Print this page
Monday, 03 October 2016 08:24

ደስተኛው ሰብዓሰገል

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(5 votes)


       …ለሁለት ሺ ዓመታት የተደሰተ ሰው ታውቃላችሁ? … በፍፁም ልታውቁ አትችሉም፡፡ ስለዚህ ይህንን ታሪክ ዝም ብላችሁ ስሙኝ፡፡
እኔ እንደናንተው ሟች ለመሆን ተወልጄ፣ በታሪኬ ረጅምነት ያልሰለቸሁ፣ አንድ የምድር ከርታታ ነኝ፡፡ ከተራ ቤተሰብ ስወለድ አለም እንዳሁኑ አልነበረችም፡፡ ትግልና መከራ የበዛባት … ምድረ በዳ ነበረች፡፡ ግን የእውቀት ፍላጎት ገና በጋለ እድሜዬ ያጓጓኝ ነበርና … ሚስጥራቱን ለመማር ወደ ሊቃውንት ተጠጋሁ፡፡ እንዳሁኑ እውቀት በተለያየ ዘርፍ ያልተከፋፈለ … ጥልቅና ድፍን ነበር፡፡ በመሆኑም ከአንድ አዋቂ ወደ ሌላ እየተዘዋወርኩኝ … በዓለም ዳርቻ ሁሉ የተቻለኝን ሁሉ ትምህርት ቀሰምኩኝ፡፡ ኮከብ ቆጣሪ ሆንኩኝ፡፡
ወደ ተወለድኩባት መንደር ስመጣ፣ በኮከብ ቆጣሪነቴ አፍታም ሳልቆይ ስሜ ገነነ… ህዝብን መምራት … ሀብትም ማፍራት አልከበደኝም። በእውቀትም ሆነ በጉልበት የሚገዳደረኝን ሁሉ  በዕውቀቴ አስገበርኩኝ፡፡ ንጉስ ሆንኩኝ፡፡ ንጉስ ተደርጌ ከመሾሜ፣ በአጎራባች ንጉሶች በደረሰኝ ጥሪ ወደ ገሊላ ግዛት አቀናሁኝ፡፡ የጉዞአችን መንስኤ ታላቅ ንጉስ የመወለዱን ዜና መስማታችን ነበር፡፡ ዜናውን ያበሰረን የማይፋቀው ሰማይ መዝገብ ነው። በክዋክብት የተፃፈው ቅኔ፡፡ በቅኔ ፍቺው መሰረት፣ አለምን የሚለውጥ የፈጣሪ ልጅ መወለዱን የምታመለክተውን ኮከብ ተከትለን አራት ሆነን ወጣን፡፡
ወደ ቤተልሄም ልንገባ ትንሽ ሲቀረን፣በአሸዋው የበረሀ ማዕበል ምክኒያት በተነሳ ንፋስ የግመሎቻችን ቅጥልጥል ተፈትቶ፣ በተለያየ አቅጣጫ ከሶስቱ ሰብዓ ሰገሎች ጋር ተጠፋፋሁኝ፡፡ እኔ የመንከራተት ታሪክ እንዳለኝ እጣ ፈንታዬን አስቀድሜም ብተነብየውም … መንከራተቴ እስከ ምን ደረጃ እንደሚሄድ መገመት አልችልም ነበር፡፡
በቤተልሄም የተወለደውን ልዑል ሳይረፍድብኝ ለማግኘት ብዙ ከተንከራተትኩ በኋላ ሄሮድስ ህፃናትን እያወጣ ሲፈጅ ከረፈደ ደረስኩኝ፡፡ አብረውን መንገድ የወጡት ሶስቱ ሊቃውንቶች … ገፀ በረከታቸውን አበርክተው ወደ ሀገራቸው የመመለሳቸውን ዜና ሰማሁኝ፡፡ በግመሌ ጭኜ የመጣሁትን የእኔን ገፀ በረከት ቢረፍድም ሳልሰጠው አልመለስም በሚል፣ ህፃኑን ልዑል ማፈላለጌን ቀጠልኩ፡፡ የእኔ እጣ የመንከራተት መሆኑን አውቃለሁኝ፡፡ የምንከራተተውም በዚህ ህፃን አምላክ እግር ስር ለመስገድ ነው፡፡ ክዋክብቱ ስለ ታላቅነቱ ነግረውኛል፡፡
