Monday, 26 September 2016 00:00

የአክሱምና ላሊበላ ሙግት

Written by  ቃልኪዳን ኃይሉ
Rate this item
(5 votes)

       አክሱምና ላሊበላ ጠበኞች ናቸው፡፡ ይህ ጠባቸው አንዴ ሲካረር፤ አንዴ ሲበርድ፤አንዴ በሰፈር ሽማግሌዎች ሲታረቁ፤ አንዳቸው ወደ አንዳቸው ሽማግሌ እየላኩ ለመምከር ለመዘከርና ወደ ራሳቸው ግል ጠባይ እንዲቀርቡ ለማድረግ ብዙ ጥረዋል፡፡ ቢሆንም ይብስ ጠባቸው ተካረረ እንጂ ወደ አንድነት ሊመጡ አልቻሉም፡፡ መካረሩ በሰፈር ሽማግሌ አልፈታ አለ፤እንዲያውም እየተባባሰ ሄዶ መናናቅና ጥላቻን ፈጠረ። ስለዚህም ነው በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ የህግ ሊቃውንትና ሽማግሌዎች ፊት ሊዳኙ የቆሙት፡፡
ላሊበላ ከጉልበቱ ሸብረክ ሸብረክ እያለ በሊቃውንቱና ሽማግሌዎች ፊት አክብሮቱን ያሳያል። አክሱም ደግሞ በላሊበላ አኳሃን ሳቅ አፍኖ ይዞታል፡፡ ስለዚህ በረዥም ቁመቱ እየተንጎማለለ  ሳቁን ተቆጣጥሮ በመወዛወዝ ለመሸወድ ሞከረ። እሱ አልሆን ሲለው ትልቅ ሞባይሉን ከኪሱ አወጣና ወዲያ ወዲህ እያለ ስልክ ሳይደወልለት ወይም ሳይደውል ዝም ብሎ ጆሮው ላይ አድርጎ ያወራ ጀመር፡፡ ለዳኝነት ከተቀመጡት አምስቱ ሊቃውንትና ሽማግሌዎች ውስጥ መሀል ላይ ያሉት በነጭ ሸማቸው ላይ ጥቁር ካባ ያደረጉት፤በቀኝ እጃቸው ጭራ ይዘው ወዲያ ወዲህ የሚወዘውዙት ባለ ነጭ ጢማሙ ሽማግሌ፤ “እህህህህምም…” ብለው ጉሮሯቸውን ጠራረጉ፡፡ ይኸኔ አክሱም ደንገጥ አለና ስልኩን ኪሱ ከትቶ፣ ሁለት እጆቹን ወደ ኋላ አጣምሮ፣ ፊቱን ወደ ሊቃውንቱ አዙሮ ቆመ፡፡
መሀል ላይ ያሉት ሊቃውንት፤ “እስኪ ጉዳያችሁን ንገሩን፤ ምንድነው እናንተን የሚያክል በእድሜ አንቱ የተባለ፤ ለሌላው መካሪ ዘካሪ ይሆናሉ የተባላችሁ ቀደምቶች ያጣላችሁ?” ሲሉ ጠየቋቸው፤ ላሊበላና አክሱምን ተራ በተራ እየተመለከቱ፡፡
አክሱም፤ ላሊበላ ሳይቀድመው ተቻኩሎ፣በዚያ በረዥሙ ቁመናው እየተውረገረገ መናገር ጀመረ፡-
“አባቶቼ! እኔና ላሊበላ የተቀያየምነው በተክለ ሰውነታችን ነው፡፡ ላሊበላ ችግር አለበት፤ተክለ ሰውነቱ ዘመኑን የዋጀ አይደለም፤ ዝም ብሎ ከመሬት ውስጥ ተቀብሮ ማንንም ምንንም አላይም ብሎ ዋሻ ውስጥ ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ መቃብር ውስጥ ምን ይሰራል፤ እንደ እኔ ውጪ ወጥቶ በአለም ላይ አያንጸባርቅም፤ የምን ሳይሞቱ መቀበር ነው፤ ሕያው ሆኖ የተቀበረ እሱን አየሁ፤ ያውም ፈቅዶና ፈልጎ፡፡ ከመሬት ምን አለው፤ለምን ቀና አይልም?
