Monday, 26 September 2016 00:00

‘አቤቱታ ለአንድዬ’ — እንደገና

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

“--- ወንበር ትወዳላችሁ… የስልጣን ወንበር፣ የሀብት ወንበር፣ አድራጊ ፈጣሪ የምትሆኑበት ወንበር ትወዳላችሁ፡፡---”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንኳን አደረሰህ!
አንድዬ፡— ምን አልከኝ! እንኳን አደረሰህ ነው ያልከኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ይቅርታ አንድዬ፣ አስቤው ሳይሆን ልምድ ሆኖብኝ ነው፡፡
አንድዬ፡— ምን ልምድ ሆኖብህ ነው… ጭራሽ የእብሪታችሁ ጥግ እዚህም ደርሶልኛል! እኔኑ እንኳን አደረሰህ ብለኸኝ አረፍከው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አትቆጣ እንጂ…የአንተ ቁጣ እኮ በጣም ያስፈራናል!
አንድዬ፡— እውነት! እንዴት አይነት ደግ ነገር ተናገርክ እባክህ! እንደውም ልንገርህ አይደል ዘንድሮ እኔ ነኝ እናንተን መፍራት ያለብኝ!
ኸረ አንድዬ እንደሱ አትበል…ይሄን ያህል ምን ብናስቀይምህ ነው!
አንድዬ፡— እንዳያያዛችሁ ነገ ተነገ ወዲያ መጥታችሁ ከመንበርህ ተነስ ሳትሉኝም አትቀሩም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ ይቅር ይበ…ይቅርታ አንድዬ ልምድ ሆኖብኝ ነው፡፡ እንደሱ አታስብ…አዲስ ዓመት ሆኖ ምነው ቁጣ፣ ቁጣ አለህ! ይኸው ዓመቱን ሙሉ ተቆጥኸን ከረምክ አይደል!
አንድዬ፡— እኔው ነኝ ተቆጥቻችሁ የከረመኩት! እናንተ ሰዎች ምን ባደርጋችሁ ይሻላል  ለምንድነው የራሳችሁን ጉድ ራሳችሁ የማትችሉት?  ለምንድነው ማላከክ የምትፈልጉት?
አንድዬ፡— ቆይ አታቋርጠኝ…ጥፋት አጥፍታችሁ፣ የራስጌውን ግርጌ፣ የግርጌውን ራስጌ አድርጋችሁ ስታበቁ ሌላ ላይ ለመላከክ ይቀናችኋል! የእናንተ ታሪክ ሁሉንም ነገር ሌላው ላይ የመላከክ ታሪክ ሆኖ ይቅር!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በቃ መቼም ስጋ ለባሽ ሆነን ጥፋት መች ይቀራል!
አንድዬ፡— እኮ እንደ እሱ ካላችሁ ለሁሉም ነገር የምትወነጅሉት ሌላ ሰው የምትፈልጉት ለምንድነው! እኔማ አንዳንዴ እኮ ‘ይቺ አመልካች ጣትን ባልፈጥርላቸው ይሻል ነበር?’ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንደሱ አታምርር እንጂ…
አንድዬ፡— ይኸው ስንት ዘመናችሁ አንዳችሁ በሌላኛችሁ ላይ ጣት ስትቀስሩ… መቼ ነው ‘የእኔ ጥፋት ነው፣’ ‘እኔ ነኝ ችግሩን የፈጠርኩት’ ማለት የምትለምዱት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እውነትም ይህን ያህል ታዝበኸናል!
