Saturday, 10 March 2012 10:24

የኩረጃ ኮሌጅ ይከፈትልን - የኩረጃ ክህሎት እንድንማር! “የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ያለ ኩረጃ ግቡን አይመታም!”

Written by  ኤሊያሰ
Rate this item
(0 votes)

ኢህአዴግ ከ20 ዓመት በኋላም “ነቄ” አላለም!

ኢቴቪ እርግጠኛ ነኝ ሰሞኑን ቢቢሲን ጠቅሶ የዘገበውን ዜና ሰምታችኋል፡፡ የባይዶዋውን Victory ማለቴ ነው፡፡ ጀግናው ሠራዊታችን በሶማሊያ ሲቀውጠው የነበረውን አልሸባብን ጠራርጐ በማስወጣት ለራሱ ድልን ለሶማሌያውያን ሰላምን አጐናፅፎአቸዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም ሶማሊያ ከአሸባሪዎች እየፀዳችና ወደ ሰላም ጐዳና እየተመመች ነው ብሏል - ኢቴቪ ቢቢሲን በእማኝነት ጠቅሶ፡፡ ዜናው መቼም የምስራች ያህል መሆኑን ከአልሸባብ   በቀር ማንም አይክደውም፡፡ ትንሽ ግራ ያጋባኝ አንድ ነገር ግን አለ፡፡ ምን መሰላችሁ? የመከላከያ ሠራዊታችን እዛው ባይዶዋ እያለ ኢቴቪ ለምን ቢቢሲን እንደጠቀሰ ነው፡፡

ኢቴቪ ራሱ ከባለቤቱ አፍ (From the horses mouth እንዲሉ) ቢያሰማን አይሻልም ነበር? ደግሞ እኮ እነ ቢቢሲ የአገራችንን መልካም ገጽታ የሚያበላሽ ዘገባ በማቅረብና የእነ “ሂዩማን ራይትስ ዎች” ተላላኪ በመሆን “ብላክ ሊስት” ውስጥ እንደገቡ ራሱ ኢቴቪ በቅርቡ ሹክ ብሎን ነበር! ወይስ ነቄ ብለው ለይቅርታ ቦርድ ደብዳቤ ፃፉ? የሠራዊታችንን ድል ከሰማሁ በኋላ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” የምትለዋ ምሳሌያዊ አባባል ደጋግማ ወደ አዕምሮዬ ተመላለሰች፡፡ ለምን መሰላችሁ … ሠራዊታችን በሶማሊያ ድል ሲቀናው ሁለት ዒላማ ነው የሚመታው፡፡ አንዱ ቀጥተኛ ከአሸናፊነቱ ሲሆን ሌላው እግር መንገዱን የውጊያ አቅሙንና ብቃቱን ለጠብ ጫሪ ጐረቤቶች (ካሉ?) እያሳየ መሆኑ ነው (አሳየው ላላየው አሉ!)

