Sunday, 09 October 2016 00:00

የቀለጠው መንደር

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(10 votes)

ግሮሰሪዋ እንደ ውይይት ታክሲ ፊት ለፊት ታፋጥጣለች፡፡ በግራና በቀኝ አግዳሚ ወንበር ላይ ወደ ሃያ ጠጪዎች ተፋጠዋል፡፡ በየነ ዘለቀ ሶስተኛ ደብል ጂኑን አጋምሷል፡፡ የመንገድ ስራ ተቋራጭ ተቀጣሪ ነው፡፡ በነጠብጣብና በጭረቶች የተሸነታተረው ፊቱ፣ የከተማ መንገድ ካርታ ይመስላል፡፡ በየነ ኑሮውን ሳይሆን ስራውን ነው የሚመስለው፡፡ ከፊት ለፊቱ የነጋሽ እንደ ጦር የሾለ ግንባር በቅርብ ርቀት ተደቅኖበታል፡፡ የባለ ልኳንዳው ነጋሽ የተንጠለጠለ ጉበት መሳይ ፊቱ ከተንጠለጠለ ስጋ ጋር ያምታታል፡፡ ሰው ኑሮውን ሳይሆን ስራውን ይመስላል አይባል ነገር፡፡
ሰዓቱ ቢገፋም በየነ ወደ ቤቱ የመሄድ አንዳችም ፍላጎት አይታይበትም፡፡ ሀገሩን፣ ራሱን፣ በተለይም የሚስቱን ዘመዶች ላለማየት በአልኮል መለኪያ መደበቅን መርጧል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት …
የባለቤቱ አጎትና አክስትየው፣ ጎረምሳ ልጃቸውን አስከትለው በእንግድነት ቤቱ ሲመጡ በአክብሮት ነበር የተቀበላቸው፡፡ ከዛሬ ነገ ይሄዳሉ በሚል ቢጠብቃቸውም ሁለት ሰንበት እንደ ዘበት አስቆጠሩ። አክስትየውም ሆነ አጎትየው “ያመናል” የማይሉት የበሽታ አይነት የለም፡፡ አክስት እያቃሰቱ፤“ጣፊዬን … መታጠፊያዬን … ጎኔን .. ጎድኔን… ወጋኝ… አሰጋኝ” እንዳሉ ነው፡፡ አጎትም፤ “ጭንቅላቴ አንገቴ ላይ ውሀ ልኩን በትክክል ጠብቆ የተቀመጠ አይመስለኝም” የሚል ለሰሚ ግራ የሚያጋባ ህመም አለባቸው። ቀጠልም አድርገው “ምንስ ሀኪም አለ? ለትንሿ ህመም እንደ መጫኛ ገመድ ረዝሞ የተንዘለዘለ የበሽታ ስም መስጠት እንደ ሊቅነት ተቆጥሯል”፡፡
ማለዳ ወጥተው ከአንዱ ክሊኒክ ወደ ሌላው ክሊኒክ እየዞሩ፣ በሽታቸውን ፍለጋ ሲንከራተቱ ውለው ይገባሉ፡፡ “ዩሪክ አሲድ ተገኘብኝ” አቶ አጎት በኩራት፡፡ ልክ ዩራኒየም የተባለ የከበረ ማዕድን ከሰውነታቸው ከርስ ውስጥ የተገኘ ይመስል፡፡ ስለ ከርስ ከተነሳ አመጋገባቸው እንደ ህመምተኛ ሳይሆን እንደ ጤነኛ፣ ያውም እንደ ስፖርተኛ ነው። የቀረበውን ጥርግ ነው፡፡ ጠገብን  የሚለውን ቃል በፍጹም አያውቁትም፡፡ ሁኔታቸው ከአንድ የረሃብ የሰቆቃ ምድር የመጡ ያስመስላቸዋል፡፡ በዚያ ላይ ወጠምሻው ጎረምሳ ሌሊት ከእንቅልፍ እንደነቃ የመብላት አመል አለበት፡፡ በውድቅት ሌሊት ረሀቡን በሁለት እንጀራ ድል ከነሳ በኋላ ነበር የሚያንቀላፋው - ያውም እያንዛረጠ፡፡
