Monday, 26 September 2016 00:00

ዕንቁላሉን ስለሰበርከው ጫጩት አታገኝም በራሱ ሙቀት መፈልፈል አለበት! - የቻይናዎች አባባል

Written by 
Rate this item
(14 votes)

     ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር ንብረት ጠፍቶ ሌባውን ለመያዝ አውጫጪኝ ይደረግ ተብሎ፤ የመንደሩ ሰው ሁሉ ተጠርቶ አንድ ዛፍ ሥራ ተሰበሰበ፡፡
ሰብሳቢው- ‹‹ጎበዝ እንዴት አደራችሁ?››
ተሰብሳቢው- ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን›› አለ በአንድ ድምፅ
ሰብሳቢውም፤
‹‹ዛሬ እንግዲህ የተሰበሰብነው፤ አንድ ችግር ተፈጥሮ ነው፡፡ እንደምታውቁት በመንደራችን ማንኛውም ንብረት፣ ከብት፣ ገንዘብ ከጠፋ የእኛው መንደር ህዝብ ተሰብስቦ መላ መትቶ፣ አውጣጥቶ፣ ሌባውን እንዲጠቁም ይደረጋል፡፡ ከህዝብ ዐይንና ጆሮ ማንም አያመልጥም፡፡ ዘዴው ከጥንት ጀምረን የምንሠራበት ፍቱን ዘዴ ስለሆነ በቀላሉ የሌባ-ሻይ ጥበቡ ሥራ ላይ ይውላል፡፡
በሉ እንግዲህ ስለጠፋው ወይፈን ምልክት የሚሰጠን ሰው ካለ፤ እጁን አውጥቶ ይነሳና ይናገር?›› አለ፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ አዛውንት እጃቸውን አወጡ፡፡
‹‹ይናገሩ›› ተባሉና ተፈቀደላቸው፡፡
‹‹ይሄ የጠፋው ወይፈን ቡሬ ነው፡፡ ቤቴ ጎረቤት ስለሆነ ሲወጣ ሲገባ አይቼዋለሁ››
 ሌላው ተነስተው፤
‹‹ዕውነት ነው፡፡ ዐይን የሚገባ፣ የሚያምር ኮርማ ነው፡፡›› አሉ፡፡
ሦስተኛው ሰው፤
‹‹መቼም ወይፈንን የሚያህል ነገር የሚሰርቅ የለመደ ሌባ መሆን አለበት›› ሲሉ፤ ህዝቡ ክፉኛ አገሩመረመ፡፡ ከፊሉ አዲስም የዱሮም ሌባ ሊሆን ይችላል አለ፡፡ ከዚያ ሰው በየተራ የዱሮም ጥርጣሬ፣ አዲስም ጥርጣሬ ያለውን ሰነዘረ፡፡ ሆኖም አንድ ሰው ላይ ለማረፍ ችግር ሆነ፡፡
ሰብሳቢው-ደጋግመው፤
‹‹ጎበዝ! እዚሁ መዋላችን ነው፤ ብትናገሩ ይሻላል›› አሉ፡፡ የሚናገር ጠፋ፡፡ ምሽቱ እየገፋ ነው፡፡ ወደመበተኑ ሆነ፡፡ በመካከል ከተሰበሰበው ህዝብ ውስጥ አንዱ ጎኑ ላለው ወዳጁ፤
‹‹ወዳጄ፤ አደራህን ለማንም አትንገር፤ ወይፈኑን የወሰድኩት እኔ ነኝ›› ይለዋል፡፡
‹‹ወስደህ ምን አደረግኸው?››
‹‹ወዲያ ማዶ ላለው መንደር ሸጥኩት››
‹‹እንግዲያው አንድ መላ ታየኝ››
‹‹ምን ታየህ?››
እጁን አወጣ ባለመላው፡፡ ‹‹ተናገር›› ተባለ፡፡
‹ማዶም፤ ወዲያኛውም መንደር፤ ከዚያ ወዲያ ባለውም መንደር አውጫጪኝ መደረግ አለበት፡፡ በእኛ መንደር ብቻ አውጫጪኝ ተካሂዶ መቆም የለበትም፡፡ ለዛሬው ብንበተን ነው የሚሻለን›› አለ፡፡ ሰብሳቢውም፤
‹‹ጎበዝ! ወይፈናችን ተሻግሯል ማለት ነው! ለዛሬው አውጫጪኙ ያብቃ!›› ብለው በተኑት፡፡
ወይፈኑን የሰረቀው ሰው ግን በጣም ከመጨነቁ የተነሳ ሚሥጥሩን የነገረውን ሰው እግር በእግር፣ የገባበት እየገባ ይናገር ይሆን አይናገር ይሆን እያለ ሚሥጥሩን የያዘውን ሰው ሲከታተል እስከ ዛሬ ይኖራል ይባላል፡፡
** ** **
ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ሌብነት ቦቃ የለውም፡፡ የጥንቱ አውጫጪኝ የዛሬ ስሙ ግምገማ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሚሥጥሩን ለማውጣጣት ሀቀኝነት ይጠይቃል፡፡ የሆድን በሆድ ይዞ ተፋጦ መዋል ፍሬ ነገሩን ከማግኘት ያቅባል። ቂም በቀል ካለ ግምገማ ግቡን አይመታም፡፡ በቅጡ ብንሰራው ጥሩ ነበር፡፡ በበቂ ትኩረት አልሰጠነውም ነበር፡፡ በቀጣይ የምናስብበት ይሆናል…. እያሉ ሸፋፍኖ ማለፍ ድክመትን ተሸክሞ መጓዝ ነው፡፡ መልኩን ይቀያይር እንጂ ሌብነት አንድ ነው፡፡ ሌብነትን በሂደት ማጣራት ለበጣ ነው የሚመስለው!
