Sunday, 11 September 2016 00:00

ዋና አሰልጣኝ መሰረት ማኔና ሉሲዎቹ በ2016 የሴካፋ ሻምፒዮና ላይ…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

  የአዲስ ዓመት ልዩ እንግዳ

                ‹‹አዲሱ 2009 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም እና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡ በስፖርቱ መስክ በተለይ በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ ካለንበት ደረጃ ከፍ ብለን መመልከት ምኞቴ ነው፡፡››
‹‹በሴካፋ እንደ ቡድን ያቀድነው ሻምፒዮን ሆነን ዋንጫውን ይዘን ለመመለስ ነው፡፡ ሉሲዎች ለዞኑ ፉክክር ብቁ ናቸው፡፡ ግን በሴካፋ የትኛውም አገር የሚናቅ ወይም የሚካበድ አይደለም፡፡››

   የ2016 የሴካፋ ሴቶች “ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ››   በኡጋንዳ አዘጋጅነት ከመስከረም 1 ጀምሮ  ጂንጃ በተባለችው ከተማ ይካሄዳል፡፡  በዋና አሰልጣኝ መሰረት ማኔ የሚመራው  የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ‹‹ሉሲዎቹ›› ዛሬ ወደ ኡጋንዳ ይጓዛል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ ሲሳተፉ  በዞኑ ከሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች ባላቸው የላቀ ስኬት እና ልምድ ዋንጫውን ማሸነፍ እንደሚችሉ ተጠብቀዋል፡፡ ‹‹በሴካፋ እንደቡድን ያቀድነው ሻምፒዮን ሆነን ዋንጫውን ይዘን ለመመለስ ነው፡፡ ሉሲዎች ለዞኑ ፉክክር ብቁ ናቸው፡፡ ግን በሴካፋ የትኛውም አገር የሚናቅ ወይም የሚካበድ አይደለም፡፡›› በማለት ለስፖርት አድማስ የተናገረችው ዋና አሰልጣኟ መሰረት ማኔ ናት፡፡
የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ የእግር ኳስ ምክር ቤት ‹‹ሴካፋ›› ተመሳሳይ ሻምፒዮና ከ30 ዓመታት በፊት ማካሄዱ ሲታወስ በ1986 እኤአ ዛንዚባር አዘጋጅታው ዋንጫውን ያሸነፈችበት ነበር፡፡ ከዚሁ የዛንዚባር መስተንግዶና ሻምፒዮንነት በኋላ የሴካፋ ምክር ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ውድድሩን ማካሄድ አልቻለም ነበር፡፡ በ2007 እ.ኤ.አ ላይ ዛንዚባር በድጋሚ ውድድሩን እንድታዘጋጅ ታቅዶ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡
የሴካፋ ምክርቤት ሻምፒዮናውን በአዲስ መልክ ለመጀመር ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር “ፊፋ” በመላው ዓለም በሴቶች እግር ኳስ እድገት ለመስራት የያዘው አቅጣጫ አነሳስቶታል፡፡ ስለሆነም የ2016 የ‹‹ሴካፋ ሴቶች ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ›› በሚል ስያሜ  በኡጋንዳ መንግስት ልዩ ድጋፍ ሻምፒዮናውን በመፍጠር የዞኑን የሴቶች እግር ኳስ በአዲስ ትኩረት ሊቀጥልበት  ወስኗል፡፡ ከውሳኔውም በኋላ በሻምፒዮናው  የሴካፋ ምክር