Monday, 03 October 2016 08:11

ከቀነኒሳ 2፡03፡03 በኋላ...

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

    በመላው ዓለም ከ500 በላይ የማራቶን ውድድሮች የሚዘጋጁ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ለ43ኛ ጊዜ የተካሄደው የበርሊን ማራቶን በተሳታፊዎቹ ብዛት፤ ሪከርድ ለማስመዝገብ ምቹ በመሆኑና ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ስለሚሳተፉበት ከታላላቅ ማራቶኖች ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌሎቹ የለንደን፤ የቺካጎ ፤ የቦስተን ፤ የኒውዮርክ ፤ የቶኪዮ የሮተርዳም ማራቶኖች ናቸው፡፡
ይህ የስፖርት አድማስ ትንታኔ በ43ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ካስመዘገበው አዲስ ታሪክ ጋር ተያይዞ የቀረበ ነው፡፡  ከ1500 ሜትር ጀምሮ እስከ ማራቶን  15 የሩጫ ዓመታትን ያሳለፈው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ ባስመዘገባቸው ሪከርዶች፤የሜዳልያዎች ስብስብ እና ተያያዥ የውጤት ታሪኮች የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ አትሌት  መሆኑ እየተረጋገጠ ይመስላል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በአገር አቋራጭ ሩጫዎች 11 የወርቅ ሜዳልያዎች አግኝቷል፡፡ በ10ሺ እና በ5ሺ የዓለም ሪከርዶችን ከ12 እና  ከ11 ዓመታት በፊት አስመዝግቦ እንደያዘ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በሁለቱ የትራክ ውድድሮች (10 ሺ ና 5 ሺ) 3 የኦሎምፒክ እና 5 የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎችንም የሰበሰበም ነው፡፡ በአጠቃላይ በሩጫ ዘመኑ ከ114 በላይ ውድድሮች ማሸነፉን  ያመለከተው በጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር የሚንቀሳቀሰው ኤአርኤስኤስ በድረገፁ ነው፡፡   በታዋቂው የአትሌቲክስ ዘጋቢ ድረገፅ ሌትስራን ከ43ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ድልን አስመከልክቶ የቀረበውን ዘገባ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በማራቶን ሁለተኛውን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ማስመዘገቡን ተከትሎ በረጅም ረቅት የምንግዜም ምርጥ አትሌት መሆኑ ተስተጋብቷል፡፡ የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበርሊን ማራቶን ባስመዘገበው ሰዓት ከራሱ ምርጥ ሰዓት እስከ 2 ደቂቃዎችን ቀንሷል፡፡ የዓለም ሪከርድን ለማሻሻል  6 ሰከንዶች ነበር የቀሩት፡፡ ለ8 ዓመታት በኃይሌ ገብረስላሴ ተይዞ የቆየውን የኢትዮጵያን ሪከርድ ሙሉ በ56 ሰከንዶች አውርዶታል፡፡ ለዚህም ነው ከበርሊን ውጤቱ በኋላ የምንጊዜም ምርጥ አትሌት ማነው በሚለው  አጀንዳ በድጋሚ ክርክር የተቀሰቀሰው፡፡ በተለይ Letsrun.com ላይ የሚፅፉ ታዋቂ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ቀነኒሳ በቀለ በረጅም ርቀት የምንጊዜም ምርጥ ሯጭ መሆኑን ከፍተኛ ክርክር አድርገውበት በመጨረሻም ተማምነውበታል፡፡ ከሌትስራን ባለሙያዎች አንዱ በረጅም ርቀት የምንጊዜም ምርጥ ሯጭ ፉክክሩ ዋንኛ ተፎካካሪዎች ኃይሌና ቀነኒሳ መሆናቸውን ሲያመልክት የሁለቱን ውጤቶች እንደሚከተለው በማነፃፀር