Monday, 03 October 2016 00:00

ምክርና ቁርስ ከቤት…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው በሆነ ነገር ጓደኛውን ‘ሲመክረው’ ኖሯል፡፡ ተመካሪው ግን የተሰጠው ምክር ሁሉ ስላልጣመው አንዱንም አልተገበረውም፡፡ ይሄኔ መካሪ ሆዬ…
“ምክሬን የማትቀበለው ለምንድነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“ልጄ፣ ምክርና ቁርስ ከቤት ነው…” አሪፍ አይደል!
‘ምክርና ቁርስ ከቤት’ መሆኑን ረስተን መከራችንን እናያለን፡፡
ሰውየው ከሚስቱ ጋር በሆነ ነገር ይጋጫል። ይሄድና ለጓደኞች ይነግራል፡፡ እናም ጓደኞቹም ‘ምክራቸውን’ ይሰጡታል…
“ቆይ… አንተ ከእሷ ጋር ቆርበሀል እንዴ! ደግሞ ላልጠፋ ሴት… በቃ፣ ቀይ ካርድ ስጣትና ወደምትሄድበት ትሂድ…” ይሉታል፡፡ እነሱን አይነካቸውማ! በሰውየው ውሳኔ የእነሱ አንዲት የጸጉር ዘለላ አትነቀልማ!  እሱ ደግሞ እንድትሄድበት ላይፈልግ ይችላል ብለው አያስቡማ!
ሰውየው ጥያቄውን ለቤተሰብ ያቀርባል…
“ከባለቤቴ ጋር ምንም ልንግባባ አልቻልንም፡፡ በትንሽ ትልቁ መነታረክ ሆኗል፡፡ ጭቅጭቁ አንገቴ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ ምን አድርግ ትሉኛላችሁ?” ቤተሰብም ምክሩን ይለግሳል…
“እስቲ ለውሳኔ አትቸኩል፣ ነገሮችን ረጋ ብለህ አስባቸው…”
“መጀመሪያ ለብቻችሁ ቁጭ ብላችሁ ነገሮችን ፍርጥርጥ አድርጋችሁ ተነጋገሩና ካልተስማማችሁ ወደ ቤተዘመድ ጉባኤም፣ ወይ ወደ ሽማግሌዎችም መሄድ ይሻላል…”
“አደራህን… መሀላችሁ ሦስተኛ ሰው እንዳታስገቡ፡፡ የጓዳችሁን በጓዳችሁ ራሳችሁ ጨርሱ…” ይሉታል፡፡ ምንም ዘመኑ የከፋ ቢሆንም እሱ የእነሱ ነዋ! ምንም ቢሆን የሰውየው ትዳር መበላሸት በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም ሊነካቸው ይችላላ!
እናማ…ምክርና ቁርስ ከቤት መሆኑን ረስተን መከራችንን እናያለን፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘ቦተሊከኞቻችን’ አንድ ነገር ሲፈጠር ‘ምክር’ ፍለጋና ለአቤቱታ ‘የፈረንጅ በር’ ማንኳኳት ለምዶባቸው የለ!