ሄሮድስ ሁለት ሺ ህፃናትን መግለዱንና ማርያምና ዮሴፍ ህፃኑን ጌታዬን ይዘው ወደ ምስር ሀገር መሸሻቸውን ስሰማ … መንገድ ላይ ብደርስባቸው ብዬ እስከ አባይ ወንዝ መነሻ ድረስ አሰስኳቸው፡፡ ምንም ፍንጭ ባላገኝም አላረፍኩም። ምክንያቱም ሀገሩንና ህዝቤን ጥዬ የመጣሁበት ምክኒያት መሲሁን ለማግኘት ነው፡፡ እጣ ፈንታዬም እንደሚናገረው … የሰማይ አሻራም በክዋክብቱ ጥለት ውስጥ ተጠልፎ እንደሚመሰክረው … ከመንከራተቴ በኋላ በስተመጨረሻም ቢሆን እንደማገኘው አስቀድሞ የተተነበየ ስለሆነ … ተስፋ አልቆረጥኩም። ፍለጋዬን ቀጠልኩኝ፡፡
በምስር ሀገር አርፌ ስለ መሲሁ መረጃ የሚሆን ወሬ እስክሰማ በመጠበቅ ብዙ አመታት አሳለፍኩኝ፡፡ በምስር ታላቁ የአሌክሳንደሪያ ከተማ የሚከማቹ የግሪክ፣ የሮማ … ሊቃውንቶችን ክርክር ሳደምጥና ከዓለም ዳርቻ በመርከብ ተጭነው የሚመጡ ድርሳኖችን ሳገላብጥ … አመታት ጭልጥ ብለው አለፉ፡፡ ግን በእውቀት ወይን ጠጅ ሰክሬ ባሳለፍኳቸው እነዚህ አመታት፣ አንድ ወሬ ሲናፈስ ሰምቼ በድንገት ባነንኩኝ፡፡ አንድ ብላቴና ናዝሬት በምትባል ግዛት፣ ትልልቅ ሊቃውንቶች መሀል ተገኝቶ ባነሳቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ነበር የሚወራው፡፡
የጠፋብኝ ህፃን ነው ብላቴናው፡፡ ምክኒያቱም ይኼም በክዋክብቱ ጥቅሻ ተፅፎ ያነበብኩት ትንቢት ስለነበር፣ማንነቱን ወዲያው አወቅሁኝ፡፡ አፍታም ሳልቆይ ግመሌን ጭኜ፣ ገፀ በረከቴን ወልውዬ፣ የአመታቱን አቧራ አራግፌ ወደ ናዝሬት ገሰገስኩ። …. አንድ ክረምትና አንድ በጋ በጉዞ አሳልፌ፣ ወደ ናዝሬት ከተማ ለመግባት ጥቂት ወራት ያህል ርቀት ብቻ ሲቀረኝ … በምድረ በዳው ላይ ወንበዴዎች አድብተው ማረኩኝ፡፡ ግመሌን ወስደው .. ገፀ በረከቴን ቀምተው፣ መጎናፀፊያዬንም ገፈው፣ ክፉኛ ካቆሰሉኝ በኋላ እንድሞት ጥለውኝ ሄዱ፡፡ ይሄንን እጣ ፈንታዬን ቀድሞ የጠበቅሁት ስላልነበር፣ በሞት አፋፍ ላይ ሆኜ የመንከራተቴ መጨረሻ አሳዛኝ የሚሆን መስሎኝ ነበር፡፡
ግን ፈጣሪ አዝኖልኝ አንድ ደግ ሳምራዊ ወደኔ ላከልኝ፡፡ ቁስሌን አስሮ… መጎናፀፊያም ከራሱ ገፎ አለበሰኝ፤ በአህያውም ጭኖ ወደ ቤቱ ወስዶ፣ ቁስሌ እስኪሽር ቤቱ አስተኝቶ አስታመመኝ። በሚያስታምመኝ ጊዜ ስለ ፈጣሪውና ስለ ህጎቹ ይነግረኝ ነበር፡፡ በበረሀ የሚጓዝበትን ምክኒያትና ስለ ብላቴናው ክርስቶስ በተረኩለት ጊዜ እንደሚያውቀው መሰከረልኝ፡፡ የፈጣሪ ልጅ እንደሚመጣ እሱም እንደተስተማረና ግን የፈጣሪ ልጅ መምጫው ዘመን አሁን እንዳልሆነ ሊያስረዳኝ በፅኑ ቢሞክርም፣ እኔ ግን ገር ልሆንለት አልቻልኩም። በሌላው እምነቱ ጥንካሬ ግን እንዳስደመመኝ መካድ አልችልም፡፡ የአይሁድን አምላክ ሀያልነት ሲነግረኝ ተማርኬአለሁ፡፡
