Sunday, 11 September 2016 00:00

“በኦሮሚያ የተጠራው የንግድ አድማ ተሳክቷል” - ኦፌኮ - “አድማው በህብረተሰቡ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከሽፏል” - መንግሥት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(65 votes)

ከጳጉሜ 1 እስከ መስከረም 2 በኦሮሚያ በማህበራዊ የንግድ አድማ መጠራቱን ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተግባራዊ መደረጉን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ያስታወቀ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ የአድማ ጥሪው በህብረተሰቡ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከሽፏል ብሏል፡፡
የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ አድማስ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ “በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች የንግድም ሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም፤ ሁሉም ነገር እንደታገደ ነው” ብለዋል፡፡ ሆቴል ቤቶች፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮችና የገበያ ስፍራዎች ዝግ ሆነው መሰንበታቸውን ኦፌኮ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በነቀምትና ደምቢዶሎ ከተማ ውስጥ ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ 4 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው አቶ ሙላቱ ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሃመድ ሠኢድ ስለጉዳዩ ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ በሁለቱ ክልሎች የተፈጠሩት ችግሮች ከህገ መንግስቱ ጋር የማይጣጣሙ እንደሆኑ ጠቁመው ሁከቱ በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ጥፋት ማስከተሉን አስታውቀዋል፡፡
“ህዝቡ በቅንነት የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከህዝቡ ከራሱ ጋር ተመካክሮ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነቱን መንግስት በመግለጫዎቹ አሳይቷል” ያሉት አቶ መሃመድ፤ ከዚህ በመነሳት የህብረተሰቡን አጀንዳ ቀምተው ለራሳቸው አላማ ለመጠቀም የሚሞክሩ አውዳሚ ኃይሎች እንዳሉ ህዝቡ የተረዳበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
“ህዝብ ከመንግስት ጋር እየተግባባ ችግሮችን ለመፍታት እየጣረ ነው” ያሉት አቶ መሃመድ፤ “በአማራም ሆነ ኦሮሚያ የተረጋጋ ሁኔታ ተፈጥሮ ህብረተሰቡ ቀድሞ ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ ነው ብለዋል፡፡
ሱቆች እንዲዘጉ፣ ከበአል ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ ምርቱን ባለማውጣት የንግድ አድማ እንዲደረግ መልዕክት የተላለፈ ቢሆንም ጥሪው በተጨባጭ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ከሽፏል ብለዋል፤ አቶ መሃመድ፡፡
በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የአድማ ሙከራ ቢኖርም ህብረተሰቡ ወደ ተጨባጭ ሰላማዊ ህይወቱ ተመልሶ በበአል ስሜት ውስጥ ሆኖ እየተገበያየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያን ከተሞች አቋርጠው ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጉዞ ያደረጉ የአይን እማኞች፤ በአብዛኞቹ ከተሞች የንግድ ቤቶች ተዘግተውና ሆቴል ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆነው መመልከታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡  


Read 10800 times