አንድዬ፡— መቼ ነው ለገዛ ሥራችሁ ኃላፊነቱን የምትወስዱት! መቼ ነው ‘እኔው ያጠፋሁትን እኔው አስተካክላለሁ’ የምትሉት! መቼ ነው አቅም ሲያንሳችሁ ‘አቅም አንሶኛል፣ አቅም ያለው ይምጣ’ የምትሉት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን መሰለህ…
አንድዬ፡— ስማ…ችግራችሁ ምን እንደሆነ ልንገርህ አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደሱማ ደስ ይለኛል…
አንድዬ፡— ችግራችሁ ብዙዎቻችሁ መገኘት የሌለባችሁ ስፍራ ላይ መሆናችሁ ነው፡፡ የማትችሉት ውስጥ እየገባችሁ ይቺን መከረኛ አገራችሁን መከራዋን ትደራርቡባታላችሁ፡፡ ከዛ ማጣፊያው ሲያጥራችሁ ወደ እኔ ማንጋጠጥ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አልገባኝም..
አንድዬ፡— ይግባሀ እንጂ… ለምን አይገባሀም! ወንበር ትወዳላችሁ… የስልጣን ወንበር፣ የሀብት ወንበር፣ አድራጊ ፈጣሪ የምትሆኑበት ወንበር ትወዳላችሁ፡፡ ለሌላው የምታስቡ፣ ለሌላው የምትለፉ አስመስላችሁ የራሳችሁን ጎን የምታሰፉበት ወንበር ትወዳላችሁ፡፡ እዛ ወንበር ላይ ተቀምጣችሁ መሠራት ያለበትን አታውቁም፡፡ ብታውቁም የራሳችሁን ጥቅም የሚነካ ስለሚመስላችሁ እንዲች ብላችሁ አትሞክሩትም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ አበዛብህን
አንድዬ፡— ደግሞ ገንዘብ ትወዳላችሁ፣ ገንዘቡን ግን በላባችሁ፣ በወዛችሁ ከማግኘት ይልቅ ሌላው የለፋበትን አደናግራችሁም፣ አምታታችሁም ትወስዳላችሁ፡፡ መቧደን ትወዳላችሁ፣ የአገር ልጆች እየተፈላለጋችሁ ሌላውን ባይተዋር ታደርጉታላችሁ፡፡ ባዶ ጉራ ትወዳላችሁ፣ አንዲት ጠጠር ማንሳት ሳትችሉ፣ የጂብራልታርን አለት የምትነቀንቁ ይመስል ጉራ ትወዳላችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱን እውነትህን ነው…
አንድዬ፡— ቆይ ተረጋጋ፣ ስነግርህ አዳምጥ እንጂ! ሌላው ትልቁ ችግራችሁ ይኸው ነው፣ ማዳመጥ አትችሉም፡፡ የምታዳምጡት ራሳችሁን ብቻ ነው፡፡ ሁሉን አዋቂ፣ ሁሉን መስካሪ እናንተው ብቻ ናችሁ፡፡ ቆይ… ለእናንተ የፈጠርኩት ጆሮ ለሌላው ከፈጠርኩት የተለየ ነው! የሌላው ጆሮ የተላከለትን እየተቀበለ ወደ አእምሮ ሲያስተላልፍ የእናንተ ጆሮ የሚመልስው የሚያነጥር ጎማ አድርጌለታለሁ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እኛ እኮ ይህን ሁሉ የሆንነው፣ ይህን ሁሉ መከራ የምናየው አንተ ተቆጥተኸን እያልን ነው…
አንድዬ፡— አልኩህ እኮ…ምድር ላይ የምታሳብቡበት ስታጡ ጣታችሁን ወደ እኔ… ‘እሱ ተቆጥቶ ነው ትላላችሁ፡፡ ለዚህ እኮ ነው የምድሩን ወንበር ሁሉ አስለቅቃችሁ ስታበቁ፣ የእኔን ወንበር ሳትመኙ አትቀሩም የምልህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ፣ ምንም ያህል ብናበዛው እዚህ ደረጃ አንደርስም! ሲቸግረን እኮ ነው ወዳንተ አቤት የምንለው! አንድዬ ምን መሰለህ… ክፋት በዛ፣ ሰው ለሰው መጨካከን በዛ…አንድዬ የሆነ ነገር አድርግልን እንጂ!
