Sunday, 09 October 2016 00:00

ተቃውሞ - ግጭት - እልቂት- ውድመት - ቀውስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(50 votes)

የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ነው
- ትላንት በአርሲ - ኦጄ፣ ከ30 በላይ ሰዎች ሞተዋል

    በኢሬቻ በዓል ላይ በደረሰው እልቂት በተቀሰቀሰው ቁጣ ምክንያት ሳምንቱን በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከፍተኛ ተቃውሞና ግጭት ተከስቶ የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል፡፡ በትላንትናው ዕለት በአርሲ ነገሌና አርሲአጄ አካባቢ፣ በተከሰተ ግጭት ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ “በክልሉ በዚህ ሳምንት የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ የሚደርሱን መረጃዎች አስደንጋጭና እርስ በእርስ የማይጣጣሙ ናቸው” ያለው የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ የበለጠ ማጣራት “አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው ቁጥሩን ከመግለፅ እንታቀባለን” ብሏል፡፡
በኦሮምያ የተለያዩ አካባቢዎች በተነሳው ግጭት የሞቱ ሰዎችን አስመልክቶ ከክልሉ መንግስት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ጫላ ያገኘነው መረጃ፤ ከሰኞ ጀምሮ በተለያዩ ወረዳዎች በተፈጠሩ ሁከቶች የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የዜጎች ህይወት መጥፋቱን ቢገልፅም የሟቾች ቁጥርን ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል፡፡
የቢሾፍቱ እልቂት የቀሰቀሰው ቁጣ፤ በምዕራብ ጎጂ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሆሮጉድሩ፣ ጊምቢ፣ በጅማ፣ በቦረና ያቤሎ፣ በቡሌ ሆራ፣ በምስራቅ ሀረርጌ፣ በአምቦ፣ ወሊሶ፣ በዝዋይ፣ በአርሲ -ነገሌና አርሲአጄ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ውስጥ በሚገኙት ሰበታና ቡራዩ አካባቢዎች ተቃውሞና ግጭቱ አይሎ መታየቱን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ የሰሞኑ የኦሮሚያ አካባቢ “ሁከት”፣ በትጥቅ የታገዘና የሽብርተኛ ድርጅትን አርማ በመያዝ የተካሄደ መሆኑን ጠቁሞ መንግስት ህግ ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡


Read 9988 times