Monday, 19 September 2016 08:00

የወንጌላዊው ደብዳቤ ለአቶ ኃ/ማርያም ወይስ ለአቶ ኦባማ?

Written by  ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
Rate this item
(27 votes)

    ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን ከቀናት በፊት በፌስቡክ ገፃቸው ላይ “ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ “ብለው የጻፉት ደብዳቤ እኔን ጨምሮ በብዙዎች ዘንድ ግርምትና አድናቆት አትርፎላቸዋል። የማስገረማቸውም ሆነ የማስደነቃቸው ዋና ምክንያት ግን ሌሎች ካነሱትና ከፃፉት የተለየ ሀሳብ አንስተው አይደለም። በሀገራችን በህዝብና በመንግሥት መካከል ግጭቶች ሲፈጠሩ የሀይማኖት አባቶች፣ የምሁራን፣ የአርቲስቶች ለህዝብ ያላቸው ወገንተኛነትና ለመንግሥት ያላቸው ወገንተኛነት ነው። “ቤቴ በሰማይ ነው” እያሉ የሚሰብኩት የሀይማኖት አባቶች፤ መንግሥት ራሱ “አጥፍቻለሁ” ብሎ የሚያምናቸውንና በግልጽ የሚታዩ ጥፋቶችን አንዴም እንኳን በግልጽ ሲተቹ አለመታየታቸው፣ ነፍሳቸውን ትተው ለስጋቸው ማደራቸው፣ ህዝቡ ሌላ ቢቀር የገቢ ምንጫቸውና ደሞዝ ከፋያቸው መሆኑን ግምት ውስጥ አለማስገባታቸው፣ ምሁራኑም በሁሉም የህዝብ ጉዳይ (መንግስት እንዲሆን ከሚፈቅደው ውጭ) ዝምታን መምረጣቸው፣ አቶ መለስ በሞቱ ጊዜ በአንድ ወር ውስጥ ከ300 – 500 ነጠላ ዜማ ሰርተው በየሚዲያውና በሚያቋቸው ሁሉ ስራቸው እንዲቀርብ ይሟሟቱ የነበሩት ድምፃውያንና ደራሲያን ህዝብ ቢራብ፣ ቢፈናቀል፣ ቢሞት፣ ቢቆስል፣ መንግሥት እስካልጠራቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል።  በአማራና ኦሮሚያ ክልል ህዝቦችና በመንግሥት ታጣቂዎች መካከል በተነሳ በሞቱ ዜጎቻችንን በሀዘን ለማሰብ ቀደም ሲል ተይዘው የነበሩ ኮንሰርቶች በሦስት ምክንያቶች መሰረዛቸውን እናስታውሳለን። የህዝብ ሞት ሀዘናቸው ሆኖ ኮንሰርታቸውን የሰረዙ የመኖራቸውን ያህል በተፅዕኖ ብዛት እስከ መጨረሻው ታግለው የሰረዙ አሉ። ሌሎች ደግሞ
ምንም ሀዘን ተሰምቷቸው ሳይሆን እዚህ ቢዘፍኑ የውጭ ኮንሰርታቸው እንደሚሰረዝ ስለተረዱ ወይም ስለተነገራቸው የሰረዙም ጥቂት አይደሉም። ይህ በምንም መመዘኛ የህዝብ ወገንተኛ መሆን ሳይሆን አማራጭን የመጠቀም ዝንባሌ ነው። አንድ ሁለት የሚባሉትም ቀደም ብለው (ወገኖቻችን እየሞቱ ባሉበት ወቅት) በገንዘብ ተደራድረው ከተቀረጹና ብራቸውን ካዝናቸው ካስገቡ፣ ዘፍነውም ከጨረሱ በኋላ ኢቢሲ ላይ መቅረቡ ያስገልለናል ብለው በመስጋት የወሰዱትን መልሰው ዘፈናቸው እንዳይቀርብ ለማድረግ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቶ መቅረቡን አይተን ወገንተኛነታቸውን ትዝብት ላይ ጥለነዋል። ይህን ብንክደው እውነቱ ጋ አያደርሰንም። