Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Sunday, 09 October 2016 00:00

‘የማይነካ አጥር’ መነቅነቅ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቀደም መሀል ከተማ አካባቢ የሆነ ነው። ሴትዮዋ የአእምሮ በሽተኛ ነች፣ አንድ ዓመት የማይሞላው ልጅ ታቅፋለች፡፡ እናም ይህንንም፣ ያንንም ትጮሀለች። የተወሰኑ ‘ደንብ አስከባሪዎች’ ከበዋታል። ይሄኔ ከመሃላቸው አንዱ በቃሪያ ጥፊ ያጮላታል፡፡ በአካባቢው  የነበረው ሰው ያጉረመርማል፡፡ የተወሰኑ ሰዎችም “ለምን ትመታታለህ…” ምናምን አይነት  ነገር ይሉታል፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ያ ‘ደንብ አስከባሪ’ የተማታው ምናልባትም ቁጣ እንደማይደርስበት ስለሚያውቅ ይሆናል፡፡ “የአእምሮ በሽተኛና የምትሠራውን የማታውቅን ሴት ስለተማታህ አስተዳደራዊ እርምጃ…” ምናምን የሚል ተቆጪ ስለሌለው ሊሆን ይችላል፡፡
የምር ግን… የሚያሳዝን ነው፡፡ አንዳንዴ… “እነዚሀ ሰዎች ሲሰማሩ የሚሰጣቸው የሥራ መመሪያ ምንድነው?” ያሰኛል፡፡ ተቆጪ የሌለው ‘እንደ ልቡ’ ሲበዛ አሪፍ አይደለም፡፡
አለቅየው ‘እንደ ልቡ’፣ ‘የማይነካ አጥር እስካልነቀነቀ’ ድረስ ያለ ሀሳብ ለሽ እንደሚል ያውቃላ!
እግረ መንገዴን… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ ደንብ አስከባሪዎች፣ የጸጥታ ሰዎች የሚይዙት ‘ዱላ’… አለ አይደል… እስከሚገባን መያዣ እጀታ አለው፡፡ እጀታውን ዘቅዝቀው በሌላኛው ጫፍ መያዝ ምን የሚሉት ‘ደንብ’ ነው! የምር እኮ… ምንም በሌለበት አውላላ ሜዳ፣ የአንዳንዶቹ ‘ዱላ’ አያያዝ … “እንደው ወገቡን የምሰብረው አንድ ሰው ልጣ!” አይነት ይመስላል፡፡ እኔ የምለው… “ዱላውን ስላልተጠቀምክበት ደብዳቤው በደረስህ በሁለት ቀናት ውስጥ ለንብረት ክፍል መልሰህ እንድታስረክብ...” ምናምን የሚባል ነገር አለ እንዴ!
እናማ… ሀሳባቸውን ጥለው እንደፈለጉ የሚሆኑ ሰዎች ‘የማይነካ አጥር እስካልነቀነቁ’ ድረስ የሚናገራቸው እንደሌለ ስለሚያውቁ ነው፡፡
ደግሞላችሁ…ልብ ብላችሁ ከሆነ ከተማችን ውስጥ ብዙ ጊዜ የተከለከለ ቦታ ቆመው የምታዩዋቸው መኪኖች ታርጋቸው ‘የተለየ’ ነው፡ እና አሽከርካሪዎቹ የማይሆን አጥር ‘እስካልነቀነቁ’ ድረስ በሌላ፣ በሌላው ተቆጪ የሌላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት ያወራናት ነገር ትዝ አለችኝማ…ከወራት በፊት አንዱ ‘ጉዳዩ የሚመለከተው’ (እንበል እንጂ!) በተከለከለ ቦታ ላይ የቆመ ሸላይ መኪና ታርጋ ሲፈታ ምን ብሎ ነበር መሰላችሁ… “ብቻ የባለስልጣን እንዳይሆን!”
