Sunday, 04 September 2016 00:00

ሰይጣኑ (ጂኒው) ከጠርሙሱ ውስጥ ወጥቷል!!

Written by  ጌታቸው ስሜ
Rate this item
(9 votes)

    አቶ ተፈሪ መኮንን ባለፈው ሳምንት እትም ላይ፤ ‹‹እውነቱን ተናግረን ሰይጣንን እናሳፍረው›› በሚል መጣጥፉ፣ ህግ አክባሪ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያምንበት ገልፆአል፡፡ (ተፈሪን አንተ ያልኩት የቀደሞ ጓዴና ወዳጄ ስለሆነ ከአክብሮትና ከቅርበት መሆኑን ከግንዛቤ ይግባልኝ) ተፈሪ እንደሚለው ሰሞኑን ያያቸው አንዳንድ ሰልፎች፤‹‹ህገ ወጥ ሰላማዊ ሰልፎች›› ነበሩ፡፡ ጠመንጃ ይዘው ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች፣ ህጉን አለማክበራቸው ለውጪ አገር ሰው አስደንጋጭ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ ለሰላማዊ ሰልፍ ባዕድ ካልሆነበት አገር የመጡ ሰዎች ጠመንጃ ሲያዩ ግር ሊላቸው ቢችልም፤ በተቃራኒው ደግሞ የመንግስት አሰራር እንዲታረም በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞ እማይደረግበት አገር መሆኑንም ሲገነዘቡ፤ በተመሳሳይ መልኩ ግር ሊላቸውና ሊያስገርማቸው ይችላል፡፡ ከአቶ ተፈሪ ጋር የማልስማማው፣ ከመንግስት ፍቃድ ሳያገኙ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ የተከለከለ ከሆነ ህጉን ማክበር ያስፈልጋል በማለቱ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የሚፈቅደው የመንግስት አካል ህጉን ካላከበረስ? ይህንን ለማለት መጀመርያ የመጫወቻ ሜዳው ለህግ አስፈፃሚውና ለህግ ተገዢው በእኩል የሚያገለግል መሆን አለበት፡፡
ዜጎች ደረሰብን የሚሉትን ቅሬታ፣ ጭቆናና በደል በሰላማዊ ሰልፍ መግለጽ ብርቅ የሆነበት አገር ውስጥ ነን፡፡ በህገ መንግስቱ ላይ፣ መሳሪያ ሳይዙ በሰላም የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ መብቶች በይፋ ቢፈቀዱም፤ ዜጎች በመብቱ እንዲጠቀሙ አልተደረገም። ከክልክላ ስለሚጀመር፡፡ ክልከላ የበዛበት አገር ነው፡፡ ለዚህም ነው - በአገራችን ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የሚያስደነግጥና መንግስትን ከስልጣን መንበሩ እንደማውረድ ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ የሚታሰበው፡፡ ለህገ መንግስቱ ቆሜያለሁ የሚለው የስልጣን አካል፤ በዚህ መሰረታዊ ዲሞክራሲያዊ መብት፣ ሃሳባቸውንና ቅሬታቸውን የሚያነሱ ወይም እንዲታረም የሚጠይቁ ዜጎችን፤ የመብቱን አጥንት ባይቆረጥሙ እንኳን ወተቱን እንዲጋቱ አልፈቀደም፡፡
የስኳር ህመምተኞች፣ የጡት ካንሰር፣ ሲጋራ የማይጨስበት ወዘተ-- ቀን በሚል ቲ-ሸርትና ኮፍያ ተጠልቆ በአደባባይ ሲከበር እናያለን፡፡ በዚህ መከበር ተቃውሞ የለኝም፡፡ ለጤና እክሎች ሰዎች አደባባይ እንደሚወጡት በፍትህ፣ በመንግስት ተቋማዊ አሰራሮች፣ በሙስና፣ በእኩልነት ጥያቄ፣  በማንነት ወዘተ ህመም ላይ ሰዎች በጋራ ሆነው ቅሬታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ መጠየቅ ለምን አይችሉም?! መቼም