Sunday, 11 September 2016 00:00

ቢሆንም፣ ባይሆንም ደግ መመኘት…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

“እንደአለመሳቅ አለማልቀስም የምንችልበት ዘመን ይናፍቀናል”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
መልካም አዲስ ዓመት!
እንኳን አደረሳችሁ! አዲሱ ዓመት ዓመት ደግ ደጉን የምንሰማበት፣ ደግ ደጉን የምናይበት፣ ደግ ደጉን የምናገኝበት ዓመት ያድርግልንማ!
ዛሬ እንግዲህ ዋዜማም አይደል…አዲስ አበባ በጥፍሯ ቆማ ልታድር ነዋ! የምር ግን በዋዜማ የሚጠፋ ገንዘብ እኮ የአራትና የአምስት ወራት የቤት ወጪ መሆን የሚችል ነው፡፡ ልክ ነዋ… “አንጀቴ ቆስሎ የሁለት ሺህ ብር መድኃኒት ታዞልኛል፡፡ አምስት መቶ ብር ልታበድረኝ ትችላላህ?…” ሲባል…
“አምስት መቶ ብር የሚባል ገንዘብ ካየሁ አምስት ዓመት ሆኖኛል…” ሲል የከረመው ሰውዬ፤ በዋዜማ ዕለት ረብጣ ረብጣውን ‘የሚመዘው’… አለ አይደል… ‘የሚያባዛለት’ እያገኘ ነው እንዴ! ልጄ…ሀያ አምስት ኪሎ ጤፍ ለመግዛት ከመሥሪያ ቤት ብድር እጠይቃለሁ የሚለው ሁሉ… “ለአንቺም ጠጪ፣ ለእኔም አምጪ …” ነገር ሲሆን ብሩ ከየት ‘እንደሚፈላለት’ አንድዬ ይወቀው።
(ለነገሩ ዘንድሮ ብር ‘እንዴት እንደሚፈላ’…አለ አይደል… ‘ኑሮና ብላቱ’ የገባው ሰው እየበዛ ነው፡፡ እንግዲህ ብላቱ እኛ ጋ እስኪደርስ — ከደረሰ — እንጠብቃለና!)
እናላችሁ…ለዋዜማ ‘የሚከሰከሰውን’ ገንዘብና የእኛን… “ዛሬን እወቅበት ነገ ራሱን ያውቃል…” አይነት ነገር ስታዩ የሚገራርሙ ነገሮች አሉ፡፡ ያ ሁሉ ፈራንክ ብተና እውነት ዓለም ዘጠኝ ለማለት ነው?!….በነገና በተነገ ወዲያ ተስፋ በመቁረጥ ነው?!… በዘንድሮ ዘመን በዚች አገር የመኖርን ‘ዕድለቢስነት’ ለመሸፋፋን ነው?!… ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ መልሱን ቢሰጡን ደስ ይለናል፡፡
ስሙኝማ…በጸሎት ስም ደጅ ለማምሸት ስለሚመች ስንት ወጣት ‘ዓይኑ የሚበራው’ በዋዜማ ነበር፡፡ ዘንድሮ ዋዜማ አያስፈልግ፣ ማግስት አያስፈልግ…ነገሩ ሁሉ ‘ተች ስክሪን’ ሆኗል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን… በቀደም የሆኑ ጎረምሶች ስለሆነች ጓደኛቸው ትሁን ምናቸው ሲያወሩ አንደኛው ምን አለ መሰላችሁ…“እሷ እኮ ‘ተች ስክሪን’ ነች!” ግራ ገብቶን ነበር፡፡ ለካስ በቃ አንድ ጣት እንኳን ካረፈባት ማግኔት እንደሳባት መጥታ ልጥፍ ትላለች ምናምን ለማለት ነው! ወይ ‘ተች ስክሪን!’