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ደግሞ የዲስኩርና የቃለ መጠይቅ ‘ጉልበት’ አለላችሁ። እሱዬው ወይ ወፍራም ወንበር አለው፣ ወይ ወፍራም ግድግዳ አለው  (ቂ…ቂ…ቂ…) እንደፈለገው ግለሰብም፣ ቡድንም፣ ‘ቡድን’ የመሰለውንም በቀጥታና በተዘዋዋሪ በምላሱ ‘ከመሬት ጋር ይደባልቃል፡፡ እኛም ‘ወይ ነዶ’ እያልን… ጨጓሯችን የአዲስ አባባን የክረምት መንገዶች ሲመስል በየዘመድ አዝማዱ እየደወልን…
“ዳግሞ አረቄ ካለህ ሰው ልላክ?”    
“ጨጓራዬን ልሞትልሽ ነው፣ ትናንት ቤትሽ ተልባ አይቻለሁ፣ አይደል!”
“ስማ…የሆነ አንታይአሲድ ምናምን ነገር ታገኝልኛለህ? ጨጓራዬን የስታዲየም መረብ ሊያደርጉት ነው እኮ!” እንላለን፡፡ አቅማችን እስከዛችው ድረስ ነዋ!
እነሱ ‘እንደልባቸው የሚሆኑት …አለ አይደል… ‘የማይነካ አጥር እስካልነቀነቁ’ ምንም እንደማይሆኑ ስለሚያውቁ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንዳንድ ንግግሮች  ወይም መግለጫዎች ስሰማ ወይም ሳነብ… አለ አይደል… “ይሄ ነገር በ1970ዎቹ መጨረሻ የሆነ ሰው ሲለው አልነበረም እንዴ!” ትላላችሁ፡፡ ልክ ነዋ…ግፋ ቢል… “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች…” የሚለው “አንዳንድ ዕድገታችን የማይዋጥላቸው…” ምናምን በሚል ቢለወጥ ነው፡፡ እናማ… ብዙ ጊዜ ነገርዬዎች ከተወሰኑ ‘ቃላት ለውጥ’ በቀር ‘እየተመሳሰሉብን’ ተቸግረናል!
ገና ከበር ስትገቡ ግቢው በባንዲራ ‘አጊጧል።’ ያኔም እንዲሁ ‘ያጌጥ’ ነበር፡፡ “ይሄ ነገር መሥሪያ ቤት ነው ወይስ የባንዲራ ማምረቻ ፋብሪካ!” የሚል ሰው አይፈረድበትም፡፡ የግቢው ዙሪያ በመፈክር ተሞልቷል፡፡ ‘ያኔም’ እንዲሁ በመፈክር ይሞላ ነበር። ከስብሰባው ‘ርእሰ ጉዳይ’ ይልቅ የባንዲራውና የመፈክሩ ብዛት ‘ኃላፊነት መወጣትን’ ማስመስከሪያ ይመስላል፡፡ ‘ያኔም’ እንዲሁ ነበርና ለምደነዋል፡፡
አዳራሹ ውስጥ ሲገባ የተሰብሳቢዎቹ ጠረዼዛ ከወረቀትና ዶሴ ይልቅ ‘በአበባ’ ተሞልቷል… ልክ የአበባ ኤግዚቢሽን ይመስል፡፡ ‘ያኔም’ እንዲሁ ጠረጴዛዎች ‘በአበባ’ ይሞሉ ነበር፡፡ የዛሬው የስብሰባ አዳራሽ ግድግዳዎች እንደ ‘ያኔዎቹ’ ግድግዳዎች በተጨማሪ መፈክሮች ተሞልተዋል፡፡
ደግሞላችሁ… ሰብሳቢውና ጎንና ጎኑ ያሉት… አለ አይደል… የሆነ ትምህርት ቤት ረባሽ ተማሪዎችን የሚያነጋግሩ ይመስል ተኮሳትረዋል፡፡ ‘ያኔም’ እንዲሁ ሰብሳቢዎችና ጎንና ጎን ያሉት እንደተኮሳተሩብን ነበር፡፡
