Monday, 26 September 2016 00:00

ከኢህአዴግ ጋር የተደረገ ምናባዊ ቃለ ምልልስ!! (ቁ-3)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(52 votes)

ጥልቅ ተሃድሶው የባህሪ ለውጥን ይጨምራል ወይስ ባለሥልጣናትን ማባረር ብቻ ነው??
   ኢህአዴግ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ለበርካታ ወራት የዘለቁትን ህዝባዊ ተቃውሞዎችና አመጾች ተከትሎ፣በጥልቅ ተሃድሶ ችግሮችን ለመፍታት እንዳቀደ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ (ብዙዎች ቢጠራጠሩትም!) ተሃድሶው በዋናነት በመንግስት ሥልጣን ተጠቅመው ራሳቸውን ያበለጸጉ ከፍተኛ ሹማምንቱን ከሥልጣን ማባረርን ወይም ማሸጋሸግን እንደሚያካትት ተጠቁሟል፡፡ ሰሞኑን የኦህዴድ ሊቀመናብርትም ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡
ህዝብ ግን ጥቂት ባለሥልጣናትን በማንሳትና በመለዋወጥ የሚረካ አይመስልም፡፡  የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች አቶ ሙክታር እና ወይዘሮ አስቴር ማሞ ራሳቸውን ከሃላፊነት በገዛ ፈቃዳቸው ማግለላቸው ቢነገርም ብዙዎች አልሞቃቸውም አልበረዳቸውም፡፡ በሌላ አነጋገር የአንጀታቸው አልደረሰም፡፡ (ጠ/ሚኒስትሩ ቢነሱም የሚረካ ላይገኝ ይችላል!) ለነገሩ ህዝብ የልቡ የሚደርሰው ጥቂት ሰዎችን ከስልጣን በማንሳት ብቻ አይመስለኝም። (ድስት ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም እንዲሉ) ህዝቡ መሰረታዊ ለውጥ ነው የሚፈልገው፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ህዝብ የጠየቀው የግለሰቦችን መቀያየር ሳይሆን የፖሊሲና የሥርዓት ለውጥ ነው፡፡ (ኢህአዴግ እኮ አላሰበውም!) ለጊዜው ግን በተሃድሶው ዙሪያ ከኢህአዴግ ጋር የተደረገውን ቃለ-ምልልስ እነሆ፡- (መልካም ተሃድሶ!)
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ከ15 ዓመት በኋላ ድርጅታችሁ ለማድረግ ባቀደው “ጥልቅ ተሃድሶ” ከከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ውስጥ እነማን ይነሳሉ ብለን እንጠብቅ? በቀጥታ ማንነታቸውን ባይሆንም ፍንጭ ቢጤ ማግኘት ይቻል ይሆን?
ኢህአዴግ፡- አይቻልም፡፡ የማይቻለው እናንተ እንደምትሉት፣ ኢህአዴግ ምስጢረኛ በመሆኑ አይደለም፡፡ ከየድርጅቶቹ የሚባረሩትን፣ የሚሸጋሸጉትን፣ በህግ የሚጠየቁትን ወዘተ ባለሥልጣናት ስም ዝርዝር ገምግመው የሚያቀርቡት ራሳቸው ድርጅቶቹ ስለሆኑ ነው። ለምሳሌ ከኦሮሚያ ክልል የሚነሱትን ኦህዴድ፣ ከአማራ ክልል ብአዴን፣ ከትግራይ ክልል ህውኃት ወዘተ ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን ኦህዴድ እንዳደረገው ማለት ነው፡፡ ምናልባት ከተባራሪዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ራሳቸው እንደሚነሱ ሊጠረጥሩ ይችላሉ - በተለይ ቀንደኛ ሞሳኞች ከሆኑ፡፡ በኢህአዴግ ወይም በመንግስት ደረጃ ግን እነ እገሌ ተብለው ገና ዝርዝራቸው አልታወቀም፡፡ ጊዜው ሲደርስ መታወቁ አይቀርም፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡-  ተሃድሶው በመንግስት ሥልጣን ለአገር ከመስራት ይልቅ ራሳቸውን ያበለጸጉ ሹመኞችን ያስወግዳል ተብሏል፡፡ ራስን ማበልጸግ ሲባል ደረጃ ወጥቶለታል ወይስ ኩርማን መሬት የወሰደም በብዙ ሚሊዮኖች ብር ፎቅ የገነባም በእኩል ዓይን ነው የሚታየው?!