አያችሁ … ሠራዊቱ በየሰው አገር እየዘመተ ባሳየው የሰላም ማስከበር ተግባር ሲቪውን እያበለፀገም ነው፡፡ በዚያ ላይ ማንም ተነስቶ “የራስዋ አሮባት የሰው ታማስላለች” የሚለውን ተረት ሊተርትበት አይችልም (የራሱ አላረረበትማ!) እውነቴን እኮ ነው … የአገር ውስጥ ሰላምና ፀጥታችን እንደሆነ አልደፈረሰም (ሁሉም ፒስ ነው!) ዳር  ድንበራችንም አልተደፈረም! እናላችሁ … ሠራዊቱ በየአፍሪካ አገሩ የሚዘምተው ለአንድቬንቸር ምናምን ብሎ ሳይሆን “ያንተ በር ሲንኳኳ የእኔ በር ይንኳኳል” በሚለው መርህ መሰረት ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የአህጉሩን ሰላም በመጠበቅ የራስን ሰላም ማስፈን ብትሉትም ያስኬዳል፡፡ መከላከያ የአገር ውስጥ ስራውን አጠናቆ የሰው አገር ሰላም ሊያሰፍን ሲዘምት አንዳንድ የአገራችን የመንግስት መ/ቤቶች ግን እዚሁ ቁጭ ብለው የአገር ሃብት ሲያዘርፉ አያሳዝንም? ምነው ሲባሉ “የመንግስት ሌቦች፤ ኪራይ ሰብሳቢዎች ወዘተ ጉድ ሠሩን” ብለው ቁጭ! እኔ የምለው ግን መ/ቤቶቹ እዚሁ እያሉ ይሄን ያህል ካዘረፉን እንደ መከላከያ ብሩንዲና ሶማሊያ ቢዘምቱ ኖሮ ምን ይቀረን ነበር! ደግነቱ ግን እንኳን ሌላ አገር ሊዘምቱ እዚህም እምነት አጥተዋል (ከፀረ ሙስና ኮሚሽን በተገኘው መረጃ) አንዳንድ “ማር አይጥምሽ” ወገኖች ወደ ሶማሊያና ብሩንዲ የዘመተውን ሠራዊታችንን ሲያሾምሩ “ሠራዊታችን የተባበሩት መንግስታትን የሰላም አስከባሪ ሃይል ተቀላቀለ እንዴ?” ይላሉ አሉ፡፡ (አሹ አበጀሁ ማለት አሁን ነው!)    ወደ ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ወይም ሳምንታዊ ሃሜት ከማለፋችን በፊት አንድ የጠቅላላ ዕውቀት ጥያቄ ልጠይቃችሁ (ግን ሽልማት የለሽ ነው!) “አውራው የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ም/ቤት ምን ያህል አባላት አሉት?” እኔ የምለው … አውራ ስል ትንሽ ተደናገራችሁ አይደል? ለካስ  ለአውራም ፓርቲ አውራ አለው፡፡ እኔ እኮ እስከዛሬ ድረስ  በዓለም ላይ ብቸኛው አውራ ፓርቲ “ኢህአዴግ” ይመስለኝ ነበር (ቀላል ተሸወድኩ) አሁን ግን ሃቁን ተገንዝቤያለሁ የዘመኑ ግንባር ቀደም አውራ ፓርቲ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ?

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ እኮ ነው!! ቆይ ግን ኢህአዴግ ለምንድነው ይህቺን ሁነኛ መረጃ እስካሁን የደበቀን፡፡ ለነገሩ አሁንም ቢሆን እኮ መረጃውን ይፋ ያደረገው ራሱ ኢህአዴግ ነው (የይቅርታ ኢቴቪ ለማለት ነው!)

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ሰሞኑን ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚያካሂደውን የም/ቤት ስብሰባ ሙሉ ዘገባ ከእነቪዲዮ ምስሉ ስፖንሰር አድርጐ በኢቴቪ የለቀቀልን የአገር ውስጥ አውራ ፓርቲያችን ኢህአዴግ ነበር (ተሳሳትኩ እንዴ?)

እኔ ደሞ ገና ዘገባውን ስሰማ የህወሃት ም/ቤት ስብሰባ መስሎኝ ጆሮዬን ቀስሬ ነበር፡፡ በኋላ ግን የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ መሆኑን ስረዳ “አወይ መመሳሰል!” አልኩኝና ቁዘማ ውስጥ ገባሁ፡፡ ይገርማችኋል … እዚያም ቻይና የዋጋ ግሽበት፤ የገጠር ልማት፣ ግብርና መር ወዘተ የሚሉ ናቸው የፓርቲው የውይይት አጀንዳዎች፡፡

