Sunday, 11 September 2016 00:00

ለዓመት በዘለቀ ተቃውሞ ከ1ሺ በላይ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ቃጠሎ 40 ሰዎች ሞተዋል

በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የዘንድሮውን ያህል ህዝባዊ ተቃውሞ ደርሶበት አያውቅም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ህዳር ወር የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተነሳው ተቃውሞ ማስተር ፕላኑ መሰረዙን መንግስት ቢያስታውቅም ተቃውሞው ግን አልበረደም። በርካታ የመብት ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ ወጣቶች የሚበዙባቸው የተቃውሞ ጎርፎች የኦሮምያ ጎዳናዎች አጥለቀለቁት፡፡  ከ10 ወራት በላይ በዘለቀው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞና ግጭት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት የቀጠፈ ሲሆን ብዙ ሺዎችም ለእስር እንደተዳረጉ የተለያዩ ሪፖርቶች ጠቁመዋል፡፡
በአማራ ክልለ ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ ከ3 ወር የማይበልጥ ዕድሜ ቢኖራቸውም በእጅጉ የተጠናከሩና በህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ናቸው፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን መረጃ መዝግቦ መያዙን የገለፁት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን፤ በአማራ ክልል ውስጥ እስከ ሐሙስ ድረስ 173 ሰዎች ሞተው፣ 130 መቁሰላቸውን ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሐምሌ 30 ተጠርቶ በነበረ የተቃውሞ ሰልፍ፤ በአንድ ቀን የሞቱትን 60 ሰዎች ጨምሮ ከነሐሴ 18 እስከ 27 ድረስ 17 ሰዎች  ህይወት መጥፋቱን አቶ አዳነ ገልፀዋል፡፡ በአጠቃላይ 77 ሰዎች ባለፉት 3 ወራት ህይወታቸው እንዳለፈ የፓርቲው መረጃ ያመለክታል፡፡
በሁለቱ ክልሎች በ3 ወር ውስጥ 250 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 135 ሰዎች ቆስለዋል ይላል- መኢአድ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበው ሪፖርት፤ በኦሮሚያ ክልል ከማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ግጭት 173 ሰዎች መሞታቸው፣ በአማራ ክልል ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ 95 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቆ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚከሰተውን ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸውን ያለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል በተጠናቀቀው ዓመት በ3 ማረሚያ ቤቶች ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የ43 ታራሚዎች ህይወት ማለፉን መንግስት አስታውቋል፡፡ በጎንደር ማረሚያ ቤት 18፣ በደብረታቦር ማረሚያ ቤት 2 እንዲሁም ከሰሞኑ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት 23 ሰዎች በጭስ በመታፈን፣ በመረጋገጥና በጥይት ተነግሯል፡፡



Read 4730 times