ቤት አባል የሆኑ 12 አገራትን እንዲሳተፉ ተጋብዘዋ፤፡፡  ሱዳን፤ ጅቡቲ ፤ ኤርትራ፤ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ለተሳትፎው ዝግጁ አልነበሩም፡፡ አዘጋጇ ኡጋንዳ፤ ብሩንዲ፤ ኬንያ፤ ዛንዚባር፤ ሩዋንዳ፤ ታንዛኒያ እና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ በምድብ 1 ኡጋንዳ፤ ኬንያ፤ ብሩንዲና ዛንዚባር እንዲሁም በምድብ 2 ኢትዮጵያ፤ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ተደልድለዋል። ሻምፒዮናው በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የሴቶች እግር ኳስ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃ ታምኖበታል፡፡ የሴካፋ ምክር ቤት፤  ከደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖችን ለመጋበዝ ጥረት ተደርጎም አልተሳካለትም፡፡
በ2016 የሴካፋ ሴቶች “ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ” ሉሲዎቹ በምድብ 2 የመጀመርያ ጨዋታቸውን የፊታችን ሐሙስ ከሩዋንዳ ጋር ያደርጋሉ፡፡ ሲሆን ሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ደግሞ ከ2 ቀናት በኋላ ከታንዛኒያ ጋር የሚገናኙበት ነው፡፡
የዋና አሰልጣኝ መሰረት ማኔ አጭር የእግር ኳስ ታሪክ
መሰረት ማኔ ትውልዷ በድሬዳዋ ከተማ 06 ቀበሌ በተለምዶ ስሙ አሸዋ ሜዳ በተባለው አካባቢ ባሳለፈችው ወጣትነት ከእግር ኳስ ጋር በጣም ብዙ ቅርበት ነበራት፡፡ በሰፈር የእግር ኳስ ጨዋታዎች አዘውትራ ስትሳተፍ ቆይታለች በ1992 ዓ.ም ለድሬዳዋ ምርጥ ተምርጣ በአገር አቀፍ ሻምፒዮና ስትጫወረወ ለስፖርቱ ያላት ትኩረት እያደገ መጥቷል፡፡ ለ2 ዓመታት በተለያዩ ቡድኖችና ውድድሮች ስትጫወት ቆይታም ከዚያም ወደ ማሰልጠኑ ትኩረት ማድረግ ጀመረች፡፡ በተለይ የሰፈር ልጆቿንና የቅርብ ጓደኞቿን የማሰልጠን ፍላጎት ስለነበራት ነው፡፡ በአሸዋ ሜዳ የድሬዳዋ ከተማ ሌሎች የእግር ኳስ ማዘውተርያ ስፍራዎች በአማተር ደረጃ ወጣቶችን ሰብስባ በማሰልጠንና ቡድኖችን በመምራት ትጉህ ነበረች፡፡ በየክረምቱ በሚደረጉ የህፃናት እና የወጣቶች የእግር ኳስ ውድድሮች በማዘጋጀት እና ሽልማት በመሸለም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ታደርግ ነበር። በዚህ ንቁ ተሳትፎዋም የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ‹‹መሰረት ሜዳ›› የሚል ቅፅል  ስም አውጥተውላታል። በድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ በነበራት አስተዋፅኦም በ2000 ዓም ላይ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፕሮጀክት የስልጠና እድል ተፈጠረላት፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ያዘጋጀውና በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ በሴቶች እግር ኳስ  ለ10 ቀናት የተከታተለችው የመጀመሪያ ስልጠና ነበር፡፡ ከዚሁ የስልጠና ኮርስ በኋላም የመጀመርያውን የስራ እድል ያገኘችው በ2002 ዓ.