ነበር፡፡ ‹‹…. ቀነኒሳ 3 የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያዎች አሉት፡፡ ኃይሌን በአንድ ይበልጠዋል፡፡ 5 የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎች አግኝቷል፡፡ አሁንም ኃይሌን በአንድ ይበልጠዋል፡፡ 11 የአገር አቋራጭ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሰብስቧል፡፡ ኃይሌ ምንም የለውም፡፡ በማራቶን 56 ሰከንዶችን የቀነሰው ከኃይሌ ሪከርድ ላይ ነው፡፡ ሁለቱ አትሌቶች 8 ጊዜ ተገናኝተው 6ቱን ያሸነፈው ቀነኒሳ ሲሆን ኃይሌ ሁለቴ ብቻ ነው ያሸነፈው፡፡ የሌትስራን ተንታኞች ኃይሌ ስፖርቱን ወደ አዲስ ደረጃ አሳደገ፤ ቀነኒሳ ደግሞ ተረክቦት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ አደረገው፡፡ Greatest Of All Time G.O.A.T የሚለውን ማዕረግም ሰጥተውታል፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች እና ኦሎምፒኮች በረጅም ርቀት ስኬታማ የሆነው ሞፋራህ ከቀነኒሳ እና ከኃይሌ በኋላ  ነው በክርክሩ የተጠቀሰው፡፡    
የሞ ፋራ አዲስ ውጤት በ2015 እና በ2016 በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ በ5 ሺ እና በ10 ሺ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች መሰብሰቡ ብቻ ነው፡፡ ሞ ፋራህ ኃይሌንም ሆነ ቀነኒሳን ለመፎካከር በ2020 እ.ኤ.አ በኦሎምፒክ አንድ ተጨማሪ ሜዳሊያ መውሰድና የዓለም ሪከርድ ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ ሌትስራን ስለ 43ኛው ማራቶን የቀነኒሳ ውጤት የዘገበውም ‹‹ዘ ኪንግ ኢዝ ባክ›› የሚል ርእስ ተሰጥቶ ነው፡፡   
ከ43ኛው የበርሊን ማራቶን በፊት    
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከ43ኛው የበርሊን ማራቶን በፊት ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በ4 ማራቶኖች ተሳትፎ ነበረው፡፡ የመጀመርያ ማራቶኑን በ31 ዓመቱ የሮጠው በፓሪስ ማራቶን በ2014 እኤአ ላይ ነበር ፡፡ በወቅቱ የማራቶን አጀማመሩን በፈጣን ሰዓት ለማሳመር ፍላጎት እንደነበረው በተደጋጋሚ ሲገልፅ  2 ከ03፤ ከ2 ከ05 እንዲሁም 2 ከ06 ለመግባት ማቀዱን በማስታወቅ ነበር፡፡ ማናጀሩ ጆስ ሄርማንስም በበኩላቸው አትሌቱ በመጀመርያ  ማራቶኑ ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች መግባት እንደሚችልና ምናልባትም የፓሪስ ማራቶንን  ሪከርድ በመስበር ጥሩ አጀማመር እንደሚኖረው በርግጠኝነት መስክረውለት ነበር፡፡ በወቅቱ ቀነኒሳ እና ጆስ ሄርማንስ ብቻ ሳይሆኑ የፓሪስ  ማራቶን አዘጋጆች እና ሌሎች ታዋቂ የአትሌቲክስ ዘጋቢ ድረገፆች ለውጤታማነቱ ከፍተኛ ግምት ነበራቸው፡፡ የፓሪስ ማራቶን አብይ ስፖንሰር የነበረው ሽናይደር ኤሌክትሪክስ በኦፊሴላዊ መግለጫው የቀነኒሳ ተሳትፎ የፓሪስ ማራቶንን ድምቀት እንደጨመረው ሲገልፅ የቦታውን ክብረወሰን የማስመዝገብ ብቃት እንዳለው ገምቶ ነበር፡፡  በግማሽ ማራቶን ውድድር ታላላቆቹን አትሌቶች ሞ ፋራህና ኃይሌ ገብረስላሴን አስከትሎ በመግባት  ሲያሸንፍ ያስመዘገበው ሰዓት 1 ሰዓት ከ09 ሰኮንዶች መሆኑን ጠቅሶ  በፓሪስ ማራቶን ማሸነፍ እንደሚችል ግምቱን የሰነዘረው ደግሞ ሌትስ ራን የተባለው የአትሌቲክስ ዘጋቢ ድረገፅ ነበር። አትሌቲክስ ኢልስትሬትድ የተባለ ድረገፅ በበኩሉ በቀነኒሳ የመጀመርያ የማራቶን ተሳትፎ ላይ በሰራው ትንታኔ አትሌቱ ፓሪስ ላይ ስኬታማ ጅማሮ እንደሚኖረው ሲያስረዳ፤ በመጀመርያው ማራቶኑ ቢፈጥን በ2 ሰዓት ከ01 ደቂቃ ከ05 ሴኮንዶች (አዲስ እና አስደናቂ የዓለም ሪከርድ ሊሆን የሚችል ነው) ከዘገየ ደግሞ ከ2 ሰዓት 06 ደቂቃዎች አካባቢ ሊገባ ይችላል በሚል ትንታኔውን ማቅረቡም ይታወሳል፡፡ የቀነኒሣ ከፍተኛ ውጤቶች ከዘረዘረ በኋላ በፓሪስ የመጀመርያ ማራቶኑን ሲሮጥ ከዓለም ሪከርድ ይልቅ የቦታውን ክብረወሰን ማሻሻል እንደሚችል የገመተው ደግሞ ራነርስ ዎርልድ የተባለው የአትሌቲክስ ዘጋቢ መፅሄት ነበር፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በእነዚህ አስተያየቶች እና ቅድሚያ ግምቶች  ተከብቦ ከ2 ዓመት በፊት በፓሪስ የመጀመርያውን ማራቶኑን ሮጠና በ2፡05፡04 በሆነ ጊዜ የግሉን ፈጣን ሰዓትና የቦታውን ክብረወሰን  አስመዝግቦ አሸነፈ፡፡  ያገኘውም የገንዘብ ሽልማት ደግሞ 41100 ዶላር ነበር፡፡
የመጀመርያ ማራቶኑን በፓሪስ  ስኬታማ አጀማመር ካደረገ ከ6 ወራት በኋላ 2ኛውን ውድድር በቺካጎ ማራቶን የሚሳተፍበት እድል ተፈጠረ፡፡ በ2፡05፡51  በሆነ ጊዜ 4ኛ ደረጃን በቺካጎ ማራቶን ለማግኘት ሲችል ሽልማቱ ደግሞ  25ሺ  ዶላር ነበር፡፡ በቺካጎ  ማራቶን ከሮጠ ከ3 ወራት በኋላ  በ2015 የውድድር ዘመን መግቢያ የመጀመርያ ወር ላይ 3ኛ ማራቶኑን ለመሮጥ የወሰነው በዱባይ ማራቶን ነበር፡፡ በተለይ የዱባይ ማራቶን ላይ የቦታን ሪከርድ ለሚያስመዘግብ አትሌት የሚቀርበው የ1 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እና የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች የላቀ ውጤትን በመጥቀስ ለቀነኒሳ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ይሁንና በ30ኛው ኪሜ ላይ ውድድሩን በጉዳት ምክንያት አቋርጦ ወጣ፡፡ ከዚያም በኋላ አራተኛ ማራቶኑን በለንደን ይሮጣል ተብሎ ቢጠበቅም ተሳትፎውን ካገረሸበት ጉዳት ጋር ተያይዞ ሰረዘው፡፡ በጉዳት ሳቢያ አቋርጦ ከወጣበት የ2015 ዱባይ ማራቶን በኋላ ቀነኒሳ 4ኛውን የማራቶን ውድድር ለማድረግ የበቃው በ2016 የውድድር ዘመን በለንደን ማራቶን ነበር፡፡ በ2፡06፡36 በሆነ ጊዜ በ3ኛ ደረጃ ጨርሶ የገንዘብ ሽልማቱ 72500 ዶላር ነበር ፡፡  
የቀነኒሳ 2፡03፡03 በ43ኛው የበርሊን ማራቶን
በ43ኛው የበርሊን ማራቶን አምስተኛውን ማራቶን ሊሮጥ የበቃው በለንደን ማራቶን 3ኛ ደረጃ አግኝቶ ከዚያም በሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን መሳተፍ ሳይሆንለት ከቀረ ከ5 ወራት በኋላ ነበር፡፡  
ታዋቂው የአትሌቲክስ ዘጋቢ ድረገፅ ‹‹ንጉሱ ተመለሰ›› በማለት ስለ  43ኛው የበርሊን ማራቶን ባቀረበው ሰፊ ትንታኔ ቀነኒሳ እና ኪፕሳንግ ያደረጉትን ትንቅንቅ በውድድሩ ታሪክ ምርጡ ብሎታል፡፡ 7 ሯጮች የማራቶኑን አጋማሽ በ1፡01፡11 ሲጨርሱ በውድድር ታሪክ ፈጣኑ አሯሯጥ ሆኖ ተመዝግቦ ነበር፡፡ ሁለት ሯጮች በ2 ሰከንዶች ርቀው አጅበዋቸዋል፡፡ በውድድሩ አዘጋጆች የተመደቡት አሯሯጮች 50 ደቂቃዎችን ከሮጡ በኋላ ተንጠባጥበው ቀርተዋል፡፡ በሪኮርድ ፍጥነት የሚሮጡ አትሌቶች እንደ አሯሯጭም እንደ ተፎካካሪም መሆን ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ አሯሯጡ የተለየ ስለነበር የኪፕሳንግን ዱካ ከሚከተሉት 3 ሯጮች ሊደርስበት የቻለው እሱ ብቻ ነበር፡፡ ከ32 ኪ.ሜ ጀምሮ እግር ለእግር ተያይዘው ይሮጡ ነበር፡፡ 34ኛው ኪ.ሜ ላይ ኪፕሳንግ አምልጦት ሮጠ በመካላቸውም የ5 እና 7 ሰከንዶች ልዩነት የተፈጠረ ይመስል ነበር፡፡ ቀነኒሳ ግን እጅ አልሰጠም፡፡ ከዚያም ከ37 እስከ 38 አማካይ ላይ ደረሰበት ግን የሁለቱም ፍጥነታቸው ቀነሰ፡፡ ቀሪውን 2 ኪ.ሜ ጎን ለጎን መሮጥ ጀመሩ፡፡ 40ኛው ኪ.ሜ ላይ ሲደርስ በጠቅላላው ሰዓታቸው 23 ሰከንዶችን በመንቀራፈፉ የሪኮርዱ ነገር የማይሳካ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡ 41ኛ ኪ.ሜ ላይ ቀነኒሳ አፈትልኮ ወጣ አያያዙም ማሸነፉ እንደማይቀር የሚያመለክት ነበር፡፡
