Monday, 26 September 2016 00:00

የምሁራኑ ውይይት በባህርዳርና በጎንደር ዩኒቨርስቲዎች እክል ገጠመው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(38 votes)

በዲላ ዩኒቨርስቲ ‹‹የህሊና ፀሎት›› ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም

   በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች መንግስት ከመምህራን ጋር እያካሄደ ያለው ውይይቶች በተቃውሞና በውዝግብ የታጀቡ ሆነዋል፡፡ በጎንደርና በባህርዳር ውይይቱ በወጣው መርሃ ግብር መሰረት አለመካሄዱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
መስከረም 4 በተጀመረው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የመምህራን ውይይት ለ2 ቀናት ብቻ ብቻ የተሳተፉ አንድ መምህር፤ እንደገለፁልን፤ መምህራኑ ተቀምጦ ከማዳመጥ ባለፈ ጥያቄም ሆነ አስተያየት በቀጥታ ማቅረብ አትችሉም መባላቸውን ተከትሎ ቅሬታዎች ተፈጥረው ነበር፡፡ በትግራይ ክልል ም/ርዕሠ መስተዳደር ዶ/ር አዲስአለም ባሌማ አጋፋሪነት በተመራው ውይይት ጥያቄ ማቅረብ የሚቻለው በየኮሌጆቹ ተወካዮች በኩል እንጂ መምህራን በቀጥታ ማቅረብ ተከልክለው ነበር።  የሚሉት መምህሩ፤ ጥያቄዎች ለኮሌጅ መሪዎች ከተሰጡ በኋላ ተጨምቆ ለመድረክ ይቀርብ ነበር ብለዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው ስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንዳንድ ያነጋገርናቸው  መምህራንም በቀሪ መቆጣጠሪያ መዝገብ ላይ እየፈረሙ ወጣ ገባ ከማለት በስተቀር ውይይቱን በአግባቡ እንዳልተከታተሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪና የዲላ ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል ሰብሳቢነት ከመስከረም 5 ጀምሮ እስከ ትናንት በተካሄደው ስብሰባ ላይ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ጥያቄ ሁሉ መምህራኑ በተደጋጋሚ በኦሮሚያ፣ በአማራና  በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ለሞቱ ዜጎች የህሊና ፀሎት እንዲደረግ ቢጠይቁም ተቀባይነት ማጣቱን የስብሰባው ተሳታፊ መምህራን ተናግረዋል፡፡ የህሊና ፀሎት ጥያቄው ሲቀርብ ተሠብሳቢው በጭብጨባ ከፍተኛ ድጋፉን ያሣየ ሲሆን ሳይደረግ መቅረቱ መምህራኑን ቅር እንዳሰኘ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ከዩኒቨርስቲው በተካሄደው ውይይት መምህራኑ፤ ‹‹ለምናቀርባቸው ጥያቄዎች እርሶ መልስ እንዲሰጡን አንፈልግም፤ ለሚመለከታቸው የበላይ አካላት መዝግበው ያስተላልፉልን›› ሲሉ ለሰብሳቢዋ የገለፁ ሲሆን በአብዛኛው ውይይቱ በዚህ አግባብ ተከናውኖ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንድ መምህር ባቀረቡት ጥያቄ፤ ‹‹ለምንድን ነው ሰው በጥይት የሚገደለው፤ በፕላስቲክ ጥይት ወይም በጭስ መበተን ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?›› ብለዋል፡፡ የመድረኩ መሪ ወ/ሮ መፈርያትም፤ ‹‹እሺ ጥያቄውን ተቀብዬ ለሚመለከተው አደርሳለሁ›› ማለታቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ምሁራኑ በአገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶችን መሰረት አድርገው ለተሰነዘሩ ጥያቄዎች ሰብሳቢዋ በተደጋጋሚ ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩም ተሰብሳቢው ሲያስቆሟቸው ነበር ተብሏል፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ለ8 ቀን መካሄድ የነበረበት ውይይት ለአንድ ቀን ብቻ ተካሂዶ ባለመግባባት መቋረጡን ምንጮች ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በጎንደር ዩኒቨርስቲ መስከረም 9 ውይይቱ እንደሚካሄድ ለሁሉም መምህራን ቀደም ብሎ በአጭር የሞባይል መልዕክት ቢተላለፍም፣ ሁሉም መምህራን ወደ ውይይቱ ቦታ ከመሄድ በመቆጠባቸው እስከትናንት ድረስ ወይይቱ ሳይካሄድ መቅረቱንና ለወደፊትም ምን እንደታሠበ ለመምህራኑ እንዳልተነገረ ምንጮቻችን ግልፀዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ቀደም ብሎ የወጣው የነባርና የአዲስ ገቢ ተማሪዎች የመቀበያ ጊዜም መራዘሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከመስከረም 22 ጀምሮ እንዲገቡ ተነግሯቸው የነበሩ ነባር ተማሪዎች፤ በመስከረም 27 እንዲገቡ፣ እንዲሁም ጥቅምት 20 እንዲገቡ ተብሎ የነበሩ አዲስ ተማሪዎች ጥቅምት 4 እንዲገቡ የጊዜ ሰሌዳ ማሻሻያ ተደርጓል ተብሏል፡፡







Read 11540 times