የሰላም ይሁንልን፣ የሰላም ይሁንልን
አዲሱ ዓመት አዲሱ ዘመን
በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የተሻለ ምኞት ያለ አይመስለኝም፡ ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልገናል፡፡ ከምንም በላይ እርጋታ ያስፈልገናል…ከምንም በላይ “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” መባባል ያስፈልገናል፡፡
እኔ የምለው፣ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…… እዚህ አገር የምግባር ነገር በጣም፡ እጅግ በጣም አሳዛኝ እየሆነ ነው፡፡ ወጣቱ እንኳን ቀና ብሎ በምሳሌነት የሚያየው ‘የዕድሜ ባለጸጋ’ እስኪጠፋ ድረስ ብዙ ነገር እየሸሸን እንደሆነ ሁሉ… ምግባርም “እንደፍጥርጥራችሁ…” ብሎ ሜዳ ላይ አንጥፎን የሄደ ነው የሚመስለው፡፡ ልክ ነዋ… የስልጣኔያችን ጫፍ ‘ሂዩማን ሄይር’ና ጭን ድረስ የሚጎተት ሱሪ ሆነና ሰብአዊ የሆኑት ነገሮች እየራቁን ነው፡፡
ስሙኝማ…በፊት ጊዜ በህዝብ መጓጓዣ እንደ ሰርግ ምናምን በመሳሰሉ ስነስርአቶች ላይ ለአዛውንቶች ቦታ መልቀቅ የተለመደ ነበር። ባህሪያቸው መልካም የማይባል ሰዎች እንኳን የሚያደርጉት ነገር ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ተለውጧል፡፡
ዱላ ተደግፈው የሚሄዱ ባልቴት አጠገቡ ቆመው ከመቀመጫው ነቅነቅ የማይል ‘ኬሬዳሽ’ አይነት ሰው እየበረከተ ነው፡፡ ታክሲ ውስጥ ምናምን ሲሳፈሩ አዛውንቶችን ገፍቶ ማሽቀነጠር እየበዛ ነው።
እናላችሁ….ዕድሜ በራሱ የሚከበርበት ዘመን ሽው እልም እያለ እያመለጠ ነው፡፡ እናማ…አዲሱ ዓመት ወደ ቀልባችን የምንመለስበት ዓመት እንዲሆን ያድርግልንማ!
የሰላም ይሁንልን፣ የሰላም ይሁንልን
አዲሱ ዓመት አዲሱ ዘመን
በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የተሻለ ምኞት ያለ አይመስለኝም፡ ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልገናል፡፡ ከምንም በላይ እርጋታ ያስፈልገናል…ከምንም በላይ “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” መባባል ያስፈልገናል፡፡
ዘንድሮ የበርካታ ወላጆች ልጅ አስተዳደግ… አለ አይደል… “እንዴት ነው ነገሩ!” የሚያሰኝበት ደረጃ ደርሷል። ወላጆች ልጆቻቸውን ሳይሆን ልጆች ወላጆቻቸውን የሚቆጣጠሩበት ዘመን ይመስላል። አንዳንድ መዝናኛ ስፍራዎች ወይም ህዝብ ሰብስብ የሚሉባቸው ቦታዎች ልጆቻቸውን ይዘው የሚመጡ ወላጆች… “አንዲት ቃል ትናገሪውና!” “አንዲት ቃል ትናገራትና!” የሚል ግዝት ነገር አለባቸው እንዴ!  አሀ…ልጆቹ እየተጯጯሁ፣ እየተራበሹ የሰዉን ሁሉ ሰላም ሲነሱ… “ማሙሽ፣ ማሚቱ አርፋችሁ ተቀመጡ…” ምናምን የሚሉ ወላጆች ማግኘት ብርቅ እየሆነ ነዋ! እንደውም በዛ ሰሞን አንድ ካፌ ነገር ውስጥ ሰባት ስምንት ዓመት የሚሆናቸው ሁለት ወንዶች ልጆች የጠረዼዛ ጨርቅ እየሳቡ መሬት ላይ ሲጥሉ፣ ወንበር ሲያተራምሱ ወላጆቻቸው ልክ ሚስተር ቢን ምናምን እያዩ ይመስል በሳቅ ይንተከተኩ ነበር፡፡
ወላጅነታቸውን የሚያውቁ ወላጆች፣ ልጅነታቸውን የሚያውቁ ልጆች የሚበረክቱበት ዘመን ይሁንልንማ!