ሁሉም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሚጠይቅ የህብረተሰብ ክፍል ፀረ ሰላም፣ ኪራይ ሰብሳቢና የውጭ ሃይሎች ተላላኪ ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉም ህዝብ አንድ ላይ ሊሳሳት አይችልም፡፡ ለእኔ በማይመስለኝ ሃሳብና መንገድ ስለምትመጡ ‹‹ወግድ›› ሲል ለሩብ ክፍለ ዘመን የተጓዘው ኢህአዴግ፤ እሱ ራሱ ባመነባቸው ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግሮች›› ላይ ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ የሚወጡ ዜጎችን እንኳ ለማስተናገድ ሆደ ሰፊ አይደለም፡፡
ማዕበሉ ገንፍሎ ህዝቡ አደባባይ ሲወጣ፣ በኃይል ፀጥ አደርጋለሁ ብሎ ተማመነ፡፡ ኔሮ የተባለው ሮማዊ ቄሳር፤ኮሊሲየም (ስታዲየም) ውስጥ ግጥግጥ ካለው ሮማዊ ህዝብ ጋር ፍልሚያ ሲመለከት፤ በፍልሚያ ያሸነፈው ተፋላሚ የጣለውን ለመግደል ከቄሳሩ ፍቃድ ይጠይቃል፡፡ ቄሳሩ ኔሮ፤ አውራ ጣቱን ወደ ታች ካደረገና ህዝቡም በተመሳሳይ መልኩ አውራ ጣቱን ወደ ታች ከቀሰረ ድል የቀናው ተፋላሚ ግዳዩን በሞት ይሸኘዋል፡፡ ግጥም ያለው ህዝብ በተመሳሳይ መልኩ አውራ ጣቱን መቀሰር ነበረበት፡፡ ኔሮ ግን ከህዝቡ ተቃራኒውን አገኘ፡፡ ኔሮ ህዝቡ ከእሱ በተቃራኒ አቋም መያዙ ስላበገነው፣ ‹‹ይህ ሁሉ ህዝብ አንገቱ አንድ በሆነልኝና በቀነጠስኩት” አለ  አሉ። ገዢው ፓርቲ ራሱን የማስተካከያ አንዱን መንገድ ጥርቅም አድርጎ በመዝጋቱ” ራሱን የሚመዝንበትን እድል አጨልሞታል ብዬ አምናለሁ፡፡መጀመርያውኑ መደላድሉን ቢያመቻች (ለራሱና ቆሜላቸዋለሁ ለሚላቸው አካላት ሲል) የሰሞኑን ዓይነት ቁጣ ያዘለ ሰልፍ ግንፍል አይልም ነበር፡፡ ሲገነፍል እንደ ኔሮ፣ የሁሉንም አንገት ልቀንጥስ ወደ ማለት ተገባ፡፡  
የህዝብ የቅሬታ መግለጫ አንዱ መንገድ የሆነውን ሰላማዊ ሰልፍ፣ አፍኖ ሲጥ ማድረጉ፤ እንደ ሰሞኑ አይነት የህዝብ ቁጣና አመፅ ያስከትላል፡፡ ቁጣ በሚገነፍልበት ጊዜ ህግ አክባሪ ባህርዩን ወይም ቀድሞ ጠይቆ ያጣውን ሰላማዊ ጥያቄ መሳሪያ በመያዝ እንዲገልፅ ይገደዳል፡፡
በሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች ላይ በየትኛውም ስፍራ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በጨዋነት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የጠየቁ ሰዎች፤ ከፈቃጁ አካል የሚሰጣቸው መልስ ምን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንዴ የጉዳዩ አንገብጋቢነት ከአቅም በላይ ሲሆን፤ ለዚያውም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠየቁት የጊዜ ገደብ ውስጥ ፈቃጁ አካል ምላሽ ካልሰጠ፤ እንደተፈቀደ ይቆጠራል በሚለው አደባባይ ይወጣሉ። እሱም ውጤቱ ለድብደባ፣ ለእስርና ለእግልት እንደሚዳርግ የአደባባይ እውነት ነው፡፡ እስቲ ባለፉት አስር አመታት የሲቪክ ተቋማት፣ የሙያ ማህበራት፣ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ተሰባስበው ያለ ምንም መሸማቀቅ በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄያቸውን