Sunday, 09 October 2016 00:00

ማራቶን ልዕልቷን ከ2 ሰዓት በታች…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

    በ43ኛው የበርሊን ማራቶን 2፡03፡03 በሆነ ሰዓት አትሌት ቀነኒሳ በቀለ  ካሸነፈ በኋላ፤ ማራቶን ልዕልቷ ከእነክብረወሰኖቿ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ተስፋዎች ተፈጥረዋል፡፡ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች በመግባት በአትሌቲክስ ታሪክ የላቀውን ስኬት የማስመዝገብ አጀንዳም ተያይዞ ተቆስቁሷል፡፡ የ34 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበርሊን ማራቶን ያሸነፈበት ሰዓት ከ8 ዓመታት በኋላ አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ደረጃ ሁለተኛ ሆኖም ተቀምጧል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከቀነኒሳ 2፡03፡03 በኋላ… በሚል ርእስ በቀረበው የስፖርት አድማስ ትንታኔ  በሮጠባቸው 5 ማራቶኖች ስለነበሩት ልምዶች፤ ስለጉዳቶቹ ፤ ስለ ማራቶን ውድድር አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም ለውድድር በሚያደርጋቸው ስልጠናዎች እና ዝግጅቶች አብረውት ስለሚሰሩት የባለሙያዎች ስብስብም ተዳስሷል፡፡ በሌላ  በኩል   ከ6 ወራት በፊት በታዋቂው የአሜሪካው ጋዜጣ ኒውዮርክ ታይምስ በሁለት  ክፍሎች ስለቀረበው ሰፊ ዘገባም ተነስቶ ነበር፡፡ በተለይ  ስኮትላንዳዊው ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ sub2hr project በሚል በ30 ሚ .ዶ በጀት እየሰሩት ስለሚገኘው ምርምርም ተወስቷል፡፡ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የሚሮጥ አትሌት ለማግኘት የሚሰራበት ነው፡፡ የበቆጂ አትሌቶች እና ቀነኒሳ በቀለ የሚሳተፉበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ከተሳካ ማርስን እንደመርገጥ የሚቆጠር ስኬት መሆኑን ጠቃቅሰን ነበር፡፡ ዛሬ በሁለተኛ ክፍል የቀረበው የስፖርት አድማስ ትንታኔ ማራቶንን   ከ2 ሰዓት በታች በስፋት የሚመለከት ነው፡፡ ማራቶን ከ2 ሰዓት በታት የት፤ መቼ፤  ማንና እንዴት ?የሚሉ  ጥያቄዎችን የሚዳስስ ትንታኔ ነው፡፡ይህን ታሪካዊ  ውጤት ኢትዮጵያዊ ወይም ኬንያዊ  ያስመዘግቡታል ተብሎ ስለሚገለፅም ፤ የሁለቱን አገራት ማራቶኒስቶች በዓለም የማራቶን የሪከርድ ታሪክና  የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ   በንፅፅር  የቃኘንበት ነው፡፡
ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የት ይገባል?
በመላው ዓለም ከሚካሄዱና የሪከርድ ሰዓት ህጋዊ ከሚሆንባቸው ትልልቅ  ውድድሮች መካከል ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ዋና እጩዎች የሚባሉት በበርሊን እና ለንደን ከተሞች  የሚዘጋጁት ማራቶኖች ናቸው፡፡ በተለይ ግን የማራቶን ሪከርዶችን ስለማሻሻል በተሰሩ ጥናቶች በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው  የበርሊን ማራቶን ነው፡፡ የቺካጎ፤ የሮተርዳም፤ የለንደን  እና የፓሪስ ለአመቺነታቸው በተሰጠ ግምት እስከ 5 ባሉት ተከታታይ ደረጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡  የበርሊን ማራቶን ለሪከርዶች ምቹ የተባለው የመሮጫው ጎዳና ቀጥታ እና ሙሉ አስፋልት በመሆኑ፤ በውድድር ወቅት የአየር ሁኔታው ማመቸቱ እንዲሁም በየዓመቱ ከሚሳተፉት ተወዳዳሪዎች ፈጣን ሰዓቶች የማስመዝገብ ፍላጎት ጋር  አዳዲስ ሪከርዶች በተደጋጋሚ ስለሚመዘገቡበት ነው። በአንፃሩ በለንደን ማራቶን  አንዳንድ ኪሎሜትሮች ላይ በኮብልስቶን ላይ መሮጡ ፍጥነትን ይገድባል፡፡ በኒውዮርክ ማራቶን ደግሞ ድልድይ አካባቢ በሚገኝ አስቸጋሪ ጎዳና መሮጡ አለመመቸቱም ይጠቀሳል፡፡  በበርሊን ማራቶን ሮጠው ከ1 እስከ 10 ደረጃ የሚያገኙት ማራቶኒስቶች በአማካይ ሰዓታቸው 2፡03፡35 ሆኖ መመዝገቡም በሌሎች ማራቶኖች የሚሳካ አይደለም፡፡ በከባዱ የለንደን ማራቶን ከ1 እስከ 10 ደረጃ የሚያገኙት ማራቶኒስቶች  አማካይ ሰዓት  2፡04፡34  ሲሆን፤  በቦስተን 2፡07 እንዲሁም በቺካጎ 2፡08  እንደሆነ በአስረጂነት መጥቀስ ይቻላል፡፡  ባለፉት 30 ዓመታት በወንዶች ምድብ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለ8 ጊዜያት በበርሊን ማራቶን የተሻሻለ ሲሆን አራቱ በቺካጎና በለንደን እንዲሁም  3 በሮተርዳም ማራቶኖች የተገኙ ናቸው፡፡ ስለሆነም ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ለመጀመርያ ጊዜ ይገባበታል ተብሎ የሚጠበቀው  ከ2003 እኤአ ጀምሮ 6 የዓለም የማራቶን ክብረወሰኖች የተመዘገቡበት የበርሊን ማራቶን ይሆናል፡፡
ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች መቼ ይሆናል?
