Saturday, 10 March 2012 09:40

የዩኒቨርሲቲ ህይወት ትሩፋቶችና ጣጣዎች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

መከባበር፣ መደማመጥ፣ መተሳሰብ ወይስ በጐሪጥ መተያየት?

ለምሳሌ በአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አዲስ መጥ ተማሪ ስለ ሦስት አዳዲስ ነገሮች የሚገልጥ በራሪ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡ ስለ ጥቁር፣ ስለ ግብረ ሰዶማዊ፣ ስለ ኤሽያ አሜሪካዊ! ይህ የሚደረገው ተማሪዎች ስለ ጉዳዩ መረጃ እንዲኖራቸውና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በማሰብ ነው፡፡ ታዲያ ያንድ ቀን ወይም የአንድ ሣምንት ፕሮግራም አይደለም፡፡ በአራቱ ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ፣ በትምህርት መሥጫ ክፍሎች፣ በጨዋታ ሜዳ፣ እና ተማሪ ባለበት ሁሉ ይቀጥላል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተማሪ በአንድ በኩል የዕውቀት መገብያ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ ነገሮችን በሕይወቱ የሚጋፈጥበትና የማህበራዊ ኑሮ ልምዱን የሚያሣድግበት ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ታዲያ ለዚህ የሕይወት አዲስ ምዕራፍ የሚታጩ ተማሪዎች ሁሉ አካዳሚያዊ ፈተናውን ብቻ ሣይሆን የማሕበራዊ ኑሮውን አሉታዊ ፈተና ለማለፍ ጠንካራ ካልሆኑ ሕይወታቸው ባክኖ፣ ተስፋቸው ጨፍግጐ ይቀራል፡፡

በተለይ የአቻ ግፊት ጫና ዋናው ረመጥ ያለው እዚያ በመሆኑ፣ ለተለያዩ ሱሶችና ልምዶች ተጋልጦ የዕድሜ ዘመን ጣጣ ይዞ መውጣት ሊገጥም ይችላል፡፡ ይህ ጣጣ ደግሞ በመጀመሪያ የሚያጠምደው በፍሬሽነት ዘመን ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ እንግዳ በሆነበትና ጓደኛን እምቢ ለማለት ድፍረት በሌለበት ጊዜ ብዙዎች ለፀፀት በሚዳርጋቸው አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡

የፍሬሽነት ፈተና ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በነባር ተማሪዎች መታለልና መሸወድ አለ፡፡ እንደ አጋጣሚ በቴሌቪዥን ላይ እንሠራ ለነበረው ፕሮግራም ግብዓት ፍለጋ ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሄደን ነበር፡፡ ጂማ፣ ደብረዘይት ጤና ሳይንስ፣ መደውላቡ (ሮቤ) እና አዳማ ዩኒቨርሲቲ በሄድንበት ጊዜ የሚገርሙ ገጠመኞችን ሠምተናል፡፡

ለምሣሌ በመውደላቡ ዩኒቨርሲቲ ጀማል የተባለ አንድ ተማሪ አንድ ኩንታል ሙሉ በሶ አሥፈጭቶ መሄዱንና ያንን በሶ ሲኒየር ተማሪዎች እያስበጠበጡት በዱቤ መጠጣታቸውን ሠምተናል፡፡ ታዲያ የማይከፈል ብድር ነበር፡፡ ይሄ ብቻ ቢሆኝ ጥሩ ነበር፡፡ ጀማልን ካፖርት ሰጥቶ ሌሊቱን “ተረኛ ነህ” ብሎ ዘብ ያሣደረውን ተማሪ ጉዳይ በሳቅ እየፈረሰ አጫውቶናል፡፡ የሣር ፍራሽ አሥጭኖ ወደ ዩኒቨርሲቲ በመምጣቱ ግቢ በር ላይ የተሣቀበትን ተማሪ ጉዳይም ሠምተናል፡፡

