Monday, 19 September 2016 07:30

ኢትዮጵያዊው ኢኮኖሚስት የአይኤምኤፍ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሆኑ

Written by 
Rate this item
(22 votes)

    የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ፣ ኢትዮጵያዊውን ኢኮኖሚስት አቶ አበበ አእምሮን የተቋሙ የአፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር አድርገው መሾማቸውን ተቋሙ ከትናንት በስቲያ በድረ-ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡ ላለፉት 22 አመታት በአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም የሰሩት አቶ አበበ አእምሮ በተቋሙ፣ በነበራቸው ቆይታ፣ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን የገለጸው ተቋሙ፤ በተለያዩ የስራ መደቦች ላይ ባከናወኗቸው ውጤታማ ተግባራት የካበተ ልምድ እንዳላቸውም ጠቁሟል፡፡
“አቶ አበበ በተቋሙ በነበራቸው ቆይታ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከአህጉሪቱ ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በቅርበት ሲሰሩ እንደመቆየታቸው የአፍሪካን ፈተናዎች በተመለከተ ጥልቅ ግንዛቤ አላቸው፡፡ በአመራር፣ በማስተባበርና በሌሎች መስኮች ያላቸውን ብቃት በተግባር ማረጋገጣቸው ለዚህ የስራ ሃላፊነት እንዲመረጡ አድርጓቸዋል” ብለዋል የተቋሙ ማኔጂንግ ዳይሬክተር፤ ክርስቲያን ላጋርድ፡፡
አቶ አበበ አእምሮ በተቋሙ ቆይታቸው፣ የአፍሪካ ክፍል የኡጋንዳ ከፍተኛ ተወካይና የደቡብ አፍሪካ ተልዕኮ ሃላፊ ሆነው ከመስራታቸው በተጨማሪ የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ትንበያን ጨምሮ በኮትዲቯር፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን በተለያዩ የስራ መደቦች ላይ ስኬታማ ስራ ማከናወናቸውንም ተቋሙ አስታውቋል፡፡
በተቋሙ የስትራቴጂ፣ ፖሊሲና ግምገማ ክፍሎች በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ በነበራቸው የስራ ቆይታ የአመራር ብቃታቸውን በተግባር ያስመሰከሩት አቶ አበበ፤ በአይ ኤም ኤፍ የአውሮፓ ክፍል፣ በቱርክ፣ ፖላንድና ፖርቹጋል ለረጅም አመታት መስራታቸውንና የተለያዩ ተልዕኮዎችን በአግባቡ እንደተወጡም ገልጧል፡፡ ከሲቲ ኦፍ ለንደን ፖሊቴክኒክ ተቋም በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ኢትዮጵያዊው የኢኮኖሚክስ ባለሙያ አቶ አበበ አእምሮ፤ ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ደግሞ በኢኮኖሚክ ሂስትሪ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንደተቀበሉ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አክሎ ገልጿል፡፡

Read 6885 times