Monday, 19 September 2016 07:42

የኮንሶው ቀውስ እያወዛገበ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

በኮንሶ ስለተፈጠረው ተቃውሞና ግጭት የኮንሶ ጥያቄ ኮሚቴ አባል የሆኑትን አቶ ገመቹ ገንፌ የደቡብ ክልል መንግስት
ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ኬይረዲን ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በተፈጠረው ግጭት መነሻ
ምክንያት ዙሪያ እንዲሁም አሁን ስላለበት ሁኔታ በስልክ አነጋግሯቸዋል፡፡

‹‹ጫካ ውስጥ ተቀምጠው
ችግሩን ወደ መንግስት እያላከኩ ነው››

በኮንሶ የተፈጠረው ግጭት ምክንያቱ ምንድነው?
ኮንሶ የተፈጠረው ግጭት የተነሳበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ነገር ግን በዋናነት ግጭቱ እንዴት ተነሣ? ለምን ተነሳ? ወዴት አመራ? የሚለውን ስናየው፤ በዋናነት በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ስር ኮንሶ ወረዳ አለ፡፡ ኮንሶ ወረዳ ሳይሆን ዞን መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ህገ መንግስታዊ መብት የተሰጠው ጥያቄ ነው፡፡ ይሄን መነሻ አድርገው የኮሚቴ አባላት ነን ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ጥያቄውን ለክልሉ ም/ቤትም፣ ለክልሉ ብሄረሰቦች ም/ቤትም አቅርበዋል፡፡ ጥያቄያቸው በሚገባ ታይቷል፡፡ ጥያቄውን ሲጠይቁ ሁለት አይነት አመለካከት ነው የነበራቸው፡፡ አንደኛ ህዝቡን በዞን እናደራጅሃለን ብለው ገብተው የተለያዩ መዋጮዎችን ሰብስበው ሲንቀሳቀሱ ነበር። ነገር ግን ጥያቄው የክልሉ መንግስት ጋ ሲመጣ ማለት ነው፡፡ ኮንሶ ዞን መሆን የማይችልበትን ምክንያት ከአካባቢው ሰላምና ከማንነት አንፃር መዝኖታል፡፡ እነዚህ አካላት፤  ‹‹ህገ መንግስቱ የሰጠንን ማንነት ክልሉ ከልክሎናል›› ነበር ያሉት፤ ነገር ግን የኮንሶ ብሄረሰብ ማንነቱ ታውቆና ተከብሮ፣ ራሱን ችሎ ራሱን በራሱ በወረዳ እያስተዳደረ ያለ ነው፡፡ ወረዳውን የሚያስተዳድረው በራሱ የኮንሶ ህዝብ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ መልስ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ኮንሶ ልክ እንደ ሌሎቹ የክልሉ ብሄረሰቦች በራሱ ቋንቋ የመዳኘት፣ ራሱን የማስተዳደር፣ የራሱን ባህልና ቋንቋ የማሳደግ መብት አግኝቷል፡፡ ከዚህ አንፃር በክልሉ መንግስትም በብሄረሰቦች ም/ቤትም ከማንነት ጋር የተቀላቀለበት ይህ ጥያቄ ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ‹‹እኛ በቁጥር ብዙ ነን፤ ስለዚህ ዞን እንሁን›› የሚል ጥያቄ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እነሱ በቁጥር ብዙ ነን ሲሉ፤ በሰገን ዞን ካሉት 8 ብሄረሰቦች በቁጥር እንበልጣለን የሚለውን መነሻ አድርገው ነው እንጂ በአጠቃላይ ከሀገር አቀፍ ቁጥር አንፃር አይደለም ጉዳዩን ያዩት፡፡
ከክልላችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ስናየው ደግሞ 56 ብሄረሰቦች አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ በ56 ዞን አደራጅተን አይደለም የምንሰራው፡፡ ተመሳሳይ ባህል፣ አደረጃጀት ያላቸውን በአንድ ዞን ነው የምናጠቃልለው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኦሞ ዞን 16 ብሄረሰቦች፣ ጋሞ ጎፋ 5 ብሄረሰቦች፣ ሰገን አካባቢ ህዝቦች 8 አለ፡፡
በዚህ መልኩ ነው የምናደራጀው፤ በዚህ መልኩ ነው መቀጠል ያለብን፤ ብለን ምላሽ ሰተናቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ኮንሶ ልዩ ወረዳ ነበር፡፡ አማሮ፣ ቡርጂ የመሳሰሉት ልዩ ወረዳ ነበሩ፡፡ ግን ይሄ ልማት አላመጣም፤ ትርፉ ግጭት ነበር፡፡ ከዚህ መነሻ ነው ወደ አንድ ዞን የተጠቃለሉት፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙም ችግር የለም ነበር፡፡ ችግራቸውን እርስ በእርስ እየተመካከሩ ይፈቱ ነበር፡፡
ህዝቡ ተወያይቶ፣ ጥናት ተጠንቶ ነው ይህ አደረጃጀት ተመራጭ የሆነው፤ ስለዚህ በዚህነ መቀጠል አለበት የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። ምላሹን በፀጋ ተቀብለው ወደ ኮንሶ ከሄዱ በኋላ ግን እናስፈፅማለን ብለው የተቀበሉት ገንዘብ ስላለ ያሳፍራቸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን የክልሉ መንግስት መልስ ካልሠጠ የፌደራል መንግስት አለ። የክልሉ መንግስት ጥያቄያችሁ ተገቢ አይደለም ብሎ መልሷል፡፡ የክልሉ የብሄረሠቦች ም/ቤትም ታች ድረስ ወርዶ ህዝቡን አወያይቶ፤ ህዝባዊ ጥያቄ እንዳልሆነ አረጋግጧል፡፡ ህዝቡ አሁን ያለው አደረጃጀት እንዲቀጥል  ፍላጎት አንዳለው ተገንዝቧል፡፡ ይሄን ውሣኔ ባለመቀበል ነው ይሄ ሁሉ ግጭት የተፈጠረው፡፡
ጉዳዩ ጭራሽ ወደ ጎሳ ነው የወረደው፡፡ የ23 ጎሣ ተወካዮች ነን ብለው ነው መንቀሳቀስ የጀመሩት ማህበረሰቡን ማስፈራራት፣ ከሌላው ማህበረሰብ እንዳይቀላቀል ማድረግ ነው የተያያዙት፡፡ ሰዉ 10 ወር ሙሉ መዋጮ አንገሽግሾታል፡፡ ከብቱን እህሉን ሸጦ ነው የሚያዋጣው፡፡ በዚህ ችግር አባሮባ የምትባል ቀበሌ ላይ ቤቶች ተቃጥለዋል። 6 ሰዎች ሞተዋል። ይሄ ቀላል ጉዳት አይደለም። 2 አዛውንቶች ተቃጥለው ነው የተገኙት፡፡ ቤት ሲቃጠል ማምለጥ ያቃታቸው ናቸው የተቃጠሉት፡፡
ቃጠሎውን ያደረሱት እነሱ ናቸው እያሉኝ ነው?
ምን መሰለህ…. በዚህች ቀበሌ ላይ የመሰረተ ልማት መንገድ ተሰርቷል፡፡ በዚህ ስራ ላይ ለተሳተፉ ገንዘብ ተከፍሏል፡፡ ይሄን ገንዘብ ለኮሚቴው እንቅስቃሴ ስጡን የሚል ጥያቄ ነው ያነሱባቸው፡፡ ማህበረሰቡ ደግሞ ከብታችንን ሸጠን፤ ንብረታችንን ሸጠን ሰጥተናችኋል፤ ከዚህ በኋላ አንችልም ይሏቸዋል፡፡ ለምንድን ነው የማትሰጡት በሚል ይሄ ጫካ ውስጥ ቁጭ ብሎ ውሳኔ የሚያስተላልፈው 23 አባላት ያሉት ኮሚቴ፤ የኮንሶ በዞን የመደራጀት ጥያቄ ላይ እንቅፋት ሆነዋል በሚል ነው ሰዎች ቤት ውስጥ በተቀመጡበት በር እላያቸው ላይ መዝጋት የጀመሩት፡፡ በዚህ ሰዓት ነው ህብረተሰቡ ድርጊቱን በመቃወሙ ግጭት የተፈጠረው፡፡ ቤታቸውን ማቃጠልና እርስ በእርስ ህይወት መጠፋፋት ውስጥ የተገባው በዚህ መልክ ነው፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ይህ ከተፈጠረ በኋላ ነው ገብቶ ፀጥታ የማስከበር ስራ የጀመረው፡፡
አሁን የክልሉ መንግስት በአካባቢው ምን ተግባር ነው እያከናወነ ያለው?
