Monday, 26 September 2016 00:00

በ43ኛው የበርሊን ማራቶን ሪከርድ ይሰበር ይሆን?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ከዓለም ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች በተደጋጋሚ  የዓለም ክብረወሰኖች የሚመዘገቡበትና  በአይኤኤኤፍ ከጎዳና ላይ ሩጫዎች የወርቅ ደረጃ  ያለው የበርሊን ማራቶን ነገ ለ43ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡የኬንያ እና የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች ከባድ ትንቅንቅ በሚታይበት የበርሊን ማራቶን በተለይ በወንዶች ምድብ በተለይ በረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ ሯጭ  ቀነኒሳ በቀለ እና የቀድሞ የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ዊልሰን ኪፕሳንግ ፉክክር ሲያነጋግር ሰንብቷል፡፡  የዓለም ሪከርድ ሊመዘገብ እንደሚችልም ተጠብቋል፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት 7 የዓለም የማራቶን ሪከርዶች በበርሊን ማራቶን ተመዝግበዋል፡፡ ዘንድሮም አዲስ ክብረወሰን የሚጠበቅ ቢሆንም ሲያነጋግርየቆየው ማን ያሸንፋል የሚለው አጀንዳ ነው፡፡ በ43ኛው የበርሊን ማራቶን ከሪከርድ ይልቅ ከ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች በታች ሊገባ እንደሚችል የውድድሩ ዲያሬክተር በሰጡት አስተያየት  ተናግረዋል፡፡
በ43ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ በተለያዩ የውድድር መደቦች የሚሳተፉት ከ58ሺ  በላይ ሯጮች ሲሆኑ ከ127 አገራት በላይ የተውጣጡ ናቸው፡፡ ውድድሩ በበርሊን ጎዳናዎች ሲካሄድ እስከ 1 ሚሊዮን ታዳሚዎች እንደሚያገኝ እና እስከ 417ሺ ዶላር የሽልማት ገንዘብ እንደተዘጋጀለት ማወቅ ተችሏል። በበርሊን ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች በነፍስ ወከፍ የ50ሺ ዶላር ሽልማት ያገኛሉ፡፡
በ43ኛው የበርሊን ማራቶን በወንዶች ምድብ አዲስ ክብረወሰንሊመዘገብ እንደሚችል በአንዳንድ ዘገባዎች የተጠበቀው በተለይ በቀድሞው የሪከርዱ ባለቤት ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ እና ቀነኒሳ በቀለ በሚኖራቸው ፉክክር ነው፡፡ በሌላ በኩል በማራቶኑ በወንዶች ከሚሳተፉ ምርጥ ማራቶኒስቶች   2 ሰዓት ከ6 ደቂቃዎች በታች የሚገቡ 7 አትሌቶች መኖራቸው  የተጠቀሰ ተጨማሪ ምክንያት ነው።  በ2013 እኤአ ላይ በስፍራው የዓለም ማራቶን ሪከርድን በ2፡03፡23 አስመዝግቦ የነበረው የኬንያው ዊልሰን ኪፕሳንግ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ዋንኛ ትኩረቱ የዓለም የማራቶን ክብረወሰንን ደግሞ መረከብ መሆኑ የገለፀ ሲሆን ሲያደርግ የቆየው ዝግጅት ልበ ሙሉ እንዳረገው ተናግሯል፡፡ ከትራክ ውድድሮች ከወጣ በኋላ 5ኛ የማራቶን ውድድሩን የሚያደረገው ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉለበርሊንማራቶንያደረገው ልምምድከጉዳት የነፃ በመሆኑፈጣንሰዓቱን በማሻሻል ሊሮጥ እንደሚችል ተናግሯል፡፡ ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ  ዊልሰን በ2010 እና በ2011 የፍራንክፈርት ማራቶንን ፤ በ2012እና በ2014 የለንደን ማራቶንን፤ በ2013 የበርሊን፤ በ2014 ደግሞ የኒውዮርክ ማራቶኖችን ለማሸነፍ የቻለ እንዲሁም በ2012 እኤአ ላይ በለንደን ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳልያ ያገኘ ምርጥ ማራቶኒስት ነው፡፡  ከ2 ዓመት በፊት በፓሪስ የመጀመርያውን ማራቶን ሲሮጥ በ2፡05፡04 በሆነ ጊዜ የግሉን ፈጣን ሰዓትና የቦታውን ክብረወሰን  አስመዝግቦ ያሸነፈው የረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ በሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን ካልተሳተፈበት አወዛጋቢ ምርጫ በኋላ በልበሙሉነት የሚሮጥበት ውድድር ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በሚሮጥበት የበርሊን ማራቶን ምርጥ ብቃት ሊያስመሰክር እንደሚችል እየተዘገበ ሲሆን የ34 ዓመቱ ቀነኒሳ ለወድድሩ አዘጋጆች በሰጠው አስተያየት፤ 80 በመቶ ሙሉ ብቃቱ ላይ እንደሚገኝ ተናግሮ፤ በፈጣን ሰዓት ማራቶንን መሮጥ እንደሚችልና እውቀቱ እንዳለው ገልፆ በማራቶን የእኔ ግዜ ይመጣል ሞራሌም ይሄው ነው ሲል ተናግሯል፡፡  አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2014 እኤአ ላይ በፓሪስ ማራቶን ካሸነፈ ካሸነፈ በኋላ በተመሳሳይ አመት በቺካጎ ማራቶን 4ኛደረጃ አግኝቶ እንደነበር ሲታወስ፤ በዱባይ ማራቶን በ2015 እኤአ አቋርጦ ከወጣ በኋላ በ2016 እኤአ ደግሞ በከባዱ የለንደን ማራቶን በ3ኛ ደረጃ መጨረሱ አይዘነጋም፡፡
ከዊልሰን ኪፕሳንግ እና ከቀነኒሳ በቀለ ባሻገር  በወንዶች ምድብ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው በ2014 እኤአ ላይ በተመሳሳይ ከተማ የኬንያው ዴኒስ ኪሜቶ አሁን የተያዘውን የዓለም ማራቶን ሪከርድ ሲያስመዘግብ በ2ኛ ደረጃ የጨረሰው ሌላው ኬንያዊ ኢማኑዌል ሙታይ ከተሳታፊዎቹበፈጣንሰዓቱ የመጀመርያው ነው፡፡ በ2014 እኤአ ላይ በዱባይ ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ32 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በወጣቶች ምድብ የምንግዜም ፈጣኑን ሰዓት በማስመዝገብ ያሸነፈው ኢትዮጵያዊ ፀጋዬ መኮንን የበርሊን ማራቶንን ለመጀመርያ ጊዜ በመሮጥ እንደሚያሸንፍ ግምት አግኝቷል፡፡  ሲሳይ ለማ ሌላው ተሳታፊ የኢትዮጵያ አትሌት ሲሆን ቪንሰንት ኪፕሮቶ፤ ኤልውድ ካኑዊ እና ኢማኑ ቺቤት ተፎካካሪነታቸው የሚጠበቅ ሌሎች የኬንያ አትሌቶች ናቸው፡፡
በሴቶች ምድብ የበርሊን ማራቶን የሚሮጡት አራቱ ኢትዮጵያውያን አበሩ ከበደ፣ አማኔ በሪሶ፣ ብርሃኔ ዲባባና ሩቲ አጋ ሲሆኑ በተለይ በበርሊን ማራቶን ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ የምትሳተፈው እና ባለፉት ሶስት ተሳትፎዎቿ ሁለቴ ያሸነፈችውና አንዴ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው አበሩ ከበደ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷታል፡፡ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች በተለይ አማኔ በሬሶ እና ብርሃኔ ዲባባ በ43ኛው የበርሊን ማራቶን ከአበሩ ቀጥሎ በ2ኛ እና በ3ኛ ደረጃ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ ምርጥ ሯጮች ናቸው፡፡