በተለያዩ ጥናቶች እና ትንታኔዎች እስከ 2028፤ 2035 ወይም 2041 እኤአ ላይ እንደሚሳካ ይገመታል፡፡ ስኮትላንዳዊው ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ ግን በsub2hr ፕሮጀክታቸው እስከ 2019 እኤአ የሚገኝ ውጤት ነው ይላሉ፡፡ ከ2 ዓመታት በፊት በርሊን ማራቶን ላይ ኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ በ2፡02፡57  የዓለም ማራቶን ሪከርድ ሲያስመዘግብ ከ2 ሰዓት በታች ይገባል የሚለው አጀንዳ የፈጠረው ትኩረት ነበር፡፡  በወቅቱ ዴኒስ ኪሜቶ የራሱን ሪከርድ የማሻሻል አቅም እንዳለው ሲናገር ግን ከ2 ሰዓት በታች መገባቱን በተመለከተ አስተያየት ሳይሰጥ በ2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ሊገባ እንደሚችል ግን ተናግሮ ነበር፡፡ ያኔ በወቅቱ የዓለም ክብረወሰን ዙርያ  በተሰሩ ትንታኔዎች 42.195 ኪሎሜትሮች (26 ማይሎች እና 385 ያርዶች) የሆነውን የማራቶን ርቀት ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት   ቢያንስ በ10 ቢበዛ በ15 ዓመታት ውስጥ ሊሳካ እንደሚችል ይገለፅ ነበር።  ይህን ግምት ለማሳካት በየዓመቱ የማራቶን ሪከርድ ሰዓት በአማካይ በ15 ሰከንዶች እየተሻሻለ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በርግጥ የማራቶን ሪከርድ ሰዓትን ከ20 ሰከንዶች በላይ ማሻሻል በጣም ልዩ ብቃት የሚያሳይ አትሌትን የሚጠይቅ ነው፡፡   በማራቶን ታሪክ በወንዶች ምድብ የዓለም ሪከርድ በ1900  2፡40 ፤ በ1920ዎቹ 2፡32፤ በ1950ዎቹ 2፡15፤ በ1960ዎቹ 2፡08 ነበር፡፡ ከ1999 እኤአ ወዲህ በ3 ደቂቃዎች ተሻሽሎ 2፡05 ደረሰ፡፡ ከ2004 እኤአ ጀምሮ 2፡04 እና 2፡03 እያለ ቀጥሏል፡፡ ከ2፡06 ወደ 2፡05 ሲወርድ አራት አመታት፤ ከ4 ዓመታት በኋላ ወደ 2፡04 ፤ ከ5 ዓመታት በኋላ ወደ 2 ፡03 እንዲሁም ከ6 ዓመታት በኋላ ወደ 2፡02 ሊወርድ ችሏል፡፡   ከ2 ዓመታት በፊት በበርሊን ማራቶን 2፡02፡57 ሆኖ ከተመዘገበው የዴኒስ ኪሜቶ የዓለም የማራቶን ሪከርድ በኋላ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት መቀነስ ያለባቸው 177 ሴኮንዶች ናቸው፡፡ እነዚህን ሴኮንዶች በፈጣን አሯሯጥ ለማራገፍ የሚፈጀውን ዓመት ለመገመት የሚከብድ ነው፡፡
ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች በማን ይገባል ?