ኢህአዴግ፡-  በሥልጣኑ አገር የሚጠቅም ሥራ መስራት ሲገባው ራሱን ሲጠቅም የኖረ ባለሥልጣን ሁሉ የሥር-ነቀል ተሃድሶው ሰለባ መሆኑ አይቀርም።
ፖለቲካ በፈገግታ፡- መቼም ይሁነኝ ብሎ በሙስና ውስጥ የተዘፈቀና ባልንጀራ አሳስቶት ትንሽ የቀመሰ እኩል ሊታይ አይችልም-----
ኢህአዴግ፡- እሱማ በመጀመሪያ ዙር ከስልጣናቸው የሚሻሩት ሙስና ከፍቶ የታየባቸውና ይሉኝታ ያጡ ዓይን አውጣ ሹማምንት ናቸው። ለዓመል ያህል የተነካካው ሁሉ ይነሳ ከተባለማ የሥልጣን (ቫኪዩም) ወይም ክፍተት ይፈጠራል፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- የመንግስት ሥልጣን ተጠቅመው ራሳቸውን በማበልጸግ በፊት አውራሪነት የሚሰለፉት የመንግስት ሹመኞች ክስ ይመሰረትባቸዋል ወይስ ምንድን ነው የታሰበው?
ኢህአዴግ፡- መጠርጠሩስ?! የተሃድሶው ዋና ዓላማ ምን ሆነና!!
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ዋና ዓላማውማ-----አንድም የህዝብ ቁጣ ማብረጃ ነው፣አንድም ደግሞ የፖለቲካ ቂም በቀል መወጪያ ነው ይላሉ፤አንዳንድ የኢህአዴግ ተቺዎች፡፡---
ኢህአዴግ፡-    ቱልቱላ በላቸው!
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ የሚል ያመጣው ጊዜ ለመግዣ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን ያውቀዋል----በሚል ትችት የሚሰነዝሩ ወገኖች አሉ፡፡
ኢህአዴግ፡-  ውሃ የማያነሳ ገለባ ትችት ነው፡፡ እኛ የጊዜ ችግር አለብን ብለን             አናስብም፤ከዚህ አንጻር ጊዜ ለመግዣ የሚለው ከየት እንደመጣ አናውቅም፡፡ ምናልባት     የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ቅዠት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለእኛ ዋናው ጉዳይ ለህዝብ ጥያቄዎች ዘላቂ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ እንቅልፍ የሚነሳን ይሄ ብቻ ነው፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ከሥልጣናቸው ተነስተው የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን የሚሸጋሸጉ ብዙ ሹመኞች እንደሚኖሩ ይነገራል፡፡ ተሳስቻለሁ?
ኢህአዴግ፡- በጣም እንጂ፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው የሚሸጋሸጉት በጣት የሚቆጠሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ከሙስና የጸዱ መሆናቸው ተረጋግጦ ነው ለአማካሪነት የሚታጩት፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ግን እንዴት ነው የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪዎች አልበዙም?! በዓለም ብዙ አማካሪዎች ያሏቸው ጠ/ሚኒስትር ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ከ15 ዓመት በላይ የመሩት እኮ በአንድ ወይም በሁለት አማካሪዎች ብቻ ነበር፡፡ አሁን ምን ተፈጥሮ ነው አማካሪዎች እንደ አሸን የፈሉት?
