Saturday, 10 September 2016 14:22

አዲሱ አመት የጤና፣ የሰላም፣ የእድገት ብልጽግና፣ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ለመላው ህብረተሰብ ይመኛል።

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(7 votes)

እንኩዋን ለ2009 ዓ.ም. በሰላም አደረሳችሁ።
              አዲሱ አመት የጤና፣ የሰላም፣ የእድገት ብልጽግና፣ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ የጽንስና
                    ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ለመላው ህብረተሰብ ይመኛል።

      ለዚህ እትም መነሻ ሃሳብ ያገኘነው ከተለያዩ ተሳታፊዎች ሲሆን ከወ/ሮ ቆንጅት የሁዋላእሸት ያገኘነው ግን የሚከተለው ነው።
“እኔ ተወልጄ ያደግሁት በጎጃም ደብረማርቆስ ነው። ገና በልጅነ ለባል ተድሬአለሁ። ታድያ በእናት አባቱ ቤት ሳድግ እናትየው እጅግ ደግ ሰው ስለነበረች ምንም ችግር አልገጠመኝም ነበር። የሁዋላ ሁዋላ ግን በቃ አድጋለች ተባለና ተሰርጌ ሚስት ሆንኩኝ። እንግዲህ ቤት ተያዘና ሴትነቱ ተጀመረ። አቅሜ የፈቀደውንም ሆነ ያልፈቀደውን የቤት ስራ ለመወጣት ደፋ ቀና ስል እርጉዝ መሆኔንም ሳላውቀው ጽንሱ ወረደ። በድንጋጤም አጀብ... ከበብ አድርገው አስታመ ሙኝ። ከዚያም ወዲያ እርግዝና አልቀናኝ አለ። እንዲያው ብቻ ይረገዛል ግን ይወርዳል። አንድ ሁለ እንደዚያ ሲያደርገኝ የባለቤ ቤተሰቦች...አአይ... ይችማ ሾተላይ ነች...ምን ታደርግል ናለች..ልጃችንን ካለዘር ልታስቀርም አይደል እንዴ? ብለው ወደቤተሰቦቼ አንድመለስ ወሰኑ። ባልተቤ ግን እንግዲህ እግዚሐር ባይሰጠን እንጂ...እስዋማ ምን ታድርግ? ብሎም ቢጠይ ቃቸው...የለም ሾተላይ ስለሆነች በቃ ፍታትና ሌላ አግባ አሉት። እሱም...እንዴ ...የማገባትስ እንደዚሁ ብትሆን ...እኔ ሳገባ ስፈታ ልኖር ነውን? የእሱዋንስ እድል አበላሽቼም የለ እንዴ? አለና እምቢኝ አሻፈረኝ አልፈታም አለ። እንግዲህማ እኛ ያልንህን ካላደረግህ ልጃችንም አይደ ለህ...እንክድሀለን ብለው ተጣሉት። እሱም ዝም አላቸውና አብረን ስንኖር ቆይተን የዛሬ ሀያ አምስት አመት ገደማ በጳጉሜ ድንገት ተነሽ አለኝና ወደ አዲስ አበባ ይዞኝ መጣ። በአዲስ አበባም በሰባተኛ እና መርካቶ ያገኘውን የቀን ስራም ጥበቃም እንዲሁ ሲል...እኔንም ጠላ ፣ቆሎ የመሳሰሉትን እንድሰራ እያበረታታኝ ኑሮ መኖር ጀመርን። ያው ልጅ የለንም እንጂ ዛሬማ በደንብ ተደራጅተናል። እንደአቅማችን ጎጆ ቀልሰን እንኖራለን። ነገር ግን እስከዛሬ የሚቆጨኝ ነገር አለ። ይሔውም ወደሐኪም ዘንድ ሄጄ እንደሰማሁት ከሆነ ልጅ በማስወርድበት ጊዜ ማግኘት የነበረብኝን ሕክምና አላገኘሁም። ስለዚያ ጉዳይ በዚያን ጊዜ በገጠር ማንም ያወቀ የለም። ማርገዜንም አላወቅሁትም እንጂ ባውቀውም