ከሳምራዊው ቤት ድኜ ስወጣ፣ ከሳምራዊው የተማርኩት የአይሁድ እምነት አሸንፎኝ... የቀድሞው መንገዴ ተረስቶ ነበር፡፡ በመሆኑም … በምስር ሀገር የፈላስፎቹንና የሊቃውንቱን ውይይት ስሰማ … እንደፈዘዝኩት … በድጋሚ ከአይሁዶቹ ጋር በመኖርና አምላካቸውን በማምለክ አያሌ አመታት ሳልይዛቸው ከነፉ፡፡ እኔም ከእነሱ እንደ አንዱ እንጂ ከዛ ባሻገር ያለው ማንነቴ ተዘነጋኝ፡፡ ከእነሱ እንደ አንዱ ሆኜ፣ በእነሱ ፈቃድ ሚስት አጭቼ አገባሁኝ፡፡ ሁለት ወንድ ልጆችም አፈራሁኝ፡፡
…. ሁለት አስርት አመታት እንዲህ አለፉ። እኔም በእድሜ ጎለመስኩኝ፡፡ ልጆቼ ሲያድጉ ደስታዬ ሙሉ የሆነ መስሎኝ ነበር፡፡ ግን በድጋሚ ከምድረ በዳ የወጣ አንድ ሰባኪ …. እየመጣ ስላለ መሲህ እየጮኸ፣ “መንገዱን ጥረጉ” እያለ፣በበረሀ እንዲያስጠነቅቅ፣ ነብይ መነሳቱን ሲያወሩ በድጋሚ ከቀለስኩት ጎጆ በርግጌ ወጣሁኝ፡፡
የእኔ እጣ ፈንታ …. ከመሲሁ ጋር እንደታሰረ አውቄአለሁ፡፡ ልጆቼን ተሰናብቼ፣ አህያዬን ጭኔ ወደ ገሊላ ወጣሁ፡፡ በምድረ በዳ የሚጮኸው ሰባኪ፣ ህዝቡን በዮርዳኖስ ውሀ ላይ እያጠመቀ እንደነበረ ሰማሁኝ፡፡ ስለ ክርስቶስ ባጠያይቅም የሚነግረኝ አጣሁ፡፡ በመጥምቁ ዮሐንስ ዘንድ … ተጠምቆ መሄዱን በግምት ተረዳሁ፡፡ ተጠምቆ የሄደው በቅርብ ስለሆነ፣ እዛው ገሊላ አካባቢ ከቤት ቤት እየጠየቅሁ … ስፈልገው ብዙ ተንከራተትኩኝ። መንከራተት ታሪኬ ቢሆንም፣ እንደዚያች ቅፅበት ቅርብ ሆኖ ሳላገኘው እንዳልቀር የፈራሁበት ጊዜ ግን አልነበረም፡፡
ሰርግ ተደግሶበት ከነበረ፣ ጥቂት ቀናት ብቻ ያሳለፈ አዳራሽ ውስጥ ጌታ ታድሞ እንደነበረ ወሬ ሲናፈስ ጆሮዬ ደረሰ፡፡ የመሲሁን ስም ሳነሳ የሚያውቁት፣ በረከቱ በሰርጉ ግብዣ ላይ ውሀን ወደ ወይን ጠጅ ሲቀይር እንዳዩ የሚያጫውቱኝ ብዙ፡፡ ያለበትን ግን ሊነግሩኝ አልቻሉም፡፡
… ወደ ባህር ዳርቻው መውረዱንና እዛው እንደሚቆይ፣ ደቀመዛሙርቱንም እያጨ ስለመሆኑ ሳውቅ… የመንከራተቴ መቋጫ በመድረሱ ደስ አለኝ። ከጌታዬ ጋር ፊት ለፊት ልገናኝ እንደሆነ እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ ግን አሁንም የኮከቦቼ ዕጣ ፈንታ አየለና፣ መልዕክተኛ ድንገት መጥቶ ከመንገዴ አሰናከለኝ፡፡ ያስላከብኝ ያ በክፉ ግዜ ያነሳኝ ደጉ ሳምራዊ መሆኑንና ወደ እርሱ እመጣ ዘንድ ባስቸኳይ እንደሚፈልግ መልዕክተኛ ሲነግረኝ… ልቤ ለሁለት ተሰነጠቀ፡፡ ግን ወደ ባለውለታዬ ቅር እያለኝም ቢሆን ውሳኔዬን አዘነበልኩኝ፡፡