ለታሪካዊው የማራቶን ከፍተኛ ውጤት ቅድሚያ ግምት ያገኙት ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ኬንያና ኢትዮጵያ የሚወጡ ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ በቆጂ በምትባለዋ የክልል ከተማ እንዲሁም በኬንያ ኤልዶሬት እና ኢቴን በተባሉት ከተማዎች የሚገኙት የሚጠበቁ ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ የምስራቅ አፍሪካ የገጠር ከተሞች በማራቶን ፈጣን ሰዓቶችን የሚያመዘግቡ እና ትልልቅ ውድድሮችን የሚያሸንፉ ሯጮች በብዛት እንደሚገኙ የውጤት ታሪኮች ያመለክታሉ፡፡ በየጊዜው አዳዲስ እና ፈጣን የማራቶን ሯጮችን በማፍለቅ በመላው ዓለም የሚስተካከላቸው የለም፡፡ በቆጂ በየጊዜው በሚወጡ ምርጥ ማራቶኒስቶቿ ከ2 ሰዓት በታች የሚገባ አትሌት ይገኝባታል በሚሉ ምርምሮች ከፍተኛ ትኩረት ስታገኝ ቆይታለች፡፡ የበቆጂ ለጥ ያለ መልክዓ ምድር እና ተስማሚ  እና ተስማሚ አየር ንብረት   ምርጥ አትሌቶች እንደሚያፈራ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል፡፡ ትውልዳቸው  ከበቆጂ የሆኑ ሯጮች ባለፉት 20 ዓመታት በኦሎምፒክ ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች እና በታላላቅ ማራቶኖች እንዲሁም የጎዳና ላይ ሩጫዎች ከፍተኛ ውጤቶችን አስመዝግበዋል፡፡  እንደበቆጂ ሁሉ የኬንያም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች በኤልዶሬት እና ኢቴን በተባሉት የገጠር ከተሞች የሚገኙ ናቸው፡፡ በተለይ ኢቴን ከቅርብ አመታት ወዲህ የማራቶን ሯጮች መገኛ ብቻ ሳይሆን የዓለም ማራቶን ሊግ አሸናፊ እና ፈጣን ሰዓት የሚያስመዘግቡ ሯጮች መናሐርያ መሆንም ጀምራለች፡፡   3ቱ የምስራቅ አፍሪካ የገጠር ከተሞች ለማራቶን ሯጮች ምቹ መፍለቂያ ከሆኑባቸው ምክንያቶች ዋናው በከፍተኛ አልቲትዩድ መገኘታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም በገጠር ከተሞቹ ያለው መልክዓምድራዊ ሁኔታዎች፤ የድህነት ኑሮ፤ የስኬታማ ማራቶን ሯጮች መብዛት፤ባህላዊ የአመጋገብ ስርዓታቸው ለስኬቱ አስተዋፅኦ ስለማድረጋቸውም ምክንያቶች ይሆናሉ፡፡
ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች  እንዴት ይቻላል?
ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት እንደሚቻል በሚነሳው አጀንዳ የፕሮፌሰር ያኒስ ፒስተሊደስ ፕሮጀክት ብቸኛው አይደለም፡፡ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች መግባትን አስመልክቶ በርካታ በአትሌቲክስ ላይ በሚያተኩር ዘገባቸው በሚታወቁ መፅሄቶች፤ ድረገፆች እና የመረጃ ሚዲያዎች በየጊዜው ትንታኔዎች ይቀርባሉ፡፡ በአጀንዳው ላይ በማተኮር የተፃፉ ታዋቂ መጽሐፍትም አሉ፡፡ በተለይ በኤድ ሲዛር የተፃፈውን “The quest to Run Impossible Marathon መጥቀስ ይቻላል፡፡  ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በርካታ ወሳኝ ሁኔታዎችን እና አስተዋጽኦዎች አሉ፡፡ ስፖይክ የተባለና ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ጋር የሚሰራ ድረገፅ ከ43ኛው የበርሊን ማራቶን በኋላ የጊዜ ሁኔታ እንጅ ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ይገባል የሚል ዘገባ ሰርቶ ነበር፡፡ ስፓይክ ለዚህ ዘገባው 13 ወሳኝ ሁኔታዎችን የዘረዘረ ሲሆን ከእነሱም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ከሪኮርዱ 5 ደቂቃም ባለፉት 20 ዓመታት ተቀንሰዋል፤ አሁን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ከተመዘገበው ሪኮርድ የቀሩት ከ3 ያነሱ ደቂቃዎች በመሆናቸው ተስፋ እንደሚፈጥር በቅድሚያ ይጠቅሳል፡፡ ከ2 ሰዓት 05 ደቂቃዎች በታች የሚገቡ አትሌቶች ከ30 በላይ መሆናቸው፤ በማራቶን የፈጣን ሰዓቶች ደረጃ በየዓመቱ እስከ 30ኛ ደረጃ አዳዲስ አትሌቶች በብዛት መግባታቸው፤ በመጀመሪያ ማራቶናቸው ከ2፡04 በታች የሚገቡ አትሌቶች ብቅ ማለታቸው፣ በትራክ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ አትሌቶች ወደ ማራቶን ሲገቡ ስኬታማ መሆናቸው በስፓይክ የተጠቀሱ ደጋፊ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ እንደ ዩሲያን ቦልት የላቀ ብቃት በአትሌቲክስ የሚያስመዘግቡአትሌቶች የሚፈጥሩት መነሳሳት፤ በፓውላ ራድክሊፍ አሯሯጥ አሰለጣጠን ላይ አንዳንድ አትሌቶች እያተኮሩ መሆናቸው ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂ የሚያግዛቸው የምርምር ተግባራት፣ በከፍተኛ አልቲትዩድ ለሚሰሩ ልምምዶች እና በሌሎችም ምክንያቶች ማራቶን ከ 2ሰዓት በታች መግባት እንደሚቻል ማመልከታቸውን የስፓይክ ዘገባ ገልፆታል፡፡