“በመጀመሪያ ውጣና አንተም ለሰው ታይ፤ አንተም ሰውንም አለምንም እይ አልኩት፤ በጄ ሊለኝ አልቻለም፤  ይብሱኑ መስቀሉን ከላዩ ላይ አድርጎ ቀና ብሎ እንኳ መልስ ሊሰጠኝ አልቻለም፤ ምንም ሊሰማኝ አልቻለም፤ ዝም ብሎ ዳዊት ይደግማል፤ ያስቀድሳል፤ እግዚኦ  እግዚኦ ይላል፡፡ ይህን ምግባሩንም ሆነ ግብሩን አልወደድኩለትም፤ ለሁሉ ነገር አጎንብሶ እንዴት ይገፋዋል፤ ዘመኑ ደግሞ የሚጎነበስበት ሳይሆን ቀና የሚባልበት ነው፤ የዘንድሮ ሰው እንኳን ተጎንብሶለት እንዲህ እንደኛ እንኳ ቀጥ ተብሎም አይቻልም። እላያችን ላይ ሊፈናጠጥ የማይፈነቅለው ድንጋይ፤ የማያስነሳው አቧራ፤ የማይዘረጋው ኔትወርክ፤ የማያመጣው መሰላል… የለም፡፡ በዚህ ዘመንና በዚህ ትውልድ መሃል እየኖሩ ጎንበስ ጎንበስ ማለት መልካም አይደለም፤ አንድም አለመታየትን አንድም ደካማነትን ያሳያል፤ ማጎንበስ ጥሩ አይደለም፤ ሽንፈት ነው፤የውድቀት ምልክት ነው፤ የምን ማጎንበስ ነው፤ ደረትን ገልብጦ መሄድ ነው እንጂ---” እንዲህ እያለ አክሱም ሲደሰኩር የእጅ ስልኩ ጠራ፤ ጩኸቱም ዳኞቹንና ላሊበላን በጠበጠ፡፡ አክሱም ደንገጥ ብሎ ስልኩን አወጣና ሊያጠፋው ሞከረ፡፡ ግን አልጠፋ አለው። ይኼኔ የስልኩን ባትሪ ነቀለውና ዲስኩሩን ቀጠለ፡፡
“…ይቅርታ! ይቅርታ? አባቶቼ በስህተት ነው… እና ነገሬን ስቀጥል በዚህ ዘመን ዝናብ ከሌለ በተለይ ጥሩ አድርጎ የሰውነት ቅርጽን የሚያሳይ ልብስ ሰውነት ላይ ጣል አድርጎ፣ ጥሩ ሰውነትን እያሳዩ መሄድ ነው እንጂ የምን ማጎንበስ ነው፤ ስለምኑስ ነው ነጠላ መስቀለኛ ተከናንቤ ጎንበስ ጎንበስ እያልኩ የምሄደው? እኔ ይህ የምታዩት ቅርፅ…” እላዩ ላይ ያሉትን ፍልፍሎች ጎንበስ ብሎ ለሊቃውንቱ እያሳያቸው ንግግሩን ቀጠለ፡፡
“ይህ የምታዩት ቅርፅ አባቶቼ የሰሩልኝ እንዲታይ እንጂ እንዲሸፈን አይደለም፤ ሰዎች እያዩ እንዲያደንቁና እንዲደነቁ እንጂ እንዲሸማቀቁና እንዲሳቀቁ አይደለም፤ እራስን ከምንምና ከማንም በላይ አጉልቶ ማሳየት ትልቅነትንና ታላቅነትን ይመሰክራል፡፡ እኔ የዚህች ሀገር የትንሽነት ሳይሆን የትልቅነት ምልክት ነኝ፤ የማነስ ሳይሆን የከፍታ ማሕተም ነኝ፤ የስርቻ ሳይሆን የማማ ላይ ነጸብራቅ ነኝ፤ የአይሆንም ሳይሆን የይሆናል ፈር ቀዳጅ ነኝ፤ ትውልዱ የሚወደውና የሚከተለው እኔን ነው። አንድም እታያለሁ አንድም ስኬትን አሳያለሁ፡፡ ይህ ለእኔ ደስታ ነው፡፡ ለትውልዱም ተስፋና ኩራት ነው፡፡
