Monday, 19 September 2016 07:54

“የአገር ሽማግሌዎቼን ማን …?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ደግ የምንሰማበት ዘመን ይሁንልንማ!
ይቺን ስሙኝማ…ነሀሴ መጀመሪያ አራት ኪሎ አካባቢ ነው፡፡ ዝናቡ አዲስ አበባን እንደ ሁልጊዜውም ‘ቦዳድሶታል፡ (እኔ የምለው… በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር የአዲስ አበባን መንገድ ‘የሚቦድሰው’ ምን እንደሆነ የሚነግረን እንጣ!) እናላችሁ…መንገዱ የኩሬ መአት ሆኗል፡፡ የሆነች ‘የዘመኑ’ መኪና ወደ ፒያሳ አቅጣጫ ትመጣለች፡፡ ሁለት በአሥራዎቹ አካባቢ የሚሆኑ ሴቶች በአሪፉ ለብስው ወደ ድል ሀውልት አቅጣጫ ያመራሉ፡፡ መኪና ባልበዛበት፣ የመንገድ ጥበት በሌለበት ይቺ የዘመኑ መኪና ጭቃማ ውሀ ወደተጠራቀመበትና ልጆቹ ይጓዙ ወደነበሩበት መንገዱ ጠርዝ ተጠግታ፣ ልጆቹን በዛ ጭቃ ውሀ ታለብሳቸዋለች፡፡ እናማ…የሚገርመው ነገር ምን መሰላችሁ… መኪና ውስጥ የነበሩት ቢያንስ፣ ቢያንስ በሰባዎቹ መጀመሪያ የሚሆኑ ሁለት ሰዎች  በሠሩት ሥራ እንደመደንገጥ ፋንታ ከት እያሉ በሳቅ እየተንከተከቱ ሄዱላችሁ፡፡
እናማ… የዘንድሮ ‘የአገር ሽማግሌ’ እንዲህ ሆኖላችኋል፡፡
የምር እኮ ‘የአገር ሽማግሌ’ የጠፋባት አገር ሆናለች። የአዛውንቶች ጣልቃ ገብነት በሚያስፈልግበት ጊዜ፣ ይህኛውም ያኛውም ወገን “እህ…” ብሎ የሚሰማቸው፣ “እንዳላችሁት…” ብሎ ቃላቸውን የሚቀበላቸው የአገር ዋርካዎች በሚያስፈለጉበት ዘመን… አለ አይደል… በልጅ ልጆቹ ላይ ውሀ ረጭቶ የሚዝናና ‘የአገር ሽማግሌ’ የተፈጠረበት የጉድ ዘመን ነው፡፡
እናማ… አንዳንዱ የዘንድሮ ‘የአገር ሽማግሌ’ እንዲህ ሆኖላችኋል፡፡
ከወራት በፊት ነው… እዚህ የፈረደበት ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ…  ‘የአገር ሽማግሌው’ የሆነች ቁምጣ አይሏት የውስጥ ሱሪ ነገር አድርገው፣ ካልሲ የሌለው ጫማ ተጫምተው፣ ስቲኪኒ ክንዳቸው ላይ የሆነች በደንብ የማትነበብ ነገር ተነቅሰው (ከምሬ ነው!) የብራድ ፒትን መነጽር ሰክተው እየሄዱ ነበር፡፡
የምር ግን እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “መቋሚያህን ይዘህ ዳዊት በመድገሚያ ጊዜህ!” የሚለው ነገር በ‘ግሎባላይዜሽን’ ጠፋልን ማለት ነው! አንዳንድ መዝናኛ ስፍራ እኮ ብቅ ስትሉ ምድረ ‘ሲኒየር ሲቲዘን’ ገና በመሰናዶ ትምህርት ዕድሜ ላይ ያለ ይመስል የሚሆነውን ስታዩ…ተስፋ ብትቆርጡ አይገርምም፡፡  ይቺ አገር እንዲህ አልነበረችም፡፡
እናላችሁ… የሆነች የእሳቸውን ቁምጣ ‘ሱሪ’ የምታስንቅ ‘ቁምጣ ቀሚስ’ ያደረገች እንትናዬ (አሥራ ስምንትም፣ አርባ ስምንትም ልትሆን የምትችል የሚለው ይግባልንማ! እስከዚህ ድረስ ነዋ ግራ የተጋባነው!) በአጠገባቸው ስታልፍ ‘ቸብ’ ያደርጓታል፡፡ የ‘አክሴፕታንስ’ ይሁን የ‘ሪጀክሺን’ የማይለይ አስተያየት አይታቸው መንገዷን ቀጠለች። ‘የአገር ሽማግሌው’ (እኚህም የፈለገ ‘እሱ እኮ ገና ልጅ ነው’ ቢባልላቸውም ከሰባ አንድ ፈሪ አያንሱም)… እየተፍለቀለቁ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡
አንዳንዱ የዘንድሮ ‘የአገር ሽማግሌ’ የሴት መቀመጫ ‘ቸብ’ በማድረጉ የሚደሰት ሆኖላችኋል፡፡
እናላችሁ…“ዓይቤን ማን ወሰደው?” እንዳለው ጸሀፊ…አለ አይደል… “የአገር ሽማግሌዎቼን ማን ወሰዳቸው?” እያለች ግራ የገባት አገር ሆናለች፡፡
እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…‘ባለፈው ስርአት’ ጊዜ ነው… የሆኑ የሁለት ሰፈር ልጆች ቅልጥ ያለ የቡድን ጠብ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ነገሩ ከመባባሱ የተነሳ፣ አይደሉም ጠበኞቹ ወጣቶች፣ የአንዱ ሰፈር ነዋሪ በሌላኛው መንደር አካባቢ መታየቱም አስጊ ሆነ፡፡ ከዛም ‘የአገር ሽማግሌዎች’ ጣልቃ ይገባሉ፡፡ የሁለቱም መንደሮች ወጣቶችና ነዋሪዎች መንደሮቹን የሚለየው ድልድይ ላይ ትላልቅ የኢትዮዽያ ባንዲራዎች ይዘው ተገናኙ፡፡ በአገር ሽማግሌዎቹ አሸማጋይነትም “ይቅር ለእግዚአብሔር…” ተባባሉ፡፡ በዛው አበቃ፡፡
