Monday, 19 September 2016 07:51

“የጎንደር ደም የኔ ደም ነው፤ የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው፤ ሁሉም ሲነሳ እኔም እነሳለሁ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

• የተሰደዱ ልሂቃን ፖለቲከኞች ይምጡና ስለ ሃገራቸው ይወያዩ
• ኢህአዴግ የሃይል እርምጃ መውሰዱ ወደ ፋሺዝም እየሄደ ነው ያስብላል
• የወልቃይት ጉዳይ፤ ጠባቦችና ትምክህተኞች እንዳይሰሙ እየተባለ ሲድበሰበስ ነው የቆየው
• እንደዚህ አይነት በኢኮኖሚ ያልተመጣጠነ ኑሮ ታይቶ አይታወቅም
• እነዚህ ሰዎች ያኔም አልታደሱም፤ አሁንም አይታደሱም

አቶ አስገደ ገ/ስላሴ (የህወኃት መስራችና አንጋፋ ታጋይ)

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች እንጀምር፡፡ በእኒህ ክልሎች ለተቀሰቀሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች መንስኤ ናቸው የሚሏቸው ነገሮች ይኖራሉ?
በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በአማራና በተለያዩ ቦታዎች ብዙ ተቃውሞች ይታያሉ፡፡ በትግራይም ይኸው ነገር አለ፡፡ ለዚህ ሁሉ መነሻው የኢህአዴግ ስርዓት ውስጣዊ ብስባሴና የፖለቲካ አስተሳሰቡ ዲቃላነት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ባህልና ልምድ ጋር የማይሄድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለመፍጠር የተደረገ ጥረት የፈጠረው ግጭት ነው፡፡ ሌላው ፌደራሊዝሙ በቋንቋ ተገድቦ መቅረቱ ነው፡፡ ይህ የተሣሣተ አወቃቀር ነው፡፡ ሶስተኛ በሃገሪቱ ያልተመጣጠነ የሃብት ክፍፍል፣የፍትህ፣ የደህንነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ ስደት፣ የኢኮኖሚ ችግር አለ። ሦስቱንም መንግስታት አይቻለሁ፤እንደዚህ አይነት በኢኮኖሚ ያልተመጣጠነ ኑሮ ታይቶ አይታወቅም። በአጠቃላይ ኢህአዴግ ይዞት የመጣው አላማና ህገ መንግስቱ የማይተገበር በመሆኑ ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡ የኦሮሚያን ጉዳይ ስንመለከት ህዝብ አላማከሩም፡፡ ፖለቲከኞችና ምሁራንን ሳያማክሩ በራሳቸው ቤት ዘግተው ነው ውሳኔውን ያስተላለፉት፡፡ ስለዚህ በኦሮሚያ ለተፈጠረው ችግር ዋናው ምክንያት የራሱ የኢህአዴግ ፖሊሲ ነው፡፡ የከተማ፣ የኢኮኖሚና የቋንቋ ፖሊሲው የፈጠረው ነው፡፡ በኦሮሚያ ህዝቡ ድሮ ከነበረው የነፍጠኛ ስርአት አልተላቀቀም፡፡ መሬታቸው እየተቆረሰ ለሃብታሞች እየተሸጠ፣ እነሱ ግን በድህነት ከመኖር አልወጡም፡፡ ስለዚህ ህዝቡ የተቃወመው ይሄን ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ በተቃውሞው ወቅት ሃብት መውደሙ ግን አግባብ አይደለም፤ግን የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ነው ነገሩ፡፡ መንግስት ደግሞ የሃይል እርምጃ መውሰዱ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ኢህአዴግ ወደ ፋሺዝም መንገድ እየሄደ ነውም ያስብላል፡፡ ወደ አማራ ክልል ቅማንት ስንሄድ፣ቅማንት ቀድሞ የማንነት ጥያቄው ትኩረት አልተሠጠውም ነበር። የራሱ የኢህአዴግ የቋንቋ ፌደራሊዝም ያመጣው ነው፡፡ ከመጣ በኋላም በህገ-መንግስቱ መሠረት፣ ውድመት ሳይከሰት በጊዜ ሊፈታ ይገባ ነበር፡፡ ደም መፋሰስ ተከተለ፤ተደናግጠው ችግሩን ፈተነዋል አሉ፡፡ ግን አሁንም ጉዳዩ ገና ነው፡፡
የወልቃይት ጉዳይም ሌላ የተቃውሞ መነሻ ነው። በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ላይ ምን ይላሉ?