አንደኛ፡- የተፈናቀሉት እንዲመለሱ፤ ቤት የተቃጠለባቸው ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲሰባሰቡ ተደርጓል፡፡ ከነከብቶቻቸው ጫካ የገቡ ነበሩ፤ እነሱንም ወደ መጠለያ የመመለሱና ለከብቶቻቸው ግጦሽ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከህዝብ ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ ትናንት ከወጣቶችና ሴቶች አመራሮች ጋር በተለያየ ደረጃ ውይይት ተደርጓል፡፡ አሁን በጣም ሠላማዊ ነው፡፡ ህዝቡ ወደ መደበኛ ስራው ተመልሷል፡፡
የደረሡን መረጃዎች ግን ግጭቱ እንደቀጠለና እንደውም ጦርነት እየተካሄደ እንዳለ ነው የሚያመለክቱት..?
እነሡ እንደዛ አይነት መረጃ ሊሠጡ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ገንዘባችንን አምጡ፤ በቃን እያለ ስለሆነ ነው፡፡ ሰው በውይይት መድረኮቹ ላይ ባንዲራ ይዞ እየመጣ፤ ‹‹በቃን እስካሁን አሳስተውናል›› እያለ ነው፡፡ አሁን በጫካ ውስጥ ተቀምጠው፤ ችግሩን ወደ መንግስት ለማላከክ ነው፡፡ መንግስት ጣልቃ ባይገባማ፣ ህብረተሰቡን ጨርሰውት ነበር፡፡ አሁን ኮንሶ ሰላም ነው፡፡
የሠራተኞች ደመወዝ አለመከፈል ጉዳይስ?
የመንግስት ሰራተኛ መደበኛ ስራውን እየሰራ ደሞዝ የማይከፈልበት ሁኔታ የለም፡፡ አገልግሎት ላይ ላሉት እየተከፈለ ነው፡፡ የኮንሶ ተወላጅ የሆኑትን ሠራተኞች ከስራ የማስወጣት ስራ ነው እነሱ የያዙት፡፡
እናንተ ከሰራችሁና ከመንግስት ደሞዝ ከበላችሁ፤ ጥያቄያችን መልስ አያገኝም፤ ስራችሁን ትታችሁ ውጡ ነው ያሏቸው፡፡ ያለው እውነት ይሄ ነው፡፡ ዛሬም ነገም ወደ ሥራቸው ከመጡ ደሞዛቸው ይከፈላቸዋል፡፡
ቤታቸው ለተቃጠለባቸውና ንብረት ለወደመባቸው የክልሉ መንግስት ምን አስቧል?
ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ጊዜያዊ መጠለያ አቅርቧል፡፡ ቋሚ የሆነ በእቅድ የተደገፈ ሥራ ደግሞ ጎን ለጎን እየተሰራ ነው፡፡


===================================

‹‹ወደ ኦሮሚያ ክልል መጠቃለል እንፈልጋለን”

በኮንሶ (ትናንት ነበር ቃለ ምልልሱ የተደረገው)
ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?