“ወንበሬን በኃይል ሊያስለቅቁኝ ነው…” — ‘የፈረንጅ ምክር’ ፍለጋ፡፡
“ወንበሩ ላይ ሙጥኝ ብሎ አልነሳም አለ…” — ‘የፈረንጅ ምክር’ ፍለጋ፡፡
“የእንትን ህግ ልናወጣ ነው፣ እስቲ የእናተን አስኮርጁን…” —  ‘የፈረንጅ ምክር’ ፍለጋ፡፡
ልክ ነዋ… የሆነ ሰነድ ትችት በደረሰበት ቁጥር… “ከእንትን አገር እኮ የገለበጥነው…” እየተባለ በኩራት የሚነገርበት አገር እኮ ነው፡፡
እናማ…‘ምክርና ቁርስ ከቤት’ መሆኑን ረስተን መከራችንን እናያለን፡፡
እሷዬዋ መሥሪያ ቤቷ ችግር ይገጥማታል፡፡ የሆነ እንደ አሞሌ ጨው ‘ወፍሮ እጠቡኝ ያለ’ ባለጊዜ… “እነሆ በረከት ካላልሽኝ በብጣሽ ወረቀት ነው የማባርርሽ…” እያለ…አለ አይደል… ‘እኔም ከኬኩ ይድረሰኝ እንጂ’ አይነት ያስቸግራታል፡፡ ባል መኖሩን ረስቶ ሳይሆን… የዘመኑ ፍልስፍና “ባል ቢኖርስ፣ ሶ ሁዋት!” ስለሆነ ነው፡፡
እኔ የምለው… እግረ መንገዴን…አንዳንድ (‘አንዳንድ’ የሚሏት ቃል እንዴት አሪፍ ‘ምሽግ’ መሰለቻችሁ!) ባለወንበሮችና ባለ ወፍራም የባንክ ደብተሮች…የምስኪን ‘ዋይፍ’ ሲያስኮብልሉ… አለ አይደል… ‘ነግ በእኔ’ ምናምን ነገር የለም እንዴ! ነው… ወይስ እነሱ ‘ዋይፎች’ ላይ ‘ዲማንዱ’ ብዙ አይደለም!  “ሰውዬው ያለ ነገር ደጅ፣ ደጅ አላሰኘውም…” ልትሉ የምትችሉ ወዳጆቼ መከራከሪያችሁ ይገባኛል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…ጓደኞቼ ለምትላቸው ታማክራለች፡፡
“አንቺ እዛ መሥሪያ ቤት ምን ይጎልትሻል! ትተሽላቸው ሂጂ…”  
“የቢሮውን ቁልፍ አፍንጫቸው ላይ ወርውሪላቸውና ሌላ ቦታ እጅሽን ስመው ነው የሚቀበሉሽ…” ይባላል፡፡ ምንም ይሁን ምን ውጤቱ እነሱን አይነካቸውማ! እሷ ሥራ አጥታ ብትከርም የእነሱ ቤት አይጎድልማ!
ይህንኑ ጉዳይ ለቤተሰብ ታማክራለች…
“ኸረ አንዱ የመሥሪያ ቤቱ ባለስልጣን አጉል ጥያቄ እየጠየቀ አላስቀምጥ ብሎኛል! ራሱ መሥሪያ ቤት መሄድ እያስጠላኝ ነው፡፡ ምን ባደርግ ይሻላል?” ትላለች፡፡ ቤተሰብም ሀሳብ ያዋጣል…
“እስቲ ሳትቸኩይ ነገሩን ረጋ ብለሽ ያዢው፣ ሰውየው አላርፍ ካለ ለበላይ ማሳወቅ ነው…”…
“እለቃለሁ ካልሽ እንኳን መጀመሪያ የምትወድቂበትን አዘጋጅተሽ ነው እንጂ ዝም ብለሽ ቦርሳሽን አንጠልጥለሽ መውጣት አይደለም…”
“ሥራ ፍለጋ ስትንከራተቺ ልጆችሽን እንዳታስርቢ...” ምናምን ይባላል፡፡ እሷ ሥራ ብትለቅ በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም እነሱን ይነካቸዋላ! ሥራ አጥታ የወር ገቢዋ ተቋርጦ ሦስት ልጆቿ ቢራቡ፣ እነሱን በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም ይነካቸዋላ!
እናማ…‘ምክርና ቁርስ ከቤት’ መሆኑን ረስተን መከራችንን እናያለን፡፡
ስሙኝማ…በዛ ሰሞን አዲስ የቱሪዝም መፈክር፣ አዲስ አርማ ነገር ወጥቶ ነበር፡፡ ምን ገረመሀ አትሉኝም… ነገርዬው ውስጥ ‘የውጪ አማካሪዎች’ ምናምን የሚባለው ነገር! ቆይ…የውጪ አማካሪ ስለዚህ ነገር እኛን ሆኖ ምን ሊያውቅ ይችላል! በየቦታው ስንት ቃላቸው መሬት ጠብ የማይል እውነተኛ አገር ወዳድ የአገር ሽማግሌዎች እያሉ! “እንዲህ ብናደርገው፣ እንደዛ ብናደርገው እኛነታችንን ይበልጥ ይገልጻል…” ብለው ከታሪክም፣ ከባህልም፣ ከትውፊቱም ከምኑም አጣምረው መናገር የሚችሉት እያሉ! ኮሚክ እኮ ነው…‘ፈረንጅ’ ስለ የ‘ሰርቲን መንዝስ ኦፍ ሰንሻይን’ እውነተኛ ስሜት ምኑን ያውቅና ነው!