ኖሮ እንዲህ እንደዛሬው ለምርመራ ተብሎ ወደሐኪም መሔድ አልተለመደም ነበር። ሐኪም ቤቱም እሩቅ ሐኪሞቹም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። እንዲህ እንደዛሬው በየመንደር በየጎጆው ድረስ እየዘለቁ እርጉዞችን ወላዶችን የተወለዱትን መመርመር ማከም የሚባል ነገርማ ጭርሱንም የማይታሰብ ነበር። ዛሬ ዛሬ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደአገሬ ስሔድ የማየው ነገር እጅግ አስደንቆኝ ነው ይህንን ማለ። እናም እንዲህ እንዳሁኑ ቢሆን ኑሮ ሕክምናው ከደጄ ስለሚሆን ምንም ችግር አይገጥመኝም ነበር።”
 ወ/ሮ ቆንጂት በህይወትዋ የገጠማትን ነበር በጽሁፍ ያወጋችን። ሾተላይ የሚለው ልማዳዊ ስያሜ እናቶች አር ኤች ኔጌቲቭ የሚባለው የደም አይነት ሲኖራቸውና ልጅ ሲወልዱ መድሀኒቱ ካልተሰጣቸው ከዚያ በሁዋላ በሚኖረው እርግዝና በተደጋጋሚ ስለሚሞትባቸው የተሰጠ ልማዳዊ አጠራር ነው። ሳይንሱ እንዲህ እንደዛሬው ነገሮችን ይፋ ባላደረገበት ወቅት እነዚህ እናቶች ሲጠሉ እና ሲወገዙ የነበሩበት ጊዜ ነበር። ዛሬ አልፎአል። ማንኛዋም እናት በሕክምና ልትረዳ ስለምትችል ያ ችግር አይገጥማትም።
የደም አይነት የተለያየ ነው። የደም አይነቶቹም ኤ .. ቢ .. ኤቢ ወይንም ኦ በመባል ሲታወቁ እነርሱም ፖዘቲቭ እና ኔጌቲቭ በሚል ይለያሉ። በተለይም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ይህ የእናትየው የደም አይነት ፖዘቲቭ መሆኑ አለዚያም ኔጌቲቭ መሆኑ በሚፈጠረው ልጅ ላይ ምን የሚያመጣው ነገር አለ? የሚል ይሆናል የዛሬው የውይይት ርእሳችን። የAmerican congress of obstetricians and gynecologists እንደሚያስነብበው ከሆነ አር ኤች ኔጌቲቭ ወይንም ፖዚቲቭ ማለት በየትኛውም የደም አይነት በቀይ የደም ሴል አካባቢ የሚገኝ ፕሮቲን ነው። በዚህ ርእሰ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጋበዝናቸው ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በሚሊኒየም ኮሌጁ መምህር ናቸው።
ዶ/ር ባልካቸው እንደሚገልጹት RH አር ኤች ማለት ማንኛውም ሰው በቀይ የደም ሴል ውስጥ አር ኤች ዲ የሚባል አንቲ ጂን አለው። የህ ጂን ያላቸው ሰዎች አር ኤች ፖዘቲቭ ሲባሉ ያ ጂን የሌላቸው ሰዎች ደግሞ አር ኤች ኔጌቲቭ ይባላሉ። ስለዚህም አንድ ሰው በተ ፈጥሮው ወይ አር ኤች ኔጌቲቭ አለዚያም አር ኤች ፖዘቲቭ ይሆናል ማለት ነው። ለምሳሌም የደም አይነቶቹ ኤ .. ቢ .. ኤቢ .. ኦ ሲሆኑ ኤ ኔጌቲቭ ወይንም ኤ ፖዘቲቭ ይሆናል እንደማለት ነው። ይህ በሁሉም የደም አይነቶች ውስጥ ሊኖር የሚችል ነው።