ም የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ነበር፡፡ ሉሲዎቹን ለመጀመርያ ጊዜ በያዘችበት ወቅት ለአፍሪካ ዋንጫ የደርሶ መልስ ማጣርያ ጨዋታዎችን ከታንዛኒያ ጋር አድርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ 3ለ1 ቡድኗ ከተሸነፈ በኋላ በመልሱ ጨዋታ በዳሬሰላም 1ለ1 አቻ የተለያዩበት ውጤት ተመዘገበ፡፡ ይህ ውጤት በኃላፊነት እንድትቀጥል አላስቻላትም፡፡ ስለዚህም ከሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ ለቅቃ በ2003 ዓም የድሬዳዋን ምርጥ የሴቶች ቡድን በመያዝ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ለመሳተፍ በቃች፡፡ ለዋንጫ የቀረበው ቡድኗ በደቡብ ምርጥ 1ለ0 ተሸንፎ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ በ2004 ዓም ደግሞ በአዲስ መልክ የተቋቋመውን የድሬዳዋ ከነማ ሴቶች ቡድን ተረከበችና 5 ክለቦች በተሳተፉበት የሊግ ውድድር በመካፈል በ4ኛ ደረጃ ያጠናቀቀችበትን ውጤት አስመዝግባለች። የድሬዳዋ ከነማ የሴቶች ቡድንን በ2005 እና በ2006 ዓ.ም ማሰልጠኗን በመቀጠል በምስራቅ እና ደቡብ ዞን ምድብ በሁለቱም የውድድር ዘመናት ሁለተኛ ደረጃዎችን ይዛ ማጠናቀቅ ብትችልም በዋናው የማጣቃለያ ውድድር ብዙም አልተሳካላትም ነበር፡፡ በድሬዳዋ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በነበራት ጉልህ አስተዋፅኦ በ2007 ዓ.ም ላይ አሰልጣኝ የወንዶቹን የድሬዳዋ ከነማ ክለብን በብሄራዊ ሊግ በሃላፊነት እንድትመራ መመረጧ ነበር። በመጀመሪያዋ የውድድር ዘመንም የድሬዳዋ ከነማ ክለብን ወደ ፕሪሚዬር ሊግ እንዲያልፍ አበቃችው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የተደነቀ ከፍተኛስኬቷን ለማስመዝገብ የቻለችበት ነው፡፡ በአፍሪካ በወንዶች ከፍተኛ የእግር ኳስ ሊግ ውድድር በአሰልጣኝነት ለመስራት የበቃች የመጀመርያዋ ሴት አሰልጣኝ ነበረች፡፡ እነሱ ሱፐር ስፖርት “ዘ አይረን ሌዲ ነው ኢትዮጵያን ፉትቦል” በሚል ዘገቡላት፡፡ ዋና አሰልጣኝ መሰረት ማኔ በተለይ ይህን ስኬቷን አስመልክታ ለስፖርት አድማስ በሰጠችው አስተያየት በፕሪሚዬር ሊጉ ላይ በነበራት ተሳትፎ በርካታ አሰልጣኞች በየጊዜው ልዩ ድጋፍ ያደርጉላት እንደነበር፤ ከልምዳቸው ብዙ እንድትቀስም ማድረጋቸውን አስታውሳለች፤ ስታደንቃቸው እና በየስታድዬሙ ቁጭ ብላ ስትመለከታቸው የኖረቻችውን ትልልቅ አሰልጣኞች ቡድን ይዛ በፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ ስትፎካከር ከፍተኛ የሞራል ግንባታ እንደነበረውም ገልፃለች፡፡ በ2007 ዓ.ም የፕሪሚዬር ሊግ ተሳትፏዋ ያገኘችው ልምድ ባሻገር በዋና አሰልጣኝነት የምትመራው ድሬዳዋ ከነማ በሊጉ 11ኛ ደረጃ በመያዝ ሲጨርስ በስምንት ጨዋታዎች ድል እንዲሁም በ6 ጨዋታዎች የአቻ ውጤት ለማስመዝገብ ችሎ ነበር፡፡ ከአንድ የውድድር ዘመን በኋላም ከድሬዳዋ ከነማ ክለብ አሰልጣኝነቷ እንደለቀቀች ደግሞ በአሜሪካ የኢትዮጵያዊያን ስፖርት ፌስቲቫል ላይ በክብር እንግድነት ተጋባዥ ለመሆን በቃች፡፡