“ስለዚህም እንደ ላሊበላ ማጎንበስን አልፈልግም፤ ማጎንበስ አንድም ሁሉን እሺ እሺ እያሉ የመቀበል፤ አንድም የሽንፈትና ምንም አላውቅም ስሜት ነው። ይህ ድካምና ሽንፈትን ለትውልዱ ያስተጋባል፤ ትውልድ በእችላለሁና ሁሉን በማድረግና በማወቅ መንፈስ እየተሞላ ማደግ አለበት እንጂ እሺ እሺ እያለ ለሁሉ አጎንብሶ ማደግ የለበትም፡፡ አባቶቻችንም አድዋና ማይጨው ላይ ዋጋ የከፈሉት ለማንም እንዳንሸነፍ፤ ለማንም እንዳንገዛ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ውጤት የመጣው አንጋጠው እኔን እያዩ ነው፤ እኔ የድል ምልክት ነኝ፡፡ ላሊበላ ግን እንደዚያ አልነበረም፡፡ ለሁሉም ማጎንበስ ይወዳል፤ ለሁሉም ፆም ፀሎት ያበዛል፡፡ ይህ መልካም አይደለም፡፡ ሀገር በጾም በጸሎት አትቀናም፤ ልማት እራስን በማድከም አይመጣም፤ ማንነት እሱ ብቻ አዋቂ ነው እያሉ የራስን እውቀት በመደበቅ ወይም ራስን በማሳነስ  አይደለም፡፡ ዘመኑንና ዘመናዊነትን መከተል ግድና አስፈላጊ ነው፡፡ ካልሆነ እንቀደማለን፤ መቀደም በጣም አልወድም፡፡ ለዚህም ነው ላሊበላንም ሆነ መሰል ወዳጆቹን እንዲዘምኑ እንዲነቁ የምጎተጉተው፡፡”
ላሊበላ በጥሞናና በእርጋታ እራሱን ስሜት ውስጥ ሳይከት፣ የአክሱምን ንግግር ጭንቅላቱን በአሉታ እየነቀነቀ እያዳመጠ ነበር፡፡ ከፊት ለፊት የተቀመጡት ሊቃውንትና ሽማግሌዎችም እንዲሁ ነገሩን በጥሞና ማዳመጥ ይዘዋል፡፡ ልክ አክሱም ተናግሮ መጨረሱን ዝም በማለት ሲገልፅ፤ “ጨረስክ?” አሉ ከቀኝ በኩል ዳር ላይ ያሉት ሽማግሌ፡፡
“አዎ አባቶቼ” አለ አክሱም ከወገቡ አጠፍ ብሎ። አክሱም ሲያጎነብስ ጭንቅላቱ ሽማግሌዎቹ ጋር ሊደርስ ምንም አልቀረውም ነበር፡፡
መሀል ላይ ያሉት ሽማግሌ፤ “መልካም ላሊበላ አንተም ጉዳይህን መናገር ትችላለህ ቀጥል” አሉት
“እሺ!” አለ ላሊበላ በትህትና እንዴት እንደሚቆም ግራ ገብቶት እየተሽቆጠቆጠ፡፡
እንደምንም እራሱን አረጋጋና ቆሞ ማማተብ ጀመረ፤ “በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን” አለና ንግግሩን ጀመረ፡፡
“እሺ አባቶቼ፤ ከእናንተ ፊት ቆሜ በአንደበቴ እንድናገር ስለተፈቀደልኝ፣ የተሰማኝን ጥልቅ ደስታ እንዲሁም አክብሮት የምገልፅበት ቃል የለኝም” ብሎ ሊወድቅ ያለውን ነጭ ሸማውን በትከሻና ትከሻው ላይ መልሶ መስቀልኛ እያጣፋ ወደ ንግግሩ ገባ፡፡
አክሱም በሆዱ እንዲህ ሲል ተቸው፤ “እዩት እዩት ሲያካብድ እኔ ያልኩት እኮ ይሄንን ነው፡፡ ዝም ብሎ
ያካብዳል፤ ባካበደ መሰለው እንዴ? ነገሩ እኮ በሆነ ነው፤ ምንድነው እንዲህ ሼባ መሆን? ፈታ አይልም እንዴ? ችግር እኮ አለበት፡፡ ምናለ ወደ አንኳሩ ጉዳይ በፍጥነት ቢገባ፡፡ ዝም ብሎ ስብከት ይወዳል፤ ዘመኑን ሙሉ ስብከት ለምዶ ነገር ባጭሩ መቁረጥ አይደላው፡፡ የምር እንደዚህ አይነት ነገር ይደብራል፤ ካወሩ ነገር ባጭር ባጭሩ አፍታቶ መናገር እንጂ ማማተብ፣ማሸብሸብ… ምንድነው?”