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የም/ቤት አባላት ግን የአንድ መለስተኛ ቀዬ ህዝብ ነው የሚያህሉት (ስንት መሰሏችሁ? አናቷ ላይ 3ሺ!! (የቻይና ህዝብ ብዛት ከግንዛቤ ውስጥ ይግባ) በዋጋ ግሽበት ግን ፈፅሞ አንደራረስም - እኛና ቻይና!! ዘገባው እንደሚለው ቻይና 5 በመቶ የሆነውን የግሸበት መጠን በቀጣዩ ዓመት ወደ 4 በመቶ ለማውረድ ዝታለች፡፡ የእኛማ የግሽበት መጠን ተከድኖ ይብሰል!! እንደ ኢኮኖሚ ዕድገታችን ባለሁለት ዲጂት እኮ ነው፡፡ እኔን ብግን የሚያደርገኝ ግን እርማችንን ዓለምን ያስደመመ የኢኮኖሚ ዕድገት ብናስመዘግብ ግሽበቱም ከዕድገቱ ጋር እሽቅድድም ይዞ ቁጭ ማለቱ ነው! (ምቀኛ!)

እኔ የምለው ግን … ዓለም በባለ ሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገታችን “ጉድ!” እያለ ሲደነቅብን እኛ ምነው አልበርድ አልሞቅ አለን? (የብዥታ ችግር ይሆን እንዴ?) ሌላ አገር እኮ ቢሆን “ፒፕሉ” ይቀውጠው ነበር! (በሰላማዊ ሰልፍ!) እኛ ግን የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከዋጋ ግሽበቱ ጋር አንድ ላይ ውጠን ጭጭ አልነ!! (በነገራችሁ ላይ የፖለቲካ ሰላማዊ ሰልፍ እንጂ የኢኮኖሚ ሰላማዊ ሰልፍ እኮ ችግር የለውም!)

ከሁሉም ግራ የገባኝ ግን ምን መሰላችሁ? እኛስ (ህዝቡን ማለቴ ነው!) በቫቱም፣  በታክሱም፣ በግሽበቱም፣ በሊዙም፣ በፀረ-ሽብር ህጉም፣ በምህዳሩም ፈዝዘን ደንዝዘን ሊሆን ይችላል ሰልፍ ያልወጣነው፡፡ አዲሱን የሊዝ አዋጅ ለህብረተሰቡ ማስረዳት ተስኖአቸው “ብዥታ” የፈጠሩት የኢህአዴግ ካድሬዎች ግን የማንን ጐፈሬ ሲያበጥሩ ነው የድጋፍ ሰልፍ እንኳን ያላደራጁት? (ኢህአዴግ ግምገማ ተወ እንዴ?) እውነቴን ነው… ኢህአዴግ ካድሬዎቹን በፍጥነት “ካልፐወዘ” እንኳን እንደ ምኞቱ 20 እና 30 ዓመት ስልጣን ላይ ሊቀመጥ ቀርቶ በቀጣዩ ምርጫም ያሰጋዋል! (ምርጫ ያለ ካድሬማ አይታሰብም!) በነገራችን ላይ እቺ 1ለ5 የመደራጀት ስትራቴጂ እኮ ሰላማዊ ሰልፍ ለማስተባበር ሁነኛ ብልሃት ናት! (ምርጫ ለማሸነፍም እንዲሁ!)

እናንተ … የድሮ ጐረቤታችን የኤርትራ አምባገነን መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ እንዴት ደፋር ናቸው ባካችሁ!! አንዱ ሥራ የፈታ ምዕራባዊ ጋዜጠኛ ሳይቸግረው አስመራ ድረስ ባህር ተሻግሮ ሄዶ “ለምንድነው በኤርትራ ምርጫ የማይካሄደው?” ሲል የጋዜጠኛ ጥያቄ አቀረበላቸው አሉ (በእሱ ቤት ማፋጠጡ ነው!) ወዲ አፈወርቂ ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ምን ምርጫ ምርጫ ትላለህ … የኢትዮጵያ ዓይነት ምርጫ እኮ በዓመት አራቴ ላካሂድልህ እችላለሁ!” አሉትና ግራ አጋብተው ወደ አገሩ ሸኙት፡፡ እሱስ የራሱ ጉዳይ! (ወደሽ ከገባሽ ቢያቅፉሽም አይከፋሽ የሚል ተረት አለ እንዴ?) ለምንድነው እኛን ግን የሚያሰድበን? (ያውም “እንከን የለሽ ምርጫ” እያካሄድን!)