ወልቃይት የማን ነው ከተባለ፣ መልሴ የኢትዮጵያ ነው የሚል ነው፡፡ በእኔ እድሜ አማራ፣ ትግሬ የሚባል ነገር አላውቅም፡፡ አፋር አልነበረም፤ ግማሹ ትግራይ ግማሹ ወሎ ውስጥ ነበር፡፡ ወልቃይት በኛ እድሜ፣ ኢህአዴግ ወደ ትግራይ እስከሚከልለው ድረስ በበጌምድር ስር ነው የነበረው፡፡ አማራ የሚል ነገር ግን አልነበረም፡፡ በጌምድር የሚባል ነው የነበረው። ሃቁን እንናገር ከተባለ፣ከተከዜ ምላሽ በጌምድር አስተዳደር ነበር፡፡ ግን ይሄ አይደለም ዋናው የወልቃይት ጉዳይ፡፡ በብአዴንና በህወሓት መካከል ያለው የበላይነትና የበታችነት ሽኩቻ የፈጠረው ነው። የወልቃይት ጉዳይ 24 አመት ሆኖታል ከተጀመረ። አንዴ ጠባቦችና ትምክህተኞች እንዳይሠሙ እየተባለ፣ ጥያቄው እየተድበሰበሰ ነው የመጣው፡፡ ጥያቄው ከተከለለ ጀምሮ የነበረ ነው፤ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ድንገት የመጣ አይደለም፡፡ ብአዴንና ህወሓት ያውቁታል፡፡ በ1986 ጥያቄውን ይዞ አንድ ቡድን ወደ መቀሌ መጣ፡፡ ምላሽ ሳያገኙ ተባረሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ይሄንኑ ጥያቄ ይዘው በየጊዜው ይመጡ ነበር፤ነገር ግን የአድማ መሪዎች እየተባሉ ይታሠሩ ነበር፡፡ ይሄ ነው እኔ በቅርበት የማውቀው ሃቅ፡፡ አሁን ሁኔታው ሰፍቶ ጥያቄው አማራ አቀፍና ትግሬ አቀፍ እንዲሆን ተደረገ፡፡ ህወኃትና ብአዴንም የዚህ ሴራ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ወልቃይት ወደ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ነው ያለው፡፡ ለምን አማራ አቀፍና ትግሬ አቀፍ እስኪሆን ተጠበቀ? ለምን በጊዜ በህዝበ ውሳኔ ምላሽ አላገኘም? ይሄ የኢህአዴግ ውስጣዊ ብስባሴን የሚያሳይ ነው፡፡
የወልቃይት ጉዳይ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው ይላሉ?
በዚህ አካሄድ ይሄ ጥያቄ ይፈታል ማለት ዘበት ነው፡፡ አከላለሉ ይቀየር ከተባለ ህገ መንግስቱ መቀየር አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ተወያይተው አይፈቱትም፡፡ የየራሳቸው ሴራ አላቸው፡፡ ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ እንደሚባለው ተናንቀዋል። ስለዚህ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ህዝበ ውሳኔ መደረግ አለበት፡፡
በእርስዎ አስተያየት በህዝበ ውሳኔው ማን ነው የሚሳተፈው? የአማራና የትግራይ ህዝብ ይሳተፋል?
አይደለም፡፡ የአማራም፣ የትግራይም ህዝብ መሳተፍ አለበት የሚለው አያስኬድም፡፡ ወልቃይት ያለ ህዝብ ነው መሳተፍ ያለበት፡፡ ከተከዜ ምላሽ ያለ ጥያቄ፣ በተነሳባቸው ቦታዎች ያለ ህዝብ ነው መወሰን ያለበት፡፡ በህገ መንግስቱ ሁለት ዓመት የተቀመጠ ዜጋ ይመርጣል ይመረጣል ስለሚል፤ይሄም ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ ግን እነዚህ ሰዎች ይሄን ማድረግ አይፈልጉም፡፡ የትግራይ ክልል፤ የትምክህተኞች ጥያቄ ነው እንጂ ጥያቄ የለም ይላል። ይሄ መቆም አለበት፡፡
በሁለቱ ክልሎች የሚታዩ ተቃውሞዎች ወዴት የሚያመሩ ይመስልዎታል?
በጎንደሩ ግጭት ወደ ትግራይ የሸሹ ሰዎች አሉ፡፡ እንደኔ እነዚህ ሰዎች ወደነበሩበት መመለስ አለባቸው። እኔ ኦሮሞ ሃገሬ ነው፣ አማራም አገሬ ነው፡፡ የትም ቦታ ሰርቼ የመኖር መብት አለኝ። የአማራ ክልል ስህተት ተፈፅሟል ብሎ ካመነ፣ ህዝቡን ማስታረቅ አለበት፡፡
እኔ ጎንደር ነው ተምሬ ያደኩት። ህዝብ ቆጠራ ቢደረግ በጎንደር 50 በመቶው ትግሬ ነው የሚሆነው፡፡ ህዝቡ እንዲህ ነው ተዋዶ፣ ተጋብቶ፣ ተዋልዶ የኖረው፡፡ ይህ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር  ችግሩ በጊዜ መታረም አለበት፡፡ የጎንደር ደም የኔ ደም ነው፤የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው ሁሉም ሲነሳ እኔም እነሳለሁ፡፡
ኢህአዴግ በጥልቅ ተሃድሶ ችግሮችን እፈታለሁ ብሏል፡፡ ከዚህ ተሃድሶ እርስዎ ምን ይጠብቃሉ?