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ወንጌላዊው ድፍረት የታየበት፣ “ምን ሊደርስብኝ ይችላል? “ከሚል ስጋት የፀዳ የሚመስል ሀሳብ ይዘው ብቅ ያሉት። ለዚህም ነው “ከብዙዎች አንድ መገኘቱም ተመስገን ነው” ያስባለን ። ይህ ማለት ግን በሀሳባቸው ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ ማለት አይደለም። “ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው” ይላል የሀገሬ ሰው። በደብዳቤ የሰጠናቸውን አድናቆት በራሳቸው አንደበት፣ “መዳን “ለሚባል በአሜሪካ ለሚገኝ ሬዲዮ በሰጡት 1:36 ሰዓት የፈጀ ቃለመጠይቅ ላይ ወንጌላዊው ራሳቸውን በራሳቸው ጥለው አገኘኋቸው። ወንጌላዊው እዚህ ሀገር እንደሌሉ፣ አሜሪካ ሆነው ደብዳቤውን እንደጻፉትና፣ ኢትዮጵያ ቢሆኑ እንደማይጽፉት እና ሌሎች ትዝብት ላይ የጣሏቸውን ሀሳቦች ሰጡን። ሌላ ምንም ምንጭ መጥቀስ ሳያስፈልግ እርስ በእርሱ የተጣረሰና የተደነጋገረ “እውነታቸውን” መሞገት እንደሚያስፈልገው አመንኩበት። ሀሳቡን መሞገት ያስፈለገው “እውነቱ ይውጣ” በሚል እሳቤ አይደለም። የወንጌላዊው ንግግር ከቆሙለት እውነት ጋር የማይሄድ፣ ሆን ተብሎ እንዲዛነፍ የተደረገው ጉዳይ ደግሞ በእሳቸው ደረጃ ካለ ሰው የማይጠበቅ በመሆኑ ነው።
ወንጌላዊው እጅግ በርካታ ተከታዮችን ያፈሩ፣ በተከታዮቻቸው ዘንድ የታመኑና የተከበሩ እንደመሆናቸው ይህ የእኔ አስተያየት የግሌ ብቻ ሲሆን የሚያነጣጥረውም ወንጌላዊው ላይ ብቻ መሆኑ ግምት ውስጥ እንዲገባልኝ በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ። በእኔ ጽሑፍ ተከታዮቻቸው ስሜት ላይ ለሚፈጠረው የስሜት መነካት በቅድሚያ አሁንም ደግሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይቅርታው ግን ምናልባት ለሚፈጠረው የስሜት ጉድለት እንጂ ለሀሳቤ መሳሳት አይደለም። ወንጌላዊው የሀሳብ ስህተታቸውን የባረኩት “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሚዲያ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ብቻ ነው” በማለት ነው። ቢያንስ ግን ይህ ጽሑፍ የወጣው EBC ላይ አይደለም። ሀገራዊ ጉዳዮች የሚፃፍበት ሀገራዊ ነፃ ሚዲያ አለ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሌለ እንኳን እኔና እሳቸው፣ እንዲኖር ያልፈቀደው መንግሥትም