እውነቴን ነው የምላችሁ … በህልቆ መሳፍርት ዘመቻዎች ባንጠመድ ኖሮ ወዲ አፈወርቅን የጥንት ፍሬንድ ስለሆኑ ብቻ አንምራቸውም ነበር - በስም ማጥፋት ወንጀል ከስሰናቸው ዓለማቀፍ ፍ/ቤት እንገትራቸው ነበር፡፡ ግዴለም ከዘመቻ በኋላ ይደርሳል! እንግዲህ ዘመቻዎቹ በጊዜ ካለቁልን ነው! (ሶማሊያን መልሶ የማረጋጋት ዘመቻ፣ የህዳሴ ግድብ ዘመቻ፣ ድህነትን ተረት የማድረግ ዘመቻ፣ የአገር ገጽ ግንባታ ዘመቻ፣ የመንግስት ሌቦችን የመዋጋት ዘመቻ፣ የዜጐች ቻርተርን ተግባራዊ የማድረግ ዘመቻ፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ዘመቻ፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት የመግባት ዘመቻ፣ ተቃዋሚዎችን እንዳያንሰራሩ የማድረግ ዘመቻ ወዘተ!!) ከፊታችን የተደቀኑብንን የዘመቻ ዓይነቶች ስንመለከት ህይወታችን ሁሉ በዘመቻ የተከበበ ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን የድህነት ምርኮኛ ከመሆን የዘመቻ ምርኮኛ መሆን ይሻላል፡፡ አንዴ ዘመቻዎቹን በዘመቻ እናጠናቅ እንጂ ዘመቻን ደሞ በዘመቻ እናጠፋዋለን!! (ደግሞስ ባይጠፋስ!) እኔ የምለው… ስለህዳሴው ግድብ ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄና አስተያየት አዘጋጃችሁ እንዴ? (ኢቴቪ ያለውን ማለቴ ነው) እኔ ግን አስቤ አስቤ ጥያቄም አስተያየትም ሊመጣልኝ አልቻለም (በግድቡ ዙሪያ) ለነገሩ ጥያቄም አስተያየትም እኮ አያስፈልግም፡፡ ግድቡ የሚፈልገው 85 ቢ. የኢትዮጵያ ብር ብቻ ነው (ፔሬድ!)

እንግዲህ ኢቴቪ ሌሎች ጥያቄዎቻችንን ለጠ/ሚኒስትሩ ለማድረስ ሌላ መድረክ እስኪያመቻች ድረስ የማያስጠብቅ ሁለት ጥያቄዎች ስላሉኝ በነፃው ፕሬስ (“በሬ ወለደ” ነው ያሉት?) ለማቅረብ ተገድጄአለሁ፡፡ መቼም ፕራይም ሚኒስትሩ በኢቴቪ ካልሆነ የዜጐችን ጥያቄ አልሰማም አይሉኝም (ጋዜጠኛ ዜጋ ነው አይደል?)

ክቡር ጠ/ሚኒስትር፡- ሌሎች አገራት የኑሮ ውድነትን እንዴት እንደሚቋቋሙት እባክዎ ከነተመክሮአቸው ይንገሩን (ፀናብና!!)

ከውጭ ተኮርጀው ዓላማቸውን የሳቱ እንደ ቢፒአር ዓይነት የከሸፉ ሙከራዎች ያደረሱት የገንዘብ ኪሳራ ምን ያህል ይሆናል? (ጉዳችንን ሰምተን ጉድ እንበል ብዬ ነው)

በነገራችሁ ላይ እኔ በትንሹም በትልቁም ጠ/ሚኒስትሩን ማስቸገር አልወድም ነበር፡፡ ክፋቱ ግን ጥያቄዎቼን የሚመልሱ ጥይት ጥይት የኢህአዴግ ካድሬዎች እንደ ዳይኖሰሮች ከምድረ ገፅ እየጠፉ ነው!! በጥናት አልተረጋገጠም እንጂ ኢህአዴግን “የካድሬ ኢንፍሌሽን” (የካድሬ ግሽበት) አጥቅቶታል ሲባልም ሰምቼአለሁ (አይቼአለሁ አልወጣኝም!)

አይገርምም ግን ግጥምጥሞሹ! እኛ የሥልጣን ባለቤቶቹ (የጦቢያ ህዝቦችን ማለቴ ነው) በኑሮ ውድነት ክፉኛ ስንጠቃ፣ እኛን ለማገልገል ሥልጣን የተረከበን ባለ አደራ ፓርቲው (ኢህአዴግን ማለቴ ነው) በካድሬዎች ግሽበት ክፉኛ ተጠቅቷል!!

ይኼውላችሁ … ለአገሪቱ ዋና ዋና ችግሮች ዋና ምክንያቱንና መፍትሔውን (በስንት ዳበሳ ያገኘሁትን) በምስጢር ኪስ ውስጥ ይዤ የአገሪቱን የስልጣን መንበር ወደተቆናጠጠው አውራ ፓርቲ ጽ/ቤት ጐራ ብዬ ነበር - ሰሞኑን፡፡ የኢህአዴግ ጽ/ቤት የጥበቃ ሠራተኞች ግን “መፍትሔ አንፈልግም!” ብለው ከበር መለሱኝ (ከበር መልስ ይጋብዙኛል ስል) ስለዚህ ሳልጨምር ሳልቀንስ መፍትሔ ያልኩትን ለእናንተ ልነግራችሁ ወስኛለሁ (ያውም እንደወረደ) ያኔ “ስማርቱ ኢህአዴግ” መፍትሔዋን ቀብ አድርጐ እንደራሱ መፍትሔ ያቀርበዋል ወይም ይጠቀምበታል፡፡ (እኔስ ዓላማዬ ምን ሆነና)

11ኛው ሰዓት ላይ እየደረስን ስለሆነ በቀጥታ ወደ ጉዳያችን፡፡ … አያችሁ ለግሽበቱ በሉት ለኑሮ ውድነቱ፣ ለትራንስፖርት ችግሩ በሉት ለመልካም አስተዳደር እጦቱ፣ ለድህነቱ በሉት ለፍትህ ማጣቱ፤ ለመንግስት ሌቦች መበራከት በሉት ለፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ወዘተ … ለችግሮቻችን ሁሉ ሰበቡ የአቅም ማነስ ችግር እንደሆነ ደርሼበታለሁ፡፡ የአቅም ማነስ ስላችሁ ደግሞ የፈጠራ እንዳትሉኝና በሳቅ እንዳልሞትባችሁ፡፡ ይኼውላችሁ እኛ በፈጠራ ችግራችንን ፈትተን ስለማናውቅ ለጊዜው እንርሳው፡፡ የአቅም ማነሱ ምን ላይ መሰላችሁ? ኩረጃ ላይ ነው!! አሳዛኝ ቢሆንም የትም የማናመልጠው ሐቅ ነው፡፡ ግን ጭርሱኑ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ ተስፋማ በደንብ አለን! (ማነው “ተስፋ እርቆ የተሰቀለ ዳቦ ነው” ያለው?)