በተመረጠ የማራቶን ውድድር በፈጣን ሰዓታቸው ከ1-20 ደረጃ ያሉት አትሌቶች በብዛት መካፈላቸው ሌላው የሚጠቀስ አስተዋጽኦ ነው፡፡ ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚችሉ እና የአሯሯጥ ጽናት ያላቸው አትሌቶች ከ7-8 ሺ ጫማ ከፍታ ላይ መኖራቸው፤ የማራቶን ልምምዳቸውን ከ4000 ጫማ በታች በመስራታቸው፣ በዝቅተኛ አልቲቲየድ መወዳደራቸው፣ የሰውነት ክብደታቸው ቀለል ያሉ መሆናቸው አጋዥ ሁኔታዎች መሆናቸውም ይገለፃል፡፡
1፡59፡59 ሰዓትን በማራቶን ለማስመዝገብ 1 ማይል ርቀትን በ4 ደቂቃ ከ34 ሰኮንዶች መሸፈን ግድ ይሆናል። ከወቅታዊ ሪከርድ በየማይሉ በ7 ሰኮንዶች በፈጣን አሯሯጥ በሚደረግ ውድድር ማለት ነው፡፡  ሳይንቲስቶች የማራቶን ርቀትን በሰው ልጅ የተፈጥሮ ብቃት ለመሸፈን የሚቻልበት የመጨረሻው የሪከርድ ሰዓት ወሰኑ 1፡57፡57 እንደሆነ ይገለፃሉ፡፡  በበርካታ ምርምሮች እና ትንታኔዎች ደግሞ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ከሚጠቀሱት ዋና ዋና ሁኔታዎች ከዚህ በታች የቀረቡት ይገኙበታል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የማራቶኑን ርቀት ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚችሉት አትሌቶች ከኬንያ ወይንም ከኢትዮጵያ የገጠር ከተሞች መልምሎ ማውጣቱ  ይጠበቃል፡፡ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚችል አትሌት በሰዓት 13.1 ማይሎችን መሸፈን የሚጠበቅበት ሲሆን ይህ ብቃት ያላቸው የሁለቱ አገራት አትሌቶች ብቻ መሆናቸውን ባለሙያዎች ስለሚያስረዱ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁለት የምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚወጣ የማራቶን ሯጭ  ከ7ሺ እስከ 8ሺ ጫማዎች በሚለካ ከፍተኛ አልቲትዩድ መኖራቸው ያጎናፀፋቸው ተፈጥሯዊ አቅም አለ፡፡  ከ4ሺ ጫማዎች በታች ባለ ስፍራ  ልምምድ መስራታቸው ደግሞ ለሚያስፈልገው ብቃት አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ከዚያም አትሌቱ  ከባህር ጠለል በታች ዝቅተኛ በሚባል አገር ውድድሩን ማድረጉ ከ2 ሰዓት በታች የመገባቱን ሁኔታ ያጠናክረዋል፡፡
 የሰው ልጅ በሚችለው ብቃት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት  የስልጠና ሳይንስ እና ቴክኖሎጂም ለውጥ የሚፈጥሩም ናቸው፡፡ 40 አመት በፊት የነበረው ስልጠና አሁን በከፍተኛ ደረጃ በምርምሮች ማደጉ እንደ አጋዥ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡  በአዲዳስ፤ በናይኪ እና በፑማ የትጥቅ አምራች ኩባንያዎች የሚቀርቡ የመሮጫ ጫማዎችም በሚኖራቸው አስተዋፅኦ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የጀርመኑ ትጥቅ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ለማራቶን ሯጮች የሚሰራቸው የመሮጫ ጫማዎች ለሪከርድ ሰዓቶች በመመቸታቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ከ2 ዓመታት በፊት ዴኒስ ኪሜቶ ለሰበረው ሪከርድ አዲዮስቡስት የተባለው መሮጫ ጫማ ጠቅሞታል ተብሏል፡፡ ሌላው ኬንያዊ ፓትሪክ ማኩ ሪከርድ ያስመዘገበው በዚሁ መሮጫ ጫማ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የማራቶንን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡት አራት የኬንያአ ትሌቶች እና ኃይሌ ገብረስላሴ ጨምሮ የሚጠቀሙበትም ነበር፡፡  ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚደረገውን ጥረት ዘመናዊ የመሮጫ ጫማ ሊያግዘው እንደሚችል እምነት ቢያሳድርም በውድድሩ  ታሪክ የተከሰቱ አስገራሚ ሁኔታዎችን መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ አበበ ቢቂላ ሁለቱን የማራቶን ሪኮርዶች በኦሎምፒክ መድረክ ሲያስመዘግብ አንዱን በባዶ እግሮቹ ሌላኛውን በጫማ በመሮጥ ነበር፡፡ በሮም ኦሎምፒክ ለአበበ አዲዳስ የመሮጫ ጫማ ቢያቀርብለትም፣ በባዶ እግሩ በመሮጥ ሪኮርድን አስመዝግቧል፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላ ደግሞ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በድጋሚ የዓለም ሪከርድ ለማስመዝገብ የበቃው በፑማ ጫማዎች ነበር፡፡ የዛሬ ማራቶኒስቶች በመሮጫ ጫማ ስፖንሰርሺፕ ከ10-100ሺ ዶላር እንደሚከፈላቸው የሚገለፅ ሲሆን ምርቶቹን የሚያቀርቡት ኩባንያዎችም ትኩረት በማድረግ እየሰሩበት ይገኛል፡፡