በኮንሶ (ትናንት ነበር ቃለ ምልልሱ የተደረገው) ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ከትናንት የቀጠለ በዞኑ ውስጥ ያሉ ሌሎች ወረዳዎች በማስተባበር፣ ተዋጊ ኃይሎች ከዚያ ውስጥ መልምለው በሁለት ቀበሌዎች ላይ የከፈቱት ጦርነት ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ ከቡርጂ፣ ከአማሮና ከደራሼ የተመለመሉ ተዋጊ ሚሊሺያዎችን በ9 መኪና አስተባብረው በኮንሶ ህዝብ ላይ አዝምተዋል፡፡ ሃሙስ ከሰዓት የጀመረው ግጭት ዛሬም (ትናንት) ቀጥሎ እንደዋለ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በሶስት ቀበሌዎች ላይ ባለፉት 3 እና 4 ቀናት በፊት የጀመሩት ዘመቻ ወደ ሌሎች ቀበሌያት እየተዛመቱ ነው፡፡ በተለይ ትናንት ማለዳ የኮሚቴ ተወካዮችን ቤት የማፍረስ፣ የመፈተሻ ስራ ውስጥ ናቸው፡፡ እቤት ያሉ ዶክመንቶች ተዘርፈዋል፡፡ በርካታ ሰዎች ታስረዋል፡፡ ያገኙትን ሰዎች በሙሉ እያሰሩ ነው፡፡ ዛሬ (አርብ) ማለዳ ብቻ 25 ሰዎች መታሰራቸውን መረጃው ደርሶናል፡፡ ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ለማቅረብ የተማማለ በመሆኑ ምንም የተለየ እንቅስቃሴ አላደረገም፡፡ እነሱ ግን ህዝቡን እያስጨነቁና እያስገደዱ ነው፡፡ በመሳሪያ አካባቢውን እያስጨነቁ ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ምን እንደሚያደርጉ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ፍተሻውና ማዋከቡ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የታሰሩ ሰዎችን መጠየቅ አይቻልም፤ ምግብም አያገኙም፡፡ ሰው ዘመድ ጥየቃ ከሄደ ይታሰራል። ኮንሶ ከአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለች ሳትሆን በልዩ ፕላኔት ላይ የተቀመጠ፣ እንዲጠፋ የተፈረደበት ህዝብ ይመስላል፡፡ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ እያገኙ አይደለም፤9 ወር ደሞዝ ያላገኙ አሉ። አካባቢው ድርቅ የሚያጠቃው እንደመሆኑ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ የነበረ ነው፡፡ ይሄን እርዳታ አመቱን ሙሉ አላገኘም፡፡ ህፃናትና እናቶች ህክምና ማግኘት አልቻሉም፡፡
በግጭቱ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል ነው?
እስከ ነሐሴ 4 ሰው ተገድሎ ነበር፡፡ ሰሞኑ ግን የሟቾች ቁጥር በርካታ እንደሆነ ይገመታል፡፡ አስክሬን ማንሳት ስላልተቻለ ለማወቅ ያስቸግራል። አስክሬኖች ለቤተሰብ አልተሰጡም፡፡ ትናንት ማታ (ሀሙስ) 6 አስክሬኖች አንድ ቦታ ተቀምጠው ሰዎች እንዳያነሱ መሳሪያ እየተተኮሰ እየተጠበቀ ነው። በተለያየ አቅጣጫ አስከሬን ውሰዱ እየተባለም ከፖሊስ ጣቢያዎች ይደወላል፡፡ ግን ሰው ፈርቷል፤ ከሄደ እንታሰራለን ብሎ ይሰጋል፡፡ እስካሁን በእጃችን ተረክበን የቀበርነው ሁለት አስክሬን ብቻ ነው፡፡ አንደኛዋ ወልዳ ቤት ውስጥ ያለች አራስ ሴት ናት፤ በጥይት የሞተችው፡፡ አራስ ህፃኑ ወዴት እንደወሰዱት እናውቅም፡፡ ከሷ ውጭ ሌላ አንድ ሰው ተገኝቶ ተቀብሯል፡፡ ሌሎች ግን በርካታ ሰዎች ጠፍተውብናል፡፡ በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ በርካቶች ተሠደዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ እናንተን ጠርቶ ለማናገር ሙከራ አድርጓል?