ላሊበላ መናገሩን ቀጠለ፤ “አክሱም ቅድም በእናንተ በአባቶቼ ፊት ቀርቦ የተናገረውን ሀሳብ ለኔም ከዚህ ቀደም ነግሮኛል፡፡ ቢሆንም እንኳን እኔ እሱን ልመስል፤ እሱም ለሆነው ይጨንቀኛል፡፡ ድርጊቱ ሁሉ አለሁ አለሁ፤ እዩኝ እዩኝ ይበዛዋል፤ ከኔ በላይ ማን አለ የሚል ስሜት አለው፡፡ በመጀመሪያ እንዲህ ያለ ተክለ ሰውነት የታደለው በአባቶች እጅ ስራ እንጂ በእሱ ፈቃድና ምርጫ አልነበረም፡፡ ታዲያ እዩት ውበቴን፤ እዩት መልኬን፤ አቋም ተክለ-ሰውነቴን ብሎ የሚኮፈሰው ነገር ጨርሶ አይገባኝም። እንዲህ ያለ ስነምግባር እንኳን የእኛም ታላቅ ከሆነው አክሱም ቀርቶ በዘመናችን የተወጠረ ጂንስ ሱሪ ለብሰው፤ ወንፊት የሆነ ብጫቂ ጨርቅ ከላያቸው ጣል አድርገው፣ ሰውነታቸውን እራሳቸው እንደፈጠሩት እያሰቡ በባዶ ኩራት የሚራመዱ ወጣቶችን ስናይ፣ ልንመክር ልንዘክር ይገባል እንጂ ጭራሽ በአክሱም ቁመናና እድሜ ጨርሶ የሚያምር ነገር አይደለም፡፡
“ስለዚህም የሰውነት አቋሙን እያነሳ ማውራቱ ነውር ነው፡፡ ለዚህ አቋሙ አንድም አስተዋፅኦ ሳያበረክት ኩራትና እብሪቱ መልካም እንዳልሆነ ነግሬዋለሁ። እኔን አልሰማ ቢለኝ ሶፍኡመርን፣ ደመራንና ኮንሶ ትክል ድንጋይን ሽማግሌ አድርጌ አስመከርኩት፡፡ ይባስ ብሎ የኮንሶ ትክል ድንጋይን፤ ‘አንተ እንደ እኔ አይነት አቋም ይዘህ እኔን ማገዝ ሲገባህ፤ እንደ እኔ መሆን ሲገባህ ጭራሽ መልሰህ እኔን ትናገራለህ፤ ጭራሽ እኔን ልምከር ብለህ ትነሳለህ’ ብሎ ኮንሶ ትክል ድንጋይን፤ መልካሙን ገራሙን ወዳጄን፣ ጠባዩን ለወጠብኝ፡፡
“በጣም ነው የደነገጥኩት፤ የአክሱምስ የለየለት ነው፤ የኮንሶ እንዲህ መሆን ግን ይረብሻል፤ደህና አርፎ
የተቀመጠውን ገሩን ወዳጄ ኮንሶን ለወጠብኝ፡፡ ቢጨንቀኝ ለአክሱም ጺዮን ተናግሬ፣ እሷ ነች ኮንሶን
ሄዳ ገዝታው፣ አደብ ገዝቶ፣ ግዝቱም ተነስቶለት በምክርና ተግሳፅ ጸባዩ የተስተካከለው፡፡  ደመራና ሶፍኡመር ከዚያ ወዲያ አክሱም ጋ ድጋሚ ልልካቸው ብል፣ በጄ አልል አሉኝ፡፡ ጥምቀትን  ብልክበት ከስድብ ያልተናነሰ ንግግር ተናግሮ አሳፍሮ መለሳት፡፡  ’ያ ደመራን ጨምሮ ሁላችሁም ችግር አለባችሁ፡፡ ሁሉ ነገር እሱ፣ የእሱ ነው የማለት አባዜ ተጠናውቷችኋል። ሁሉ ነገር በሱ ፈቃድ ነው ትላላችሁ፤ ካለ እሱ ምንም ነገር አታውቁም፤እኔ ከክርስቶስ በፊት አባቱን አብን የማውቅ ነኝ አታካብዱ …’ ብሎ ተናገራቸው፡፡” ላሊበላ አክሱም የተናገረውን በመድገሙ የሚቀሰፍ እየመሰለው አንዴ እያማተበ፤ አንዴ እጁን ወደ ሰማይ እየቀሰረ ነው የሚያስረዳው፡፡