ቀነኒሳ ልክ የማሸነፊያውን ሪባን በጥሶ ሲገባ ሰዓት ቆጣሪው ቦርድ 2፡02፡59 ያሳይ ነበር፡፡ ይህ ቦርድ ግን በኦፊሴላዊ ደረጃ የሚመዘገብ አልነበርም፡፡ ከትክክለኛ የሪከርድ ሰዓት በ2 እና 3 ሰከንዶች ስለሚዘገይ ነው፡፡ ስለዚህም የቀነኒሳ የበርሊን ማራቶን የማሸነፊያ ሰዓት 2፡03፡03 ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ሁለተኛ የሆነው ዊልሰን ኪፕሳንግ የግሉን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ ሲገባ 2፡03፡11 በሆነ ጊዜ ሲሆን ሌላ ኬንያዊ ኢቫን ቺቤት 3ኛ እንዲሁም ሲሳይ ለማ 4ኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በ43ኛው የበርሊን ማራቶን ቀነኒሳ ያሸነፈበት  ሰዓት ብዙ ታሪኮች የተቀየሩበት ነው፡፡ ከ2፡04 በታች በመግባት በውድድሩ ታሪክ 10ኛ ሯጭ ሆኖ ለመመዝገብ የበቃበት  ነው፡፡ በ2008 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን ኃይሌ ገብረስላሴ በወቅቱ የዓለም ሪከርድ የነበረው 2፡03፡59 የሆነ ጊዜን አስመዝግቦ ነበር፡፡ ይህ የኃይሌ ሰዓት የዓለም ማራቶን ሪከርድ መሆኑ በ2009 እኤአ በኬንያዊው ፓትሪክ ማኩ የተሰበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ ሆኖ ያለፉትን 8 ዓመታት የቆየ ነበር፡፡ ከቀነኒሳ የበርሊን ማራቶን ውጤት በኋላ ግን  በ56 ሰከንዶችን አሻሽሎ አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርዱ ሊመዘገብም በቅቷል፡፡ በተጨማሪም ይህ የቀነኒሳ ሰዓት 2፡03፡03 በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ሁለተኛ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡   ክብረወሰን ለመስበር ቀነኒሳ በ6 ሰከንዶች ብቻ መዘግየቱ የሚያስቆጭ ነበር፡፡ ዝቅተኛ በጀት ባለው የበርሊን ማራቶን አትሌቶች ፈጣን ሰዓት ስለሚያስመዝገቡ ብዙ የገንዘብ ሽልማቱ እንደለንደን ባይሆንም ቀነኒሳ በቀለ በበርሊን ማራቶን ድሉ በሽልማት መልክ ከ150ሺ ዶላር በላይ አግኝቷል፡፡
ከ43ኛው የበርሊን ማራቶን በኋላ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ለአይኤኤኤፍ በሰጠው አስተያየት የግሌን ፈጣን ሰዓት ለማመዝገብ በነበረኝ እቅድ ተሳክቶልኛል፤ ግን ሪከርዱ ለጥቂት ስላመለጠኝ አልተደሰትኩም.. ያለ ሲሆን ካስመዘገበው ሰዓት ፈጥኖ ሊገባ እንደሚችልም ገልጿል፡፡ሌትስ ራን በትንታኔው ቀነኒሳ የዓለም ሪከርድ መስበር የሚችልበትን እድል ከእንግዲህ  ላያገኝ ይችላል ብሎ በጥርጣሬ ድምዳሜ ላይ ቢደርስም ከዓመት በኋላ በዚያ በበርሊን ማራቶን በ35 ዓመቱ ሲሮጥ ወይንም ከዚያ በፊት ለንደን በምታስተናግደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሪከርዱን በድጋሚ ለመስበር ሊሞክር እንደሚችል አስተያየት የሰጡም አሉ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በሪዮ ኦሎምፒክ  በነበረኝ እድል ያሳለፈው ውሳኔን ያማረርኩት ያለምክንያት