Monday, 19 September 2016 08:42

በዓል በሕክምናው አለም ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

    ሰዎች እንደስራ ባህሪያቸው አዋዋላቸው ይለያያል። ውትድርና፣ የመገናኛ ብዙሀን፣ የኢንዱ ስትሪው እና የተለያዩ መሰል የስራ ባህሪያት በዚህ ቀን ስራ ነው በዚህኛው ቀን በአል ነው የማይባልባቸው ናቸው፡፡ እንደዚህ ያለ የሙያ ባህሪይ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ምናልባትም በአልን ወይንም ሌሎችንም የእረፍት ቀናትን ምክንያት አድርገው ስራቸውን ቢያስተጉዋጉሉ ተጠቃሚ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል እንዲሁም አገልግሎቱን የምትሻው ሀገር በተለያየ መንገድ ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም የዘመን መለወጫ በአል በተለይም በጽንስና ማህጸን ሐኪሞች የስራ ድርሻ ምን መልክ ነበረው በሚል የኢድአልአድሀ አረፋ እለት በጠዋት ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ በመሄድ ያደረውንና የእለቱን ሁኔታ ታዝበን ለንባብ ብለናል፡፡
ከማዋለጃ ክፍሉ በአንድ አልጋ ላይ አንዲት ሴት እግሩዋን አጣጥፋ ሙሉ አካልዋን አልጋው ላይ አድርጋ ልክ ቡና እንደሚያፈላ ሰው ስብስብ ብላ ተቀምጣለች። ጠየቅናት...
ጥ/ ወደሆስፒታሉ ለምን መጥተሸ ነው?
መ/ ለሊት ላይ ወልጄ ነው፡፡
በእርግጥ ወጣት ናት፡፡ ነገር ግን በጭራሽ የወላድ መልክ አይታይባትም፡፡ ጥያቄው ቀጠለ፡፡
ጥ/ ታድያ ለምን እንደዚህ ቁጭ አልሽ?
መ/ የምወጣበትን ሰአት እየጠበቅሁ ነው፡፡
ጥ/ ትናንት ለሊት መውለድ ማለት የዘመን መለወጫ እለት ነው?
መ/ እኔማ ከቤቴ ከወጣሁ አራት ቀኔ ነው፡፡ የምኖረው አሰላ ነው፡፡ ምጥ ይዞኝ በዚያ ከቆየሁ በሁዋላ የዘመን መለወጫ ትናንት ማለት ነው ወደዚህ ልከውኝ ነው የወለድኩት፡፡
ጥ/ ታዲያ ለበዓሉ ያለሽ ስሜት እንዴት ነው?
መ/ በዓሉ 2009/ዓም በጭንቅ ነው የታለፈው፡፡ ደግነቱ መጀመሪያ ብሰቃይም ወንድ ልጅ ግን አግኝቻለሁ። እንግዲህ የእኛ ቤት ዘመን መለወጫ የሚከበረው አሁን ከዚህ ስወጣ ነው፡፡
ሌላዋ ወላድ ደግሞ አልጋዋ ላይ ቁጭ ብላ ልጅዋን በትኩረት ትመለከታለች፡፡ ገና ወጣት ናት፡፡
ጥ/ የወለድሽው መቼ ነው?
መ/ አሁን ንጋት ላይ ነው፡፡
ጥ/ መቼ ወደሆስፒታል ገባሽ?
መ/ ትናንት በዘመን መለወጫ እለት፡፡
ጥ/ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ተቀምጠሸ ለሚያይሽ ገና የወለድሽ አትመስይም፡፡
መ/ አዎን፡፡ የወለድኩት በእስቲች ስለሆነ ሰውነትሽ እንዲጠነክር ተቀመጭ ብለውኝ ነው፡፡
ጥ/ በአሉ እንዴት ነው ታድያ?
መ/ እኛ ቤትማ በአል አልነበረም፡፡ እኔ ስለታመምኩ ባለቤቴም እናም እህቶቼም ሁሉም የዋሉት ያደሩት እዚሁ ሆስፒታል ነው፡፡ አሁንም ገሚሶቹ እደጅ አሉ፡፡ ያው በስተ መጨረሻው ግን ወንድ ልጅ ስላገኘን መላው ቤተሰብ ደስ ብሎታል፡፡ ከእንግዲህ የልጃችን ልደትም የዘመን መለወጫ በአልን ታክኮ ስለሆነ ድካምም የለብንም፡፡
በጳውሎስ ሆስፒታል በስራ ላይ ያገኘነው አዋላጅ ነርስ አንዲት ህጻን አጠገብ ቆሞ የራሱን ስራ ይሰራል። ህጻኑዋ ንቅት ያለች ናት፡፡ ምግብ ፈልጋለች፡፡ እጁዋን ወደአፉዋ እያደረገች እግሩዋን እጁዋን ታወራጫለች፡፡አዋላጅ ነርሱን አነጋገርነው፡፡
ጥ/ ማን እንበል?