አንድዬ፡— እኔ ምን ላደርግላችሁ እችላለሁ… ተጨካከኑ አልኩ! አንዳችሁ ለሌላው ጉድጓድ የምትቆፍሩበት ዶማና አካፋ አቀበልኩ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደ እሱ ሳይሆን አንተ አለሁ ካላልከን እኮ ነገን ፈራነው!
አንድዬ፡— እኮ ነገን ከፈራችሁ ማስታካከሉ የእናንተ ፈንታ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ያላንተ እርዳታ ምንም ማድረግ አንችልማ፣ አንተ ጎናችን ከሌለሀ ጉልበት የለንማ!
አንድዬ፡— እናንተ እኮ ለእኔም አልተመለሳችሁ…የእብሪታችሁ ብዛት እኮ እኔንም ቤቴ ድረስ መጥታችሁ ልታሙኝ ትፈልጋላችሁ፡፡ አታላችሁም፣ ሌላውን አስለቅሳችሁም ላገኛችሁት ገንዘብ ለእኔ የምስጋና ስለት የምታገቡ ጉዶች ናችሁ እኮ! እኔው ቤት በር ላይ ቆማችሁ… ‘እከሌን እንዲህ ካላደረግህልኝማ የለህም ማለት ነው…’ እያላችሁ በክፋታችሁ ልታነካኩኝ የምትሞከሩ ጉዶች ናችሁ እኮ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ከመሀላችን አንዳንዶች ናቸው እኮ እንዲህ በአንተ ፊት የሚያሳጡን!
አንድዬ፡— የአንዳንድ ሰው ነገር ቢሆን ኖሮማ፣ አገሪቷን እንዲህ አታደርጓትም ነበር፡፡ እንዲህ ዓለም ሁሉ አይጠቋቆምባችሁም ነበር፣ እኔንም እጄ በሌለበት ነገር ‘ከልጅ ልጅ ይለያል፣’ አታስብሉኝም ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ቢሆንም አንድዬ መቼም ሜዳ ላይ ለጅብ ጥለኸን አትሄድም…
አንድዬ፡— ስማ…ችግሬ እኮ እሱ ነው፣ አሁን እኮ ነገራችሁ ሁሉ ልገምተው ከምችለው በላይ እየሆነብኝ አውሬና ሰዉንም መለየት ሊያቅተኝ ነው፡፡ እስቲ…በገዛ ፍጡሬ እንዲህ ልቸገር!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ኸረ ይሄን ያህል ተስፋ አትቁረጥብን…
አንድዬ፡— ብቻ የዘንድሮ ነገረ ሥራችሁ ሁሉ ስላላማረኝ…መለስ ቀለስ እያልኩ አያችሁ… ይሆናል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሰይ አንድዬ! እሰይ! ዞርክልን ማለት ነው፡፡ አንድዬ እሺ እንደው ይቺን አዲሷን ዓመት እንኳን አንተ ጋ መጥተን እሪ ሳንል፣ አሥሬ በርህን ሳናንኳኳ፣ ዕንባችንን ሽቅብ ወዳንተ ሳንረጭ እንድንኖር እርዳን…
አንድዬ፡— ራሳችሁን እርዱና፣ ከዛ እርዳን በሉኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አንድ ጊዜ፣ አንድ ጊዜ ብቻ በረከቱን አዝንብልንና እንዴት እንደምንሆን ታየናለህ፡፡ ግዴለህም… ምሬያችኋለሁ በለን…
አንድዬ፡— መጀመሪያስ መች እየቀጣኋችሁ ነው አልኩ… መማር አለመማርም የራሳችሁ ጉዳይ ነው፡ በል ደህና ሁን፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ሳታስጨርሰኝ…
አንድዬ፡— የእናንተ ነገር ማለቂያ ስሌለው ተመልሰህ መምጣትህ እንደሁ አይቀር… ያኔ አስጨርስሀለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን መሰለሀ…
አንድዬ አቤቱታ ወደማያበዙ ሰዎች ስለዞረ አልሰማውም፡፡ ምስኪን ሀበሻ ግን እስካሁን እየጮኸ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 3536 times