፡ በመቀጠል ደግሞ ለተፈናቀሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከለየ በኋላ ቁሳቁሶች ገዝቶ እያሰራጨ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ደርሶታል፤ ያልደረሳቸውም ያሉ ይመስለኛል፡፡
በመሠረቱ ችግሩ ይህን ያህል ይሆናል ተብሎ አልተጠበቀም፡፡ ሲነሳ በተደራጀ መልኩ ቀደም ብሎ የተሠራበት አይደለም፡፡ ለንግዱ ማኅበረሰብ ተወስኗል የሚል ነገር ነው ለኅብረተሰቡ ተሰራጨው። አብዛኞቹ የኅብረት ሥራ ዩኒየኑ አባላት በአርሶ አደሩ መሃከል ያሉ ናቸው ወሬውን ያሰራጩት፡፡ ውሳኔው ተላላፊ እንጂ ወደ አፈጻጸም አልተገባም፡፡ የዞኑ አመራርም በአንድ ጊዜ ችግሩ በዚህን ያህል ይሰፋል፤ ኅብረተሰቡ በአንድ ጊዜ ይህን ውሳኔ ይሰማል የሚል ግንዛቤ አልነበረውም። ጥፋቱ ከአካባቢ አካባቢ ይለያል፡፡ ዲላ በስፋት ተጎድቷል። ወናጎ ላይና ይርጋጨፌ ላይ በጣም በስፋት ጉዳት ደርሷል፡፡ ሌሎች ወረዳዎች ላይ መጠነኛና ቀላል ነበር፡፡ መነካካቱ አለ፡፡ ግን ችግሩ አጠቃላይ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡
በአሁኑ ወቅት ይህንን ችግር ፈጥረዋል የተባሉ የተጠረጠሩ ሰዎች ተይዘዋል፡፡ የሕግ ሂደት መጠበቅ ስላለበት እነዚህ ሰዎች ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር ስለጉዳዩ ውይይት ሲደረግ እነዚህ እነዚህ ናቸው ብሎ የሰጣቸው ሰዎች አሉ፡፡ ቁጥራቸው ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል፡፡
ከዝግጅት ክፍሉ
የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ ስለጉዳዩ ለመጠየቅ ደውለንላቸው ሞባይሉ አይሰማም፣ በቢሮ ስልክ ደውሉ ብለውን ቁጥር ሰጡን። ስንደውል አይነሳም፡፡ መልሰን ደውለን ስልኩ አይነሳም አልናቸው፡፡ ቆይ እኔ እደውላለሁ ብለው ሳይደውሉ ቀሩ፡፡ ዞኑ አስተዳዳሪ ጋ ደውለን ስለጉዳዩ ልናናግራቸው መፈለጋችንን ስንነግራቸው አሁን አልችልም ስብሰባ ላየ ነኝ አሉን፡፡

Read 4473 times