ከ10 ወራት በላይ ባሳለፈችበት የአሜሪካ ቆይታዋ በኢትዮጵያዊያኑ የባህልና የስፖርት ፌስቲቫል ከበርካታ የቀድሞ ስፖርት ሰዎች ጋር በመተዋወቅ እና የተለያዩ ምክክሮች በማድረግ ጥሩ ልምድ ማግኘቷን ለስፖርት ገልጻለች ስትገልፅ፤ ከስፖርት ፌስቲቫሉ ባሻገር 3 እና 4 የእግር ኳስ አካዳሚዎችን እንዲሁም ዲሲ ዩናይትድ የተባለ የሴቶች ክለብን የመጎብኘት እና ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር የምክክር እና የልምድ ልውውጥ በማድረጓም ብዙ ተስፋ እንደፈጠረላት ትናገራለች። በዚያው በአሜሪካ ቆይታዋ ሌላው አጋጣሚ የባርሳ የሰመር ካምፕን የጎበኘችበት አጋጣሚ ሲሆን የስልጠና ሂደቱንም ተከታትላለች፡፡ የአሜሪካ ጉብኝቶቿ በተለይ በድሬዳዋ ከተማ በታዳጊ እና ወጣቶች የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች መስራት የምትችልባቸውን መነሻ ሃሳቦች አግኝታለታለች፡፡ ወደፊትም እቅዶቿን በማቅረብ ድጋፍ ልታገኝባቸው የምትችልባቸውን እድሎች ፈጥራለች። በሌላ በኩል በቅርቡ ከአሜሪካዊቷ አሰልጣኝ ሌሲል ጋሊሞል ጋር የታክቲክ እና የሀሳብ ብሎም የልምድ ልውውጥ እንድታደርግ የአሜሪካ ኤምባሲ ልዩ እድል ፈጥሮላትም ነበር፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ልምዶች እና ጠቃሚ ተመክሮዎች በኋላም ዋና አሰልጣኝ መሰረት ማኔ ሉሲዎቹን ለሁለተኛ ጊዜ ለመረከብ በቅታለች፡፡
ሉሲዎቹ እና የሴካፋ ዝግጅታቸው
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ብሄራዊ ቡድን እንድትመራ ዋና አሰልጣኝ መሰረት ማኔን ከሾማት ወዲህ  2 ወራት አልሞላም፡፡  የኢትዮጵያ ቡና ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽ በምክትል አሰልጣኝነት  አብራት እየሰራች ሲሆን ሁለቱ አሰልጣኞች እና ሉሲዎቹ የመጀመርያው ውድድራቸው በኡጋንዳ የሚካሄደው የሴካፋ ሴቶች ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ በማድረግ ውጤታማ ለመሆን ትኩረት አድርገዋ፡፡ በመጀመርያው ምርጫ  31 ተጨዋቾችን ከተለያዩ ፕሪሚዬርሊግ ክለቦች ያሰባሰበው የሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ምሥራቁ ክልል ድሬዳዋ ከተማ በማቅናት ለ15 ቀናት ዝግጅት ሲያደርግ ሰንብቷል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰውም ከኡጋንዳ ጉዟቸው በፊት ለ3 ቀናት በአዲስ አበባ ስታድዬም የመጨረሻ ዝግጅታቸውን አከናውነዋል።