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተስማሙበት አንድ ብቸኛ ጉዳይ ምን መሰላችሁ? “ኩረጃ” ነው፡፡ እስከዛሬ በአንዲት ጉዳይ እንኳን ተስማምተው የማያውቁት ሁለቱ ባላንጣዎች የኩረጃ ጊዜ ተስማምተው ቁጭ አሉ፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ … ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ ሲናገሩ “በዲሞክራሲ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት መኮረጅ አያሳፍርም” ብለው ነበር፡፡ (ሲፎግሩን በሆነ!) በፓርላማ የመድረክ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉስ? እሳቸውም ከፓርላማ ውጭ በሰጡት ቃለ ምልልስ “መኮረጅ አንፈራም፤ አሪፍ ከሆነ ከኢህአዴግም እንኮርጃለን” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ መሪዎቻችንና ባለከባድ ሚዛን ፖለቲከኞቻችን እንዲህ የኩረጃን ነገር አብዝተው እያበረታቱ ለጉዳዩ ትኩረት መንፈግ ራስን በራስ ማጥፋት ነው የሚሆነው፡፡

ሆኖም ግን ከት/ቤት ጀምሮ ኩረጃን የማያበረታታ ባህል ውስጥ በማደጋችን የቱንም ያህል ኩረጃን የማስረፅ ርብርቦሽ ቢያደርጉም እስካሁን ጥረቱ ፍሬ አላፈራም፡፡ አንድ ጉደኛ መፈክር ብልጭ አለልኝ “የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ያለ ኩረጃ ግቡን አይመታም” እኔ የምለው የኢህአዴግ ደጋፊ ባለሃብቶች ፎረም ምነው ድምፃቸው ጠፋ? (ይሄን መፈክር በትልቅ ቢልቦርድ እንዲያሰሩት ፈልጌ እኮ ነው!) ወደ ቁም ነገሩ እንመለስ - ኩረጃ ትኩረት ተነፍጐታል ወዳልነው! ከምዕራብ አገራት ኮረጅነው ያልነው (ቃል በቃል የቀዳነው ማለቴ ነው) መሠረታዊ የአሰራር ሂደት BPR ከረዥም ዓመት በኋላ ዓላማውን ይሁን ኢላማውን ስቷል ተብሎ እንደሰባራ ድስት የተወረወረው ለምን መሰላችሁ? ኩረጃ ትኩረት ስለተነፈገው እኮ ነው፡፡ እኔ የምለው “ውሃ ማቆርም”   ኢላማውን ስቶ ነው አይደል ከጨዋታ ውጭ የሆነው? እስካሁን ከኮረጅናቸው ነገሮች ሁሉ በአጭሩ በመቀጨት የዋጋ ተመኑን የሚያህል አልተገኘም አሉ፡፡ በ3 ወር የጨቅላ ዕድሜው እኮ ነው “ዳይ!” የተባለው፡፡ ግን እኮ የተኮረጁ ነገሮች ሁሉ በተፈጠሩበት አገር ወርቅ ወርቅ የሆነ ውጤት አስመዝግበዋል ነው የሚባለው (ምንጮች እንደሚሉት)  ስለዚህ ችግሩ ያለው ከተኮረጀው ነገር ሳይሆን ከአኮራረጁ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር “ጐበዝ ኮራጅ” እንኳን መሆን አቅቶናል ማለት ነው (እድሜ ለኢህአዴግ!)  እንዴት የተባለ እንደሆነ ደሞ … መልሱ በቂ የኩረጃ ክህሎት ሳያስታጥቀን ኮርጁ ስላለን የሚል ነው፡፡ አያችሁ 20 ዓመት ሙሉ ከየአገሩ ስንኮርጅ የነበረው በጨበጣ ነበር ማለት ነው፡፡ እናም የፈጠርነው ሳይሆን የኮረጅነው ነገር ሁሉ ውሎ አድሮ በአፍጢሙ እየተደፋ መከራችንን አበላን፡፡ ለዚህ ቁልፍ ችግራችን ያገኘሁት ቁልፍ መፍትሔ ምን መሰላችሁ? ኩረጃን በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ደረጃ በአፋጣኝ ከፍቶ የኩረጃ ክህሎት መስጠት ነው፡፡ የኩረጃ ሥልጠናው የሚሰጠው ግን በጨበጣና በልምድ ሳይሆን በሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ነው ይላል - የመፍትሄ ሃሳቤ!!

