Sunday, 09 October 2016 00:00

ኢ/ር ኃይሉ ሻውል በ80 ዓመታቸው አረፉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

   የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መስራችና ፕሬዚዳንት እንዲሁም በ97 ምርጫ የቅንጅት ሊቀመንበር የነበሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ኢ/ር ሃይሉ ሻወል በ80 አመታቸው ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል አስክሬናቸው ዛሬ አዲስ አበባ የሚገባ ሲሆን፡፡ የቀብር ስነስርዓታቸው መቼ እንደሚፈፀም አልተወሰነም ተብሏል፡፡
ኢ/ር ሀይሉ ሻወል በ1997 ምርጫ ማግስት በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ታስረው ከተፈቱ በኋላ የጀርባና የእግር ህመምን ጨምሮ በተለያዩ ህመሞች ሲሰቃዩ እንደነበር ያስታወቀው ፓርቲያቸው፤ በተለይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ህመማቸው ፀንቶ በታይላንድ ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ትናንት እዚያው ታይላንድ አርፈዋል ብሏል፡፡
ኢንጀነር ኃይሉ በ1984 ዓ.ም የመላው አማራ አንድነት ድርጅትን (መአዕድ) ከፕሮፌሰር አስራት ወ/የስ ጋር በመሆን ከመሰረቱ በኋላ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ለ10 ዓመት መርተውታል፡፡ መአዕድ ወደ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት  በ1995 (መኢአድ) ከተቀየረ በኋላ እስከ 2005 ዓ.ም ለ10 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ማገልገላቸው ይታወቃል።
በ1997 አራት ድርጅቶች ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የተሠኘውን ስብስብ ሲፈጥሩ ኢ/ር ሃይሉ ሊቀ መንበር በመሆን ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ  ብዙሃን በሚሠጧቸው መግለጫዎች የሚታወቁ ሲሆን ከታሰሩት የቅንጅት ከፍተኛ አመራሮች አንዱ ነበሩ፡፡ ከሁለት ዓመት እስር በኋላ ሲፈቱ ወዲያው ለህክምና ወደ ውጭ ሃገር አምርተዋል ወደ ሃገር ቤት እንደተመለሱም ድርጅታቸውን በመኢአድ አሰባሰበው መምራት መቀጠላቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢ/ር ሃይሉ ሻውሎ ከፖለቲካ ተሣትፎአቸው ባሻገር የኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ በተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ውስጥም በአመራርነት ማገልገላቸውን የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል፡፡
በአባይ ሸለቆ የውሃ ልማት ጥናት በመሃንዲስነትና በግድብ ስራዎች ምርምር ላይ የሠሩ ሲሆን አሁን እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብን መሠረት-ንድፍን ከሠሩት ሙያተኞች አንዱ ናቸው ተብሏል፡፡
በሼል ኩባንያ በተለያዩ ሀገራት በማናጀርነት የሰሩት ኢንጅነር ኃይሉ፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት በዋና ስራ አስኪያጅነት መርተዋል፣ በወንጂና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች በስራ አስኪያጅነት፣ በመንግስት እርሻ ልማት ሚኒስቴር በሚኒስትርነት፣ በብሄራዊ ባንክ የቦርድ አባልነት፣ በአውሮፓ ህብረት በብራስልስ አማካኝነት በአግሮ ኢንዲስትሪ ልማት ቡድን መሪነት፣ በጀርመን ተራድኦ ድርጅት በአፍሪካ ገጠር ልማት ዳይሬክተርነት እና በአውሮፓ ህብረት ለአፍሪካና ካሪቢያን ሀገሮች የውጭ ገበያ ምርት ማሻሻያ ፕሮጀክት ላይ የሰሩ ሲሆን በመንገድና በኤርፖርት ግንባታዎችም በግል የኮንስትራክሽን ኩባንያቸው ተሳትፈዋል፡፡
ኢ/ር ሀይሉ ሻወል መኢአድን በፋይናንስ፣ በእውቀትና በበላይ ጠባቂነት በማገልገል ወደር የለሽ መሪያችን ነበሩ ያለው ድርጅቱ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል፡፡


Read 5819 times