ከክልሉ መንግስት ጋር ልናደርግ የሚገባንን ውይይት ከዚህ ቀደም አድርገን አጠናቀናል። ጥያቄያችንን ለመመለስ ፍቃደኛ አይደለም፡፡ ጥያቄውን ካልመለሳችሁ፣ በቃ በዚህ ጉዳይ ከእናንተ ጋር መወያየት የለብንም፤ ነገር ግን በሌሎች ጉዳዮች ላይ እንወያይ ብለናቸው ነበር፤ ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ውይይት የማናደርግ ከሆነ ሌላ የሚያገናኘን ነገር የለምና አናውያያችሁም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ሠራተኞቹ ደሞዝ አጥተው በሌሎችም ላይ ጫና እያደረሠ ያለው፡፡ ባለፈው ጊዜ በምክር ቤት ስብሰባም ሆነ በደህዴን ስብሰባ ‹‹ከዚህ በኋላ የኃይል እርምጃ ይወሰዳል›› ብለዋል፡፡
ህዝቡ ነው ሠላማዊ እንጂ እነሱ ነገሩን በኃይል ለማስተናገድ ነው የተዘጋጁት፡፡ ድርድር አያስፈልግም በሚል ነው የሃገር ሽማግሌዎችን እንኳ ለማነጋገር ሳይፈልጉ፣ የኃይል እርምጃ እየወሰዱ ያሉት፡፡
የሠራተኞች ደሞዝ ያለመከፈል ጉዳይ ላይ የክልሉ መንግስት ለፋና ሬድዮ በሠጠው ምላሽ፤ ‹‹የመንግስት ደሞዝ እንዳትቀበሉ›› በሚል ሰራተኞች ላይ ማስፈራርያ በመድረሡ ነው ያልተቀበሉት እንጂ ክልሉ ደሞዝ አይከፈልም አላለም ብለዋል እርስዎ ደግሞ ደሞዝ አልተከፈለም እያሉ ነው፡፡ ሁለቱን እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው?
የሚያሣዝነው ነገር ይሄ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ‹‹በሬ ወለደ›› ውሸት ነው የሚዋሸው፡፡ መንግስት እንደ መንግስት መዋሸቱ በጣም ያሳዝናል፡፡ ግለሠብ ሰዎች ቢዋሹ ምንም አይደለም፡፡፡ የሚዋሸው እኮ ወደፊት አስተዳድረዋለሁ የሚለውን ህዝብ ነው። ያንን ህዝብ እንዲህ እየዋሸ ነገ በምን ሞራል ነው ፊቱ መጥቶ የሚቀመጠው፡፡ አንድ ሰራተኛ ስራ ላይ የሚቀመጠው የስራ አከባቢው ደህንነትና ሰላም ሲጠበቅለት ነው፡፡
በኮንሶ ያለው እውነት ጥያቄውን ካልተዋችሁ መስራት አትችሉም ነው፡፡ ሠራተኛ ለስራ ሲሄድ ስብሰባ ነው የሚጠሩት፡፡ እኛ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት ነው የጠየቅነው፡፡ ጥያቄውን የማትመለሱ ከሆነ በስርአቱ በፅሁፍ ምላሽ ስጡን ነው  ያለው ህዝቡ፡፡ ይሄ ነው ያለው እውነታ፡፡  ሰራተኛ ሲወጣና ሲገባ ይታሠራል፡፡ የሰው ሃይል አስተዳደር ሃላፊዎች ሁሉ ከስራቸው ተባርረዋል። ሰራተኛውን በተለያዩ መንገዶች እያዋከቡ ነው። በመጨረሻ ላይ ያደረጉት ቢሮዎች መቆለፍ ነው። ቢሮ ከተቆለፈ በኋላ ሰራተኛ የት ገብቶ ይሰራል? ቢሮዎች ደግሞ በልዩ ሃይል ነው የሚጠበቁት። ሠራተኞች ወደ አካባቢው ከሄዱ ይደበደባሉ፣ ይታሠራሉ፡፡ ሠራተኛው ስራ ተው የሚሉት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ለጥያቄያችን መልስ ስጡን ስንል ‹‹የትም ብትሄዱ የተለየ ነገር አታገኙም፡፡ ፌደራል ብትሄዱም እኛው ነን ያለነው ይሉናል፡፡ ሰራተኛው አማራጭ በማጣቱ ነው ቤቱ ቁጭ ያለው፡፡ የሚሉት ሁሉ ውሸት ነው፡፡
የክልሉ መንግስት ምላሽ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ እናንተ ደግሞ ጥያቄያችንን እንቀጥላለን ብላችኋል በምን አግባብ ነው ጥያቄውን የምትቀጥሉት?
