Sunday, 11 September 2016 00:00

ኢዴፓን ጨምሮ የ16 ፓርቲዎች ‹‹ጥምረት›› አስቸኳይ እርቅ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

     በሃገሪቱ ያለው ውጥረት ይረግብ ዘንድ ብሄራዊ እርቅ እንዲፈጠር ኢዴፓን ጨምሮ 16 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሠባሠቡበት ‹‹ጥምረት ለብሄራዊ መግባባትና አንድነት›› ሰሞኑን ጥሪ ያቀረበ ሲሆን መንግስት እርቁን ካልተቀበለ ሃገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላታል ብሏል፡፡
ኢህአዴግ አሁን በጀመረው መንገድ ግጭቶቹ ሊፈቱ እንደማይችሉ የጠቆመው ጥምረቱ፤ የሃይል እርምጃዎች ከቀጠሉ ሃገሪቱ ከኢህአዴግ ቁጥጥር ውጭ ልትሆን ስለምትችል በጊዜ የብሔራዊ እርቅ መድረክ ተፈጥሮ ሠላምና መግባባት እንዲሰፍን ጠይቋል፡፡ የተፈጠረውን የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ለማረጋጋት ብሄራዊ እርቅ ወሳኝ ነው ያለው የፓርቲዎች ጥምረት፤ እርቁ ለዘመናት ስር እየስደደ የመጣውን የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ ያለመተማመን፤ የቂም በቀልና የመገዳደል ስሜትን ለማስወገድ ወሳኝ ነው ብሏል፡፡ በዋናነት በተቃውሞዎች የተንፀባረቀው ‹‹የህወሃት የበላይነት የተረጋገጠበትና የታየበት አሰራር እንዲለወጥ›› የቀረበ ጥያቄ ነው ያለው ጥምረቱ፤ የአንድ ፓርቲ የበላይነት ሠፍኗል የሚለው አመለካከት እንዲቀረፍ ከተፈለገ፤ በጉዳይ ላይ የመድረክ ላይ ክርክር ውይይት ወሳኝ ነው ብሏል፡፡
የፖለቲካ እስረኞች ተፈተው ብሄራዊ እርቁ እንዲከናወን የጠየቀው ጥምረቱ፤ በእርቅ መድረኩ የተለያዩ ሃገራት መንግስታት፣ ታዋቂ አለማቀፍ ድርጅቶችና የዲፕሎማቲክ ተቋማት የታዛቢነት ድርሻ እንዲኖራቸው ጠይቋል፡፡

Read 4212 times