መ/ ጥላሁን አለሙ እባላለሁ፡፡ በሙያዬ አዋላጅ ነርስ ነኝ
ጥ/ ይህች ልጅ መቼ ነው የተወለደችው?
መ/ ልጅቷ ከአስር ደቂቃ በፊት ነው የተወለደችው። እናትየው በስቲች ስለሆነ የወለደችው ተሰፍቶ ሲያልቅላት ወደ እናትዋ እንወስዳታለን፡፡ እንደምታያት ትቁነጠነጣለች። ምክንያቱም ውጭውን ገናአልለመደችውም፡፡ ምግብም መውሰድ ትፈልጋለች፡፡ በጣም ንቁና ጤነኛ ልጅ ናት፡፡
ጥ/ መቼ ነው ተረኛ ሆነህ የገባኸው?
መ/ የዘመን መለወጫ ማለትም ትናንትና ጠዋት ገብቼ ይኼው አረፋ በአልንም ቀጥያለሁ፡፡
ጥ/ በ24 ሰአት ተረኝነቱ ሲያልቅ ለምን አልወጣህም?
መ/ ጉዋደኛዬ ሙስሊም ስለሆነ የእሱን ተራ ልሸፍን ብዬ ዛሬም ውዬ አድራለሁ፡፡
ጥ/ ሁለቱንም በአል በስራ ስታሳልፍ አይከብድህም?
መ/ ምንም አይከብደኝም፡፡ ምክንያቱም እናቶችን ከጭንቅ ማገላገል እንዲሁም ይህንን አለም የማያውቁ ልጆችን ወደዚህ አለም ማምጣት ስለሆነ የእኔ ትኩረት ምን ያህል ጤናማ ስራ እሰራለሁ ነው እንጂ በአልን ሳልሳተፍ የሚል አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ በበአል ተራ ይደርሰኛል፡፡ እኔም ስራዬን በደስታ እሰራለሁ፡፡
 በሆስፒታሉ ባደረግነው ቆይታ ተጨማሪ ወላዶችንም አነጋግረናል፡፡ አንዱዋ በኦፕራሲዮን ሌሊቱን ወልዳ የተኛች ናት፡፡ ልጅዋ ዘጠንኛውን ወር ሳይጨርስ እንዲወለድ ነበር የተደረገው፡፡ የኦፕራሲዮኑ ምክንያት የደም ግፊት ነበር፡፡ ምንም እንኩዋን እለቱ በአል ቢሆንም ህይወትን በማዳን በኩል የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ በጥንቃቄ የሚሰራበት መሆኑን ነው ከዚህ መረዳት የሚቻለው፡፡ ሌላዋ አልጋ የያዘች እናት ደግሞ የ7 ሰባት ልጆች እናት ናት፡፡ የዘመን መለወጫ2009እለት ከሌላ ጤና ጣብያ ሪፈር ተደርጋ የመጣች ስትሆን ጽንሱ ሕይወት ስለሌለው በምጥ እስኪመጣ ድረስ እየተጠበቀ ነው ነበር ያለችን፡፡
በመቀጠል ያነጋገርናት ዶ/ር ትዝታ ትባላለች። ከጠቅላላ ሐኪምነት ወደ ጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት በመዛወር ላይ ያለች ሐኪም ናት፡፡ ዶ/ር ትዝታ እንደምትለው...