ሳምራዊው ባልንጀራዬ ቤት ስደርስ ደክሞ ጠበቀኝ፡፡ ከአንደበቱም ቃል ሳይተነፍስ በሚንከራተቱ አይኖቹ ሊነግረኝ የሚሻው ነገር እንደነበረ ከመጠቆም በቀር ምንም ከአንደበቱ የሚወጣ ንግግር አልነበረም፡፡ በብዙ ጣር ነፍሱ ስትወጣ… እንደ አባቴ አልቅሼ ቀበርኩት፡፡ ሀዘን ተቀመጥኩኝ፡፡ ሀዘኔን ጨርሼ ስወጣ… በሀገሩ ከእየሱስ ክርስቶስ በስተቀር የሚወራ ሌላ ነገር ፈፅሞ አልነበረም፡፡ እየሱስ… የፈወሳቸውን… አጋንንት ያወጣላቸውን… ከሞት ያስነሳቸውን-- የመበለቷን ሴት ልጅ፣ አልአዛርንም ጭምር አገኘሁዋቸው… ክርስቶስን ግን ለማግኘት አሁንም ዘገየሁኝ፡፡ ከመድረሴ ትንሽ ቀደም ብሎ አልፏል… ተባልኩኝ፡፡  
…ከብዙ መንከራተት በኋላ የአይሁድ ሊቃውንት ከስሰውት ሄሮድስ ጋር እንዳቀረቡት፣ ከዛም ጲላጦስ ዘንድ እንደገባ መረጃ አገኘሁኝ፡፡ አውራ ዶሮው ሶስት ጊዜ ሲጮህ ---- ከሩቅ ሰምቻለሁ፡፡ ግን ክርስቶስን አሁንም አላየሁትም፡፡ ደቀመዛሙርቶቹ በተሸሸጉበት አነፍንፌ…ተማጠንኳቸው፡፡ ሊሰቅሉት መሆኑን ስሰማ፣ ለክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ለራሴም እጣ ፋንታ አለቀስኩኝ፡፡ ሳላገኘው መርፈዱ … ነው ያስለቀሰኝ፡፡ ከለቅሶዬ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ ከመሞቱ በፊት እንኳን ባገኘው በሚል.. መስቀል ተሸክሞ በሚያልፍበት የቀራኒዮ ቀጭን ኩርባ ላይ ቆሜ ስጠብቀው ዋልኩኝ፡፡ ቀትር ላይ በወታደር አጀብ ….ተከቦ.. የሚተፉበትንና የሚሰድቡትን ሁሉ ከመስቀሉ ጋር አዳብሎ አጠገቤ ደረሰ፡፡ በእሾክ አክሊሉ ስር በደም የተሸፈነውን ፊቱን ቀና አድርጎ ልክ ጎኔ ሲደርስ፣ እኔን ነጥሎ ተመለከተኝ፡፡ በአይኑ ውስጥ እስካሁን የተጓዝኩበት ጊዜ አንድም ሳይቀር ተፅፎ ታየኝ፡፡ ከፅሁፉ ጋር አንድ ነገር ተናገረ፡፡ ቃሉን የሰማሁት እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ስሜን ጠይቆ፡- ‹‹.. አንተ የህይወቴ ምስክር ነህ… የሞቴና፤ የትንሳኤዬ፡፡ ዳግም በሰው ልጆች ላይ ለመፍረድ የመጨረሻ ቀን ስመጣም ምስክር እንድትሆን መርጬሀለሁ፡፡…. ስለ እኔ ብዙ ተንከራትተሀልና የእኔ ህያው ምስክር ሆነህ ተመልሼ እስክመጣ ትቆየኛለህ›› አለኝ፡፡
