Sunday, 09 October 2016 00:00

ኃይሌ ለ“ዓለማቀፍ የእድሜ ዘመን ስኬት ሽልማት” ተመርጧል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   አለማቀፉ የማራቶንና የረጅም ርቀት ውድድሮች ማህበር፣ለአትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ የኤአይኤምኤስን የእድሜ ዘመን ስኬት ሽልማት በመጪው ህዳር ወር መጀመሪያ ሊያበረክት መወሰኑን አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ፓኮ ቦራኦ፤ኃይሌ ለአለማችን ማራቶን ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት በመቻላቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸው፣ የአትሌቱ ስኬት ከአፍሪካ አልፎ በመላው አለም ለሚገኙ በርካቶች የመነቃቃት ምንጭ መሆኑንና የዓላማ ጽናቱም ለተምሳሌትነት የሚበቃ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ ባወጣው መግለጫ፤በመጪው ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ በግሪክ አቴንስ በሚካሄድ ሥነስርዓት ላይ ለኃይሌ የእድሜ ዘመን ሽልማቱን እንደሚያበረክት አስታውቋል፡፡ ኃይሌ ገብረ ስላሴ የማህበሩን አለማቀፍ ሽልማት ሲቀበል ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ያስታወሰው መግለጫው፣ አትሌቱ እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2008 ባሉት ዓመታት የማህበሩን የዓለማችን ምርጥ አትሌት ሽልማት፣ለሶስት ተከታታይ ጊዚያት ማግኘቱንም ገልጧል፡፡ ኃይሌ ለማህበሩ ሽልማት በመመረጡ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰማው ገልጾ፣ በአቴንስ በሚካሄደው ስነስርዓት ላይ ተገኝቶ ሽልማቱን እንደሚቀበልና በማራቶን ማህበረሰብ ውስጥ ካሉ ጓደኞቹ ጋር አስደሳች ጊዜ እንደሚያሳልፍ ተናግሯል፡፡
አለማቀፉ የማራቶንና የረጅም ርቀት ውድድሮች ማህበር፣የበርሊን ማራቶንን ጨምሮ በአለማችን 110 አገራትና አካባቢዎች የሚካሄዱ እጅግ ዝነኛና ግምባር ቀደም አለማቀፍ የሩጫ ውድድሮችን በአባልነት መያዙ ታውቋል፡፡

Read 1359 times