በበርሊን ማራቶን ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 እኤአ ለአራት ተከታታይ ጊዜያት ያሸነፈው እና ሁለት ጊዜ የዓለም ክብረወሰኖች ያስመዘገበው ኢትዮጵያዊው ኃይለ ገብረስላሴ ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ሌላ ኢትዮጵያዊ አትሌት አሸንፎ አያውቅም፡፡ በተለይ ከ2010 እኤአ ጀምሮ ባለፉት 5 የበርሊን ማራቶኖች ኬንያውያን ሲያሸንፉ 4 ጊዜ ክብረወሰኖች የተሻሻሉ ሲሆን በ2015 እኤአ አሸናፊ የነበረው አሁን የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃውሌላው ኬንያዊ ኤልውድ ኪፕቾጌ ነበር፡፡ በሴቶች ምድብ በበርሊን ማራቶን ታሪክ በርካታ የኢትዮጵያ ሴት ማራቶኒስቶች አሸንፈዋል፡፡ የመጀመርያውን ድል ለኢትዮጵያ ያስመዘገበችው በ2006 እኤአ ጌጤ ዋሚ ስትሆን በ2007 እኤአ ላይም ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ ነበረች፡፡ ከጌጤ በኋላ በ2009 እኤአ ላይ አፀደ ሃብታሙ፤ በ2010 እና በ2012 እኤአ ላይ ለሁለት ጊዜያት አበሩ ከበደ እንዲሁም በ2014 እኤአ ላይ ትርፌ ፀጋዬ አሸናፊዎች ነበሩ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን 42ኛውን የበርሊን ማራቶን ያሸነፈችው ኬንያዊቷ ግላዲስ ቼሮኖ ነበረች፡፡
ባለፉት 11 ዓመታት በወንዶች ምድብ 7  የዓለም ማራቶን ሪከርዶች በበርሊን ማራቶን ተሰብረዋል፡፡  በ2003 እኤአ ላይ ኬንያዊው ፖል ቴርጋት በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ55 ሴኮንዶች፤ በ2007 በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ26 ሴኮንዶችና በ2008 እኤአ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሴኮንዶች ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገብረስላሴ የዓለምሪከርዶቹ ተመዝግበው ነበር፡፡ ከኃይሌ ገብረስላሴ በኋላ በበርሊን ማራቶን ኬንያውያን በተከታታይ የሪከርድ መዝገቡን ተቆጣጥረውታል፡፡ በ2011 እኤአ በ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ38 ሴኮንዶች  ፓትሪክ ማኩ፤ በ2013 እኤአ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ23 ሴኮንዶች  ዊልሰን ኪፕሳንግ እንዲሁም በ2014 እኤአ በ2 ሰዓት ከ02 ደቂቃዎች ከ57 ሴኮንዶች ዴኒስ ኪሜቶ ናቸው፡፡
ከ2 ዓመታት በፊት በተካሄደው 41ኛው የበርሊን ማራቶን የ31 ዓመቱ ኬንያዊ ዴኒስ ኪሜቶ ርቀቱን ከ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች በታች በመግባት አሁን ያለውን የዓለም ሪከርድእንደያዘ ሲሆን በወቅቱ ማራቶኑን ከ2ሰዓት 03 ደቂቃዎች በመግባት የመጀመርያው ሰው ተብሎ ተደንቆ ነበር፡፡ የዓለም ሪከርድን ሲይዝ ወቅት ማራቶን መሮጥ ከጀመረ ገና የ5 ዓመታት ልምድ የነበረው  ዴኒስ ኪሜቶ፤ በወቅቱ ያስመዘገበው አዲስ የማራቶን ክብረወሰን 2 ሰዓት ከ02 ደቂቃዎች ከ57 ሴኮንዶች ሲሆን በ2013 እኤአ ላይ በሌላው ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሳንግ ተይዞ ከነበረው ሪከርድ ላይ 26 ሰከንዶችን ያሻሻለበት ነበር፡፡ ዴኒስ ኪሜቶ በሪከርዱ የተሳትፎ እና የስፖንሰር ክፍያዎችን ሳይጨምር እስከ  154ሺ ዶላር ክፍያ ማግኘቱን በወቅቱ ያመለከቱ ዘገባዎች በውድድሩ አሸናፊነት 40ሺ ዶላር፤ ከ2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች ስለገባ የ30ሺ ዶላር ቦነስ እንዲሁም ለሪከርዱ 50ሺ ዶላር እንደተከፈለው አትተዋል፡፡
ዴኒስ ኪሜቶ የራሱን ሪከርድ የማሻሻል አቅም እንዳለው ተናግሮ፤  በሚቀጥለው ውድድር 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ልገባ እችላለሁ ብሎ ነበር፡፡ በበርካታ ጥናቶች በተሰሩ ትንታኔዎች 42.195 ኪሎሜትሮች (26 ማይሎች እና 385 ያርዶች) የሆነውን የማራቶን ርቀት ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት  እስከ 30 ዓመታት ሊፈጅ ይችላል ተብሎ ነበር፡፡

Read 1182 times