አለመሆኑን የበርሊን ማራቶን ያረጋግጥልኛል ሲል የተናገረው ቀነኒሳ፤ አሁንም በኦሎምፒክ መድረክ በማራቶን የመሮጥ እቅድ እንዳለው ቢገልፅም፤ በ2020 እኤአላይ የጃፓኗ ከተማ የምታተናግደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሲደርስ እድሜው  38 መድረሱ ጥቂቶችን አሳስቧቸዋል፡፡  ማናጀሩ የሆኑት ጆስ ሄማንስ ግን የኦሎምፒክ ህልሙን ማሳካት እንደሚችል በልበሙሉነት የተናገሩ ሲሆን  የሩጫ ዘመን እንደሻማ መቅለጥ  ነበር፤ አሁን ቀነኒሳ ብዙ የሚያቀልጠው ነገር ባለመኖሩ በኦሎምፒክ ተሳትፎው ተስፋ መቁረጥ የለበትም ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከበርሊን ማራቶን በኋላ ዋና ትኩረቱ በለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን መወዳደር መሆኑን የገለፀው ቀነኒሳ ፌደሬሽኑ ከመረጠኝ የሚል አስተያየት ቢጨምርም ያስመዘገበው ሰዓት ሚኒማን በአንደኛ ደረጃ ያሟላበት በመሆኑ መስጋት የለበትም፡፡
ስለጉዳቶቹ ፤ ስለማራቶን እና አብረውት ስለሚሰሩት የባለሙያዎች ስብስብ   
የቀነኒሳ የማራቶን ህልም ገና ያበቃ አይመስልም፡፡ በበርሊን ማራቶን አስደናቂውን ሰዓት ካስመዘገበ በኋላ ሌሎች ህልሞች በጭንቅላቱ ተፈጥረዋል፡፡ የዓለም ሪከርድን ማሻሻል ይፈልጋል፤ ማራቶን ከሁለት ሰዓት በታች የሚገባበትን እድል በሩጫ ዘመኑ ራሱ ሙከራ ሊያደርገበት፤ ወይም ሌሎች እንዲያሳኩት ተስፋ ያደርጋል፡፡ ለእነዚህ ህልሞቹ መሳካት ግን ከጉዳት የነፃ የውድድር ዘመን ማሳለፍ ይኖርበታል፡፡  አትሌት ቀነኒሳ በቀለ  ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት በማራቶን እቅዶቹ ላይ ሲፈታተኑት ከቆዩት ሁኔታዎች ዋንኛ በየጊዜው የሚያጋጥሙት ጉዳቶች መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ ከ2010 እኤአ ወዲህ ‹‹አኪለስ ቴንደን›› ተብሎ በሚጠራ የአትሌቶች ጉዳት ሲቸገር ቆይቷል፡፡ይህ ጉዳት በጀርባ አካባቢ፤ በተለያዩ የሰውነት መገጣጠሚያ ክፍሎች፤ በእግር ጡንቻዎች ላይ የሚፈጠሩ ህመሞች ናቸው፡፡ መሰል ጉዳቶች በልምምድ እና በውድድሮች ላይ በየጊዜው የሚያገረሹ በመሆናቸው ለማገገም ከባድ ይሆናል፡፡ ቀነኒሳ በእነዚህ ጉዳቶች ውጤቶች ሲበላሹበት፤ የውድድር እድሎችን ለመሰረዝ ሲገደድ  እንዲሁም ውጤታማ ለመሆን ባተኮረበት ማራቶን የልምምድ ሁኔታዎች ላይ መዛባት እና መስተጓጎል ሲፈጠርበት ነበር፡፡ ከጉዳቱ እንዳያገግም ካደረጉ ምክንያቶች ዋንኛው በተለይ የትራክ ውድድሮችን ሳያቆም በጎዳና ላይ መሮጡ መሆኑን ለስፖርት አድማስ ሲያስረዳ በትራክ እና በማራቶን በተለያየ ጫማዎች ስለሚሮጥ ይህ ሁኔታ ጉዳቶቹ እንዲባባሱ ማድረጉን ገልጿል፡፡ የመጀመርያ ማራቶኑን በ2014 እኤአ ላይ በፓሪስ ሲያደርግ ለማሸነፍ ቢችልም በከፍተኛ ህመም ውድድሩን መሮጡን አስታውሶም ከዚያም በኋላ በሮጣቸው ማራቶኖች በቺካጎ 4ኛ ደረጃ ለወጣበት እና በዱባይ ማራቶን ከ30 ኪሎሜትር በኋላ አቋርጦ ለወጣበት እንዲሁም የለንደን ማራቶንን ተሳትፎ ሊሰርዝ የተገደደው ከእነዚህ ጉዳቶች ጋር በተያያዘ ነበር፡፡