በልማድ ሾተላይ የሚባለው ነገር እንዴት ይከሰታል የሚለውን በሚመለከትም ዶ/ር ባልካቸው ሲገልጹ ሁሉም እርጉዝ ሴቶች የደም ውጤታቸው ሲመረመር የሚገኘው የአር ኤች ውጤት የሚወስነው ነው። በእርግጥ ብዙዎች ሴቶች ሲመረመሩ አር ኤች ፖዘቲቭ የሚሆኑ ቢሆኑም ከ8-10ኀ የሚሆኑት ደማቸው አር ኤች ኔጌቲቭ ሆነው ይገኛሉ። እርጉዝ የሆነችው ሴት አር ኤች ፖዘቲቭ መሆንዋ ምንም ችግር የለውም። ነገር ግን አር ኤች ኔጌቲቭ ከሆነች ማወቅ የሚገባን ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው የጽንሱን አባት አር ኤች ማወቅ አስፈላጊ ይሆናል። አባትየው እንደሚስቱ አር ኤች ኔጌቲቭ ከሆነ በጽንሱ ላይ የሚያመጣው ምንም ችግር የለም። ምክንያቱም ልጁ የሚይዘው ከሁለቱም የደም አይነት ስለሚሆን ልጁም አርኤች ኔጌቲቭ እንደሚሆን አያጠያይቅም። ነገር ግን የልጁ አባት ከእስዋ በተቃራኒ አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ የልጁ ደም ግማሹ ከአባቱ ስለሚወሰድ አር ኤች ፖዘቲቭ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው።
ጽንስ በሚፈጠርበት ጊዜ ከላይ በዶ/ር ባልካቸው እንደተገለጸው የእናትና አባት የደም አይነትን ተከትሎ ስለሚሆን ከዛ ሂደት በሁዋላ የሚከሰተው እናትየው በደምዋ ውስጥ ዲ አንቲጂን ስለሌላት ከልጁዋ ደም በመቀላቀል ምክንያት ዲ አንቲጂን ደምዋ ውስጥ ስለሚገባ ለልጁ አጥቂ የሚሆን አንቲ ቦዲ ታመርታለች። ያ የተመረተው አንቲ ቦዲ በእንግዴ ልጅ በኩል አልፎ ወደልጁ ስለሚሄድ የልጁን የቀይ የደም ሴሎች ሊያጠቃባት ይችላል። ይህ ተፈጥሮአዊ አካሄድ ለጁን በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳ ይችላል። በእርግጥ ይህ በመጀመሪያው የእርግዝና ወቅት ወይም መጀመሪያ በሚወለደው ልጅ ላይ አይታይም። የደም መቀላቀሉ በብዛት የሚታየው በወሊድ ጊዜ ስለሆነ የመጀመሪያው ልጅ በደህና ሊወለድ ይችላል። ነገር ግን እናትየው ያመረተችው አንቲ ቦዲ የሁለተኛው ልጅ ደም አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ የቀይ የደም ሴሉን ያጠቁታል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የደም ማነስ እንዲሁም የልብ ድካም ከዚያም ሲያልፍ ልጁን ለሞት ሊዳርግ ይችላል። በልማድ ሾተላይ የሚባለው ከዚህ ጋር በተያያዘ የተሰጠ ልማዳዊ አጠራር ነው። ልጅ ከተረገዘ በሁዋላ የእርግዝና ጊዜውን ጠብቆ ወይንም ጊዜውን ጨርሶ ሳይወለድ በተለያየ ምክንያት ቢቋረጥ ወይንም ከማህጸን ውጭ እርግዝና ቢከሰትም እንኩዋን በእናትየው ሰውነት አንቲ ቦዲ የማምረት ሂደቱ ሊካሄድ ስለሚችል መድሀኒቱን ካልተጠቀመች በሁለተኛው ልጅ ላይ ችግር መፈጠሩ አይቀርም። ነገር ግን በተከታታይ ለሚፈጠረው ችግር በሕክምናው ረገድ እርዳታ መስጠት ይቻላል እንደ ዶ/ር ባልካቸው አገላለጽ።