በየነ ዘለቀ እኩለ ሌሊት ሞቅ ብሎት ወደ ቤቱ ሲገባ፣ ባለቤቱ ቆዝማ “እነጋሽዬ እሁድ ሊነሱ ነው” ስትል አበሰረችው፡፡ ቀጠል አድርጋም፤ “እንዲሁ መቸም በደረቁ አይሸኙንም፤መካከለኛ በግ”
አይቻልም ማለት ልቧን መስበር ነው፡፡
እናም ቅዳሜ ጠዋት መካከለኛ በግ ገዝቶ ገባ፡፡
የእሁድ ተጋባዦች ዱለቱን፣ ጥብሱን፣ ቅቅሉን፣ በፍጥነት - በብቃት ዋጥ!  ስልቅጥ እያደረጉ መቁለጭለጭ ሆነ፡፡ 3 ሰዓት፣6 ሰዓት፣ 9 ሰዓት፣ 12 ሰዓት፣ በአራት ዙር በገፍ የቀረበውን ማዕድ ሲያግበሰብሱ ዋሉ፡፡ በአንድ ቀን ውሎ በጉ 90 ፐርሰንት በፍጥነት መጠናቀቁ አስገራሚ ነበር፡፡ እሁድ ማለዳ ባለቤቱ፤ “እነ ጋሽዬ ነገ ለመሄድ ቢቆርጡም በስንት ልመና ሰኞ ለመሄድ አሳመንኳቸው” አለችው የዋህ ሚስቱ፡፡
ተጨማሪ አንድ ቀን ቅንጣቢ ስጋ ሳያስቀሩ፣ የበጉን የመጨረሻውን ፍጻሜ ሳያዩ እንደማይሄዱ ታውቆት ነበር፡፡ እሁድ ጠዋት የወጣ፣ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ቤቱ ገባ፡፡ በሚያየው ነገር ደንዝዞ ቀረ፡፡ አክስት ተብየዋ ጥብስ ስትጎሰጉስ… ጎረምሳው ልጅ ባሌስትራ የሚያክል ቅልጥም እንደ ጅብ ሲግጥ፣ አቶ አጎት አጥንት እየጎረደመ፣ በጥም እንደተቃጠለ የበረሃ ግመል ሙሉ ሰሃን መረቅ ምጥጥ አድርጎ ሲጠጣ… ሁኔታቸው ቤት ውስጥ የተዘጋጀን ማዕድ ሳይሆን አውሬ አድነው በመቀራመት ላይ ያሉ ያስመስላቸዋል፡፡ አቶ አጎት ተብየው ሰላም ሲለው ሲነሳ ነበር በሙሉ ሱፍ ተሰትሮ ያየው፡፡ ምትሃት እንዳዬ ክው ብሎ ቀረ፡፡ ያቺ የዋህ ሚስቱ አንስታ እንደሰጠችው እርግጠኛ ነበር፡፡ ከዓመት ደመወዙ በየወሩ 300 ብር እየከፈለ በክሬዲት የገዛው ሙሉ ልብስ። ሰው ፊት የሚቀርብበት ብቸኛውን ሙሉ ልብስ፡፡ በቀጭን ሰንጢ ልቡ ላይ እንደተወጋ ተንዘፈዘፈ፡፡ በፍጥነት ወጣ፡፡ ሎጥ በሶዶም በወጣበት ፍጥነት ለአፍታም ዞር አላለም፡- የጨው አምድ ሆኖ የሚቀር ይመስላል፡፡…
በATM ካርድ የቀረውን 3.000.00 ብር አወጣ።
ግሮሰሪ ተሰየመ፡፡ አከታትሎ 5 ደብል ብራንዲ ቢጣም ሞቅ አላለውም፡፡ እንደውም ቀዝቅዞ አረፈው፡፡ ጥንብዝ ብሎ መስከር አለበት፡፡ ጎርደን ጅን አዘዘ፡፡ ሲጋራውን ለኮስ። ሁለት ደብል ጎርደን ጅን እንደተጎነጨ በመጠኑ ቸስ አለ፡፡ ግሮሰሪው እኩለ ሌሊት ተዘጋ፡፡
ከአንዱ ግሮሰሪ ወደ ሌላው ቡና ቤት እየገባ እየወጣ፣ እስከ ውድቀት ቀመቀመ፣ ገንዘቡን ሙጥጥ አድርጎ ጥንብዝብ ብሎ ሳይሰክር ወደ ቤቱ ላለመግባት ወሰነ፡፡ በቂ ገንዘብ ይዟል፤ ግን ስካር የለም፡፡ ገንዘብና ስካሩ ፉክክር የያዙ ይመስላሉ፡- በአንደኛው ፅንፍ የብሩ አላልቅ ማለት በሌላኛው ጥንፍ ደግሞ መጠጥ አልበቃው ያለው ስካር፡፡ ገንዘብ፣ ስካር እሱ፣ የሚስቱ ዘመዶች፡፡ ሙሉ ሱፍ ልብሱ፡፡ “ለምን አልሰክርም?” ሲል ራሱን ጠየቀ፡፡