“የፈጣሪን የበላይነት እንዳናምንና ሕልውናውን እንድንጠራጠር ያለውን ብርቱ ፍላጎት ሊጭንብን ይፈልጋል፤ ያየው ሁሉ ያምረዋል፤ ለእሱ ስልጣኔ ማለት መጠቀም የማይችልበትን የእጅ ስልክ ይዞ ከተማ መሀል መፏነን ነው፤ የያዘውን የስልክ ጩኸት እንኳ መቆጣጠር የማይችል፤ ማወቅ ማለት በንግግሩ መሀል የትውልድ ሀገሩን ቋንቋ መጠቀም ሳይሆን በግድም ቢሆን ለጉብኝት የሄደባትን ሀገር ቋንቋ መቀላቀል ይመስለዋል፡፡ ከጣልያን ስልጣኔ ይዞ መምጣት ሲገባው ስብርባሪ የጣልያንኛ ቃላት ይዞ መጣ፤ ምን እሱ ብቻ አባቶቻችን አድዋና ማይጨው ላይ ያሸነፉት እኔን እያዩ ነው ብሏል፡፡ አባቶቻችን ግን በተሸነፉና ጣልያን ለአምስት አመት በቆየ ጊዜ የወሰደውም አክሱምን ነው፡፡ አክሱም ልታይ ልታይ በማለቱ የተረፈው ይሄው ነው፡፡
“ስልጣኔን አንድ ያሉት የእኔና የእሱ አባት ቀድሞ ነው፤ እውቀትን ተመራምረው ከስነፅሁፍ እስከ ምሕንድስና፤ ከህክምና እስከ ሥነ-ከዋክብት፤ ከዜማ መሳሪያ እስከ ሙዚቃ ኖታ ድረስ የቀመሩት የእኔና የእሱ አባት ናቸው፡፡ የአለም ቋንቋ መጀመሪያ የሆነውን ግእዝን አቀላጥፎ የሚናገር ፍጡር፤ መልሶ ደግሞ በንግግሩ መሀል ጣልያንኛና እንግሊዝኛ ጣል እያደረገ ያወራ ጀመር፤ የሰለጠነ መስሎት፡፡ ስልጣኔ ይህ አይደለም፡፡ ስልጣኔ ሌሎችን መምሰል ሳይሆን በትክክል ሌሎችን መብለጥ ማስከንዳት ነው፡፡
“ሌላው እኔን ብዙ ትህትና ያበዛል ይላል፤ቢሆንልኝስ ከዚህም በላይ ትሁት ብሆን መልካም ነው፤ ትውልድ ከእኔ ትህትናን መማር አለበት፤አባቶቻችን ብዙ እያወቁ እንዳላወቁ የሚሆኑት ስለ ትህትና ብለው ነው… ለእሱ ግን ሁሉም ተረት ተረት ነው፤ ለፈጣሪ የዚህ አለም እውቀት ቀልድ፣ ትርፍና እንቶ ፈንቶ ነው፡፡ ይህንን እውቀት እንኳ በቅጡና በምላት ሳያውቅ እንዲሁ በጥራዝ ነጠቅ ከኔ በላይ አዋቂ የለም ይላል። እውቀቱ ለታይታና የታይታ ነው፤ ቁጭ ብለን ብንመረምረው ጥልቀት ይጎድለዋል፡፡ ቁንጽል ነው። እንደዚህ አይነት የላይ ከላይ እውቀት ለወሬ ይመቻል፤ ጥልቅ ስላልሆነ የቀረ እውቀት ያለው አይመስለውም፤ አባቶቼ እናንተ ታውቃላችሁ እውቀት ብዙ ነው፡፡ ታላቁ መጽሐፍም እውቀት በብርቱ መፈለግ እንደሚያደክም በብርቱ ይገልጻል እንጂ አያዘባብትም፤ እውቀት መገለጥስ ያለው ከላይ ነው እንጂ እዚህማ የእውቀት ድንግዝግዙን አይደል የምናውቀው?