በማራቶን ውድድሮች በሚመደቡ አሯሯጮችም ብቃት የሚያከናውኑ የቡድን ስራዎች አጋዥ ምክንያት እንደሚሆንም ተጠቅሷል፡፡ አሯሯጮቹ  ሙሉ ለሙሉ ማራቶን ቢሮጡ ሪከርዶች እና ፈጣን ሰዓት የማስመዝገብ ብቃት አላቸው፡፡ በ2011 እኤአ ላይ የኃይሌን ሪከርድ የነጠቀው ፓትሪክ ማኩ በፊት አሯሯጩ እንደነበር ይታወቃል፡፡  
ከሶስትና አራት የውድድር ዘመናት በፊት ከ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በታች ከሚገቡ 10 አትሌቶች ሰባቱ እድሜያቸው በአማካይ 24 የሆኑ ነበሩ፡፡ ባለፉት አምስት አመታት የታየው ግን ሪከርድ የመስበር እድል ያላቸው በእድሜያቸው በሰል ያሉ አትሌቶች መሆናቸውም ሌላው ሁኔታ ነው፡፡ በ2011 እኤአ ላይ የኃይሌን ሪከርድ የሰበረው ፓትሪክ ማኩ 29፤  የፓትሪክ ማኩን ሪከርድ ያሻሻለው ሌላው ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሳንግ 31 ዓመታቸው ነበር፡፡ በ2007 እና በ2008 እኤአ በቅደም ተከተል ለሁለት ጊዜ ሪኮርዶቹን የሰበረው ኃይሌ ገብረስላሴ በ34 እና 35 አመት እድሜው ነበር፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር የሚካሄዱ የትራክ ውድድሮች በመመናመናቸው በርካታ አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫዎች በተለይ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ወደ ማራቶን ውድድር ወጣት አትሌቶች በብዛት መግባታቸው ቢስተዋልም፤ በአንድ ውድድር ፈጣን ሰዓት አስመዝግበው የሚጠፉበት ሁኔታ ግን አለ፡፡
ማናቸውም  የማራቶን ሯጭ ለአንድ ውድድር ቢያንስ የ3 ወራት ጥብቅ የልምምድ እና የዝግጅት ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ምርጥ የሚባሉት የማራቶን ሯጮች በእንደዚህ አይነት የልምምድ ሁኔታዎች በአንድ አመት ሁለት እና ሶስት ማራቶኖችን በብቁ ተፎካካሪነት መሳተፍ ይችላሉ፡፡ ይሁንና ከ2 ሰዓት በታች የሚገባ አትሌት በዓመት  3 ማራቶኖችን የሮጠ ሊሆን አይችልም፡፡ በመጀመርያው ማራቶኑ ይህን ፈጣን ሰዓት ቢያስመዘግብ እንኳን በቀጣይ ውድድሮች ሊሳካለት መቻሉ ያጠያይቃል። ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በማራቶን የሚገኙ ዳጎስ ያሉ ገቢዎችም የሚፈጥሩት ግፊት የሚጠቀስ ነው፡፡ ማራቶኖችን ከሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚለያቸው በሽልማት መልክ፤ በስፖንሰርሺፕ እና በቦነስ ክፍያዎች ከፍተኛ ገቢ ስለሚገኝባቸው ነው፡፡  አብዛኛዎቹ የማራቶን ውድድሮች ለአሸናፊ አትሌቶች ከ50ሺ እስከ 100ሺ ዶላር በመሸለም ይታወቃሉ፡፡ የፓሪስ ማራቶን 150ሺ ዶላር ፤ የኒውዮርክ ማራቶን 130ሺ ዶላር፤ የበርሊን ማራቶን 150ሺ ዶላር፤ የቦስተን ማራቶን 150ሺ ዶላር፤ የቺካጎ ማራቶን 100ሺ ዶላር፤ የለንደን ማራቶን እስከ 55ሺ ዶላር  በነፍስወከፍ በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች ያበረክታሉ፡፡ አንድ የማራቶን ሯጭ በአሸናፊነቱ ከውድድሮቹ አዘጋጅ ከሚያገኛቸው ሽልማት ባሻገር በሚያስመዘግበው ፈጣን ሰዓት እና ሪከርድ  የቦነስ ሽልማች የሚያገኝበትም እድል አለው፡፡ አሁን ለምሳሌ በኒውዮርክ ማራቶን የቦታውን ሪከርድ  ለሚያስመዘግብ 70ሺ ዶላር ቦነስ አለ፡፡   ከ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በታች ለሚገባ አትሌት በለንደን ማራቶን 100ሺ ዶላር፤ በኒውዮርክ ማራቶን 50ሺ ዶላር ቦነስ ይሰጣል። በብዙዎቹ ማራቶኖች የቦታ ሪከርድ ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ከ25 እስከ 100ሺ ዶላር ይሰጣል፡፡  ሌላው የገቢ ምንጭ ትልልቅ አትሌቶችን በውድድሮቻቸው ለማሳተፍ የሚፈልጉ አዘጋጆች ከ100ሺ ዶላር ጀምሮ መክፈላቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የለንደን ማራቶን ለአንዳንድ አትሌቶች ተሳትፎ እስከ 200ሺ ዶላር እንደሚሰጥ ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል አትሌቶች ትጥቃቸውን ስፖንሰር ከሚያደርግላቸው ኩባንያም በአንድ ማራቶን ውድድር በመሳተፍ ውጤታማ ሲሆኑ ከ50 እስከ 70 ሺ ዶላር ይበረከትላቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም አንዳንድ እውቅ አትሌቶች የሚያገኙት የመሮጫ ጫማቸውን በሚያቀርብላቸው ኩባንያ የሚያገኙትም ጥቅም አለ፡፡ በአጠቃላይ በትልልቆቹ የዓለማችን ማራቶኖች አንድ ታዋቂ አትሌት ተሳትፎ ጥሩ ሰዓት በማስመዝገብ የሚያሸንፍ ከሆነ በአማካይ እስከ 750ሺ ዶላር ሊያካብት ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኬንያ  በዓለም የማራቶን ሪከርዶች ታሪክ
በዓለም የማራቶን ሪከርድ ታሪክ በወንዶች ምድብ የኢትዮጵያ 3 አትሌቶች በክብረወሰኖቹ መሻሻል ጉልህ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ይሁንና ባለፉት 8 ዓመታት የበላይነቱ በኬንያውያን እጅ ገብቷል፡፡  በማራቶን ታሪክ በወንዶች የመጀመርያው የዓለም  ሪከርድ የተመዘገበው እኤአ በ1908 በለንደን ማራቶን በአሜሪካዊው ጆን ሄይስ በ2 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ከ18 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡ ይህ የመጀመርያ ሪከርድ ከተመዘገበ ከ32 ዓመታት በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያዊ አትሌት የተመዘገበው በ1960 እኤአ ላይ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ባሸነፈው አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ በወቅቱ አበበ ያስመዘገበው የማራቶን ክብረወሰን 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃዎች ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላ አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ሪከርድን   በ1964 እኤአ ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ያስመዘገበ ሲሆን ጊዜውም 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃዎች ከ11 ሰኮንዶች ነበር፡፡ አበበ በቂላ  በኦሎምፒክ መድረክ ባስመዘገበባቸው  ሁለት የዓለም የማራቶን ሪከርዶች  ለአምስት አመታት ነግሶ ቆይቷል፡፡ ከአበበ ቢቂላ ሁለት የዓለም  ሪከርዶች 24 ዓመታት  በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊያዝ የበቃው  ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ ነበር፡፡ በላይነህ እኤአ በ1988 በተካሄደው ሮተርዳም ማራቶን ሲያሸንፍ ርቀቱን የሸፈነበት 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃዎች ከ50 ሴኮንዶች የሆነ ጊዜ አዲስ የዓለም ሪከርድ ነበር፡፡ በላይነህ ዴንሳሞ በዚህ ሪከርዱ ርቀቱን ከ2 ሰዓት 7 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያው አትሌት ከመሆኑም በላይ ክብረወሰኑን ለ10 ዓመታት ይዞ ቆይቷል። ከበላይነህ ዴንሳሞ በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ክብረወሰን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ከ19 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በ2007 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ26 ሰኮንዶች   በሆነ ጊዜ ባሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ አማካኝነት ነበር፡፡ በ2008 እኤአ ላይ ኃይሌ ይህን ክብረወሰኑን በድጋሚ ሲያሻሽል 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ነበር።  በዚሁ ሁለተኛ የማራቶን  ሪከርዱ ኃይሌ ገብረስላሴ ርቀቱን ከ2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያ አትሌት ሲሆን በክብረወሰኑ ባለቤትነት ለ5 ዓመታት ቆይቷል። በአጠቃላይ በወንዶች የዓለም ማራቶን  ታሪክ ሶስት የኢትዮጵያ አትሌቶች 5 ጊዜ ሪከርዶችን አሻሽለዋል። 