Saturday, 08 October 2016 16:15

ቃለ መጠይቁ

Written by  ከግዛቸው ኃይሉ
Rate this item
(4 votes)

 እኔና ከዩኒቨርሲቲ አብረን የተመረቅን ጓደኞቼ የመሰረትነው ማህበር አለን፤ በየሶስት ወሩ የሚያገናኘን፡፡ ባለፈው እሁድ እንደተለመደው ባለቤቴንና የ8 አመት ልጄን ይዤ ወደዚያው ሄድኩኝ፡፡ ልጄ ከማህበርተኞቼ ልጆች ጋር ኳስ መጫወት ስለለመደ፣ የማህበር ቀንን በጉጉት ነው የሚጠብቃት፡፡
ያለፈው እሁድ ግን ሀይለኛ ዝናብ ስለ ጣለ፤ ኳሱ ቀርቶ ልጆቹ ቤት ገቡ፤ አንድ ቦታ መቀመጥ የሰለቻቸው ልጆች፤ ወዲያ ወዲህ እየተሯሯጡ ቤቱን አመሱት፡፡ እኛንም ረበሹን፤ አንድ የታከተው ማህበርተኛ ልጆቹን ለማረጋጋት፤ የጥያቄና መልስ ውድድር እናድርግ፤ አሸናፊውም የቸኮሌት ሽልማት ይሰጠዋል ብሎ ልጆቹን አግባባቸው፡፡ እኛም ሰላም በማግኘታችን እፎይ አልን፡፡ ባንድ በኩል ሽልማቱ ሲያስደስታቸው፣ በሌላ በኩል ያ ሁሉ ወላጅ ፊት ቀርቦ ጥያቄ መመለስ ፍርሀት ለቀቀባቸው፤ከሰልፍ መጨረሻ ለመሆን ይላፉ ጀመር፤ እውነት ለመናገር የወላጅ ልብም የዛን ያህል ተንጠልጥሎ ነበር፡፡
ሀሳቡን ያመጣው ማህበርተኛ፣ የልጆቹን ስም ተራ በተራ ሲጠራ፣ ወደ ፊት እየመጡ ጥያቄዎቹን ይመልሱ ጀመር፡፡ አንዳንዱ ልጅ በፍርሀት ሲንተባተብ፤ የአንዳንዱ መልስ ሲያስገርመን፤ የአብዛኞቹ ግን ያስቀን ነበር፡፡ በተለይ ‹ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?› ለሚለው ጥያቄ፣  የልጆቹ መልስ በጣም የሚያስቅና የሚገርም ነበር፡፡ አንዷዋ ልጅ ‹የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ነው የምፈልገው? ብላ ከባድ ጭብጨባ ሲደረግላት፣ ሌላው ‹የአንቡላስ ሹፌር መሆን ነው የምፈልገው፤ እንደ ልቤ በፍጥነት እንድነዳ› ብሎ በሳቅ ገደለን፡፡ የእኔ ልጅ እንደ አጎቱ ፓይለት መሆን እፈልጋለሁ ይላል ብዬ ጠርጥሬ ነበር። ተራው ሲደርስ፤ ‹እኔ ሳድግ ፌዴራል መሆን ነው የምፈልገው› ብሎ አስደነገጠን፡፡
ለምን? ሲባል ‹ክትክት አሪፍ ናቸው፤ ማንም አይችላቸውም› ብሎ እርፍ!! ማንም አልሳቀም፡፡ እኔና ባለቤቴ ከሩቅ ተያየን፡፡

Read 2721 times