አትሌት ቀነኒሳ  ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ካነሳቸው ጉዳዮች ሌላኛው ስለማራቶን ውድድር ያወጋበትም ይገኝበታል፡፡ የማራቶን ውድድር ከትራክ ላይ ሩጫ በእጅጉ የተለየ መሆኑን ሲገልፅ ልምምዱ ከባድ እና ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር፤ በየሳምንቱ የልምምድ መርሃ ግብሮች እና የሚሮጣቸው ርቀቶች መለዋወጣቸው እና መጨመራቸው ፈታኝ መሆኑን በማስገንዘብ ነበር፡፡  ‹‹በትራክ ውድድር ምንም አይነት ፍርሃት አላውቅም፡፡ በማራቶን ግን እንደምሸበር አልደብቅም›› ብሎም በማራቶን ሩጫ ወጥ የሆነ ፍጥነትን ከአካል ብቃት እና ከአዕምሮ ጥንካሬ አዋህዶ መወዳደር ፈታኝ እንደሆነ፤ ከውድድር በፊት የሚደረጉ ልምምዶች አሰልቺ መሆናቸውምን ጠቅሷል፡፡ በማራቶን በሚሰራው ልምምድ ሙዚቃ አልሰማም ያለው ቀነኒሳ ይህን የሚያደርገው በአሯሯጥ ቴክኒኩ ላይ የሚያደርገውን ትኩረት እንዳያበላሽበት፤ በሚሮጥበት አካቢ ዙርያ ገባውን ለመቆጣጠር እና የሚሮጥበትን ርቀት እና ፍጥነት ለመከታተል ስለሚፈልግ መሆኑን አብራርቷል፡፡ ከማራቶን ልምምድ የሚያስደስተኝ ነገር በየመልክዓምድሩ መሮጤ ነውም ብሏል፡፡ በማራቶን አተኩሮ መስራ ከጀመረ በኋላ ለውድድሮች በሚሰራቸው ልምምዶች እና በሚያደርጋቸው ዝግጅቶች የተለያዩ ባለሙያዎችን በበቡድን በማደራጀት በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ለስፖርት አድማስ የገለፀው ቀነኒሳ፤ በስነምግብ ባለሙያነት ስኮትላንዳዊው ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ እንዲሁም በቅርበት ያለችው ባለቤቱ ዳናዊት ገብረእግዚአብሄር ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉልኝ ነው ይላል፡፡ የፊዝዮቴራፒ ባለሙያ፤ የስነልቦና አማካሪ፤ የግል አሰልጣኝ እና የስልጠና አማካሪዎች የተሰበናሰቡበት ቡድን በቀነኒሳ የማራቶን እቅድ አብረው የሚሰሩ ባለሙያዎች ይህም ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ በአርዓያነት ሊጠቀስ የሚበቃ ነው፡፡  
የፒስታሊደስ ፕሮጀክት ከተሳካ ማርስን እንደመርገጥ ይቆጠራል
ከ2 ሰዓት በታች የት እና መቼ? የበቆጂ አትሌቶች  
ከ6 ወራት በፊት በታዋቂው የአሜሪካ ሚዲያ ኒውዮርክ ታይምስ ስለ ስኮትላንዳዊው ያኒስ ፒስታሊደስ sub2hr project በማራቶን ከ2 ሰዓት በታች የሚገባ አትሌት የመፍጠር ፕሮጀክት ጄሪ ሎንግማን የተባለ ፀሃፊ በሁለት ክፍሎች ሰፊ ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡
በረጅም ርቀት ሩጫ በተለይ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ የተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮችን በመስራት ከ10 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ስኮትላንዳዊው ያኒስ ፒስታሊደስ በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የፀረ ዶፒንግ ኤክስፐርት ሆነው የሚያገለግሉ፤ በስፖርት እና የልምምድ ሳይንስ ከእንግሊዙ ብራይተን ዩኒቨርስቲ በፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተመረቁ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በተጋባዠ ሌክቸረርነት ግልጋሎት ይሰጣሉ፡፡ ፒስታሊደስ የዓለማቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የህክምናና የሳይንስ ኮሚሽን አባል የsub2hr project መስራችና ዋና ተመራማሪ ሳይንቲስት ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሳይንሳዊ አሰራሩ ይልቅ ባህላዊ የስልጠና መንገዶች በአትሌቲክሱ ዓለም መንሰራፋታቸውን የሚያወግዙት ፕ/ሩ በዚህ ፕሮጀክታቸው ይህን አመለካከት የመቀየር አላማ አላቸው፡፡
ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ በማራቶን ከ2 ሰዓት በታች የሚገባበትን ሁኔታ ለማሳካት በቀረፁት ፕሮጀክታቸው  የመጀመሪያው ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች አትሌቶች እየተፈለጉና እየተመለመሉ ናቸው፡፡ ባለፉት 16 ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመዘዋወር ፕ/ር ያኒስ ፒስታሊደስ ከ1000 ሺህ በላይ የኦሎምፒክ አትሌቶችን የደም ናሙና በመሰብሰብ ምርምራቸውን ሲያደርጉ ነበር፡፡ በተለይ በከፍተኛ አልቲቲዩድ እና ኦክስጅን እንደ ልብ በማይገኝበት መልክአ ምድር የሚኖሩትን አትሌቶች ብቃት ሲመረምሩ ቆይተዋል፡፡
በዋናነት እየሰሩ የሚገኙት ግን በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በበቆጂ አትሌቶች ላይ  ነው፡፡ በርካታ መሰል ምርምሮች እና ጥናቶች ከ2 ሰዓት በታች ማራቶንን የሚጨርስ አትሌት ቢገኝ እስከ 2030 እንደሚሆን ቢገልፁም የያዙት እቅድ እስከ 2019 እኤአ ለማሳካት በተለይ ከአርሲዋ ትንሽ ከተማ በቆጂ ይገኛል በሚል እየሰሩበት ነው፡፡ ከ2 ሰዓት በታች ማራቶንን መግባት በሩጫው ዓለም አይሳካም የሚለው ግምት ቢያይልም ይቻላል በማለት ጠንክረው የሚሰሩት ብቸኛው ሳይንቲስት ፕ/ር ያኒስ ፒስታሊደስ ናቸው፡፡ በተጠና የልምምድ መርሀ ግብርና የስልጠና ዘዴዎች ምርጥ ብቃት ያለው አትሌት ያለ ዶፒንግ ድጋፍ ማሳካት ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡ ፒስታሊደስ በፕሮጀክቱ በልምምድ፤ በአመጋገብ፤ በትጥቅና፤ በዘረ - መል ምቹነት ዝግጁ የሚሆን አትሌት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች እንደሚገባ እርግጠኛ ናቸው፡፡ 1፡59፡59 በሆነ ጊዜ ማራቶንን ለመጨረስ በ2 ደቂቃ ከ50 ሰኮንዶች አንድ ኪ.ሜ መሸፈን ግድ ይላል፡፡ ከዚሁ ሰዓት የወቅቱ የዓለም ሪከርድ በ7 ሰኮንዶች የዘገየ ነው፡፡ በማራቶን ሰዓት ሰከንዶች እንደ ዘለዓለም ይቆጠራሉ፡፡  አሁን ከተያዘው ሪከርድ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ድፍን 2 ደቂቃዎች ከ57 ሰከንዶች ይቀራሉ፡፡ 117 ሰከንዶች ማለት ነው፡፡ አንድ የፖፕ ሙዚቃ ወይንም ማስታወቂያ ሊሰራበት የሚችል ጊዜ ነው፡፡ በማራቶን ግን ዘመናትንም ይፈጃል፡፡
የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ስፖርት ከሳይንሳዊ ምርምሮች እና አሰራሮች ጋር ለማቀራረብ ከጅምሩ ከባድ ፈተና እንደሆነባቸው ለኒውዮርክ ታይምስ አስተያየት የሰጡት ፕሮፌሰሩ፤ በበቆጂ ለሚሰሩበት ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ በፕሮጀክቱ እንቅስቃሴም ላይ የአልቲትዩድ ኤክስፐርት በመሆን አብረዋቸው የሚሰሩት ዘሩ በቀለ እንዲሁም በበቆጂ ታላላቅ አትሌቶችን በማፍራት ዝና ያላቸው አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ናቸው፡፡ በ100ሺ ዶላር የሚገመቱ የቴክኖሎጂ መሳርያዎች ያሉበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልዩ ላብራቶሪም የፕሮጀክቱ አካል ነው፡፡
ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ በፕሮጀክታቸው ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የሚገባ እና ቀጣዩን ቀነኒሳ ለማውጣት  የሚፈልጉ ሲሆን፤ በምርምር ስራቸው በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰራው የ14 ዓመቱ ታዳጊ አትሌት ጫላ ቱሉም ይህን ህልም በመጋራት  እየሰራ ይገኛል፡፡ ኒውዮርክ ታይምስ በበቆጂ ተገኝቶ ፕሮፌሰሩ ከዘሩ በቀለ እና ከአሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ጋር እየሰሩ ያሉትን ልምምድ በስፋት ተመልክቶታል፡፡ በአልቲቲትዩድ ትሬኒንግ ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን እየሰሩ የሚገኙት የአትሌቲክስ ተመራማሪው አቶ ዘሩ በቀለ ለስፖርት አድማስ  በሰጡት አስተያየት ማራቶን ከ2 ሰዓት በታ ሊገባ እንደሚችል ፍፁም እምነት እንዳላቸው ሲያስገነዝቡ ለማራቶን ልምምድ የሚደረግበት እና ውድድር የሚደረግባቸው አካባቢዎች፤ በውድድር ወቅት የሚኖር የንፋስ ሁኔታ፤ የመሮጫው ጎዳና፤ የአትሌቱ አመጋገብ፤ የስነልቦና ጥንካሬ እና የተሟላ ብቃት ወሳኝ መሆናቸውን ገልፀው በሳንሳዊ የልምምድ መርሃ ግብሮች፤ በተሟላ የባለሙያዎች ስብስብ እና በእቅድ መስራ ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ እንደ አቶ ዘሩ አገላለፅ ማራቶንንን ከ2 ሰዓት በታች ሊገባ የሚችል አትሌት የሚገኘው ከምስራቅ አፍሪካ ሁለቱ አገራት ኬንያ እና ኢትዮጵያ ብቻ ሲሆን ከታዳጊ አትሌቶች ይልቅ በትራክ እና ከዚያም በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አትሌቶች ሊያሳኩት እንደሚችሉ ነው፡፡
እስቲ ኒውዮርክ ታይምስስለ ያኒስ ፒስታሊደስ ፕሮጀክት ከታዘበው እንፀምር፡፡‹‹‹ የ14 ዓመቱ ታዳጊ አትሌት ጫላ ቱሉ የብሄራዊ ቡድን ማሊያ ለብሶ በበቆጂ አንደኛ ደረጃ ተምህርት ቤት ሜዳ ላይ ፊቱ ላይ ማክስ ገጥሞ ይሮጣል፡፡ በፊቱ ላይ የገጠመው ማስክ ‹‹ጋዝ አናላይዘር›› የሚባል ሲሆን የሯጩን ከፍተኛ የኦክሲጅን አወሳሰድ የሚለካ ልዩ እና ዘመናዊ መሳርያ ነው፡፡ ስለምርምር ስራቸው እና ስለሚጠቀሙባቸው ዘመናዊ መሳርያቸው ፕሮፌሰሩ ለኒውዮርክ ታይምሱ ዘጋቢ ሲያስረዱ  አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ብቁ አትሌቶችን የሚለዩበት አይን ቢኖራቸውም የእኔ ምርምር እና ማሽኖች ግን የሯጮቹን ውስጣዊ ሁኔታና ብቃት በግልፅ የሚያሳውቁ ናቸው ይላሉ፡፡
በርግጥ ፕሮፌሰሩ ቁጭት አለባቸው፡፡ በበቆጂ አትሌቶች ይህ አይነቱን ምርምር ከ20 ዓመታት በፊት ብንጀምረው ኖሮ የሚል፡፡ በነገራችን ላይ በዚሁ ፕሮጀክት ላይ ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ ከቀነኒሳ በቀለ ጋር እየሰሩ መሆናቸውን የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ አትቷል፡፡ ፕሮፌሰሩ ለአትሌቱ በአመጋገቡ፤ በልምምድ መርሃ ግብሮቹ እና በተለያዩ ሳይንሳዊ መንገዶች የሚደረጉ ዝግጅቶችን በማስተማር እያገዙት ነው፡፡ ከፕሮፌሰሩ ጋር መስራት ከጀመረ በኋላ ቀነኒሳ በለንደን ማራቶን 3ኛ ደረጃ አግኝቷል ከዚያም ባለፈው ሰሞን የበርሊን ማራቶንን በሚያስደንቅ ፈጣን ሰዓት ለማሸነፍ በቅቷል፡፡ ቀነኒሳም ቢሆን ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት በርግጥ  ከ2 ሰዓት በታች ሊገባ ይችላል እንዲህ በቀላሉ ግን አይደለም ብሏል፡፡ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት እቅድ በጭንቅላቴ ሊኖር ይችላል እኔ ባይሳካልኝ ግን በእርግጠኝነት በቅርብ አመታት ይህን ታሪክ ለመስራት እድል ያላቸው አትሌቶች መኖራቸውን አምናለሁ የሚለው ቀነኒሳ ለስፖርቱ ጠቃሚ ሪከርድ መሆኑ ከታመነበት በአሁኑ ግዜ ፈጣን ሰዓት ያላቸውና ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ አትሌቶች በአንድ ውድድር ላይ ተመካክረው እና ውድድሩን ተጋግዘው በመሮጥ ሊያሳኩት እንደሚችሉ እገምታለሁ ሲል ተናግሯል፡፡
ይቀጥላል

Read 3990 times