ሌብነት ሲያስጨንቅ የሚኖር አባዜ ነው፡፡ ሣር ቅጠሉን ሲጠራጠሩ መኖር ነው፡፡ ይሰውረን! አንድ የማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት የዱሮ ባለስልጣን አንድ የተፈታ እስረኛ ውጪ አግኝተው ሦስት ምክሮችን ለገሡት ‹‹1ኛ/ ከፖለቲከኞች ጋር አለመገናኘት 2ኛ/ ፖለቲካ አለመናገር፤ 3ኛውና ዋናው ግን ማንም ፖለቲካ ሲናገር ቢያጋጥምህ አለመስማት፤ ምክንያቱም በእኛ ግምት መስማት አደገኛ ወንጀል ነው-ለምን ቢሉ የሰማኸውን የት አረግኸው? የሚል ጥያቄ ያስነሳልና! ሄደህ አንዱ ጋ መተንፈስህ አይቀርም ተብለህ ከመጠርጠር አታመልጣትም! ስለዚህ ከሁሉም ክፉ ወንጀል መስማት ነው! ጆሮህን ድፍን አድርገህ መቀመጥ ምን ይጎዳሃል?!›› አሉት፡፡ የምንሰማው ሁሉ ለጥፋት የሚዳርግ አደገኛ ነገር ነው ብሎ የሚያስብ ለጥርጣሬ እንደተዳረገ ይኖራል፡፡ ቁም ነገሩ ግን የሚሰማ ነገር አለ ወይ? ነው፡፡ በብዛት ተደጋግመው የሚነገሩ ነገሮች በጣም ከመለመዳቸው የተነሳ እንኳንስ ቁም ነገራቸው ጣዕማቸውም ይጠፋል፡፡  በዛሬው ዘመን የሁሉ ነገር መጠቅለያ፤ ‹‹ህዝቡ የሚለውን በወቅቱ በትክልል አላዳመጥነውም ወይም ከናካቴው ጆሮ አልሰጠነውም ነበር›› የሚል ነው፡፡ አሁን ድንገት ጆሮአችን ተከፈተ ዓይነት ይስሙላም ያለው ይመስላል፡፡
‹‹ካለአቅሟ ካፒታሊዝም አስታቅፈው ካልወለድሽ ብለው ሲያማምጧት ከነሶሻሊዝሙም አስወረዳት›› እንደተባለው ነው፡፡ አቅማችንን እንመርምር፡፡ ዘልማድ ትተን ጥናታዊ አካሄድን እንያዝ ጥናታዊ አካሄድን የያዘ ሥርዓት የመገምገሚያም ወግና ደንብ አብሮ ያስቀምጣልና እከክልኝ ልከክልህም፣ የአብዬን እከክ እምዬ ላይ ልክክም ሆነ ሀሳዊ- ተዋናይነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ፔትሮስ ጊዮርጊስ ለራስ አሉላ የፃፈውን ደብዳቤም አንርሳ፡-
‹‹ታሪክ አላነበቡም እንጂ ፈረንጅና ቁንቁን አንድ ነው፡፡ ቁንቁን ከትል ሁሉ ያንሳል፡፡ ነገር ግን ታላቁን ግንድ በልቶ፣ አድርቆ ይጥለዋል፡፡ እነዚህም መጀመሪያ በንግድ ስም ይመጡና ጥቂት በጥቂት እየገቡ የሰውን አገር ይወርሳሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ቶሎ ደብድቧቸው፤ ይለቁ፡፡ አለዚያ አገርም መጥፋቱ ነው፡፡… ዛፍ ሳያድግ በእግር ጣት  ይነጫል፡፡ ካደገ በኋላ ግን ብዙ መጋዝና መጥረቢያ ያስፈልገዋል፡፡ እንደዚሁ የሞራ ግልገል ክንፉ ሳያድግ የስድስት ዓመት ልጅ ከዛፍ አውርዶ ሲጫወትበት ይውላል፣ ክንፉ ካደገ በኋላ ግን ከሰው እጅ ሥጋ ነጥቆ እስከ አየር ይወጣልና የሚያገኘው የለም፡፡ እንደዚሁም እነዚህ ናቸውና ለአገርዎ፤ ለግዛትዎ፣ ለጠጅዎ፣ ለጮማዎ ከሁሉም ይልቅ ለታላቅ ክብርዎ ይሞክሩ›› (ባህሩ ዘውዴ)