ዋና  አሰልጣኝ መሠረት ማኔ  በድሬዳዋ ስላደረጉት ዝግጅት ለስፖርት አድማስ ስታብራራ ከጅምሩ  ለ31 ተጫዋቾች ጥሪ ማቅረቧን ገልፃ፤ በዚሁ ምርጫዋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10  ፣ ደደቢት 6 እንዲሁም መከላከያ 5 ተጫዋቾችን በማስመረጥ የሚጠቀሱ ክለቦች ነበሩ ብላለች፡፡ በግብ ጠባቂነት የደደቢቷ ሊያ ሽብሩ፣ የመከላከያዋ ማርታ በቀለ እና የድሬዳዋ ከነማዋ ታሪኳ በርገና ዋና ምርጫዎቿ የነበሩ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ገነት አክሊሉና የቅዱስ ጊዮርጊሷ ብዙዬ ታደሰ በተጠባባቂ ግብ ጠባቂነት ተይዘው ነበር፡፡ በተከላካይ ስፍራ ጥሩአንቺ መንገሻ፣ ፅዮን እስጢፋኖስ፣ እፀገነት ብዙነህ እና ሀብታም እሸቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ፤ አትክልት አሸናፊ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መስከረም ካንኮ ከደደቢት፣ ምህረት መለሰ ከመከላከያ፣ አሳቤ ሙሶ ከዳሽን ቢራ፣ አረጋሽ ፀጋ ከሲዳማ ቡና እና ገነት ኃይሉ ከአዳማ ከነማ በመጀመርያው ምርጫ የተያዙ ተጫዋቾች ናቸው። በአማካይ ስፍራ ኤደን ሽፈራው፣ ሰናይት ቦጋለ እና ብርቱካን ገብረክርስቶስ  ከደደቢት ፣ ፍቅርተ ብርሃኑ እና እመቤት አዲሱ ከመከላከያ፣ ብሩክታዊት ግርማ፣ ሕይወት ደንጊሶ፣ ትዕግስት ዘውዴና ቅድስት ቦጋለ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፤ ሰርካለም ቦጋለ ከዳሽን ቢራ፣ አዲስ ንጉሴ ከሀዋሳ ከነማ የተመለመሉ ነበሩ። በአጥቂ ስፍራ ደግሞ  የፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረችው የደደቢቷ ሎዛ አበራ የመጀመሪያዋ ተመራጭ ስትሆን፤ የመከላከያዋ ምስር ኢብራሂም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮቹ ረሂማ ዘርጋው እና ሽታዬ ሲሳይ እንዲሁም የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲዋ መዲና አወል በመጀመሪያው ምርጫ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ነበሩ፡፡
ዋና አሰልጣኝ መሰረት ማኔ እነዚህን በመጀመርያ ምርጫ ላይ ከተያዙ 31 ተጨዋቾች ጋር በድሬዳዋ የተደረገው ዝግጅት የሚያረካ መሆኑን ገልፃ፤ ከልምምዶች ባሻገር ከሀ17 የወንዶች ቡድን ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎችን በማድረግ ሁለቱንም 1ለ0 እና 3ለ1 በሆኑ ውጤቶች ድል ማድረግ መቻላቸውን ጠቅሳ ከዚያም ሁለተኛውን ምርጫ እንዳከናወነች አስረድታለች፡፡ ሁሉም የቡድኑ አባላት በዝግጅቱ ላይ ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው፤ በአጠቃላይ የሉሲዎቹ ስብስብ ጥሩ ልምድ ያካበቱ፤ በሞራላቸው ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በዝግጅቱ መገንዘቧንም ጠቅሳለች ዋና አሰልጣኟ ፤ የሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ በድሬዳዋ ለሴካፋ ሻምፒዮና ዝግጅት የከተሙበትን ሁኔታ ለስፖርት አድማስ   ስታስረዳም  አሁን ባለው የአየር ንብረት በአዲስ አበባ ዝግጅት ማድረግ እንደማይጠቅም ስለታመነበት መሆኑን ገልፃ የድሬዳዋ የአየር ሁኔታ ሴካፋን ከምታዘጋጀው የኡጋንዳ ከተማ ጋር ተቀራራቢ የአየር ንብረት በመኖሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ታቅዶ የተከናወነ መሆኑንም አስገንዝባለች፡፡
ሉሲዎችና ሌሎቹ….
