Print this page
Sunday, 11 September 2016 00:00

ያልተረጋጋው መረጋጋት

Written by  ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
Rate this item
(3 votes)

 መጀመሪያ ሰላማችሁን ትነጠቃላችሁ፡፡ ሁከት ቦታውን ይወርሰዋል፡፡ ሰላም ይናፍቃችኋል። ሁከቱ ሲበርድ፣ ሰላም ገና ባይመጣም “ሰላም ነው” ትላላችሁ፡፡ ሰላሙ ግን ሰላም አይደለም፡፡ መረጋጋቱም አልተረጋጋም፡፡ ያልተረጋጋ ሰላም ነው፡፡ የሁከቱን መቀዝቀዝ፣ የአመጹን መደብዘዝ ነው ሰላም ያላችሁት፡፡ ሰላም ግን ሰላም ነው፡፡ እኛ አሁን ያለነው ሰላም በማይባል ሰላም፣ ባልተረጋጋ መረጋጋት ውስጥ ነው፡፡
ቀደም ሲል የአዲስ አበባን ማስፋፊያ ፕሮጀክት ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ ክልል፣ በኋላም ከድንበር ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአማራው ክልል፤ ህዝብና መንግስትን ነፍጥ ያስነሳ፣ ሕይወት ያስከፈለ፣ አካል ያስገበረ ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህ ግጭት ከአንዱ ወደ ሌላው እየተዛመተ፣ እዚያም እዚህም እንደ ብጉር እየበቀለ፣ አየሩን በጥይት ባሩድ፣ ምድሩን በደም ፍሰትና አካል ጉድለት አናውጦታል። ሁኔታዎች በአጭር ጊዜ እንደ ሰደድ እሳት ከወዲያ ወዲህ እየተራገቡ ተቀጣጥለዋል፡፡ ከአሁን ቀደም አመጽና ሁካታ የማያውቃቸው አካባቢዎች ሁሉ የግጭት ቀጠና ሆነዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በጥፍራቸው ቆመዋል፡፡ ሁላችንም ቆመን የምንራመድ፣ ውለን የምንገባ፣ ተኝተን የምንነሳ ይመስለናል እንጂ እንደዚያ አይደለንም፡፡ ሀገር ታማ የሚተኛ ዜጋ የለም፡፡ አሁን ሀገር ታማለች፡፡ ሰላማችን ሰላሙን አጥቷል። አይነትና ሰበባቸው የተለያየ ቢሆንም መንግስት በሁለቱ ክልሎች የተነሱ ግጭቶች ምንጫቸው፤ የመልካም አስተዳደር እጥረትና ሙስና መሆኑን አምኗል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች እንደ አሁን ቀደሙ ሁሉ “የኤርትራ መንግስትና የፀረ ሰላም ኃይሎች እጅ አለበት” ቢልም ዋንኛ የግጭቱ መንስኤ ግን ውስጣዊ መሆኑን አምኗል፡፡
ግጭቱን ተከትሎ ከመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡ መግለጫዎች ተበራክተዋል፡፡ የሁሉም መግለጫዎች ሲጠቃለሉ፤ ችግሮቹ ተለይተው የታወቁ በመሆኑ መፍትሄውም ከግንባሩ ቁርጠኝነት እንደሚመነጭ የሚገልጹ ናቸው፡፡ በተለያየ መልኩ የሚገለፀው፣ መንግስት ከተለያዩ የኦሮሚያ ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ተከታታይ ውይይቶች፣ ግጭቱ መብረዱና መረጋጋት መፈጠሩ ነው፡፡ በአማራው ክልልም ይኸው እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ በእርግጥም በአንፃራዊ መልኩ ሲታይ፤ ከቀደሙት ቀናትና ወራት የተሻለ መረጋጋት ይታያል፡፡ መረጋጋቱ ግን ያልተረጋጋ ነው፡፡ ያለው ፀጥታ እንጂ ሰላም አይደለም፡፡