ምሁራንም ሚናቸው አይናቄ ነው፡፡ ምሁራንን ማዳመጥ በጎ ነገር ነው፡፡ እንደ ሩሲያ ምሁራን ‹‹ማነው ባለ አባዜው?›› ፤ ‹‹ምን መደረግ አለበት?›› ወይም ‹‹የህዝቡ ወዳጆች እነማናቸው?›› የሚሉ ፀሀፍት ማስፈልጋቸውን እናስተውል!
ለሁሉ ጥያቄ አንድ መጠቅለያ (ፓኮ) ፍለጋ፤ ሁለንተናዊ መድህን (Panacea) አድርጎም ሙሉ በሙሉ መቀበል፤ ትንተናዊ አቅጣጫዎችን እንዳናይ ይገድበናል፡፡ ከተለመዱት መጠቅለያዎች እንደ ‹‹መልካም አስተዳደር››፤ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› ወዘተ ብሎ አለማቆም ብልህነት ነው፡፡ ይሄው ዛሬ ብዙ ያልተመረመሩ የህዝብ ችግሮች ብቅ ማለታቸውን እያመንን ነው፡፡ ራስ-ፍተሻው ይቀጥል! የህዝብን ድምፅ እንደ ባህል መያዝ ዋና ነገር ሲሆን ብዙ ድካም የሌበት ነው፡፡ የሚጠይቀን አንድ ጉዳይ ብቻ ነው- ቀናነት! በቀናነት ጥፋታችንን ማመን! በቀናነት ወገናዊነታችንን ትተን መጓዝ፡፡ መነሳት ያለበትን ሹም ማንሳት፤ በቀናነት እዚህኛው ሥልጣን ላይ ድክመቱ በይፋ የታየውን  ሰው ሌላ ቦታ አለመሾም! በቀናነት ‹‹እንደተጠበቀው አይደለም›› የሚልን ሽባ ሰበብ (Lame excuse) መተው፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ፡- ግብርናው እንደተጠበቀው አይደለም፤ ኢንዱስትሪው እንደተጠበቀው አይደለም፣ ለወጣቱ የተሰጠው ትኩረት እንደጠበቀው አይደለም….›› ይሄ ሄዶ ሄዶ ‹‹እኛም እንደጠበቅነው አይደለንም›› እንዳይሆን መጨረሻውን ማስተዋል አለብን፡፡ ሲደጋገሙ ወደ ፌዝነት የሚለወጡ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፤ ‹‹ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠት….›› ዓይነት፡፡ ‹‹የመልካም አስተዳደር›› አይነት … ወዘተ Stereotype እንደሚሉት ፈረንጆቹ፡፡ በውጥረትና በስጋት እርስ በርስ በመወጣጠር፣ በመወሻሸት፣ የተሳተ መረጃ በመስጠት፣ አላየንም አልሰማንም በማለት… ያለወቅቱ መፍትሔ እንፈጥራለን ብሎ መሯሯጥ ከንቱ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ሀገራችን የዛሬ ወቅታዊ ሁኔታ ዐይን-ከፋች ሁኔታ የለም፡፡ ይህን ሁኔታ በግልፅ የሚያፀኸልን ‹‹ዕንቁላሉን ስለሰበርከው ጫጩት አታገኝም፡፡ በራሱ ሙቀት መፈልፈል አለበት!›› የሚለው አባባል ነው፡፡ ልብ ያለን ልብ እንበል!!

Read 4843 times