3 ደቂቃዎች 49 ሰኮንዶች ከማራቶን የሪከርድ ሰዓት ላይ በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያ በሪከርዱ ባለቤትነት ለ19 ዓመታት የበላይ ሆና እንድትቆይም አድርገዋል፡፡ የዓለም ማራቶን ሪኮርድ በኬንያ ቁጥጥር ስር የገባው  በ2012 እኤአ ላይ በፓትሪክ ማካው ሲሆን በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ38 ሴኮንዶች በሆነ ጊዜ በማሸነፉ ነበር፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በድጋሚ የበርሊን ማራቶን ላይ ሌላው ኬንያዊ አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ሪከርዱን ተረከበው ፡፡ በመጨረሻም       በ2014 እኤአ በተካሄደው 41ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ የ31 ዓመቱ ኬንያዊ ዴኒስ ኪሜቶ ርቀቱን ከ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች በታች በመግባት ወቅታዊውን  የዓለም ሪከርድ ይዞታል፡፡
በሴቶች ምድብ የመጀመሪያው የዓለም ማራቶን ሪኮርድ የተመዘገበው በ3፡04፡22 በእንግሊዛዊቷ ቫዬሌት ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የሪኮርድ ሰዓቱ ለ38 ጊዜያት ተሻሽሏል። አሁን ያለው ክብረወሰን ከ13 ዓመት በፊት 2፡15፡23 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችው ፓውላራድ ክሊፍ ነበረች፡፡ ራድክሊፍ ለአሯሯጧ ከተከተላቸው የልምምድ ስትራቴጂ ብቻ ሳይሆን ከተጠቀመቻቸው የልምምድ መስርያ ቴክኖሎጂ አንፃር ነው። በተለይ ለልምምድ ከምትጠቀመው “ትሬድ ሚል ማሽን” ጋር ስሟ ይነሳል፡፡ ራድ ክሊፍ ልምምድ የምትሠራበት ይህ ማሽን 60ሺ ዶላር የሚያወጣ ነው፡፡ በዓለም የማራቶን ውድድሮች በሴቶች የሚመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች ብዙዎቹ ከፓውላ ራድክሊፍ ሪከርድ በ5 ደቂቃዎች የሚዘገዩ ናቸው። በውድድሩ ታሪክ በሴቶች ምድብ ከተመዘገቡ የዓለም የማራቶን ሪከርዶች  የኢትዮጵያ አትሌቶች የሉበትም። ሁለት የኬንያ አትሌቶች ግን ሪከርዱን ከራድክሊፍ በፊት ለሁለት ጊዜያት ክብረወሰኑን በማሻሻል ስማቸው ተጠቅሷል።  እነሱም በ1998 እና በ1999 እ.ኤ.አ ላይ በሮተርዳም እና በቺካጐ ማራቶኖች 2፡3047 እንዲሁም 2፡20፡43 በሆኑ ሰዓቶች ያስመዘገባቸው ቴግላ ላውሩፕ እንዲሁም በ2001 እ.ኤ.አ በቺካጐ ማራቶን 2፡18፡47 በሆነ ጊዜ  ካተሪን ንድሬባ ያስመዘገቧቸው ናቸው፡፡
ከ3 ሳምንታት በፊት በበርሊን ማራቶን በተሳትፎ ታሪኳ ለ3ኛ ጊዜ ያሸነፈቸው ኢትዮጵያዊቷ አበሩ ከበደ ያስመዘገበችው ሰዓት ከ2 ሰዓት ከ21 ደቂቃዎች ለመግባት የቻለችበትን ውድድር ለ4ኛ ጊዜ አድርጎላታል፡፡ በዚህ ብቃቷም አበሩ ከበደ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በያዘችው ፓውላ ራክሊፍ በ1 ውድድር ብቻ ነው የምትበለጠው፡፡ በአንፃሩ ከ2 ሰዓት 22 ደቂቃዎች በ5 ማራቶኖች ስለተሳካላት ከራድክሊፍ ጋር አበሩ ክብረወሰኑን ትጋራለች፡፡ አበሩ ከበደ ለራድክሊፍ የቀረበች ማራቶን ሯጭ ብትሆንም የእሷ ምኞት የዓለም ሪከርድ ማስመዝገብ ሳይሆን ወደፊት በምትሮጣቸው ማራቶኖች ከ2፡20 በታች መግባት ነው፡፡
ኢትዮጵያ እና ኬንያ  በውጤት ታሪኮች እና በምንግዜም  ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ  
በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኬንያና ኢትዮጵያን በማራቶን ሯጮቻቸው ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ማነፃፀር ይቻላል፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያ በወንዶች ምድብ 4 የወርቅ፣ 3 የነሐስ ሜዳልያዎች ስታስመዘግብ ኬንያ ደግሞ 2 የወርቅ፣ 3 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች አሏት፡፡ በሴቶች ምድብ በኦሎምፒክ መድረክ 1 የወርቅና 1 የነሐስ ሜዳልያ በኢትዮጵያ ሲመዘገብ ኬንያ ያገኘችው ደግሞ 2 የወርቅና 3 የብር ሜዳልያዎች ናቸው፡፡  በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ላይ ደግሞ በወንዶች 1 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች ኢትዮጵያ ስታስመዘግብ የኬንያ 4 የወርቅና 3 የብር ሜዳልያዎች ናቸው፡፡  በሴቶች ደግሞ በዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 1 ወርቅና 1 የነሐስ ሜዳልያ ሲኖራት ኬንያ 40 ወርቅ 3 የብርና 1 የነሐስ ሜዶልያዎች ሰብስባለች፡፡  