የመብረድ እንጂ የመቀዝቀዝ ተስፋው ያለ አይመስልም፡፡ ለጊዜው ግጭቶች ቢበርዱም ሁኔታዎች ዘላቂ አይመስሉም፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹ ግጭቶች ከቀደሙት በመሰረታዊ ጠባያቸው ይለያሉ። በስፋትም በጥንካሬም ያሁኖቹ ከቀደሙት ይለያሉ። ላለፉት 25 ዓመታት ብልጭ ድርግም የሚሉት አለመግባባቶች የከፉ ቢመስሉም መልሶች ነበሩ፡፡ ከክልላዊነት በላይ የአካባቢያዊነት ጠባይ የነበራቸው ነበሩ፡፡ የቅርቦቹ ግን በአመዛኙ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የተነሱና እንደ ሰደድ እሳት የተቀጣጠሉ ነበሩ፡፡ ሞትም፣ የአካል መጉደልም፣ እስርም ያልመለሳቸው ነበሩ፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ግልፅ ነበር። የምሬቱ ብዛት፣ የበደሉ ቁልል ነው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ እስካሉት ባለስልጣናት፤ “በኦሮሚያ ግጭቱ በርዶ መረጋጋት ይታያል፡፡ በአማራ ክልልም ተመሳሳይ እየሆነ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከላይ ሲታይ እንደተገለፀውም፤ ግጭቱ የበረደ፣ መረጋጋቱም የመጣ ይመስላል። ይህ ግን ጊዜያዊ ነው፡፡ ዜጎች ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉበት ግጭት፤ መነሻው እንደስካሁን ቀደሞቹ ጊዜያዊ ያለመሆኑን ያህል፣ መልሱም በቃል ብቻ የሚታመን አይሆንም። “ሙስናና የመልካም አስተዳደር ድርቀት የስርዓቱ ችግሮች ናቸው” ማለት አሁን ለተነሳው አለመግባባት አጥጋቢ መልስ አይሆንም፡፡ ላለፉት 11 ዓመታት (በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ) በተደጋጋሚ የተባለ ጉዳይ ነው፡፡ መባሉ ብቻም ሳይሆን መልስም በተጨባጭ ያልታየበት ነው፡፡ ያለፉት ዓመታት የሙስናና መልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ የተነገረበትና መንግስት የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ያለበት ቢሆንም፣ ሙስናም ሆነ መልካም አስተዳደር ይበልጥ እየደረጁና ጥርስ እያወጡ የሄዱበት ሆኗል፡፡ ዓመጹ የገነፈለው፣ ቁጣው የነደደውና ደረጀ በላይነህ ባለፈው ሳምንት የጋዜጣው እትም ላይ ለጽሑፋቸው ርዕስ እንዳደረጉት “ህዝብ አፈሙዝ የሚያስልስ ብሶት” ውስጥ የገባው ችግሮች በመባባሳቸው ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት “ተረጋግቷል” የተባለውና የተረጋጋ መስሎ የታየው እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ሳይመለሱና ህዝብ በችግሮቹ ማጥ ውስጥ ተዘፍቆ እንዳለ ነው፡፡ መንግስት “አድገናል” ቢልም፣ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም “አድጋችኋል” ቢሉም ዋናው ተቀባዩ ህዝብ ግን “አድጌያለሁ” ብሎ መቀበሉ እየታየ አይደለም፡፡ ህዝብ “መንግስት ከዚህ በላይ ምን ያድርግ ነው የምትሉት?” ማለት ያልቻለው፤ ተአምር ጠብቆ አጥቶ አይደለም፡፡ ከተዐምር ጠባቂነቱ ባገኘው ረክቶ “ተመስገን!” ባይነቱ ሚዛን ይደፋል፡፡
ህዝብ ከሞላለት፣ ባይሞላም ካልጎደለበት፣ ጎድሎም እንኳ ተጭበርብሮና ተሰርቆ ካልሆነ፣ ምሬትን ከየትም አያመጣውም፡፡ ሆዱ መጉደሉ፣ አንጀቱ መታጠፉ ብቻ ሳይሆን የእሱ ድርሻ ሌላው ባለስልጣን ሆድ ውስጥ እየገባ መጠራቀሙ ነው “አፈሙዝ ለማስላስ ያደረሰ ምሬት” ውስጥ የከተተው። ህዝብ የምሬት ሱስ ለበትም፡፡ ቢሆንለት ለምን ብሎ? አያደርገውም፡፡ አሁን ግን አለ አለና፤ ግፉ ተጠራቅሞ አንገቱ ደርሶ፣ የመልካም አስተዳደሩ ድርቀት ሀሩር ሆኖ ለበለበው፡፡ ከዚያም ከመንደር ተርፎ አደባባዩን ሞላው፡፡ ከጉምጉምታ አልፎ ዛቻና ቁጣው ይንቀለቀል ገባ፡፡ ይህ የቁጣ ማዕበል፣ ይህ የንዴት ወጀብ፣ ይህ የበደል እልህ እንዲሁ በአንድ ጊዜ እንደተጣደ  ወተት ገንፍሎ የታየ አይደለም፡፡ ወተቱም ሳናውቀው ውስጥ ውስጡን ፈልቶ ነው “በአንዴ” የሚገነፍለው። ይህ ህዝብ ነው ያለ ምንም ተጨባጭና አሳማኝ ካሳ የተረጋጋ የመሰለው፡፡ ይህን ህዝብ ነው “ተረጋግቷል” የምንለው፡፡ ይህን ነው “ሰላም ነው” የምንለው፡፡ ግን ምን አግኝቶ? ምን ተገኝቶ?
መንግስት እራሱ ያመነበት የመልካም አስተዳደር እባጭ በምን ፈረጠና ነው ፈውስ የሚገኘው? የሙስናውን ክርፋት ከህዝብ አፍንጫ ስር ማን አነሳውና ነው፣ ህዝብ “ተረጋግቷል” የሚባለው? ይህ ህዝብ እኮ በችግሩ መጠን ገና አደባባይ አልወጣም፡፡ እውነት ለመናገር … መንግስት ሆይ፤ ይህ የምትመራው ህዝብ፤ “ጋዝ ተወደደ፣ ስኳር ከመደብር ጠፋ” ብሎ ለአመጽና ምሬት እጁን የሚሰጥ ህዝብ አይደለም፡፡ ይህ ህዝብ በየትኛውም የሂሳብ ቀመር በማይደርስበት የሰከረ የንግድ ስርዓት ውስጥ ገብቶ፣ ለወር ያለውን በሳምንት በልቶ እየጨረሰ፤ አብዛኛውን  የሕይወቱን ከፍል ሃይማኖቱ ከሚያዘው በላይ “እየጾመ”፣ ይህን ኑሮ ብሎት እንኳ አመፅ አልጠነሰሰም፡፡