ጥያቄውን በአግባቡ አሁንም ቀጥለናል፡፡ የክልሉ መንግስት አመቱን ሙሉ አልመልስም ሲለን ቆይቶ፣ መጨረሻ ላይ አሁን ‹‹ባላችሁበት ቆዩ›› የሚል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡ ይሄን ውሳኔ በመቃወም ወደ 81 ሺህ ሰው ፊርማ ተሰብስቦ፤ ወደ ፌደሬሬሽን ም/ቤት አስገብተናል፡፡ አሁን ጉዳዩ ያለው በፌደሬሽን ም/ቤት እጅ ነው፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ ለፋና ሬድዮ በሰጡት ምላሽ፤ ጥያቄው የማንነት ሳይሆን የአስተዳደር ጉዳይ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል…
እኛ እንደውም ለፌዴሬሽን ም/ቤት ሁለት አማራጮች ነው ያቀረብነው፡፡ ፌዴሬሽን ም/ቤት ጥያቄያችንን ውድቅ የሚያደርግበት አንዳችም ህገ መንግስታዊ የሆነ መሠረት የለውም፡፡ ምክንያቱም ሟሟላት ያለብንን መስፈርት በሙሉ ነግረውን  አሟልተናል፡፡
ሶስት መስፈርቶች ነበሩ የነገሩን፡- አንደኛ የክልሉ የብሄረሠቦች ም/ቤት ውሳኔ፣ ሁለተኛ ይሄን ጥያቄ እንዲከታተሉ የተወከሉ ሰዎች ውክልና 3ኛ ደግሞ ከህዝቡ አጠቃላይ ብዛት 5 በመቶ ፊርማ ነበር የተጠየቅነው፣ እኛ ግን ወደ 26 በመቶ ህዝብ ፊርማ ነው ያቀረብነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ጥያቄ ውድቅ የሚያደርግበት ምክንያት የለም፡፡ ይሄን ውድቅ የሚያደርግ ከሆነ በፊት ‹‹እዚህም ፌደራል ያለነው እኛው ነን፤ የትም ብትሄዱ አይሳካም›› የተባለው እውነት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ምላሽ ካላገኛችሁ የመጨረሻው አማራጫችሁ ምንድን ነው የሚሆነው?
ሪፈረንደም እንጠይቃለን፡፡ ውድቅ የሚሆንብን ከሆነ ሪፈረንደም እንጠይቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ ክልሉ እንደሚለው ኮንሶ በዚያ ዞን ውስጥ ተጠቃሎ ሊኖር አይችልም፡፡ ሪፈረንደም ስንል፣ አንድም ብቻችን እንደ አንድ ልዩ ዞን ሆነን፣ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት ሆኖ እንዲኖር፣ ካልሆነ ደግሞ ወደ ኦሮሚያ ክልል በዞንነት ለመጠቃለል እንጠይቃለን። የኮንሶ ህዝብ በባህልም፣ በቋንቋም፣ በማህበራዊ ስነ ልቦናም ሆነ ዋና ምንጩ ኦሮሚያ ስለሆነ፣ ወደ ኦሮሚያ ክልል መጠቃለል እንፈልጋለን፡፡ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንደመጣ፣ የኮንሶ ህዝብ ወደ ኦሮሚያ ነው መሆን የምፈልገው ብሎ ህዝቡ የመረጠውን አንዳንድ ግለሰቦች አጭበርብረው ነው ወደ ደቡብ የጠቀለለው እንጂ የኮንሶ ህዝብ ድሮም ቢሆን ሲመርጥ የነበረው ከኦሮሚያ ጋር መኖርን ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የህዝቡን የዞንና የወረዳ ጥያቄ በአግባቡ እየመለሰ መሆኑን እያየን ነው፡፡
እንዲህ የህዝብን ችግርና ጥያቄ ሰምቶ ምላሽ የሚሰጥ ክልል እያለ እኛን ረግጦ እያማረረ፣ ከሚያስተዳድረን ክልል ጋር የምንኖርበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

Read 3190 times