‘በዘር ሃዴ ውስጥ አደገኛ ቮድካ ጠጭ ሩስኪ ደም ይኖርብኝ ይሆን? ወይንስ የመስከሪያ መሣሪያዬ ብልሽት ደርሶበት ይሆን?’ ሲል በውስጡ እያውጠነጠነ ወደ ሌላ ግሮሰሪ ገባ፡፡
የገባበት ግሮሰሪ በመዝጋት ላይ ነበር። ከመቀመጡ “ጎርደን ጅን በፍጥንት” ሲል አምባረቀ። ከሌላ ፕላኔት የመጣ ይመስል ዌይተሩ በግርምት አፈጠጠበት። ሊያስተናግደው ፈቃደኛ አልሆነም። እንደ አማራጭ ትንሷን ሚኒ ድራይድ ጂን ገዝቶ ወጣ። ሁሉም መጠጥ ቤቶች ተጠርቅመዋል። ያልተዘጋ ቤት ባገኝ በሚል ተስፋ ይዞር ጀመረ። አዙሪት ውስጥ ገባ፤ ከየት ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ መሽከርከሩን ቀጠለ፡፡ አዙሪት ውስጥ ገባ፤ እራሱን ከአውላላ ሜዳ ላይ ቆሞ አገኘው፡፡ ፀጥ ረጭ የጨለማ አዘቅት፡፡ ከዚያ የጨለማ ማህፀን አንድ ሰው ብቅ አለ፡፡ ወደ እሱ ተራመደ፡፡ እንደ ጥላ ኮቴው አይሰማም፡፡
“ያልተዘጋ መጠጥ ቤት እየከፈለክ ነው?” ሲል የልቡን መሻት ጠየቀው፡፡ መልሱንም ሳይጠብቅ፤ “በሃይቁ ግርጌ እስከ ንጋት የቀለጡ የምሽት ጭፈራ ቤቶች አሉ” ብሎ ወደ ሃይቁ አቅጣጫ ጠቆመው። ወደ ጠቆመው የምሽት ጭፈራ ቤቶች ወደ ሀይቁ አዘገመ። አሞራ ገደል በሚያስገባው ቅያስ አቀና። የሀይሌ ሪዞርት በቅርብ ርቀት እንደሚገኝ ትዝ አለው፡፡ የአዋሳ ሀይቅ በዝምታ ተገማሽሯል፡፡ ሀይቁ ጠርዝ ደረሰ፡፡ ሚኒ ድራይ ጅን ከኪሱ አውጥቶ በቁሙ ጨለጠው። በአየር ላይ የሚበር፣ በደመና የሚራመድ መሰለው፡፡ ጥንብዝ ብሎ ሰከረ- ባለ ሰባት ኮከብ የስካር ደረጃ፡፡ በቆመበት እንደ ቄጤማ ይውረገረግ ጀመር፡፡ አይኖቹን ሽቅብ ወደ ሰማይ ላከ። መላዕክት መሳይ ፍጡር፣ በጥቁር ደመና ጥላሸት የለበሰውን ሰማይ፣ በነጭ መሀረብ ሲጠርግ ያየ መሰለው፡፡ ከጠራው ሰማይ ከዋክብት እንደ አሸዋ ፈሰሱ … ከቁልል ደመና የምትወጣውን ጨረቃ እንደ ፓውዛ ብልጭ ብላ አበራችበት፡፡
በክዋክብት ጥቅሻ ካበደው ሰማይ ዓይኖቹን ወደ ሀይቁ መለስ አደረገው፡፡ የጨረቃና የክዋክብቱ ነፀብራቅ፣ ሀይቁን የነጠረ ብር የፈሰሰበት አስመስሎታል፡፡ ሞገዱ ሲነሳና ሲወድቅ፣ ክዋክብቱ እንደ ርችት ፍንጥቅጥቅ… ብልጭ! ድርግም! ሀምራዊ ቀለማት ህብር… ከአፍታም በኋላ ቦግ! እልም! ብርቱካናማ የቀለማት ርችት… ምትሀታዊ ውበት፡፡ ቅኔያዊ ህልም፡፡ እናም ሰተት ብሎ ገባ ወደ ቀለጠው መንደር፡፡ ሰመጠ፡፡

Read 4137 times