ኢህአዴግ፡- ያኔ ዓመት ሙሉ የሚንቀለቀል የህዝብ ዓመጽና ቁጣ አልነበረማ!! ያኔ በቀናት ውስጥ 10 የአበባ እርሻዎች በእሳት አይጋዩማ!! ያኔ ወህኒ ቤቶችን የሚያቃጥል የለማ!! ያኔ የማንነት ጥያቄ በየቦታው እንደ አሸን አልፈላማ!! ያኔ ለቀናት ቤት ከርችሞ የመቀመጥ አድማ አይደረግማ!! የአሁኑንና የቀድሞውን እንዴት ታወዳድራለህ!? ያኔ እኮ ከባዱ ሥራ የሚባለው ከስንት አንዴ ለፓርላማ አባላት ጥያቄዎች ማብራሪያ መስጠት ነበር፡፡ አሁን እኮ እንቅልፍ የለንም፡፡ በየቀኑ ሥጋት ላይ ነን፡፡ የትኛው ህዝብ አመጸ? ማን ምን ጥያቄ አቀረበ? ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስንት ሰው ሞተ አሉ? ህዝቡ የመንግስት ለውጥ ጠየቀ ወይ? ---- ለእንዲህ ያለው ስጋትና ሰቀቀን ------ ሺ አማካሪዎችስ ይበቃዋል እንዴ!?
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ግን እኮ የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪዎች መብዛት እሳቸውን ወይም መንግስትን አሊያም ገዢውን ፓርቲ ከወቀሳና ከጥፋተኝነት አላዳነም፡፡ በአገር ውስጥም በውጭም ከህዝባዊ ተቃውሞው ጋር ተያይዞ በወሰደው እርምጃ መንግስት  ክፉኛ እየተነቀፈ ነው፡፡ ታዲያ የአማካሪዎች መብዛት ምን ፈየደ?
ኢህአዴግ፡-   የእኛ ዓላማ ሥራችንን በአግባቡ መወጣት እንጂ ከአገር ውስጥና ከውጭ ትችትና ነቀፋ መዳን አይደለም፡፡ እንደ መንግስት ሃላፊነታችንን እንወጣ እንጂ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ግን እኮ የመንግስት ሃላፊነታችሁን አልተወጣችሁም፤ በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ከመጠን ያለፈ ሃይል ተጠቅማችኋል፤ መሳሪያ ባልያዙ ዜጎች ላይ ተኩሳችሁ ህይወት አጥፍታችኋል-----የህዝቡን ህገ መንግስታዊ መብት አላከበራችሁም----የሚል እኮ ነው ነቀፌታው፡፡
ኢህአዴግ፡-  እነዚህ ውንጀላዎች ሁሉ መሰረተ-ቢስ ናቸው፡፡ ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን ከመጣራቱ በፊት የሚቀርቡ ክሶች በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ውሳኔ ላይ ደረሳችሁ?
ኢህአዴግ፡- አዎ፤ በራሳችን ገለልተኛ ወገን እናጣራዋለን፡፡ በህገ-መንግስቱ መሰረት፤ ከማንም ሳይወግን ነጻ ሆኖ የተቋቋመ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አለን፡፡ ኮሚሽኑ ጉዳዩን አጣርቶ በሚያቀርብልን ሪፖርት መሰረት፣ ጥፋተኛ የተባለውን ለህግ እናቀርባለን፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡-   ግን እኮ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተወነጀለ ያለው መንግስት ነው-----
ኢህአዴግ፡-   ኮሚሽኑ አጣርቶ በሚያቀርበው ሪፖርት፤መንግስትን ጥፋተኛ ካደረገ፣ ለህግ የማናቀርብበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ ከዚህ ቀደም አድርገነዋል፤ አሁንም እናደርገዋለን። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስትን ጨምሮ ማንም ከሃገሪቱ ህግ በላይ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም።
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ከህዝባዊ ተቃውሞው ጋር በተያያዘ ከዜጎች ህይወት መጥፋት ይልቅ የንብረት ውድመት ይበልጥ ያንገበግባችኋል በሚል ትተቻላችሁ፡፡ ምላሻችሁ ምንድን ነው?
ኢህአዴግ፡- የሰዎች ህይወት መጥፋት የሚያሳስበንን ያህል የህብረተሰቡ ንብረት መውደምም ያሳስበናል፡፡ ልማታዊ ተቋማት የህዝቡ እስትንፋስ ናቸው፤ያለ እነሱ ህይወት የለውም፡፡ ስለዚህ እነዚህን የህዝብ ሃብቶች ከውድመት የማዳን ሃላፊነት አለብን፡፡
የመንግስት ሥራ ልማት ብቻ አይደለም፤የለማውን ከውድመት መጠበቅም ሥራው ነው፡፡ ለኛ ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡

Read 7112 times