ደብረ ዘይት ጤና ሳይንስ ደግሞ በሶ ሲበጠብጥ ድምፅ በሰሙ ቁጥር እየጠበቁ በመምጣት፣ በሶውን ሲጠጡበት የተማረረ ተማሪ፣ በሶውን ሲበጠብጥ ሠምተው እንዳይመጡ፣ ጠረጴዛውን እንደከበሮ እየደበደበ በመዘመር የበሶ ብጥበባ ድምፅ እንዳይሰማ መከላከሉን አውርቶን ነበር፡፡ እዚያው ደብረ ዘይት ካምፓስ፣ ወፈር ያለ ተማሪ መምህር መሥሎዋት እጥፍ ዘርጋ ብላ ሠላምታ እንደሰጠችው አንድ ተማሪ ተርካልናለች፡፡ የፍሬሽነት ችግር ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች፤ የተለያየ ባህል ያላቸውና በእምነት የማይገናኙ ሰዎች በአንድ ጣሪያ ሥር ሲያድሩ የሚፈጠረው ችግርና መደነጋገር ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ መጀመሪያ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች በመጀመሪያው ቀን ባብዛኛው እንቅልፍ ሣይወሥዳቸው እንደሚያድሩ አውግተውን ነበር፡፡ ፍሬሽማን ላይ ሁሉም ይፈራራል፤ ሁሉም ይጠራጠራል የሰውነት ጠረን፣ የጫማ ሽታ፣ ወዘተ ፈተናዎች ናቸው፡፡

በተለይ በዘመናችን የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ በጉልህ በወጣበትና ቀደም ሲል አላስፈላጊ ወሬዎችና ግጭቶች የሚፈጥሩ ፕሮፓጋንዳዎች በመዘራታቸው ተማሪዎች ውስጥ የተቀመጡ አለመቀባበሎች ስለሚኖሩ የሚኖረው አደጋ ቀላል አይደለም፡፡ አንዱ ላንዱ ያለውን አመለካከት መሞረድና ማበጀት ይጠይቃል፡፡ የሃይማኖት ጉዳዮችም እንደዚሁ! ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቅቆ የመጣ አንድ የቤተሰቤ አባል እንደነገረኝ ከሆነ፤ ተማሪው ሁሉ ካምፓስ እንደገባ ለአንድ ወር ያህል ሃይማኖተኛ ይሆናል፡፡ ሙስሊሙ ይሰግዳል፣ ኦርቶዶክሱ ቤተክርሲያን ማልዶ ይሄዳል፣ ፕሮቴስታንቱም ይፀልያል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም አይዘልቅበትም፡፡ ባብዛኛው በጓደኝነት ወጥመድ ሥር ገብቶ አዲስ ሃይማኖት ይጀምራል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ራሱ የሚፈጥረው ልማድ፣ ሃይማኖት አለ፡፡ በዚያ ሥር አንገታቸውን ያስገባሉ፡፡ ብዙዎቹም ያላቸውን ሣንቲም ተካፍለው በመብላት፣ በመበዳደር፣ በመረዳዳት በጋራ መኖርን የቤተሰብ ያህል ይለምዳሉ፡፡ ችግሮቻቸውንም በጋራ ይፈታሉ፡፡ በተለይ ከትልልቅ ከተሞች የመጡ ተማሪዎች በዚህ አይቸገሩም፡፡ የዘርም ሆነ የሃይማኖት ጉዳይ ላይ ብዙ አያጠብቁም፡፡ ምናልባት በአክራሪ ቤተሰቦች ጫና ያደረባቸው ካልሆኑ በቀር፡፡