እናላችሁ…ዛሬም፣ ትናንትም ሰብሳቢዎቻችን ልክ ልካችንን የሚነግሩን…‘የማይሆን አጥር እስካልነቀነቁ’ ምንም እንደማይሆኑ ስለሚያውቁ ነው! የምር ግን…አለ አይደል… ‘ታሪክ ሆነዋል’ ያልናቸው ነገሮች ‘በተከታዩ ገጽ ይዞራል’ …አይነት የቀጠሉ ሲመስሉን አሪፍ አይደለም፡፡ እናማ… ባይሆን ልክ ልካችንን ‘መጠጣታችን’ ካልቀረ ‘ኤክስፐርቶች’ ሰብሰብ ብለው… ‘ከፊተኛው ገጽ የቀጠለ’ የማይመስሉ አዳዲስ ቃላት ይፍጠሩልንማ። ደግሞ የ‘ኤክስፐርቶች’ ችግር የለብንም አይደል! የአገሪቱ ፕሮፌሰርና ረዳት ፕሮፌሰር ብዛት እንደሁ ከአርሴ ቲፎዞዎች ብዛት ሊስተካከል ምንም የቀረው አይመስልም፡፡  
እናላችሁ… ‘የማይነካ አጥር እስካልነቀነቅን’ ድረስ ምንም የማንሆንና ምንም የማንሆን የሚመስለን ሰዎች ይህን ምስኪን ህዝብ ግራ እያጋባነው ነው፡፡
ስሙኝማ…ችግሩ ምን መሰላችሁ-----ይቺ ጉልበተኝነቷ ወርዳ፣ ወርዳ ታች ስትደርስ፣ መንገድ ላይ የተነጠፈ ዕቃ በስርአት ከማስነሳት በእርግጫ የሚበትን ደንብ ማስከበር ይፈጠራል፡፡
እግረ መንገዴን…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… አንድ ሰው መለዮ ከለበሰ ሥራ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ሥራ ላይ ካልሆነ እንደ ሁላችን አይደል የሚለብሰው! እናማ የደንብ ልብሱን ለብሶ በ‘ሥራ ላይ’ ሁለት እጆቹን ኪስ ከቶ መሄድ ግራ አይገባም!
ደግሞላችሁ… ‘እንደልቡ’ የሆነ አለቃ ሞልቶ የለ… የቃል ማስጠንቀቂያ፣ የመጀመሪያና የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ምናምን ነገሮች ሳይሰጥ… ምስኪኑ ሠራተኛ ጧት ሥራ ሲገባ የቢሮ በሩ ተከርችሞ እንዲጠብቀው ያደርጋል፡፡ ምስኪኑም በደብዳቤ ወይም ግድግዳ ላይ በተለጠፈ ማስታወቂያ ሳይሆን የቢሮው በር በመከርቸሙ ብቻ  መባረሩን ያውቃል። እኔ የምለው… የአሠሪና ሠራተኛ ህጉስ! መብት ምናምን የሚባሉት ነገሮችስ! የህብረት ስምምነቱስ!  የቅጥርና ቅጥር የማቋረጥ ሂደቶቹስ! ለነገሩ እነኚህን ሁሉ ለመጠየቅ፣ ለምስኪኑ የሚወግን ‘ጠያቂ’ ሲኖር አይደል!
ሰውየው ከበርካታ ዓመታት በሁዋላ ትምህርቱን ካቆመበት ለመቀጠል ይፈልግና አንድ ትምህርት ቤት ያመለክታል፡፡ ሰዎቹም መጨረሻ ከተማረበት ትምህርት ቤት ‘ትራንስክሪፕት’ እንዲያመጣ ይነግሩታል፡፡ ይሄኔ ድሮ የሚያውቀውን ሰው ያገኝና ከድሮው ትምህርት ቤቱ ትራንስክሪፕቱን ለመውሰድ እንደሚሄድ ይነግረዋል፡፡ ሰውየው ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“እንኳን ትራንስክሪፕትህ ሊገኝ፣ ትምህርት ቤቱም ፈርሷል፡፡”
ማፍረስ ቀላል የሆነባት አገር! አጥርና ቤት ብቻ ሳይሆን ባህሪይና ሞራል እየፈራረሰ ያለባት አገር፡፡ መንደር ፈርሶ ትርምስምሱ ከወጣ በኋላ፣ በስህተት ነው የፈረሰው የሚባልባት አገር!
ይኸው ስንት ነገር ‘ፈርሶ፣ ፈርሶ’ መጨበጫው እየጠፋ አይደል!
‘የማይነካ አጥር’ እስካልነቀነቁ ‘እንደ ልብ’ ቢኮን የማያሰጋበት ዘመን ሆኗላ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5108 times