አዎ፣ እንዲህ አይነት የህዝብንና የአገርን ችግር ተረድተው ጣልቃ የሚገቡ እውነተኛ የአገር ሽማግሌዎች የነበሯት አገር ነች፡፡
አንዳንዱ የዘንድሮ ‘የአገር ሽማግሌ’ ህጻናት ላይ ውሀ በመርጨቱ ደስ የሚለው ሆኗል፡
ምን መሰላችሁ… እውነተኛ የአገር ሽማግሌ የሚያስፈልገን ጊዜ ላይ ነን ሲባል…አለ አይደል… “ሁሉንም እርግፍ አድርጋችሁ ተዉትና አብራችሁ ጠላ ከአንድ ሽክና ጠጡ…” አይነት ‘ማስታረቅ’ ሳይሆን…አለ አይደል… ቢያንስ፣ ቢያንስ አንዳችን የሌላችንን ሀሳብ እንድንደማመጥ የሚያደርጉ፤ ቢያንስ፣ ቢያንስ ይክፋም ይልማም፣ እንግባባም አንግባባም… መጀመሪያ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን የሆዳችንን እንድንነጋገር የሚያስችሉንና ‘አጉራህ ጠናኝ’ ስንል የሚገስጹን የአገር ሽማግሌዎች ያስፈልጉናል፡፡ ነገራችን ሁሉ ገደል አፋፍ ደርሶ…
ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ
ከማለታችን በፊት፣  
ታድያ እንግዲህ አንቺ አትዮዽያ፣ እኛስ ልጆችሽ
ምንድነን
አመንኩሽ ማለት የማንችል፣ ፍቅራችን
የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅንነት የሚያሳፍረን፣ ቂማችን የሚያስደስተን
ኸረ ምንድነን? ምንድነን?
ማለቱ የዝንተ ዓለም ውርሳችን ከመሆኑ በፊት፣ “እንዲህ ሲሆን ቁጭ ብለን አናይም…” ብለው ጣልቃ የሚገቡ፣ ለጎጣቸውና ለቡድናቸው ሳይሆን ለሀገርና ለህዝቧ የሚጨነቁ የአገር ሽማግሌዎች የሚያስፈልጉን ወቅት ላይ ነን፡፡
እናላችሁ…አገርም “የአገር ሽማግሌዎቼን ማን ወሰዳቸው?” እያለች ግራ የተጋባችበት ጊዜ ነው፡፡
ስሙኝማ…በየትኛውም እምነት ይሁን ኃይማኖት አባቶችን የሚያከብር ህዝብ ነው፡፡ አብዛኛው ህዝባችን የእነሱን ምርቃት የሚሻ፣ የእነሱን ግሳጼ የሚቀበል፣ ከእነሱ ቃል ላለመውጣት የግል ፍላጎቶቹን እንኳን ወደ ጎን እስከማድረግ የሚደርስ ነው፡፡ ታዲያ… በዚህ በከፋ ጊዜ የት አሉ? አማኙ ህዝብ ከምንም በላይ የእነሱን እገዛ፣ የእነሱን አባታዊ ቃል በሚፈልግበት ጊዜ የት አሉ? እንዲሁ “አልቅሱ! እሪ በሉ!” ብቻ እየተባለ የተረፈችንን እንጥፍጣፊ ተስፋ ማሟጠጥ ሳይሆን ለቅሶአችን ለእስከወዲያኛው የሚያበቃበትን መንገድ በመጥረጉ አባታዊ ጣልቃ ገብነታቸውን እየፈለግን እነሱ የት አሉ?
ደግሞላችሁ…ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ……አልፎ፣ አልፎ ድንገት ‘የሚናገሩ’ ብቅ ካሉም ከኃይማኖታዊ አስተምህሮት ይልቅ ከማኦ ‘ቀይ መጽሐፍ የተቀዱ የሚመስለን ለምንድነው? እናላችሁ… አገር እየታመሰ፣ የአደጋው ደመና እየጠቆረ፣ ህዝብ ፈጣሪውን…“ኧረ በቃችሁ በለን!” እያለ… ስንት መነገር ያለባቸውና ጊዜ የማይሰጣቸው ጉዳዮች እያሉ…‘አንዳንድ’ የኃይማኖት አባቶች… “ዛራና ቻንድራን ያየ ውጉዝ ከመአረዮስ…” አይነት ‘ትምህርት’ መስጠት…አለ አይደል…ትንሽ ግራ ያጋባል፡፡
እናማ…አገርም “የአገር ሽማግሌዎቼን ማን ወሰዳቸው?” እያለች ግራ የተጋባችበት ጊዜ ነው፡፡
አዬ፣ ምነው እመ ብርሀን? ኢትዮዽያን
ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀንዋን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
ይለናል ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‘በሰቆቃው ጴጥሮስ’። ያኔም እንዲህ እንዲህ እየተባለ ነበር፤ አሁንም እንዲሁ እያልን ነው፡፡ ደግመን ደጋግመን…
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
እያልን አገር… “የአገር ሽማግሌዎቼን ማን ወሰዳቸው?” እንዳለችው ሁሉ እኛም እንደዛው እንላለን፡፡
5:00 PM 9/17/2016
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3230 times