 “...በአል ማለት ከቤተሰብ ጋር በእርጋታ እና በደስታ የምታሳልፊው እለት ስለሆነ ተረኛ ወጥቻለሁ ሲባል ቤተሰብ ትንሽ ቅር መሰኘቱ አይቀርም፡፡ በሐኪሙ በኩል ግን ምንም በአል ቢሆን ተረኛ ከተሆነ ምንም ቅሬታ የለም፡፡ ኃላፊነቱን ወስዶ ሕይወትን ለማዳን እንዲሁም አዲስ ትውልድን ወደዚህ አለም ለማምጣት ያለእረፍት የሚሰራበት እለት ነው፡፡ በእርግጥ እኔ ትዳር ባልመሰርትም ባለትዳሮች እንደሚሉት በበአል ቀን ስራ ላይ መዋል ማለት ትንሽ ቅር ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ባልና ሚስት አብረው የሚሰሩ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ አብረው እንዲገቡና አብረው እንዲወጡ የሚደረ ግበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ትዳር ባይኖርም ከእናት አባት ጋር የሚኖር ከሆነም እንዲያውም አውቀሽ ተረኛ ለመሆን የምትፈልጊ አድርገው የሚወስዱበት አጋጣሚ አይጠፋም፡፡ ነገር ግን ይህ እየዋለ እያደረ የሚለመድ ነገር ስለሆነ ከትንሽ ጊዜ በሁዋላ ቅሬታ አይሰማም፡፡በተረፈ እንደ እምነታችን ሙስሊሙ ክርስቲያኑን ክርስቲያኑ ሙስሊ ሙን በበአል ተረኝነት ወቅት እሚሸፋፈኑበት ሁኔታ አለ፡፡ ለማንኛውም የማዋለድ ስራው ቀጠሮ የማይሰጠው ሁሌም ተረኛ ሆኖ ነቅቶ የሚጠበቅበት ነው፡፡ ልጅ መውለድ እንደሌላው ታማሚ በዚህ ቀን በዚህ ወር ተብሎ ቀጠሮ የማይያዝበት በማንኛ ውም ቀንና ሰአት የሚመጣ በመሆኑ ሐኪሞቹ አዋላጆቹ ሌሎቹም የህክምና ባለሙያዎች ረዳቶች ሆስፒታሎች ጤናጣቢያዎች ምንጊዜም በራቸው ክፍት ሆኖ በመጠባበቅ የሚሰሩት ስራ ነው፡፡ ስራው ከባድ ነው ፡፡ ቢሆንም ግን እኔ እወደዋለሁ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እናትና ልጅን ማዳን በመቻሌም እረካለሁ፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሁለት አባቶችንም ለማነጋገር እድሉን አግኝተናል፡፡ አንደኛው የሰጠን አስተያየት የሚከተለው ነው፡፡
“...ስሜ ዎድሮስ መላኩ ይባላል፡፡ ገና የመጀመሪያ ልጅ መወለዱ ነው፡፡ የ2009 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በአል ለእኔ የተለየ ቀን ነው፡፡ ከተወለድኩ ጀምሮ የዘመን መለወጫን በአል ከእናት አባቴ እንዲሁም ከቤተሰቤ ጋር በመሆን ስበላ ስጠጣ በደስታ ነበር የማሳልፈው፡፡ ባለፈው አመት ገና ትዳር መመስረ ነው፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ሁሉም ነገር ቀርቶ ጭርሱንም ሆስፒታል አደርኩ፡፡ ነገር ግን አንድ ቆንጆ ወንድ ልጅ ስላገኘሁና ባለቤቴም በሰላም ስለተገላገለች በጣም ደስ ብሎኛል፡፡”
 ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና መምህር በእለቱ ተረኛ ሐኪም ነበሩ፡፡ እንደእሳቸው እማኝነት...
“...ባለሙያዎች ተረኛ ከሆኑ ካለምንም ቅሬታ ገብተው ግዴታቸውን መወጣታቸው ሙያውን ተምረው ሲመረቁ ከሚገቡት ቃል ኪዳን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቤተሰብ ምንም ያህል ቅር ቢለው ስራው ላይ ጫና አያስከትልም። ምክንያቱም ባለሙያው በሙያው አስገዳጅነት የተነሳ ለሕዝቡ የገባው ቃል ስለሚበልጥ ነው ፡፡ ማንኛውም የህክምና ባለሙያ በበአል እለት ተረኛ ከሆነ በአል የሚለውን ነገር ጭርሱንም አያስታውሰውም፡፡ ሙያውን አክብሮ ህብረተሰቡን ማገልገል ወቅት የማይመረጥበት የሁልጊዜ ግዴታ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በተለይም የማዋለድ ስራ ቀጠሮ የሌለው ሁሌም ድንገተኛ በመሆኑ ምንጊዜም ተጠንቅቀን የምንሰራው ስራ ነው፡፡”

Read 2337 times