የትምህርት ስርዓቱ ሲበከልበት፣ ልጆቹ ተምረው የማያውቁ ሲሆኑበት፣ ዲግሪን ሰርቶ ራስና አካባቢን ለመለወጫነት ሳይሆን ለፀሀይ መከለያነት አውሎና ሊስትሮነት እየሰራ መማር ኪሳራ ሲሆንበት፣ በየትም ብሎ ሰርቆ መገኘት አዋጪ የኑሮ ብሂል ሆኖ እያየ እንኳ “በቃ!” አላለም፡፡ ህዝብ ራሱን ሲሰድብ የኖረው፤ “ይሄ ህዝብ ምን ሲሆን ነው የሚነሳው” እያለ ነው፡፡ ይህ ምሬት ነው ተጠራቅሞ የደም አበላ ያወረደው፡፡ 5.00 ብር የነበረው ቤንዚን 20.00 ብር ሲገባ፣ ትናንት “መንግሥት የለም እንዴ?” ያስባለው የአንድ ኪሎ የስጋ ዋጋ፣ ከ90 ብር በአጭር ጊዜ 300 ብር ሲገባ ህዝብ ጠመንጃና ጦሩን አልሰበቀም። ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ማስፋፊያ ፕሮጀክት፣ ጎንደርና ጎጃምንም የወልቃይት የማንነት ጉዳይ ብቻ አይደለም በመንግስት ላይ ያስነሳቸው፡፡ አዲስ አበባም “በፀጥታ ውስጥ ናት” ብዬ እኔ በግሌ አላምንም፡፡ ይህ ህዝብ እንኳን ለመሪዎቹ ለራሱም ነው ግራ የሚያጋባው፡፡ ዝም ሲል ሰላም ነው ወይስ ተቃውሞ? ማንም የሚያውቀው ያለ አይመስለኝም። እየሳቀና እየተጫወተ የምታዩት ህዝብ ነው ውስጡ ምሬት አዝሎ የሚገኘው፡፡ በ1997 በዚያ መጠን መስቀል አደባይ ሞልቶና ተርፎ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስን ስሜታዊ አድርጎ “ይህን ህዝብ ይዘን ሳናጭበረብር ማሸነፍ እንችላለን” አስብሎ፣ በሳምንቱ መቶ በመቶ ተሸናፊ አድርጎ የመረጠውን፣ አሸናፊ ያደረገ ህዝብ የትም ሀገር የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ በምን ነበር የተማከረውና አንድ የሆነው? አይታወቅም!! ያኔ ፌስቡክ እንኳ የለም፡፡ ካልተሳሳትኩ በስልክ ቴክስት ማድረግም ተዘግቷል። ይህን ህዝብ ነው “ተረጋግቷል” የምንለው። ይህ ህዝብ ነው “የተረጋጋው”
ገዢው ግንባር ወይም መንግስት (ሁለቱን መለየት ብዙ ጊዜ ያምታታኛል!) በአዲሱ ዓመት አዲስ ለውጥ አምጥተን፣ ለህዝባችን “እናሳውቃለን” ብሎ ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ቃል ብቻ ህዝቡን ሊያረጋጋ አይችልም፡፡ ከዛሬ 15 ዓመት ጀምሮ ገዢው ግንባር “በስብሻለሁ”ም ብሏል፡፡ “እለወጣለሁ”ም ብሏል። መሪው ህዝብ በሚጠብቀው ደረጃ ባለመለወጡ አንስቶ በተቃውሞ አደባባዮችን በመሙላትም፣ አደባባይን ባዶ በማድረግም ተቃውሞውን እያሰማ ያለው፡፡ አሁንስ ለውጥ አለ ሲባል የክ/ከተማ አመራሮችንና እንደነ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ያሉ ለህዝብ ጥያቄ ያልሆኑ ሚኒስትሮችን በማንሳትና በመሾም ነው ለውጡ “መጣ” የሚባለው? ህዝብ እነሱን መች “ጉቦ ግጠዋል” አለ? “መች የእኔ ድርሻ የእነሱ የባንክ አካውንት ውስጥ (በሌላም ስም ቢሆን) ገብቷል!! አለ? “መች ባዶአቸውን ገብተው ባለፎቅና ባለፋብሪካ ሆኑ” አለ? መልካም አስተዳደሩስ ምን አድርሶት እነርሱ ጋ ይሄዳል? ህዝብ እንዲረጋጋ ከተፈለገ፤ የእውነትም “ተረጋግቷል” ለማለት ከታሰበ፣ ሰላሙ ከተፈለገ እነማንን ምን ማድረግ እንደሚያሻ መንግስት ያውቃል!!    
መልካም አዲስ ዓመት

Read 6084 times