Sunday, 11 September 2016 00:00

ተመድ በተቃውሞው የታሰሩ በአፋጣኝ እንዲፈቱ ግፊት እንዲያደርግ 15 ተቋማት ጠየቁ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

- የሞቱ ዜጎች ጉዳይ በገለልተኛ አካል ይጣራ፤ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ በህግ ይጠየቁ ብለዋል

   የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ በአማራና ኦሮምያ ክልሎች ከተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ የታሰሩ ዜጎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲፈታ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊት እንዲያደርግ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሰሩ 15 የተለያዩ ታዋቂ አለማቀፍ እና ብሄራዊ ተቋማት ጠየቁ፡፡
ተቋማቱ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በላኩት የጋራ ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ በቀጣዩ ሳምንት በሚያካሂደው አመታዊ ጉባኤው በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ቀዳሚ አጀንዳው እንዲያደርግና ጉዳዩን በተመለከተ መግለጫ እንዲያወጣ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላትና ተቃዋሚዎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔ በአፋጣኝ እንዲፈታ እንዲሁም የጸጥታ ሃይሎች በሁለቱም ክልሎች ሆነ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በተቃዋሚዎች ላይ ያልተመጣጠነና ተገቢ ያልሆነ የሃይል ጥቃት መፈጸማቸውን እንዲያስቆም ግፊት እንዲያደርግም ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የተገደሉና የሰባዓዊ መብቶች ጥሰቶች የደረሱባቸው ዜጎች ጉዳይ በአለማቀፍ ገለልተኛ ተቋማት እንዲጣራ እንዲፈቅድ፣ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግና ህገ መንግስቱን፣ አለማቀፋዊና አህጉራዊ የሰብዓዊና የፖለቲካዊ መብቶች ህግጋትና ስምምነቶችን እንዲያከብር ለማስቻል ምክር ቤቱ ጫና እንዲያሳድርም ጠይቀዋል፡፡
ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ የጋራ ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ከእነዚህ 15 ተቋማት መካከል፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ፍሪደም ሃውስ፣ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስና ወርልድ ኦርጋናይዜሽን አጌንስት ቶርቸር ይገኙበታል፡፡




Read 2357 times