እናማ…‘ምክርና ቁርስ ከቤት’ መሆኑን ረስተን መከራችንን እናያለን፡፡
ሰውየው አከራዩ መከራውን ያበሉታል፡፡ የተሰበረች ወንበር አስጠግኖ በገባ ቁጥር ኪራይ እየጨመሩበት ግድግዳ ላይ ስዕል መስቀል እንኳን ትቶታል፡፡ ገና ኩርንችቱን ሲመታ ሰምተው ኪራይ ይጨምሩበታላ! ጓደኞቼ ለሚላቸው ያማክራል፡፡ እነሱም ‘ይመክሩታል’…
“አንተ ለምን ቤቱን አትተውላቸውም፣ ደግሞ ለኪራይ ቤት!”
“ዛሬ፣ ነገ ሳትል ይስፋችሁ ብለህ ጥለህላቸው ውጣ…”
“አንተ እሱን ቤት ትተህ እንዳትሄድ ግዝት አለብህ እንዴ!”
ምን ይወስን ምን እነሱን አይነካቸውማ! እሱ እቃውን ተሸክሞ “የፖሊስ ያለህ አትሉም ወይ...” ምናምን እያለ ቢንከራተት፣ እነሱን ‘ጥቁር ፍቅር’ን ከመከታተል አያግዳቸውማ! ቂ…ቂ…ቂ…
ችግሩን ለቤተሰብ ያማክራል…
“ሽማግሌው እኮ ሴት ልጃቸውን አስኮብልዬባቸው ቂም የያዙብኝ ይመስል መውጫ መግቢያ አሳጥተውኛል፡፡ ግቢው ራሱ ከርቸሌ እየመሰለኝ ነው፡፡ ምን ትመክሩኛላችሁ?”
ቤተሰብም…
“ካልተመችህማ መልቀቅ ነው፡፡ ግን ሌላ የሚሆንህ ቤት ሳታገኝ ዝም ብለህ በብስጭት ዕቃህን ጭነህ እንዳትውጣ!”
“በአሁኑ ጊዜ ቤት መከራየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ኪራዩም አይቀመስም፡፡ ከመወሰንህ በፊት በደንብ አስብበት…”
“ደግሞ ሌላ ቦታ ቸኩለህ ዘለህ ገብተህ፣ በሁለት ወርህ ሌላ ችግር ውስጥ ከምትገባ፣ ጊዜ ወስደህ አጠያይቀህ ለረጅም ጊዜ የምትቆይበት ቤት አግኝና ከዛ ትለቅላቸዋለህ…” ምናምን ይላል፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእሱ ቤት መልቀቅ ይመለከታቸዋላ! እሱ ሜዳ ላይ ቢወድቅ ችግሩ የእነሱም ይሆናላ!  እሱ ፍራሽና ሳጥን ተሸክሞ፣ ከሰፈር ሰፈር ቢንከራተት፣ የእነሱም ስሜት ይነካላ!
እናማ…‘ምክርና ቁርስ ከቤት’ መሆኑን ረስተን መከራችንን እናያለን፡፡
ስሙኝማ… ‘ቤተሰብ’ ስንል ገና ህሊናቸው ‘ሀክድ’ ያልሆነውን (ቂ..ቂ..ቂ…) ባህሪያቸው በሉሲፈር ያልታገተውን ...ምናምን ማለታችን እንደሆነ ልብ ይባልማ፡፡ መጥፎ ምክር ለመምከር አንዳንድ ቤተሰብ ‘ከባዳ’ ባይብስ ነው!
እናማ…‘ምክርና ቁርስ ከቤት’ መሆኑን ረስተን መከራችንን እናያለን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5156 times