ከዛስ? ከዛማ የኩረጃ ሳይንቲስቶች፤ የኩረጃ ፖለቲከኞች፣ የኩረጃ አብዮተኞች፣ የኩረጃ ፓርቲዎች፣ የኩረጃ ምርጫዎች፣ የኩረጃ ዳኞች፣ የኩረጃ የፍትህ ስርዓቶች፣ የኩረጃ ዲሞክራቶች፣ በጥራትና በብዛት ማፍራት! (ከተቻለ በፋብሪካም ማምረት!) በውጤቱም ታላቅ ስመ ጥር የኩረጃ አገር መፍጠር!

ልብ አድርጉ! ኩረጃን ለአገራችን በማስተዋወቅና ዕውቅና በመስጠት ረገድ ቀዳሚው ፓርቲ ኢህአዴግ ሲሆን መድረክ ደግሞ የሁለተኝነት ቦታውን ተቆናጦታል - ግንባር ቀደም የኩረጃ አቀንቃኝ በመሆን!! እንግዲህ … ኩረጃ ኮሌጅ በመክፈት የሚገኘውን ትሩፋት ስደረድርላችሁ በስሜትና በጉጉት ተጥለልቃችሁ፣ ዛሬውን የማሰልጠኛ ተቋሙ እንዲከፈት ብላችሁ ኢህአዴግን እንዳትወጥሩት … አደራ! አያችሁ የኩረጃ ማሰልጠኛ ካሪኩለሙ የሚቀዳው (የሚኮረጀው) በኩረጃ የዳበረ ልምድና ተመክሮ ካላቸው አገራት ስለሆነ ትንሽ ፋታና ጥሞና ይፈልጋል፡፡

አሁንማ ነቄ ነን! 20 ዓመት የተሸወድነው ይበቃናል፡፡ እነ ውጤት ተኮር፣ እነ ነጭ ካፒታሊዝም፣ እነ መዋቅራዊ ለውጥ፣ እነ ቢፒ አር ወዘተ በኩረጃ የአቅም ማነስ ከ10 እና አንዳንዴም 20 ዓመት በኋላ ዒላማቸውን እየሳቱ ተጥለዋል፡፡ በዚህ ብንንገበገብም የኩረጃ ኮሌጅ ከተከፈተ በኋላ የሚከሽፉ ኩረጃዎች ስለማይኖሩ በዚህ ደሞ እንፅናናለን፡፡

አንድ የሚገርመኝ ነገር ግን አለ - ኩረጃዎችን በተመለከተ፡፡ ምን መሰላችሁ? ቢፒአርና ዘመዶቹ እየከሸፉ ሲወረወሩ በተመሳሳይ ሁኔታ ከውጭ አገር ተኮረጁ (ተቀዱ) የተባሉት ለምሳሌ የፀረ ሽብር ህጉ፣ የፓርላማ የሥነምግባር ደንቡ፣ የፕሬስ ህጉ፣ የመያዶች አዋጁ … ወዘተ አንዳቸውም ኢላማቸውን ሳይስቱ እስካሁን ዘልቀዋል (ያውም ተቃውሞና የነቀፋ ውርጅብኝ እየወረደባቸው!)  በነገራችሁ ላይ የኩረጃ ኮሌጁ ተከፍቶ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች እስኪመረቁ ድረስ ምንም ዓይነት አዋጅ፣ መመሪያ፣ ስትራቴጂ ወዘተ ከየትኛውም አገር መቅዳት ወይም መኮረጅ አይፈቀድም (ከቻይናም ቢሆን!)

በመጨረሻ ኩረጃ የተጣፈችልን እጣ ፈንታችን መሆኑዋ ከታወቀ ዘንዳ የኩረጃ አማልዕክት ከኛ ጋር እንዲሆኑ ተመኝተን ብንለያይስ!! ሠናይ የኩረጃ ዘመን!!

 

 

Read 4376 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 10:29