አይክድም ። ላለመኖሩ የምንሰጠው ምክንያት ላይ ብቻ ነው የምንለያየው። በነፃ ብዙሀን መገናኛ ድርቀትና ጋዜጠኞችን በማዋከብ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚብጠለጠልበትና በዚህ ዘርፍ ሀገራችን ስመጥር ከሆኑ ጥቂት የዓለማችን ሀገራት አንዷ መሆኗ የሚያሳዝነን ነው። ይህ ግን የኢትዮጵያ ነፃ ሚዲያ እጥረት መኖሩን እንጂ በየቱም መመዘኛ በሀገሪቱ ያለው ብቸኛ ሚዲያ ኢብኮ መሆኑን አያመላክትም። “የመረጃው ፍሰት ከፍተኛ ነው” ባሉበት በየትም ሀገር ያለው ሚዲያ ሁሉ መንግሥት “በደፋው!” እያለ ሲፀልይበት የሚያድረው “ኢሳት” እንኳ ሳይቀር አራት ኪሎ ቤተ መንግሥቱ አጠገብ እንኳን ሳይቀር ይገኛል። በውጭ አገኛቸዋለሁ ያሏቸው እነየጀርመንና አሜሪካ ድምፅ፣ አይጋ ፎረም አይነቶቹ ሀገር ውስጥ ለእርሳቸው እንዴት እንዳልተገኙ አላውቅም። ወንጌላዊ ያሬድ “ለአቶ ኃይለማርያም “ደብዳቤ ለመጻፍ ዋና ምክንያት የሆናቸው በዶ/ር ደብረ ጽዮን “ኦፊሻል ዌብ ሳይት” ላይ ያገኙት ጽሑፍ እንደሆነ ይናገራሉ። ጽሑፉ “እንኳን ለ30 ሚሊዮን ህዝብ (አማራን ማለት እንደሆነ ገልጸዋል) አፍሪካን መደምሰስ የሚችል ኃይል አለ ‹‹ማለታቸው እንደሆነ ይገልፃሉ። እዚያው ቃለመጠይቃቸው ላይ በጋዜጠኛው “ደብዳቤውን ለምን ለራሳቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ቀጥታ እንዲደርስ አላደረክም? “ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የራሳቸው የፌስቡክ አካውንት ካላቸው ብዬ ፈልጌ በእሳቸው ስም የተከፈተ አምስት የሚሆን የፌስቡክ አካውንት አገኘሁና፤ የእሳቸው ትክክለኛው የቱ እንደሆነ ማወቅ ስላልቻልኩ ተውኩት“ ይላሉ፡፡ የተጠየቁትን ያላደረጉበት ትክክለኛው ምክንያት ያሉት ብቻ ባይሆንም፣ ሀሳቡ መድረስ ያለበት ለእሳቸው ብቻ ባይሆንም ያሉትን እንመንና በአቶ ኃ/ማርያም ስም ሀሰተኛ የፌስቡክ ገጽ ከተከፈተ (ሌላው ቢቀር አምስት አይኖራቸውምና) “የዶ/ር ደብረ ጽዮንስ እውነት ባይሆን? “ ብሎ ማሰብ ሩቅ አይደለም። ይህም ብቻ ሳይሆን ለመጠርጠር እጅግ የቀረበ ሌላም ምክንያት አጠገባቸው ነበረላቸው። አንድ የሀገር መሪ አንድን ብሔር በሙሉ ለማውደም ይፈልግ። በተግባርም ይሞክር። በምንም አይነት ይህን ጸያፍ ንግግር ፎቶውንና ስሙን ለጥፎ በአደባባይ ይጽፈዋል ተብሎ አይታመንም። አሁንም ሌላ አላሳመነም ቢባል እንኳን የሚያስጠረጥር ምክንያት። ለገዢው ግንባር ቅርብ የሆኑና የመንግሥትን ውበት ሲያደንቁ የሚውሉ ፌስቡከሮች፤ ዶክተሩ ምንም አይነት የፌስቡክ አካውንት እንዳልከፈቱ ደጋግመው ሲጽፉ እንዴት ተለይቶ ወንጌላዊው ዓይን ውስጥ ላይገባ ቻለ? ወንጌላዊው ይህን ደብዳቤ እንዲጽፉ ሜሪላንድ / አሜሪካ ሳሉ፤ “ጌታ ለእኔ ለብቻዬ ነገረኝ” ይላሉ። የጌታን ሀሳብ በጥሬው አልተቀበሉትም። “ጌታ ሆይ ተወኝ። ይህ የእኔ ቦታ አይደለም” ሲሉት ጌታ “ይህም የጥሪህ አካል ነው” እንዳላቸው ይገልጻሉ፤ ይሁንና ወንጌላዊው የጌታን ቃል ቀጥታ ተናገር እንደተባሉ አለመናገራቸውን ይናገራሉ። ጌታ ለእሳቸው የስጋ ደህንነት አስቦ ከሀገር እስኪወጡ ጠብቆ መልዕክት “ለእሳቸው ለብቻቸው” መላኩ አጠያያቂ ቢሆንም ቃል በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሊመጣ እንደሚችል እንመን። ለማንኛውም “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንገር “የተባሉትን መልዕክት የተናገሩት ለባለጉዳዩ ሳይሆን እንደ እርሳቸው አባባል ለቤተሰባቸው ነው። ቤተሰባቸውም “አምላክ ካለ አለ ነው። ተናገር! “አላላቸውም። “ለቤተሰቦቼ ስነግራቸው ፈርተው፤ ተው አሉኝና እኔም ሳልናገር ተውኩት” ይላሉ። በተለይም ለአንድ ወንጌላዊ ከአምላክና ከቤተሰብ ቃል የቱ ነው ተሰሚው? የአምላኩን ፈቃድና ሐሳብ ለመናገር የተጠራ ወንጌላዊ፤ ወዲያው ከሥጋና ደም የምክር አገልግሎትን ጠይቆ መልዕክቱን ማዘግየትን መፅሐፍ ቅዱሱስ ቢሆን የቱን ያህል ያበረታታል? ጋዜጠኛው የሚያውቀው
ሚስጥር ኖሮ ይሁን ወይም በሌላ ወንጌላዊውን ካሁን ቀደም በኦሮሚያ ግጭት ሲነሳና ሰው ሲሞት ዝም ብለው አሁን አማራ አካባቢ ሲመጣ መናገራቸው ወገንተኛ አያስብላቸው እንደሆነ ጠይቋል። ወንጌላዊው ግን በዚያን ወቅት ዝም አላሉም። በመካኒሳ ቃለህይወት አገልግሎታቸው ላይ “መንግስት ሳይፈቅድ ለተቃውሞ መውጣት አይገባም። ያለፍቃድ ወጥተው መከላከያ ሰራዊቱ እርምጃ ቢወስድ ጥፋተኛ የሚሆነው ወታደሩ ሳይሆን ህዝቡ ነው” ነበር ያሉት። ይህን ቃል የቤተክርስቲያኒቱ ሰዎች ወንጌላዊው ባሉበት ቢልኩላቸው መልካም ይሆናል። ረስተው ከሆነ ያስታውሱታል። ይህን ቃል የተናገሩት፤ “ከልብ ጭንቀት፣ ከመሸከም “እንደሆነ ተናግረው ወዲያው ደግሞ “ ምን ሊደርስብኝ እንደሚችል እገምታለሁ“ም ይላሉ። ግን ምንድነው ሊደርስባቸው የሚችለው? ቢበዛ እስር፣ እጅግ ቢበዛ ደግሞ ሞት። ሁለቱስ ግን ለአንድ ወንጌላዊ ምኑ ነው? ክብሩ አይደለም? ቃሉን ካልተጠራጠሩት የአምላክን ቃል ሲሰብኩ መሞት የጽድቅ ተግባር አይደለምን ? ይህ እርሳቸው የሚያገለግሉበት የፕሮቴስታንት ሀይማኖት ከሌሎቹ ይልቅ ብዙ ዋጋ የተከፈለለት ነው፡- ሞት፣ እርዛት፣ ግርፋት፣ ረሀብ…፣ የተደረገውን ሁሉ የደርግ ገራፊዎችና አስገራፊዎች ይመስክሩ። ራስን ከአደጋ ነፃ ቀጠና ውስጥ ካስገቡ በኋላ ለመናገርማ አንደኛውን የሚያውቁትን ከመመስከር ከታቀቡት የሀይማኖት አባቶች በምን ተለዩ? በምንም። “ይህን ድምጽ የሰጠኝ እግዚአብሔር ነው” ያሉት ወንጌላዊ ቀጠል አድርገው ደግሞ “ሌሎችም ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ነው የፃፍኩት” ይላሉ። ሌሎቹ መቼ እንዲያሰሙ ነው የፃፉት? እንደ እሳቸው አሜሪካ ሲሔዱ? ቤተሰቦቻቸው ሲፈቅዱላቸው? ወይስ እንደ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ከአምላክም መልዕክትም፣ ከቤተሰብ “ይቅርብህ “ም በላይ የሚያበሳጭ ፖስት ሲያገኙ? ወይስ ምን? “ወንጌላዊውን ምን ነካቸው? “ያስባለኝ ደግሞ በአማራ ክልል ስለተካሔደው ግጭት ሲገልጹ፤ “የክልሉ መንግሥት ሳያውቀው ታጣቂዎች ገብተው በደል አደረሱ “ማለታቸው ነው። ይህ የአንድ ወንጌላዊ ቃል ባይሆን እመርጥ ነበር። ለምንድነው የክልሉን መንግሥት ከተጠያቂነት ነፃ ያደረጉት? የክልሉ መንግሥት መከላከያ ሰራዊትን እርዳታ ጠይቆ መግባቱን ገልጿል። እሺ ወንጌላዊው አልሰሙም እንበል። ያም ቢሆን የክልሉ መንግሥት አልጠየቀም ብንል እንኳን ላያውቅ ግን በጭራሽ አይችልም። የዚህ ቃለመጠይቅ መጣረስ ትክክለኛው ምክንያት ወንጌላዊው እውነት ለመናገር አለመፈለግ ነው። ከቃለመጠይቁ ጀርባ የራሳቸው፣ የግላቸው እውነት መኖሩ ነው። ወንጌላዊው ብቻቸውን ሳይሆን ልጃቸውንም ይዘው (ስለ ባለቤታቸው መረጃ የለኝም። ግን እሳቸው ካልመጡ ባለቤታቸው መሄዳቸው አይቀርም ወይም ሄደዋል። አንዱ ወይም ሌላው ይሆናል።) አሜሪካ መሆናቸው ነው። በአሁኑ ሰዓት ልጃቸውን ት/ቤት ለማስመዝገብ እየተሯሯጡ መሆናቸው ነው።
የእሳቸው የቅርብ ሰዎች ቀድሞውንም እንደማይመለሱ ማወቃቸው ነው። ወንጌላዊው በአንደበታቸው “እዚያ (ኢትዮጵያ) ብሆን ይህን አደርገዋለሁ? መልሱ አይመስለኝም ነው “ብለው ጋዜጠኛው ሊጠይቀው የሚገባውን ራሳቸው ጠይቀው፣ ራሳቸው የመለሱትን ካየነው የወንጌላዊው ወደ ሀገር ቤት መመለስ ሩቅ ነው። ካልተመለሱ ደግሞ ከአሜሪካ መንግሥት የሚፈልጉት ጉዳይ አለ። እነዚያን ጥቅማጥቅሞች እጃቸው ለማስገባት ደግሞ ከሁሉም በላይ ከዚህ መንግሥት ጋር ከፍ ባለ የምሬት መጠን ጠብ ውስጥ መግባት አቋራጭ መንገድ ነው። አንድ የታወቀ ወንጌላዊ ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሲላተም ደግሞ ጉዳዩ ይፈጥናል። ይህ የታወቀ ጉዳይ ስለሆነ ማስረጃ አቅርብ የሚያስብል አይደለም። እናም ለወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን አንድ ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ። በትክክል ይህን ደብዳቤ የፃፉት በእርግጥም ከላይ እንደሚለው ለአቶ ኃ/ማርያም ነው ወይስ ውስጥ ለሚታዩት አቶ ኦባማ?

Read 15624 times