Monday, 26 September 2016 00:00

ሠማያዊ ፓርቲ ያቀደው ጠቅላላ ጉባኤ በምርጫ ቦርድ መደናቀፉን ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

    አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን በነገው እለት በመኢአድ ፅ/ቤት ግቢ ሊያከናውን ቀጠሮ ይዞ የነበረው ሠማያዊ ፓርቲ፤ ከህግ አግባብ ውጪ በምርጫ ቦርድ ጉባኤውን እንዳያካሂድ መከልከሉን አስታወቀ፡፡ ፓርቲው ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ በዛሬው ዕለት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ የነበረበትን የውስጥ ፓርቲ ችግር ለመፍታት አቅዶ እንደነበር ጠቅሶ፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት፤ ‹‹በፓርቲው ላይ የሚጣሩ ጉዳዮች በመኖራቸው የጉባኤው ቀን እንዲራዘም›› በሚል የማሳሰቢያ ደብዳቤ መላኩን አመልክቷል፡፡
የምርጫ ቦርድ ሃላፊነት ተወካይ በመላክ ሂደቱን መታዘብ እንጂ የጉባዔ ቀን መወሠን አለመሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው፤ ጉባኤው በዚህ ምክንያት ከመደናቀፉ ባሻገር ለጉባኤው ፓርቲው ያወጣቸው ወጪዎች ለኪሣራ እንደዳረገው አስታውቋል፡፡
ለደረሰው ኪሣራም ፓርቲው ምርጫ ቦርድን በህግ እንደሚጠይቅ አስታውቆ፤ የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ይልቃል ጌትነትና  ሌሎች አካላት ጉባኤውን ከማደናቀፍ ተግባር እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡ ጉባኤውንም በቅርቡ በድጋሚ እንደሚጠራም የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሠጡን የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ፤ ‹‹የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለማሠናከል አይደለም፤ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ይልቃል ጌትነት ውጭ ሃገር በነበሩበት ጊዜ ጉባኤውን ለማካሄድ ሂደቶች ተጀምረው ስለነበርና እሣቸውም ቅሬታ በማንሳታቸው የተለያዩ የህግ አግባቦችን ለመመርመር ነው እንዲራዘም የጠየቅነው›› ብለዋል። አለመግባባቱ ወደባሠ ነገር እንዳይሸጋገር ነው ጉባኤው ለሌላ ቀን እንዲተላለፍ የጠየቅነው እንጂ የማስገደድ ጉዳይ ሲሉ አስረድተዋል፡፡  

Read 3152 times