ወይም ተቃውሟቸውን ያሰሙበት አጋጣሚ ካለ ይጠቀስ፡፡ በግሪክ ሚቲዎሎጂ (አፈ-ታሪክ)፣ ውብ የሆነች ኮረዳ በኩሬ ውስጥ መልኳን አይታ እጅግ በውበቷ በመማረኳ፤ መልኳን ለመንካት ብላ ኩሬው ውስጥ ሰጥማ እንደገባቸው፣ ኢህአዴግም በራሱ ስራ እጅግ በመማረኩ ህዝብ ደስ እንደተሰኘ አድርጎ ይመለከታል፡፡ ለዓመታት የተቆለሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ስር የሰደደ ሙስና፣ ቅጥ ያጣ አድልዎ … ምላሽ ሳይሰጣቸው ዛሬ ላይ የደረሰው ራሱን በማሞካሸት ጊዜውን ስለሚያጠፋ ነው፡፡ ወይም አውቆ ችላ ማለትም ሊሆን ይችላል፡፡
ተፈሪ በጽሁፉ፤የህግ ባርያ መሆንም መልካም ነው ብሏል፡፡ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን ለህግ ባርያ እንድሆን ህጉ ያጎናፀፈኝ ነፃነት ሊከበርልኝ ይገባል። ነፃነት የሚያጎናፅፍ ህግም ሆኖ፣ ህጉን በስራ ላይ የሚያውለው መንግስት የሚባለው አካል ነፃነቱን ከነፈገ ወይም ሸራርፎ ከሰጠ፤ ህጉ ውስጥ የሰፈሩት መብቶችና ነፃነቶች እንደሌሉ ይሰማኛል፡፡ ሰሞኑን በሙስና ክስ (Impeachmenttrial) ተመስርቶባቸው ከስልጣናቸው ገደብ የተደረገባቸው የብራዚል ፕሬዚዳንት ዴልማ ሩሴፍ፤የፓርላማው አባላት ፊት ቀርበው፣ ከሙስና ጋር እንዳልተነካኩ ተከራክረዋል። ብራዚላዊ የመሆን ቅናት አደረበኝ፡፡ ተግባራዊ ዲሞክራሲ ወይም ህገ መንግስታዊነት በተግባር የታየበት በመሆኑ ለአንድ ብራዚላዊ ዜጋ በአገሩ ያለው የስልጣን ክፍፍልና የስልጣን አካላት እርስ በእርስ የመቆጣጠር አሰራር፣ እንዴት እንደሚያኮራው ለመገመት አያዳግትም፡፡ ብራዚላውያን የሪዮ ኦሎምፒክ ከመካሄዱ ቀደም ባሉት ጊዜያት በአደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በሙስናው የተሳተፉ እንዲጠየቁ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ከክሱ ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ የተሟገቱበት መንገድ፣ የተጠያቂነት ሂደቱ በራሱ፣ ዲሞክራሲን ተቋማዊ የማድረግ ደረጃ ማድረሳቸውን ያሳየናል፡፡ እንደ ብራዚል ዓይነት የጀማሪ ዲሞክራሲ አገር፣ ለህግ ስርዓት ተገዢነትና ህግ አክባሪነት መሰረቱን ስለጣለ፤ ህግ አስፈፃሚውም ሆነ ዜጎቹ ለህጉ ባርያና ባርቾ ይሆናሉ፤ የህግ የበላይነቱ ህግ አክባሪ ዜጎችን የማፍራት ኃይል ይኖረዋል፡፡
አንተ እንዳልከውም፣ ፈላስፋው ዢን ዣክ ሩሶ፤ ሰዎች በፈቃዳቸው ለፈጠሩት አንድ ስርዓት ‹‹ባርያ›› ይሆናሉ የሚል ክርክር ያነሳል፡፡ ነገር ግን እኔ እንደተገነዘብኩት ሩሶ ሰዎች በፈቃዳቸው ያፀኑት ያ ስርዓት (መንግስት) ፤ለተገዢው ህዝብ ሙሉ ፍቃድና ፍላጎት (General will) መገዛት እንዳለበትም ይከራከራል፡፡ ይህ ማለት በተገዢው ሙሉ ፍቃድና ፍላጎት የቆመና የፀና መንግስት ለሚያወጣው ህግ፣ ተገዢው ባርያ ይሆንለታል፡፡ እዚህ ጋ ውሉ የሚፀናው መንግስት የሚባለው ተቋም፣ በአብዛኛው ተገዢ ሙሉ ፍቃደኝነት መቆሙን ሲያረጋግጥ ነው፡፡ እንግሊዛውያኑ ፈላስፎች ቶማስ ሆብስና ጆን ሎክም በዚህ እሳቤ  ይስማማሉ፡፡ ስለዚህም መንግስት የሚያወጣቸውም ህጎች፣ የብዙኃኑን ጥቅም ወይም ተፈጥሮአዊ መብቶች በተግባር ከሰነድነት አልፈው መሬት መታየት እንዳለባቸው ለማመላከት ነው፡፡ ይህ ሲሆን  (Proper function of government) አለ ተብሎ ይታሰባል፡፡ የህግ ባርነት በአብዛኛው ነፃ ፍላጎት ላይ በቆመ ስርዓት የሚሰፍን መሆኑን ሲያመለክት ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ብዙኃን መካከል ቁጥሩ የትየለሌ የሆነ ህዝብ ተቃውሞውን ሲያሰማ፤ ውሉ ፈርሷል ብለን ልናስብ እንችላለን፡፡ በብዙኃኑ ፍላጎት የቆመ ነው- ተብሎ ክርክር ካልተነሳ በስተቀር፡፡ መንግስት መድኃኒት በሚሆን ደረጃ ተቃውሞውን ይፈልገዋል ብለሃል፡፡ ቢሆን እሰየው። እንደ እኔ አመለካከት፤ እንደውም አይፈልገውም ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም በገዘፉና ተፅእኖ አሳዳሪ በሆኑ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተለቀቁ የቪዲዮ ምስሎች፤ የፀጥታ ሃይሎች መፈክር እንጂ ጠመንጃ ሳይዙ መስቀል አደባባይ በወጡ የገዛ ወገናቸው ላይ እንደዛ ዘግናኝ የሆነ ድብደባ ሲፈፅሙ ሲታይ፤ ሚዛናዊ አመለካከት ያለው ማንኛውም ዜጋ፣ ተቃውሞውን መድኃኒት በሚሆን ደረጃ መንግስት ይፈልገዋል ብሎ ሊያስብ አይችልም፡፡ ገዢው ፓርቲ መድኃኒት በሚሆን ደረጃ ሳይሆን፤ በመድኃኒቱ ማርከሻ ላይ በእጅጉ ኃይልና እመቃ ይጠቀማል፡፡ ውጤቱ አስፈርቶት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ደረጃ እንዲደርስ መጀመርያውኑ ዜጎች በህግ የተሰጣቸውን መብት እየተጠቀሙ እንዲገሩ ቢያደርግ፣ መድኃኒቱን ለማግኘትና ለመፈወስ ጊዜ አይፈጅበትም ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ መድኃኒት የሚሻ ከሆነ ህመሙን ያቀዋል፤ እናም ህመምህ አሳምሞናል የሚሉ ዜጎች ፈዋሽ መድኃኒት ይፈለግላቸዋል እንጂ ህመማቸውን የሚያባብስ እርምጃ ሊቃጣባቸው አይገባም፡፡
ሰይጣኑ (ጂኒው) ከጠርሙሱ ውስጥ ከወጣ በኋላ፣ እውነቱንም ቢነግሩት ሰይጣኑን መመለስ አይቻልም። እውነት አለመሆኑን ለመመዘን ሰይጣን ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ መጀመርያውኑ ጠርሙሱ ውስጥ ሆኖ እውነቱን በመንገር ነበር - ማለዘብ፡፡
ከሰላማዊ ሰልፍ አካሄድ ጋር የተያያዘ አንድ አወዛጋቢ ጭብጥ መኖሩን እንደምታውቅ ጠቅሰሃል፡፡ ጭብጡ ምን እንደሆነ ባልረዳውም፤ዜጎች ከመንግስት ጋር በገቡት የውል ሰነድ ወይም በህገ መንግስቱ በተሰጠው መብትና ህጉን በሚያስፈፅሙት አካላት መካከል አለመናበብ አለ? ወይስ ህገ መንግስቱን ተንተርሰው የወጡ ዝርዝር ህጎች፣ ዜጎችን ተጠቃሚ አላደረጉም? ስለዚህ ይከለሱ ነው? ከሰላማዊ ሰልፍ ክልከላ ይልቅ የሁሉም ድምፅ የሚሰማበት አሰራር ይስፈን ነው? ወይስ ሌላ ? አውዱ ወይም ጭብጡ ይታወቅና ሃቅ ላይ የተንተራሰ ከሆነ፣ ውይይት ይደረግበት ያልከው ተገቢ ነው፤በተረፈ እዳው ገብስ ነው ተብሎም የሚተው አይደለም፡፡ አሳሳቢነቱንና የለውጥ ፍላጎቱን በቅንነትና በሆደ ሰፊነት ከመቀበል መጀመር አለበት፡፡
በሌላ በኩል እኔም እንደ አንድ ቅን አሳቢ ዜጋ፤ ተቃውሞው በህዝቦች መካከል ቁርሾና ግጭት የሚያስከትል መሆን የለበትም የሚለውን የተፈሪን ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ በተረፈ ለሁላችንም ልብና ልቡናውን ይስጠን!

Read 4612 times