Sunday, 11 September 2016 00:00

አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ!

Written by 
Rate this item
(26 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አንበሳ እና አንድ ድብ በየፊናቸው ለአደን ወጥው ድንገት መንገድ ላይ የወደቀ ግልገል ያገኛሉ፡፡
አንበሳ፤
“እኔ ነኝ ቀድሜ የደረስኩት፡፡ ስለዚህ ይሄ ግልገል የእኔ ሊሆን ይገባል፡፡” አለ፡፡
ድብ፤
“አንተ ገና መድረስህ ነው፡፡ እኔ ቀደም ብዬ ነው የደረስት፡፡ ስለሆነም ቀድሞ የደረሰ ያገኘውን ዕድል ቀድሞ ይወስዳል” አለ፡፡
አንበሳ፤
“እንደዚህ ልታታልል የፈለግህ ከሆነማ፣ ጉልበት ያለው በኃይሉ የሚወስድበት ሁኔታ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይዋጣልን!” አለ፡፡
ድቡም፤
“በሕግ የማታምን ከሆነ፤ የሚያዋጣው ጉልበት ይሆናል፡፡ እስከ ዛሬ የጫካ ንጉሥ እየተባልክ ስትፈራ፣ ስታስፈራራ፣ ኖረሃል፡፡ አሁን ግን አንድ ግልገል ላይ እንኳ ፍትሐዊ ክፍፍል ለማድረግ በጡንቻ ካልሆነ አይሆንም ስትል እየተሰማህ ነው፡፡ በጡንቻህ ክፉኛ የተማመንክ ይመስለኛል፡፡ ጡንቻ ግን ሁልጊዜ አያበላም፡፡ በል እንጋጠምና ይለይልን፡፡ ፍርሃት ዱሮ ቀረ!” አለው፡፡
አንበሳው አመነታ፡፡ ከድብ ጋር ትግል ገጥሞ አያውቅም፡፡ አሁንም ማስፈራራቱን መቀጠል ያዋጣኛል ብሎ፣
 “ህይወትህን አትፈልገውም እንዴ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ድቡም፤
“ህይወት የሚያስፈልግህ ማንንም ሳትፈራ በነፃነት የምትኖርበት ከሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ተዋጥቶልን ዕውነተኛው ኃይለኛ ሊለይ ይገባል!” አለ ፍርጥም ብሎ፡፡
 አንበሳ፤ድቡ እንዳልፈራው ገባውና፡፡ ወደ ትግሉ የግዱን ገባ፡፡ ተናነቁ፡፡ ተያያዙ፡፡ ትግሉ ቀጠለ፡፡ አንዴ አንበሳ ከላይ ሲሆን፤ ሌላ ጊዜ ድቡ አንበሳን ገልብጦ ከላይ ሲሆን፤ ሲገለባበጡ ብዙ ሰዓት አለፈ፡፡ ሆኖም አልተሸናነፉም፡፡ አልለየላቸውም፡፡ ቀስ በቀስ ግን አቅማቸው እየደከመ ሄደ፡፡ ምንም መታገል የማይችሉበት ደረጃ ደረሱ፡፡ ክንዳቸው ዛለ፡፡ ጉልበታቸው ላመ፡፡ መታገሉን ትተው ተኙ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ዳር ሆኖ ያስተውል የነበረ ቀበሮ፤ የሁለቱንም አቅል አልባ መሆን ተገንዝቦ ግልገሏን ይዞ መጭ አለ፡፡
ሁለቱም ዐይናቸው እያየ የቋመጡላትን ግልገል አጡ፡፡
ድቡም፤
“አየህ አያ አንበሳ፤ ግባችንን ልናሳካ እንችል የነበረው በእኩልነት ብናምንም፣ስለ ጡንቻችን ባናስብ ነበረ፡፡ ይሄው ውጤቱና ጥቅሙ ዳር ቆሞ ላስተዋለን ቀበሮ ሆነ!” አለው፡፡
*        *      *
በጡንቻ መተማመን በታሪክ እንዳላዋጣ ሁሉ፤ ዛሬም አያዋጣም፡፡ ውሎ አድሮ የድካም ጊዜ መምጣቱን ፈላስፎች ይናገራሉ፡፡ The endpoint is fatigue ይሉታል፡፡ የአሜሪካ የጦር ጠበብት፤የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ሁለቱም ወገኖች ሲደክማቸው ይፈፀማል አሉ ይባላል፡፡