አንዲት ሴት የመጀመሪያውን እርግዝና ስትወልድ በእርግዝናው ወቅት በሰባት ወርዋና ከወለደችም በሁዋላ አንቲ አይዲ የተሰኘው መድሀኒት መሰጠት አለበት ። በዚሁ አጋጣሚ መታወቅ ያለበት አንቲ ቦዲ የሚያመርቱት ሁሉም እናቶች ሳይሆኑ እናት ኔጌቲቭ ልጅ ደግሞ ፖዘቲቭ ሆነው አንቲ ቦዲ የሚያመርቱት እስከ 16 ኀ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ከ80 ኀ በላይ የሚሆኑት አያመርቱም። ነገር ግን የትኛዋ አምርታለች? የትኛዋ አላመረተችም የሚለውን መለየት ስለማይቻል ምርመራ በማድረግ ይታወቃል። ካላመረተች ሁለተኛው ልጅም ስለማ ይጠቃ ምንም የሚያነጋግር ነገር የለም። ካመረተች ግን የሚቀጥለውን ልጅ ለማትረፍ ሲባል መድሀኒቱን እንድትወስድ ይደረጋል። እርግዝናው አስራ ሰባት እና አስራ ስምንት ወር ድረስ ምርመራም ቢደረግ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ከዚያ በሁዋላ ግን ምርመራ በማድረግ የልጁ የቀይ የደም ሴል እየተጠቃ የደም ማነስ እንዳለውና እንደሌለው የመሳሰለውን ምርመራ በማድረግ ማወቅ ይቻላል። ሕጻኑ ጉዳት እንደደረሰበት የሚያሳይ ምልክት ካለ በሁለት መንገድ ሕክምናውን መስጠት ይቻላል።
ማንኛውም ሰው የደም ማነስ ሲገጥመው ደም እንደሚሰጠው ሁሉ ጽንሱም ገና በእናቱ ማህጸን ውስጥ እያለ ደም መስጠት ይቻላል። ይህ ሕክምና በሀገራችን በብዙ ቦታ የማይሰጥ ቢሆንም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ግን ይሰጣል።
ልጁ ለመሞት ያሰጋዋል እስካልተባለና ጉዳቱን መከታተል የሚቻል እስከሆነ ድረስ ግን ከፍተኛ ክትትል በማድረግ ዘጠኝ ወር ባይሞላውም በ36/ወይም 37 ሳምንት ላይ እያለ አንዲወለድ ይደረጋል። በዚህም ጊዜ በጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ክፍል ገብቶ ደም ከመቀየር ጀምሮ አስፈላጊው ክትትልና ሕክምና እንዲደረግለት ይሆናል።
አር ኤች ኔጌቲቭ የሆኑ እናቶች ከመውለዳቸው በፊትም ሆነ ልክ እንደወለዱ የሚሰጣቸው መድሀኒት በዋጋው ውድ መሆኑ ሳያንስ እንደልብ መገኘት የማይችልም ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ መድሀኒቱ በሰው ሰራሽ ዘዴ መመረት የማይችል በመሆኑ እና አምራች ካምፓኒዎቹም ውስን በመሆናቸው በአለም ላይ የሚያጋጥም ችግር ነው እንደ ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ ማብራ ሪያ። በዚህም ምክንያት መድሀኒቱ የሚያስፈልጋቸው ቤተሰቦች ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር አስቀድመው በመግዛትና በማስቀመጥ በወሊድ ጊዜ ከመቸገር ሊድኑ ይችላሉ። መድሀኒቱ ከማቀዝቀዣ ውጭ በፍጹም መቀመጥ እንደማይችል እና የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜውም በውል መታወቅ እንደሚገባው ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና መምህር ገልጸዋል።

Read 17142 times