ምንድን ነው መታደስ?! ህወኃት ከተመሰረተ ጀምሮ በትግሉ ጊዜ አብሬ ነበርኩ፡፡ ህዳሴ ተብሎ በ1985 ዓ.ም ከ32 ሺህ በላይ ታጋይ ነው የተባረረውና የታሠረው፡፡ እኔም ከነዚህ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ አናት መጡና በ1993 በውስጣቸው ክፍፍል መጣ፡፡ በ1985 የነበረው የኤርትራ ሪፈረንደም ጉዳይ ነበር፡፡
የባህር በር ማጣት የለብንም የሚለውና የኢትዮጵያን የሠለጠነ ሰራዊት አንበትነው የሚለው ሃሳብ ነበር ከድርጅቱ ለመባረር ያበቃን፡፡ ግን የሆነው የጅምላ እስርና ማባረር ነው፡፡ በ1993 የነበረው ተሃድሶ ላይ ደግሞ በትግራይ የገብሩ አስራት እቅድ፣ የኪራይ ሰብሳቢዎችና የሙሰኞች ተብሎ አንዲቋረጥ ተደረገ። 500 ግድቦች ሊሰራ እቅድ ወጥቶ 15 ያህል እንደተሰራ ይህ ችግር ተፈጥሮ፣ የግድቡን እቅድ ትተው ወደ ውሃ ማቆር ገቡ፤ ግን አልቻሉም ከሰሩ። ከዚያ በኋላ ያመጡት ለውጥ የለም፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት----ለአፍ ቀሎ እስከ ዛሬ አለ፡፡ ህዝብ እየተቸገረ ይሰደዳል፡፡ ወጣቱ ደህይቷል፣ ይሰደዳል፤ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ያኔም አልታደሱም፤ አሁንም አይታደሱም፡፡ የበሰበሰ ስርአት ስለሆነ አይታደሱም።
አሁን ህገ መንግስቱ በኢህአዴግ ተሸርሽሯል። ተቃዋሚዎች የሉም፡፡ ይህን ማስተካከል ከፈለጉ ወደ ውጭ የተሰደዱ ልሂቃን ፖለቲከኞች አሉ፡፡ ወደ ሃገር ውስጥ ይግቡና ስለ ሃገራቸው ይወያዩ፣ እንዲህ ካላደረጉ እነዚህ ሰዎች ከችግሩ አይወጡም። አሜሪካኖች እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት ለ300 ቀናት ያህል ነው ከሁሉም ህዝብ ጋር በጥልቀት ተወያይተው ችግራቸውን የፈቱትና ዛሬ ላይ የደረሱት፡፡
እኛም እንዲህ ነው ማድረግ ያለብን። አሁን ይሄን ሳያደርጉ በጥልቀት እንታደሳለን ካሉ፣ ለኔ የሚገባኝ ትርጉም፤ በጥልቀት ጭቆናችንን እናጠናክር እያሉ እንደሆነ ነው፡፡
ሠሞኑን ተማሪዎች እንሰበስባለን ብለዋል፤ ከ8ኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርስቲ። ግን እንዴት የ8ኛ ክፍል የ13 ዓመት ተማሪ ፖለቲካ ይማራል? ይህ ህገ መንግስቱን በግልጽ መዳፈር ነው። ለዚህ ነው በጥልቀት መታደስ የሚሉት ውሸት ነው፤ ሊታደሱ አይችሉም የምለው፡፡፡ ሰው ከስልጣን ማንሳትና ሌላ መሾም መታደስ አይደለም፡፡
እርስዎ ለፖለቲካዊ ችግሮቹ መፍትሄ ነው ብለው የሚያስቀምጡት ምንድን ነው?
እኔ የሚታየኝ፣ አንደኛ፡- እንታደሳለን ካሉ ብቻቸውን ቤት ዘግተው ሊታደሱ ስለማይችሉ፣ የገለልተኛ ልሂቃን ተሳትፎ መኖር አለበት፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ነጋዴዎች፣ ገበሬዎች---ሁሉም መሳተፍ አለበት በግምገማው፡፡ ሁለተኛ፡- የፌደራሊዝም አወቃቀሩ ነው ለሀገራችን ጠንቅ የሆነው፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱም መፈተሽ አለበት። ይሄን መፈተሽ ያለባቸው ልሂቃኖቹ ናቸው እንጂ ኢህአዴግ ራሱ አይደለም፡፡
ሶስተኛ፡- ተቃዋሚዎች በውስጥም በውጭም ያሉ በነፃነት በዚህ ሂደት ይሳተፉ፡፡ አራተኛ፡- የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ፤ ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች ሁሉ ይፈቱ። አምስተኛ፡- በውጭ ያሉ ትጥቅ አንስተው የሚዋጉ ትጥቅ አውርደው፣ ዋስትና አግኝተው ገብተው፣ የመደራደርና የሀገራቸውን እጣ ፈንታ የመወሰን እድል ሊያገኙ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
አሁን ትልቁ ጠንቅ እየሆነ ያለው የሀብት አለመመጣጠን ነው፤ይሄ በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ ሚዲያዎችም ይፈትሹ፡፡

Read 3606 times