Sunday, 11 September 2016 00:00

አባገዳዎች፤ መንግሥት እንዲያነጋግረን እንፈልጋለን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

 “ያለ ህግ አግባብ የታሰሩ ሰዎች በአስቸኳይ ይፈቱ”

ከኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተሠባሠቡ አባገዳዎች በክልሉ ባለው ተቃውሞና ግጭት ሳቢያ የበርካታ ሰዎች ህይወት እየጠፋ መሆኑን በመግለፅ ችግሩን ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ በውይይት መንግስት እንዲያነጋግራቸው ጠይቀዋል፡፡
ከነሐሴ 23 ቀን ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሶደሬ ሆቴልና ሪዞርት ከ2 ሺ በላይ የሀገር ሽማግሌዎችና ሴቶች ባካሄዱት የ3 ቀን ጠቅላላ ጉባኤ በክልሉ ባለው ተቃውሞና ግጭት ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ ባለ 13 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት ጦር የሃገሪቱን ዳር ድንበር የመጠበቅ ስራውን ትቶ በክልሉ መስፈሩን የጠቆሙት አባገዳዎች፤ ጦሩ የህዝቡን ቋንቋ የማያወቅ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን በመግለፅ በአስቸኳይ ከክልሉ እንዲወጣ ጠይቀዋል። ሰላማችንን ራሳችን እንጠብቃለን በማለት፡፡
“የጦር ሰራዊቱ ኦሮሚኛ ቋንቋን ስለማያውቅ ከህብረተሰቡ ጋር በቅጡ እየተግባባ አይደለም፤ ክልሉን በአፋጣኝ ለቆ እንዲወጣ እንጠይቃለን” ብለዋል የቱለማ አባገዳ በየነ ሰንበቶ፡፡
አብዛኛው የኦሮሞ ማህበረሠብ አባገዳዎች ጋር እየቀረበ፣ የደረሰበትን በደል እየተናገረ መሆኑን የጠቀሱት አባገዳው፣ ግጭቶችን ተከትለው የኦሮሞ ልጆች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “በኦሮሞ ባህል እንኳን የሰው ልጅ የበሬ ደም እንኳ ያለ ስርአት አይፈስም ብለዋል፡፡
በቅርቡ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በክልሉ ችግሮች ዙሪያ ተወያይተው መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች መጠቆማቸውን የገለፁት አባ ገዳው፤ ጠ/ሚኒስትሩም ችግሩን እናስተካክላለን ብለው እንደነበርና እስካሁን አለመስተካከሉን ጠቁመዋል፡፡ “ሀገራችንን ውድቀት ላይ ይጥላል፣ ሀገር የጋራ ነው፤ የእርስዎም አይደለችም፤ አለበለዚያ ይህቺ ሀገር ሃገር ሆና አትቀጥልም ብለን ነግረናቸዋል” ብለዋል አባገዳዎች በመግለጫቸው፡፡
“አባ ገዳ ማለት እርቅ ማለት ነው፤ እርቅ ይፈፀም ዘንድ ጠይቀናል እስካሁን ግን ምላሽ አልተገኘም ያሉት አባገዳዎቹ፤ አሁንም መንግስት የአቋም መግለጫችንን አይቶ እንዲያነጋግረን እንፈልጋለን፤ ለችግሮች ሁሉ ተወያተን መፍትሄ ማበጀት አለብን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ተማሪዎቻችን መስከረም ላይ ወደ ትምህርት ይመለሳሉ፤ በችግሩ ዙሪያ ተወያይተን መፍትሄ አለመሰጠቱ ችግር ይፈጥራል፡፡ በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡
ተቃውሞና ግጭቶችን ተከትሎ ያለህግ አግባብ የታሰሩ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቀዋል - አባገዳዎቹ፡፡ “በኦሮሞ ልጆች ህይወት እየቀጠፋችሁና እያስቀጠፋችሁ ያላችሁ እንዲሁም የሃሰት ምስክርነት የምትሰጡ ወገኖች የገዳው ይፋረዳችኋል፡፡  በማስተር ፕላን ስም የከተማ መስፋፋት እንዲቆምና ገበሬዎች እንዳይፈናቀሉ የጠየቁ ሲሆን የኦሮሚያን ዳር ድንበር በመሸራረፍ ከሌሎች ህዝቦች ጋር የማጋጨት ስራ እንዲቆም፣ ከፊንፊኔ የአያት ቅድመ አያቶቻቸው መሬት በግፍ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ልጆችም የመኖሪያ ቦታ ተመልሶ እንዲሰጣቸው በአቋም መግለጫቸው ጠይቀዋል “የአፋን ኦሮሞ የፌደራል መንግሥቱ ተጨማሪ ቋንቋ እንዲሆን እንጠይቃለን” ብለዋል - አባገዳዎቹ፡፡
አባገዳዎቹ ከ144 አመታት በኋላ 4 ስልጣኖችንም ለተመረጡ ግለሰቦች አስረክበዋል፡፡ በገዳ ስርአት ውስጥ ዘጠኝ ስልጣን ክፍፍሎች እንዳሉት ያብራሩት የቱለማ አባገዳ በየነ ሰንበቶ፤  በጉባዔው አቶ  አበራ ቶላ አባ ሃዩ (ፕሬዚዳንት እንደማለት ነው) ሆነው ተመርጠዋል ብለዋል፡፡ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት አቶ ድንቁ ደያስ አባ ዱላ (የጦር መሪ) በመሆን መመረጣቸውም ተገልጿል፡፡ አባ ዱላ የተመረጠው  አሁን በተግባር ጦር አደራጅቶ ለመምራት ሳይሆን ባህሉ እንዳይጠፋ ለመጠበቅ እንደሆነ የገለፁት አባ ገዳው፤ ዋነኛ ተግባሩም ከ16-24 አመት ዕድሜያቸውን ወጣቶች ማደራጀትና የአባ ገዳውን ስልጣን ማስከበር ነው ብለዋል፡፡
በእለቱ የሴቶች ጉዳይ ሃላፊ (አዶ ስንቄ) መመረጡም ታውቋል፡፡

Read 10564 times