ይህ የፍሬሽ ተማሪ ችግር መልኩ ይለያይ እንጂ በሌሎች ሀገራትም አለ፡፡ ይሁን እንጂ የነርሱ ችግሮች ለኛ የሚከብዱ ይመሥለኛል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አዲስ መጥ ተማሪ ስለ ሦስት አዳዲስ ነገሮች የሚገልጥ በራሪ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡ ስለ ጥቁር፣ ስለ ግብረ ሰዶማዊ፣ ስለ ኤሽያ አሜሪካዊ! ይህ የሚደረገው ተማሪዎች ስለ ጉዳዩ መረጃ እንዲኖራቸውና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በማሰብ ነው፡፡ ታዲያ ያንድ ቀን ወይም የአንድ ሣምንት ፕሮግራም አይደለም፡፡ በአራቱ ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ፣ በትምህርት መሥጫ ክፍሎች፣ በጨዋታ ሜዳ፣ እና ተማሪ ባለበት ሁሉ ይቀጥላል፡፡  የባህል ስብጥሩም በሚገባ በተማሪዎች አእምሮ እንዲሠርፅ ይደረጋል፡፡ ስለ ቀለም፣ ዘር፣ ባህል፣ ፆታና ሃይማኖት ልዩነት ብዙ ወጪ ተደርጐ፣ ተጠብቦ ተጨንቆ ማስተማር የግድ ይላል፡፡ ለነጮቹ ተማሪዎች ስለ ጥቁሮች በሚገባ ማስረዳት በራሱ ጊዜና ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ የተመሳሳይ ፆታ ተጠቂዎችን እንዲረዱና አካል ጉዳተኞችንም እንዳያገልሉ ብዙ መሥራት የግድ ይላል! .. የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ጣጣ ብዙ ነው፡፡ ብዙ አይነት ልማድ፣ ብዙ አይነት ሃይማኖት፣ ሌላም ብዙ ነገር አለ፡፡

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ለቴሌቪዥን ፕሮግራም ሥራ በሄድኩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች አይቻለሁ፡፡ የመጀመሪያ ፕሮግራማችንን በሠራንበት የአዳማ ዩኒቨርሲቲ፣ ሴት ተማሪዎችን ከተለያዩ እንቅፋቶች ለመጠበቅ የተወሰዱትን እርምጃዎች ከልቤ አድንቄያለሁ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የሴት ተማሪዎች ፕሬዚዳንት ወጣት ቤዛ ሸዋንግዛው እንደነገረችን፤ የትኛዋም ተማሪ በገዛ ፈቃድዋ ካልሆነ በስተቀር በግሬድ /በውጤትዋ/ ላይ ጫና በማሳደር መምህርዋ አንሶላ እንድትጋፈፈው ሊያስገድዳት አይችልም፡፡ የዚያ አይነት ሙከራ ቢደረግባት በመምህሩ ላይ የሚወሰደው ርምጃ ቀላል አይደለም፡፡ ህጉ ተግባራዊ መደረጉንም ከተማሪዎች ተነግሮናል፡፡ … ግቢ ውስጥ ሴት ተማሪዎችን መተንኮስና መጐንተል የሚያስከትለው ቅጣት ቀላል ስላልሆነ ወንድ ተማሪዎች በሴቶች ላይ የፈቀዱትን ማድረግ አይችሉም፡፡ ተከባብረውና ተፋቅረው መኖር ግን ይችላሉ! ማፍቀርም አይከለከልም! ታዲያ ሲግባቡ ነው፡፡

የሴቶችን ጉዳይ ካነሣን አይቀር የጂማ ዩኒቨርሲቲ ለሴት ተማሪዎች ያደረገው መልካም ምግባር ምሣሌነት ያለው ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዲን እንደተነገረንና ተማሪዎችም እንዳረጋገጡልን፣ ለሴት ተማሪዎች መኝታ ክፍሎቻቸው አካባቢ ፀጉር ቤቶች፣ ኢንተርኔት ካፌዎች፣ ተከፍቶላቸዋል፡፡ ይህም የተደረገው ሴት ተማሪዎች ከመኝታ ክፍላቸው ርቀው ሲሄዱ ለጥቃት እንዳይጋለጡ ለመከላከል ነው፡፡ ደስ ይላል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ማውራት ብቻ ሣይሆን ለሴቶች አጋርነቱን በተግባር አረጋግጧል!