…እስከ መጨረሻ ትንፋሹ፣ ከተሰቀለበት ኮረብታ ባሻገር ቆሜ ያደረጉትን ሁሉ አየሁኝ፡፡ መንከራተቴ አብቅቷል፡፡ ከዛች ንግግር በኋላ ለእኔ የተስፋ ጊዜ ሆነ፡፡ ሌሎቹ ደቀ መዝሙሮች ጥበቃቸው ከሶስት ቀን በኋላ ክርስቶስ ሲነሳ ለማግኘት ስለነበር፣ በአጭር ጥበቃ የተመኙትን አገኙ፡፡ የእኔ ተስፋና ጥበቃ ግን ትንሽ ይርቃል፡፡ እናም መጠበቄን ቀጥያለሁ፡፡
… አንዳንዶች አራተኛው ሰብዓ ሰገል ብለው ይጠሩኛል፡፡ ሌሎች ደግሞ ‹‹The Wondering Jew›› ይሉኛል፡፡ እኔ ግን ለመንከራተት የተፈጠርኩ ነኝ ብዬ የማስበው፣ ክርስቶስን በቀራኒዮ ጎዳና ላይ እስካገኘው ብቻ ነበር፡፡ ካገኘሁት ጊዜ ጀምሮ ተልዕኮዬ የምስክርነት ሆነ፡፡ ክርስቶስን ከመሞቱ በፊት… ከመነሳቱ በኋላ ----- ከማረጉ በኋላ… ተመልሶ በክብር እስኪመጣ ያለውን ጊዜ የምመዘግብ ነኝ፡፡ ሲመጣም መጀመሪያ ከሀገሬ ገፀ በረከት ይዤለት ስወጣ እንደተመኘሁት፣ ተንበርክኬ እሰግድለታለሁ፡፡ ይኼን ለመጠበቅ መቆየቴም እጅጉን ያኮራኛል፡፡
ስለዚህ የተንከራተትኩት ለሰላሳ አመታት እንጂ  ---ለሁለት ሺ አመታት በማይበርድ ደስታ ውስጥ ነኝ፡፡ መንግስታት ሲመጡ ሲሄዱ፣ በታሪክ ሳይሆን በቁሜ አይቻለሁ፡፡ ዙፋን ሲለዋወጡ… ትውልድ ሲያልቅና ሲተካም ታዝቤአለሁኝ፡፡ ግን ከዚህ ሁሉ ነፍሴን የሚያስደስታት በህይወቴ ሆኜ መንግስት ሰማያትን መጨበጤ ነው፡፡ ደግሞም ያንን ቃል በቀራኒዮ ጎዳና ላይ ከተናገረኝ በኋላ ፀጋውን በጥቂቱም ቢሆን አካፍሎኝ ነው በመስቀል ላይ የሞተው፡፡ ስለዚህ፤ አይደክመኝም.. አይርበኝም--- አይሰለቸኝም --- በሁሉም እደሰታለሁ… ሁሉም ደግሞ አያጓጓኝም፡፡
እኔና ምድር ባህሪያችን አንድ ሆኗል፡፡ ሁለታችንም ሳንለወጥ.. የሰው ልጅ ሲለዋወጥና ሲንከራተት እናያለን፡፡… ሁለት ሺ አመታት አለፉ… ግን ከራሳቸው ውስልትና እና የህይወት ጥላቻ አንፃር እያዩኝ… በስቃይ ላይ ያለሁ… ሞትን የተቀማሁ… የተረገምኩ አድርገው በቁሜ ይተርቱብኛል፡፡ የእርግማን መጨረሻ አድርገው ታሪኬን የሚያወሩና የሚፅፉም አሉ፡፡
ለእኔ ግን ሁለት ሺ አመታት… ከድሮ ተንከራታችነቴና እርካታ ቢስነቴ አንፃር አሁን ስመዝነው፣ ሁለት ሺ አመታቱን እንደ ሁለት ቀናት እንኳን ቆጥሬአቸው አላውቅም፡፡… አሁን፤ የደረሰ ይመስኛል፡፡ የጌታዬ ዳግም መምጫ፤ ምልክቶቹ እየታዩ ነው… ግን ሁሉም በሰአቱ ነው የሚሆነው… የምድር ስቃዮች ከተረሱኝ ሁለት ሺ አመት አልፏቸዋል፡፡ ግማሽ ነፍሴ… በሰማይ በር ጉብታ እፎይታ ሳታገኝ እንዳልቀረች ይታወቀኛል፡፡ …. ጊዜ እንደ ቅቤ ማንም ሳያቀልጠው እየቀለጠ ---- እኔን እያወዛ ሌላውን እየቀጠፈ ወይንም እያገረጣ በማለፍ ላይ ነው፡፡ አሜን፤ሁሉም ለበጎ ነውና ይሁን፡፡

Read 3331 times