በ2016 የሴካፋ ሴቶች ‹‹ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ›› ላይ አዘጋጇ ኡጋንዳ፤ በ2016 ካሜሮን ለምታስተናግደው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ያለፈችው ኬንያ እንዲሁም በሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የላቀ ደረጃ ያላት ኢትዮጵያ ለዋንጫው አሸናፊነት ቅድሚያ ግምት ወስደዋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ሉሲዎቹ በወቅታዊ የፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃቸው 1155 ነጥብ በማስመዝገብ ከምስራቅ አፍሪካ በአንደኛ ደረጃ፤ ከዓለም 105ኛ ደረጃ ላይ በመገኘታቸው፤ ባላቸው የውድድር ልምድ እና የአፍሪካ ዋንጫ ተመክሮ ግንባር ቀደም ግምት እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ በዋና አሰልጣኝ መሰረት በሚመራው የሉሲዎች ስብስብ አንጋፋ፤ ወጣት እና በፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች በመኖራቸው ስብስቡን የተጠናከረ ያደርገዋል፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ለሉሲዎች ብዙ ጨዋታ ያደረገችው ለረጅም ጊዜ ዋና አምበል ሆና የቆየችው ብዙሃን እንዳለ ፤ የፕሪሚዬር ሊጉ ኮከብ አግቢ ሎዛ አበራ እና የቅርብ ተቀናቃኟ ሽታዬ ሲሳይ ፤ የሉሲዎቹ የምንግዜም ከፍተኛዋ ግብ አግቢ ብርቱካን ገብረክርስቶስ፤ እንዲሁም ከፍተኛ ልምድ ያላት ረሂማ ዘርጋው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የሉሲዎቹ አህጉራዊ ልምድም ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡  የመጀመርያው ኢንተርናሽናል ጨዋታ በ2002 እኤአ በአዲስ አበባ ኡጋንዳን 2ለ0 ያሸነፉበት ሲሆን በሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፉባቸው ጨዋታዎች በ2004እና በ2012 እኤአ ላይ ማላዊ እና ኬንያ በተመሳሳይ 5ለ0 ያሸነፉባቸው ናቸው። በሰፊ የግብ ልዩነት የተሸነፉበት ጨዋታ በ2003 እኤአ በሌጎስ ከተማ በናይጄርያ  የደረሰባቸው የ7ለ0 ሽንፈት ነው፡፡ በአጠቃላይ ከምስራቅ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች የተሻለ ደረጃ ያላቸው ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ በ2002 እኤአ ለመጀመርያ ጊዜ ከተሳተፉ በኋላ በ3 የአፍሪካ ዋንጫዎች በ2002፤ በ2004 እና በ2012 እኤአ በመሳተፍ ግንባርቀደም ናቸው፡፡ በ2004 እኤአ ላይ በአፍሪካ ዋንጫ 4ኛ ደረጃ በማግኘት ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ሉሲዎቹ በምድብ 2 በሴካፋ ሴቶችሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ላይ የተደለደሉት ከሩዋንዳ እና ከታንዛኒያ አቻቸው ጋር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሩዋንዳ ሴቶች ብሄራዊ  ቡድን ‹‹ሴቶቹ ተርቦች›› በሚል ቅፅል ስማቸው የሚታወቁ ሲሆን በዋና አሰልጣኝ ግሬስ ኒያናውሙንቶ የሚመሩ ናቸው፡፡ ግሬስ ኒያናውሙንቶ ኤኤስ ኪጋሊ የተባለ የሴቶች ክለብ አሰልጣኝ የነበረች፤ በ2004 እኤአ የመጀመርያዋ የሩዋንዳ ሴት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን የበቃች እና በ2008 እኤአ ደግሞ የመጀመርያዋ ሴት ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ አሰልጣኝ ለመሆን የቻለች ሩዋንዳዊት ናት፡፡ በተለይ በኤኤስ ኪጋሊ ክለብ አሰልጣኝነቷ ለ6 ጊዜያት ሻምፒዮን በመሆን ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፤ በ2009 እኤአ ላይ በሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች ሆና አገልግላ ከ2014 እኤአ ጀምሮ ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ‹‹ሴቶቹ ተርቦች›› በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈው የማያውቁና እስከ 2012 እኤአ ድረስ በፊፋ እውቅና ያገኘ ጨዋታ ያላደረጉ ሲሆኑ ብዙም አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድር ባለመሳተፋቸው በወቅታዊ  የፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ እንኳን አልገቡም፡፡ ዋና አሰልጣኟ ግሬስ ኒያናዉሙንቶ ሰሞኑን በሻምፒዮናው ስለሚኖራቸው ተሳትፎ በሰጠችው አስተያየት ምድባቸው ጠንካራ መሆኑን ገልፃ በወጣት፤ ጠንካራ ፈጣን ተጨዋቾች የተሞሉትን የታንዛኒያ እና የኢትዮጵያ  ቡድኖች ለመፎካከር ጠንካራ ዝግጅት ሲሰሩ መሰንበታቸውን አስታውቃለች፡፡ የቡድኗን የተጨዋቾች ስብስብ ከጠንካራው የሩዋንዳ ሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ማዋቀሯን የገለፀችው አሰልጣኟ ኤኤስኪጋሊ፤ ካሞኒዪ እና ራምቡራ የተባሉ ክለቦች አብዛኛውን ተጨዋቾች እንዳስመለመሉ ገልፃለች፡፡ ቡድናቸው ግማሽ ፍፃሜ የመግባት አቅም እንዳለውም በልበሙሉነት ተናግራለች፡፡
ሌላው የሉሲዎቹ የምድብ 2 ተቀናቃኝ የታንዛኒያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ሲሆኑ በቅፅል ስማቸው የትዊጋ ኮከቦች ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ የታንዛኒያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቡድኑን ዋና አሰልጣኝ  እስከ ሐሙስ ያላስታወቀ ቢሆንም ኤድና ሌማ እና ሂልዳ ማሳንቼ የተባሉ ምክትል አሰልጣኞችን ስራ ያስጀመረው ሰሞኑን ነው፡፡  የትዊጋ ኮከቦች በወቅታዊው የፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ 947 ነጥብ በማስመዝገብ ከምስራቅ አፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም ከዓለም 125ኛ ላይ ሲሆኑ በታሪካቸው ትልቁ ስኬት ሆኖ የተመዘገበው በ2010 እኤአ አንድ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን መሳተፋቸው ነው፡፡
በምድብ 1 የሚገኙት አራቱ ቡድኖች አዘጋጇ ኡጋንዳ፤ ኬንያ፤ ዛንዚባር እና ብሩንዲ ናቸው፡፡ ክሬስትድ ክሬንስ በሚል ቅፅል ስም የሚጠሩት የኡጋንዳ  ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በወቅታዊው የፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ 855 ነጥብ በማስመዝገብ ከምስራቅ አፍሪካ በሶስተኛ ደረጃ እንዲሁም ከዓለም 129ኛ ላይ ሲሆኑ   ሻምፒዮናውን በአገራቸው ላይ በማስተናገዳቸው ከፍተኛ ድጋፍ የሚያገኙበት ይሆናል፡፡ በቅርቡ የወንዶች ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉም ከፍተኛ ሞራል ነው፡፡ ይሁንና ኡጋንዳ በሴቶች እግር ኳስ ብዙም ልምድ የሌላት አገር መሆኗ ተሳትፎዋን ሊያከብድባት እንደሚችል እየተገለፀ ሲሆን የአገሪቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ተሳትፎው በሴቶች እግር ኳስ ያለውን ሁኔታ ለማነቃቃት ዋና ግባቸው መሆኑን ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡  ከምድብ 1 በሴቶች እግር ኳስ የተሻለ ልምድ ያላት ኬንያ ስትሆን በወቅታዊ የፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ በ822 ነጥብ ከምስራቅ አፍሪካ በ4ኛ ደረጃ ከዓለም 132ኛ ላይ የምትገኝ ናት፡፡ የሃራምቤ ስታርሌትስ በሚል ቅፅል ስሙ የሚጠራው የሴቶች ብሄራዊ ቡድኗ በዋና አሰልጣኝ ዴቪድ ኦኑዋ እና በዋና አምበል ኤሴ ምባዬ አኪዳ የሚመራ ሲሆን ከ3 ወራት በኋላ በካሜሮን አዘጋጅነት በሚካሄደው የ2016 የሴቶችአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፉ እና በቅርብ ሳምንታት በስፔን ቫሌንሽያ በተደረገ ውድድር ልምድ ማግኘቱ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚያደርገው ተጠብቋል፡፡፡  ሌሎቹ የምድብ 1 ተፋላሚዎች ዛንዚባር እና ብሩንዲ በፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ ለመግባት ያልቻሉ፤ በአፍሪካ ዋንጫ ያልተሳተፉ ቡድኖች ናቸው፡፡

Read 1916 times