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የደብረ ዘይት እንስሳት ጤና ፋካልቲ ደግሞ ሴቶች በቁጥር ጥቂት ስለሆኑ እንደ ዋልያ ብርቅና ጥንቃቄ የሚደረግላቸው ናቸው፡፡ ለዚያም ይመሥላል የሴቶች መኝታ ክፍል አካባቢ ሣቅ በሣቅ የነበረው፡፡ የሳቁ ሰበብ የፈተና ሰሞን ባለመሆኑ ብቻ ሣይሆን ተከብረውና  በነፃነት ስለሚኖሩ እንደሆነ የነገሩን ተማሪዎቹ ራሣቸው ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ስለ ዩኒቨርሲዎቻችን ስናስብ፣ ተማሪዎችን በክህሎትና በዕውቀት ከማሣደግ ያለፈ ሃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ የሃይማኖትና የዘር ልዩነቶችን አቻችሎ፣ በጋራ ከመበልፀግና ሀገራዊ አንድነትን ከማስረፅ አንፃር ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በተማሪዎች ልብ የተዘሩ አሉታዊ ሃሣቦችን ነቅሎ፣ የፍቅርና የመቻቻል ሀሣብን በውስጣቸው መትከል፣ ለነገው ሀገራዊ ማንነታችን እጅግ ወሣኝ ነው፡፡

በሥራ አጋጣሚ በጐበኘናቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንዳየነው፤ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች አንዳንድ የገጠር ከተሞች አካባቢ ካሉ ነዋሪዎች የተሻለ ብሔራዊ አንድነትን የሚያንፀባርቁ ስሜቶች ይስተዋልባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በአብዛኛው ኦሮምኛ ተናጋሪ ተማሪዎችን ባገኘንበት የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ (ሮቤ ከተማ)፣ ተማሪዎቹ የምረቃ ዋዜማ ዜማቸውን ሲያዜሙ መላውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እየጠሩና እያሞገሱ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በልባቸው የነበረ እንጂ ማንም “ዘምሩ” ብሎ አስገድዷቸው አልነበረም፡፡ በዚያው ዩኒቨርሲቲ የነበሩ የመሀል ሀገር ልጆችም በብሔርና በሃይማኖት ተቻችለው መኖር እንደተላመዱ ይናገራሉ፡፡ … በመጀመሪያዎቹ ሠሞናት መጠራጠርና መፈራራት፣ ከዚያም መላመድና መከባበር፣መተሣሠብ ይቀጥላል፡፡ ይህ ደግሞ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያስፈልግ ልምምድ ነው፡፡

አማራ … ትግሬ .. ኦሮሞና ጉራጌ … ወይም ሌላው በአንድነት ለአንድ ሀገር ከሠራ ብቻ ነው ድህነትን ከጫንቃው ላይ መንጭቆ መጣል የሚችለው፡፡

ትናንት እንደነበረው ዛሬም እገሌ ከእገሌ ይሻላል ወይም ይበልጣል የሚለው በሽታ ካልተወገደ ግን  ከድህነትም ባሻገር ሌላም መዘዝ ሊያስከትል ስለሚችል ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በጐ አስተሳሰብና የመከባበር ልምድን ማዳበር ይገባል፡፡ ዩኒቨርሲቲ የተወለደው ቀና አመለካከት ደግሞ ወደ መላው ሀገሪቱ ይሠራጫል፡፡ ይህ በሃይማኖት ልዩነቱም በኩል ሊሠራ የሚገባ የቤት ሥራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከባበርና መተጋገዝ ልማዱ ነው፡፡ አወቀውም ሆነ ሳያውቁ በሃይማኖት ይሁን በዘር ልዩነት ሰበብ የጥላቻን መርዝ የሚዘሩ አይጠፉም - ጥቂትም ቢሆኑ፡፡

በጥንቃቄ፣ ተደማምጠንና፣ ተከባብረን በሰለጠነ መንገድ ከኖርን ግን የፍላፃቸው ሰለባ አንሆንም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ፣ የእኛም ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት ጥራቱም ሆነ በልዩነቶቻችን ላይ ያለመታከት ሊሠሩ ይገባል - እንደፋሽን ለአንድ ሰሞን ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት፡፡ ይህ ከሆነ ብቻ - ዛሬ የምናልማትን ኢትዮጵያን ለትውልድ እናወርሳለን፡፡ በጐ ጅምሮች ይቀጥሉ፤ ያልተጀመሩ አሁን ይጀመሩ! በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ሰላምና አንድነት ይታወጅ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

 

 

Read 4882 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 09:46