“ወደ ነጥቤ ስመለስ ማወቅ አያኮራም፤ ይበልጥ ትሁትና እውቀት ፈላጊ ያደርግ ይሆን እንጂ? እንዲያ ካልሆነ ይህ የሚያስታብይ፤ ከኔ በላይ ላሳር፤ ማን አህሎኝ የሚያስብል እውቀት የጤና ነው ብዬ አልቀበልም፡፡” አክሱም ቱግ ብሎ ተቆጣ፡፡ የሚይዝ የሚጨብጠው ነገር አጣ፡፡ ላሊበላ እንዲህ ደፍሮ የሚናገረው አልመሰለውም፡፡ እንደው ነጠላውን አጣፍቶ የሚሽኮረመምለት ነበር የመሰለው፡፡ ግን ላሊበላ እንዲያ ሊሆንለት አልቻለም፡፡ በቁጣ የአክሱም ግዙፍ ሰውነት መንቀጥቀጥ ጀመረ፤ “አባቶቼ ልብ አድርጉልኝ! ይህ ውቅር እየሰደበኝ ነው፤ እንዲሰድበኝ ደግሞ አልፈቅድለትም፡፡”
መሀል ያሉት ሽማግሌ ተናገሩ፤ “አክሱም አንተን ሰምተናል፤ የፈለከውን ስትናገር ነበር፤ እሱም የፈለገውን የመናገር ነጻነት ልንሰጠው ይገባል፤ አንተም እኮ ቀላል ቃላት አልነበረም ስትጠቀም የነበረው፡፡ ላሊበላ ግን አንገቱን እየነቀነቀ ብቻ ነበር ያዳመጠህ፡፡ አንተም ልታዳምጠው ይገባል፡፡ ባይሆን አይገልፀኝም የምትለው ሀሳብ ካለህ እድሉን በስተመጨረሻ እንሰጥህና እራስህን ትከላከላለህ እንጂ ላሊበላን እንዲህ ተናገር፣ እንዲህ አትናገር እያልን የመናገር ነጻነቱን አናሳጣውም፡፡”
አክሱም እልህና ቁጣ እየተናነቀው እራሱን ተቆጣጥሮ፤ “እሺ አባቶቼ ከቃላችሁ አልወጣም ---- እሺ አባቶቼ” አለ፡፡
ላሊበላ ንግግሩን አገባዶ ስለነበረ፤ “አባቶቼ ይናገር፤ በኔ በኩል ሀሳቤን ጨርሻለሁ፡፡” አለ ከወደ ጎኑ ጎንበስ፤ ከወደ እግሩ ሸብረክ ብሎ እጅ እየነሳ፡፡
ካባ ያደረጉት አባት ጉሮሯቸውን ጠራረጉና ወደ አክሱም እየተመለከቱ፤ “እሺ አክሱም
ቅድም ልትለው የፈለከውን አሁን መናገር ትችላለህ” አሉት፡፡
አክሱም ትንሽ እንደማኩረፍ ብሎ፤ “አይ አባቶቼ ትቸዋለሁ” አለ፡፡
ባለ ካባው አባት፤ “በሉ ከጨረሳችሁ ወዲያ ዞር ዞር በሉ፤ እኛ በጉዳዩ እንመክርና መልሱን እናሳውቃችኋለን” አሉ፡፡
አክሱምም ላሊበላም የፍርድ መልሱ እስኪመጣ በየፊናቸው ዞር ዞር ማለት ያዙ፡፡

Read 2748 times