ቢሆንም፣ ባይሆንም ደግ መመኘት ይሻላል፡፡
የሰላም ይሁንልን፣ የሰላም ይሁንልን
አዲሱ ዓመት አዲሱ ዘመን
በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የተሻለ ምኞት ያለ አይመስለኝም፡ ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልገናል፡፡ ከምንም በላይ እርጋታ ያስፈልገናል…ከምንም በላይ “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” መባባል ያስፈልገናል፡፡
ደግሞላችሁ...በከተማ መንገዶች ለሥራ ተፍ ተፍ እያሉ በፍጥነት መሄድ ህልም እየሆነ ነው። አምስትና ሰባት ሆነው መንገዱን ዘግተው በኤሊ እርምጃ መንገድ የሚዘጉ ‘ስልጡኖች’ በዝተዋል። ከኋላቸው ለማለፍ የሚሞክሩ ሰዎች እንዳሉ እያወቁም መንገድ መልቀቅ፣ ቀዳዳ መክፈት የሚባል ነገር የለም፡፡ (እግረ መንገዴን አንዳንድ እንትንዬዎች መንገድ ላይ ማስቲካ እያፈነዱ መሄድ ‘የአራዳነት’ መለኪያ መሆኑ ቀርቷል፡፡ አይ…ትዝብት እንዳትገቡ ብለን ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እኔ የምለው እዛውንቱ ሁሉ የወጣት ሴቶችን ‘መቀመጫ’ ‘ቸብ’ ማድረግ ወረርሽኝ ነው እንዴ?! ኧረ ‘ቸብ’ ማድረግ ድሮ ቀርቷል፡፡ አሁን ስንት ‘ሾርትከት’ እያለ! ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን አንዳንድ ከምንለው በላይ ወጣት ሴቶችን ‘የሚለክፉ’ የዕድሜ ባለጸጎች በዝተዋል፡፡ አለ አይደል… ድሮ የልጅ ልጅ ‘መልከፍ’ የመጨረሻ ቀሺም ነገር ነበር። ‘የልጅ ልጆቹ’ም ቢሆኑ የብረት ሳጥኑ የት እንዳለ፣ የእንጨት ሳጥኑ የት እንዳለ፣ ምንም ሳጥን የሌለበት፣ የት እንደሆነ አውቆ ‘መንቀሳቀስ’ የህይወት መርህ ያደረጉት ይመስላል፡፡   
እኔ የምለው ‘ሹገር ዳዲ’ በከተማው ሲበዛ…በቀበሌ ‘ሹገር’ የሚጠፋበት ምክንያት ይነገረንማ!  ቂ…ቂ…ቂ…
የሰላም ይሁንልን፣ የሰላም ይሁንልን
አዲሱ ዓመት አዲሱ ዘመን
በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የተሻለ ምኞት ያለ አይመስለኝም፡ ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልገናል፡፡ ከምንም በላይ እርጋታ ያስፈልገናል…ከምንም በላይ “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” መባባል ያስፈልገናል፡፡
እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ
ይባል የነበረበት የተስፋ ዘመን የምር ይናፍቃል። ስለ አደይ አበባ ብቻ እያሰቡ…አለ አይደል…
አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ
እየተባለ የሚከበር እንቁጣጣሽ ይናፍቀናል። በአበባ መሀል መምነሽነሽ ‘ዘፈን’ ብቻ ሳይሆን የእውነትም መምነሽነሽ የሚሆንበት ጊዜ ይናፍቀናል።
አለመሳቅ ይቻላል አለማልቀስ ነው ጭንቁ
የመንፈስን እንጉርጉሮ በመንፈስ እንባ ማመቁ
ውስጥ ውስጡን እየደሙ በቀቢፀ—ተስፋ መድቀቁ
ለተስለመለመ እውነት የደም ደብዳቤ ማርቀቁ
በቅሬታ ሰደድ እሳት ህዋሳትን መጨፍለቁ
አለመሳቅ እኮ ይቻላል አለማልቀስ ነው ጭንቁ
ይላል ደበበ ሰይፉ፡፡ እንደ አለመሳቅ አለማልቀስም የምንችልበት ዘመን ይናፍቀናል፡፡
ቢሆንም፣ ባይሆንም ደግ መመኘት ይሻላል፡፡
የሰላም ይሁንልን፣ የሰላም ይሁንልን
አዲሱ ዓመት አዲሱ ዘመን
በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የተሻለ ምኞት ያለ አይመስለኝም፡ ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልገናል፡፡ ከምንም በላይ እርጋታ ያስፈልገናል…ከምንም በላይ “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” መባባል ያስፈልገናል፡፡
እኔ የምለው…እግረ መንገዴን… አንዳንዶቻችን በሞባይል ስናወራ ‘ሞንታርቦ’ ጉሮሯችን ላይ የተገጠመልን ይመስል ጩኸቱ አይገርማችሁም! አሥራ ምናምን ሰው ያለበት ታክሲ ውስጥ ተቀምጦ ልክ ሚሌኒየም አዳራሽ ውስጥ በባዶ ድምጻችን እንናገር ይመስል መጮህ አሪፍ ልማድ አይደለም፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!
ቢሆንም፣ ባይሆንም ደግ መመኘት ይሻላል፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 4000 times