ገጣሚ ደበበ ሰይፉ፤ እራሴን በላሁት በሚለው ግጥሙ፣ በስብሰባ ብዛት ሰውነቱ ዝሎ፣ ተቆራርጦ ያለቀን ሰው ነው ያመላከተው (Symbolize) ስብሰባዎች ልባዊ ከሆኑ ራስን ለማየት ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ራስን መገምገምና ራስን ወደ ውስጥ ማየት፣ትክክለኛ መፍትሄ ለመሻት ዓይነተኛ ዘዴ ነው፡፡ ሆኖም ህዝብን በሚያሳምን መንገድ ከሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ራሱን መፈተሹ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ሆኗል፡፡ ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ይላል፤የዱሮው ፖለቲከኛ ቭላዲሚር ሌኒን፡፡ ሁለት እርምጃ ወደ ፊት፣ አንድ እርምጃ ወደ ኋላም መባሉን አንዘንጋ፡፡ ወፎች በጮሁ ዛፉ አይነቃነቅም፤ የሚለውንም የቻይናዎች ተረት ልብ እንላለን፡፡ “ግመሎች ይሄዳሉ ውሾቹ ይጮሃሉም›› ስንባል ኖረናል፡፡ ‹‹በኢህአዴግ ካመነ ዘበኛም ሚኒስትር ይሆናል›› ከሚለው ብሂል ተነስተን፣ሚኒስትር ለመሆን ኢህአዴግ መሆን አያስፈልግም የሚል እሳቤ ጋ መድረስ አንድ መልካም ምሥራች ነው! ምናልባትም የተራንስፎርሜሽን ምልክት ነው!
‹‹ራሳችንን እንፈትሽ!›› በተግባር እንዲታይ ከፈለግን፣አስፈታሽ ያስፈልገናል፡፡ ‹‹አገር ሁሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነው›› ካልን እንግሊዞች እንደሚሉት፤ Who guards the guards ጋ ልንደርስ ነው፡፡ ጠባቂዎቹን ማን ይጠብቃቸዋል እንደ ማለት ነው፡፡ ‹‹በስብሰናል፤ ተቸክለናል!›› የሚል ሰው መጥፋቱ አንዱ መሠረታዊ ችግራችን ነው፡፡
‹‹አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ፣ ከመሆን የማይቀር”
--- ይሉናል ከበደ ሚካኤል፡፡ የማይቀረውን እንቀበለው እንደማለት ነው፡፡
‹‹አይደለም እንዴ?
ዋሸሁ እንዴ?!››
ብለን እንደ ዘፋኙ የማናልፋቸው አያሌ አጀንዳዎች አሉን፡፡ ከዋሸን ዋሽተናል፡፡ ካጠፋን አጥፍተናል-ተጠያቂዎች ነን!! ‹‹ኤጭ አይባል የአገር ጉዳይ!›› ይለናል፤ፀጋዬ ገብረመድህን፡፡ የአገር ጉዳይ መሸዋወጃ መድረክ አይሆንም! አንድ አንደበተ- ርቱዕ ሰው፤‹‹መንግሥት ተቃዋሚዎችን በገንዘብ ልግዛ ቢልም የማይችልበት ደረጃ ደርሷል›› አሉ ይባላል፡፡ ያለ ተቃዋሚ ኃይል እኛ የለንም፤ሲባል የነበረውን ልብ ይሏል!
ዛሬ አገራችን መጠንቀቅ ያለባት ብርቱ ጉዳይ፤አንዱ ባጠፋ ሌላው እንዳይመታ ማስተዋል ነው፡፡ ይሄ ክልል ለሌላ ክልል ተጠያቂነት ሰበብ መሆን የለበትም! ‹‹በእነሞር ዳፋ ቸሃ ተደፋ›› የሚለው አስተሳሰብ መወገዝ አለበት፡፡ ‹‹አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ››ን ከልብ ካጤንነው መፍትሔያችንም ፍትሐዊ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ይሆናል፡፡ አዲሱ ዓመት ይሄን ዕድል ያጎናፅፈን ዘንድ እንፀልይ! የመጨረሻውን የ2008 ቅዳሜ ዛሬ እንሰናበተው!
መልካም አዲስ ዓመት!!
አዲሱ ዘመን፤
አዲስ ስርዓት፤ አዲስ ራዕይ ያሳየን!!

Read 6419 times