ከ43ኛው የበርሊን ማራቶን በኋላ በምንግዜም የማራቶን ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ላይ በወንዶች ምድብ ለውጦች ተፈጥረዋል፡፡ በዚህ የደረጃ ዝርዝር ከተመዘገቡት ማራቶኒስቶች 7 ኬንያውያን  ሲሆኑ  3 ደግሞ ኢትዮጵያውን ናቸው፡፡ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠው በ2014 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን ኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ ያስመዘገበው 2፡02፡57 የዓለም ማራቶን ሪከርድ ሲሆን የቀነኒሳ በቀለ ሰዓት 2፡03፡03 በሁለተኛ ደረጃ የተመዘገበ ነው፡፡  ኤሊውድ ኪፕቾጌ በ2016 የለንደን ማራቶን ሲያሸንፍ 2፡03፡05፤ ኢማኑዌል ሙታይ በ2014 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን በሁለተኛ ደረጃ ሲጨርስ 2፡03፡13፤ ዊልሰን ኪፕሳንግ በ2013 በበርሊን ማራቶን 2፡03፡23፤ ፓትሪክ ማኩ በ2011 በበርሊን ማራቶን 2፡03፡38 እስከ 5 ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ በ2008 በበርሊን ማራቶን ሲያሸንፍ 2፡03፡59 በ8ኛ ደረጃ እንዲሁም አየለ አብሽሮ በ2012 ዱባይ ማራቶን ሲያሸንፍ 2፡04፡23 10ኛ  ደረጃ ላይ ነው፡፡ በሴቶች ምድብ በምንግዜም የማራቶን ፈጣን ሰዓቶችደረጃ በ2፡15፡23 በሆነው የዓለም ሪከርድ ፓውላ ራድክሊፍ ቀዳሚ ስትሆን የኬንያዋ ማሪ ኪታኒ፤ የሌላዋ ኬንያዊት ካተሪን ንድሬባ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ደረጃ ሲከተሉ የኦሎምፒክሻምፒዮኗ  ቲኪ ገላና በ2፡18፡58 ሰዓቷ 4ኛ ናት፡፡
በማራቶን ውድድሮች  የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን የበላይነት ሌላው ዓለም የሚቀናቀነው አይደለም። በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ የተሰባሰበ አሃዛዊ መረጃ እንደሚያመለከትው ደግሞ በወንዶች ማራቶን ፈጣን ሰዓት ደረጃ እስከ 100ኛ ድረስ ከተመዘገቡት ከምስራቅ አፍሪካ ውጭ የሌሎች አገራት  ውክልና በ9 አትሌቶች ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ከ101 እስከ 200 ባለውም ደረጃ ቢሆን 14 አትሌቶች ብቻ ከጃፓን፤ ከብራዚል፤ ከደቡብ አፍሪካ ፤ ከአሜሪካ እና ከጣሊያን ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በዓለም ዙርያ ከሚገኙ 300 ፕሮፌሽናል የማራቶን ወንድ ሯጮች 246 ያህሉ ከምስራቅ አፍሪካ የፈለቁ ናቸው፡፡  
ባለፉት 15 ዓመታት በዓለም የማራቶን ውድድሮች መድረክ  የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ የበላይነት ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡ ከ5 ዓመታት ወዲህ ግን በተለይ የኬንያ ወንድ አትሌቶች ከኢትዮጵያውያኑ ከፍተኛ ብልጫ እያገኙ ናቸው። በአንፃሩ በማራቶን ከኬንያ አቻዎቻቸው በመፎካከር እየተሳካላቸው  የሚገኙት የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ሆነዋል። ትልልቅ ማራቶኖችና በማሸነፍ፤ በዓለም የማራቶን ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ሰንጠረዦች ውስጥ በመግባት በወንዶች ምድብ  ኬንያውያን እጅግ የተሻሉ ሲሆኑ በሴቶች ኢትዮጵያውያን የተሻሉ ናቸው፡፡ በተለይ በወንዶች ምድብ በማራቶን ውጤት የኬንያ አትሌቶች ከኢትዮጵያውያን ተቀናቃኞቻቸው ጋር ያላቸው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል፡፡
የመረጃ ምንጮቻችን
www.nytimes.com   , www.sub2hrs.com,  www.runnersworld.com/sub-2/, www.letsrun.com www.sportsscientists.com , www.all-athletics.com ,runningmagazine.ca, www.running.competitor.com,  www.spikes.iaaf.org

Read 3022 times